Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊሠርቶ ማደር የናፈቃቸው ተፈናቃዮች በደብረ ብርሃን መጠለያ

ሠርቶ ማደር የናፈቃቸው ተፈናቃዮች በደብረ ብርሃን መጠለያ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ቅዝቃዜው እንኳን ሜዳ ላይ ውሎ ለሚያድርና ሆዱ ለተራበ ሰው ይቅርና በልቶ የሚሞቅ ልብስ ለደረበውም ያንዘፈዝፋል፡፡

እየጣለ ያለውን የበጋ ዝናብ ተከትሎ ደመናው ከመሬት በቅርብ ርቀት ከወዲያ ወዲህ በሚንገዋለልበትና አፈናው (ጉሙ) ባየለበት በዚህ ሥፍራ፣ በርከት ያሉ ሕፃናት ግማሽ አካላቸውን የሚሸፍን ልብስ ጣል አድርገው ካፊያውን ከቁብ ሳይቆጥሩት በጭቃው ላይ ይሯሯጣሉ፡፡

- Advertisement -

የልጆቻቸውን እንቅስቃሴ በአርምሞ የሚመለከቱ ወላጆች ፊታቸው ላይ ሐዘን ይስተዋላል፡፡ የልጆች በጭቃ መለዋወስ፣ በካፊያ ዝናብ መራስ፣ ከእኩዮቻቸው ጋር ማልቀስና መሳቅ ለወላጆች ችግር አይደለም፡፡ ይልቁንስ ከእዚያ ሰፈር ለእናቶች በእጅጉ የሚያሳስባቸው፣ ልጆች ከጨዋታ ሲመለሱ ምን ላቅርብላቸው የሚለው መልስ ያጣ ጥያቄ ነው፡፡

ማጀታቸውን ትተው፣ መሶቦቻቸውን ከድነው፣ የሚወዷቸውን ከብቶች በዱር በትነው ቤታቸውን ሳይዘጉ ቀዬአቸውን ለቀው ለሚኖሩ እናቶች፣ አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ከብዷቸዋል፡፡ በቀደመ ቀዬአቸው ጧት ማታ ያለመታከት በትጋት የሚሠሩ ክንዶችና ለሌላ የሚተርፉ እጆች የሚሠሩት አጥተው ተመጽዋች ሆነዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘው የወይንሸት መጠለያ በከተማዋ ካሉ ስድስት የመጠለያ ጣቢያዎች አንዱ ሲሆን፣ ከሰባት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮችን ይዟል፡፡

ከከጨቅላ ሕፃናት እስከ 95 ዓመት ዕድሜ ያላቸው አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡሮችና በጀርባቸው ልጆችን ያዘሉ እናቶች፣ መሥራት የሚችሉ ወጣቶች፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትን ጨምሮ ከ30 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በከተማዋ ባሉ በመጠለያዎች ሥር ተሰባስበው በጎ አድራጊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች በሚያደርጉላቸው ሰብዓዊ ድጋፍ ለመኖር ተገደዋል፡፡

ተስፋ መቁረጥና ተስፋ ማጣት፣ ንዴትና ብስጭት የሚፈራረቅባቸው ተፈናቃዮች፣ ችግራቸው ሐዘንና ጭንቀታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ የመጡበት መንገድ፣ ያዩትና የቀመሱት ግፍ ያሳለፉት መከራ፣ በሞት ያጧቸው ቤተሰቦቻቸው አንዱ አንዱን እንኳን እንዳያፅናና አድርጓቸዋል፡፡

በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ሆነው፣ በሬሳ ላይ ተረማምደው በቤታቸው ውስጥ በተኙት በእሳት ሳይቃጠሉ በመትረፋቸው ፈጣሪያቸውን ቢያመሠግኑም፣ በግፍ የተገደሉ ልጆቻቸው፣ በጭካኔ የተገደሉ ወላጆቻቸውንና ወንድም እህቶቻቸውን በማስታወስ ሐዘናቸው ከሆዳቸው ሊወጣ እንዳልቻለ በጣቢያው ተገኝተን ባነጋገርንበት ወቅት ሰምተናል፡፡

ለበርካታ ዓመታት ለፍተው፣ ጥረው፣ ግረውና ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያካበቱት ንብረት ሳያስቡት በደቂቃ ወደ አመድነትና ፍርስራሽነት እንዴት እንደተቀየረና ከብቶቻቸው እንዴት እንደተወሰዱ ሲናገሩም ዓይኖቻቸው በዕንባ እየተሞላ ነው፡፡

በመካከላቸው እናት ወይም አባት፣ ልጅ፣ እህት ወይም ወንድም አሊያም የቅርብም ሆነ የሩቅ ወዳጅ ያልተገደለበት ሰው እንደማይገኝ በመግለጽም እነሱ ለምስክርነት መትረፋቸውን ይናገራሉ፡፡ 

ይህ ሁሉ ግፍና መከራ የተፈጸመው ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች በተካሄደ ብሄርን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ መሆኑን ከጭፍጨፋው አምልጥው በደብረ ብርሃን ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ይናገራሉ፡፡

ተወልደው ባደጉበት ቀዬ አፈር ፈጭተው፣ ውኃ ተራጭተው፣ በመስኩ ቦርቀውና ተጫውተው፣ ተኩለውና ተድረው ለቁም ነገር በቅተው ወልደው በሳሙበት፣ ሠርተው ሀብት ንብረት ባገኙበት፣ አብበው ባፈሩበት አገሬ ወንዜ ብለው ባህል ቋንቋውን በተማሩበት፣ በጋብቻ፣ በክርስትና በሐዘንና በደስታ ተዋልደውና ተጋምደው ከልጅነት እስከ ዕውቀት ከኖሩበት መገፋፋታቸው ዛሬም ዕውን አይመስላቸውም፡፡

አረጋውያን በመጦሪያቸው፣ ወጣቶች ሠርተው በማትረፊያቸውና ተማሪዎች ዕውቀትን በመሰብሰቢያቸው ወቅት እናቶቻቸው አልያም ቅደመ አያቶቻቸው ከዚህ ዘር አይደሉም ተብለው ሰው ካልደገፋቸው መውደቅ መነሳት የማይችሉ አዛውንቶች ከአካባቢያቸው ውጪ ሌላ መኖሪያ ስለመኖሩ የማያውቁ እናቶችና ሕፃናት ወግና ባህሉን ቋንቋውን በአግባቡ ወደማያውቁት ማኅበረሰብ ገብተው በወይንሸት የወረቀት ፋብሪካ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

በመጠለያው ታጭቀው የሚገኙት የማኅበረሰብ ክፍሎች እየጣለ ያለውን ዝናብ ከደብረ ብርሃን ብርድ ጋር መቋቋም እንዳቃታቸው ከፊታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ መጠለያው በተለምዶ የመጠለያ ካምፕ ይባል እንጂ፣ ለስደተኞች ወይም ለተፈናቃዮች ተብሎ የተሠራ አይደለም፡፡ የወይንሸት የወረቀት ፋብሪካ ለሌላ ሥራ ይውል ዘንድ ያዘጋጀው ሼድ እንደሆነ የደብረ ብርሃን ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎችና በአዲስ አበባ ዙሪያ ማንነትን መሠረት አድርጎ እየተካሄደ ያለውን ግድያና ማፈናቀል የሚመለከተው አካል ሊያስቆም ባለመቻሉ በየቀኑ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በከተማዋ ያሉ መጠለያዎች መያዝ ከሚገባቸው በላይ ይዘው በመጨናነቅ ላይ መሆናቸውን የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዩ በየነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተፈናቃዮች ከሼድ ውጪ በመሆን በድንኳን ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን፣ በሼዶቹ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትም ቢሆን አንድ ሺሕ ሰዎች በአንድ ክፍል ታጭቀው በመኖራቸው ለተለያዩ በሽታዎች እንደሚጋለጡ ተናግረዋል፡፡

ሰውን ‹በሞቴ አፈር ስሆን› ብለው አላፊ አግዳሚውን ያለ ስስት የሚያበሉ እናቶች አሁን ላይ ግን እጅ አጥሯቸው ቀን ጥሏቸው ለልጆቻቸው የሚያቀርቡት አጥተው የሰው እጅ በመጠበቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ ማኛ ጤፍ፣ ቆሎ፣ ስንዴ፣ አተርና ባቄላ አምርተው ለዓመት ቀለብ የሚበቃቸውን አስቀርተው የተረፋቸውን ለገበያ ጭነው የሚያቀርቡ እጆችና ወፍ አዕላፊውን የሚመግቡ ታታሪ አርሶ አደሮች አሁን ላይ እጅና እግራቸው ታስሮ ዕርዳታን ተጠባባቂ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

በግብርና፣ በንግድ፣ በመንግሥት ሥራ እንዲሁም በሌሎች የሥራ ዘርፎች ሌት ተቀን ሲባዝኑ የነበሩ ወጣቶች ለራሳቸው ተርፈው ለሌሎች ሲለግሱ የነበሩ እጆች አሁን ላይ ራሳቸውን መመገብ ተስኗቸው ከሌሎች እጆች በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ከባድ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ማስከተሉንም ተናግረዋል፡፡

ተምረው አገርን ይረከባሉ ቤተሰብና ወገንን ይረዳሉ በማለት አገር ተስፋ የጣለችባቸው ታዳጊ ሕፃናት መማር ቅንጦት ሆኖባቸው በመጠለያ ጣቢያ መኖር ከጀመሩ ሁለትና ሦስት ዓመታትን ማስቆጠራቸው ትክክል እንዳልሆነም ያክላሉ፡፡

የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮሚኛ በመሆኑ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር መግባባት ያልቻሉ ታዳጊዎች በለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ባልተመቻቸ ሁኔታ በድንኳን ተጠልለው የአማርኛ ፊደላትን ሲማሩ ሪፖርተር ለመታዘብ ችሏል፡፡

በካምፑ ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙ ከሰባት ሺሕ በላይ ሕፃናት መካከል   ከአንደኛ ክፍል እስከ ሦስተኛ ክፍል እየተማሩ የሚገኙት 1150 ሕፃናት ብቻ መሆናቸውን የደብረ ብርሃን ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ በለጡ ግርማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከሞት አምልጠው በብዙ ውጣ ውረድ ደብረ ብርሃን ከተማ ከደረሱ ተፈናቃዮች መካከል አቶ ሽኩር አንዳርጌ ሞላ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ሽኩር የ41 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ተወልደው እንዳደጉ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደር ሽኩር ስድስት ልጆችን በማፍራት አረጋውያን ወላጆቻችን በመጦር ልጆችን በማስተማር ጥሩ ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

በማኅበራዊ ኑሮአቸውም ቢሆን ዘር ቀለም ሳይለዩ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በፍቅርና በሰላም ክፉውንም ደጉንም ዘመን ተሻግረው በአብሮነት ይኖሩ እንደበር የሚናገሩት አቶ ሽኩር፣ በሚሠሩትና በሚያገኙት ልክ የተጠየቀውን ግብር ለመንግሥት በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጡ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ከዛሬ አንድ ዓመት ተኩል በፊት በእነሽኩር ቀበሌ አዲስ ወሬ እንደተሰማ ያስታውሳሉ፡፡ ከብቶቻችንን ከዱር አውሬ የምንከላከልበት አለፍ ሲል አጥርን ጥሶ የመጣ ጉልበተኛን የምንከላከልበትንና ከመንግሥት ፈቃድ ጠይቀን በገንዘባችን የገዛነውን መሣሪያ በአካባቢያችሁ የኦነግ ሸጌ ታጣቂ መሣሪያችሁን ሊቀማችሁ እየመጣ ስለሆነ ቀድማችሁ ወደ ወረዳ በመሄድ ለመንግሥት አካል እንድታስረክቡ የሚል ትዕዛዝ ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች እንደሰሙ ይናገራሉ፡፡

እነሱም የመንግሥትን ትዕዛዝ በማክበር ያላቸውን መሣሪያ ለወረዳው ገቢ እንዳደረጉ የሚናገሩት አቶ ሽኩር፣ ነገር ንግ ያስረከቡት መሣሪያ ሳይውል ሳያድር ሌሎች እንደታጠቁት በኋላም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል፡፡

ታጣቂዎችን ‹‹መሣሪያዎቻችንን አስረክበናል፣ ሌላ ምን አድርጉ ነው የምትሉት›› ብለው ሲጠይቋቸው እኛ የምንፈልገው የኦሮሚያን መሬት ለኦሮሚያ ማድረግ እንደሆነና ሀብትና ንብረታችሁን ትታችሁ በፍጥነት ክልሉን ጥላችሁ እንድትወጡ በማለት ባደጉበት ቀዬ ላይ እንዳሳደዷቸው ከስምንት በላይ ከብቶቻቸውን አርደው እንደበሉባቸው ሁለት መኖሪያ ቤታቸውን እንዳቃጠሉባቸው አቶ ሽኩር በንዴት ይናገራሉ፡፡

ሰውም ‹‹ከመሞት መሰንበት›› እንደሚባለው የተከፈተ ቤቱን ሳይዘጋ ሜዳ ላይ የተበተኑትን ንብረቶቹን ሳይሰበስብ የደረሰ ጤፍና በቆሎው ሳይሸለቅቅ የሞተው ሞቶ ያለው ልጆቹንና መላ ቤተሰቡን በመያዝ አካባቢውን ለቆ መውጣት ጀመረ፡፡

በመንገዳቸው ላይ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ሸቦካና ትቢ በተባሉ ከተሞች ላይ ጠብቀው ‹‹አካባቢያችሁ ተረጋግቷል ተመለሱና ወደ ቤታችሁ ግቡ›› የሚል መልዕክት ለኅብረተሰቡ ሲያስተላልፉ ሁሉም ቃላቸውን አምኖ ሲመለስ በተደራጁና በታጠቁ ኃይሎች የጅምላ ጭፈጨፋ እንደተደረገባቸው ብዙዎችም ህይወታቸውን እንዳጡም ያስታውሳሉ፡፡

ይኼ ይመጣል ብለው ባላሰቡት ሁኔታ ገንዘብ ወደ ባንክ ሳያስቀምጡ የሚያገኙትን ገንዘብም ለልጆች ማስተማሪያ ለልብስ እንዲሁም ከብቶችን በመግዛትና ያላቸውን ገንዘብ የሚያኖሩት ንብረት ላይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ልጆችን አስተምረው የተሻለ ደረጃ በማድረስ ወደ ከተማ ቦታ ለመግዛትና የተሻለ ኑሮን ለመኖር የወደፊት ህልማቸው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሽኩር፣ ‹‹ቤቱም ቤቴ አገሩም አገሬ ነው ብዬ በምኖርበት ሁኔታ ሁሉንም ተቀምቼ የሰው እጅ እየጠበቅኩኝ እገኛለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በዱር በጫካ በመሸ ከታጠቂዎች አምልጠው ከመጡ ወጣቶች የሚልቁ ለዱር አውሬ ቀለብ ሆነው ቀርተዋልም ብለዋል፡፡ መንግሥት አድሎአዊ ንግግሩን ትቶ አጥፊው ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ቦታቸውን እንዲያስመልስላቸውም ጠይቀዋል፡፡

አገር ሰላም ሆኖ ተወልደው ወዳደጉበት ቀዬ፣ ወንዛችን ቤት ንብረታችን ወደሚሉት አካባቢ እንዲመለሱ የሚጠይቁም በርካታ ናቸው፡፡

በሰፊው የለመደ እጅ ከአሥር በላይ ቤተሰብን ይዞ በሰው እጅ ከዓመት በላይ መቀመጥ እጅግ ከባድ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ገልጸዋል፡፡ ከፈጣሪ በታች ተስፋቸው መንግሥት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...