Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መገልገል ላልቻሉ አርሶ አደሮች ዲጂታል የግብርና ኪዮስኮች ሊከፈቱ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘመናዊ የስልክ ቀፎና የኢንተርኔት አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ዲጂታል የግብርና ኪዮስኮች እንደሚከፈቱ ተነገረ፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ለአርሶ አደሩ የዲጂታል ኤክስቴንሽን አገልግሎት ለማቅረብ በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉት የእጅ ስልኮች መሆናቸውን፣ በቀጣይ ግን አንድሮይድ ያልሆነ የእጅ ስልክ ላላቸው አርሶ አደሮች በእያንዳንዱ የግብርና ማሠልጠኛ ማዕከል ኪዮስክ በማቋቋም የዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት እንዲገኙ በፍኖተ ካርታው ላይ መቀመጡን አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሮች ኪዮስክ ያለበት ቦታ ወይም በቀበሌዎች አማካይ ቦታ ሄደው በኢንተርኔት በተገናኘው ኪዮስክ መረጃዎች እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር፣ ማዕከላቱ የልማት ሠራተኞች አርሶ አደሮችን የሚያስተምሩበትና መረጃዎችን የሚያሠራጩበት እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

ዘመናዊ የግብርና መረጃዎቹ ከማዕከል በቀጥታ ወደ ሁሉም አካባቢዎች የሚሠራጩ እንደሆነ ያስረዱት ማንደፍሮ (ዶ/ር)፣ ይህም የሚሆነው አንደኛው ከአርሶ አደሮች በጥያቄ (በድምፅ፣ በጽሑፍ መልዕክት) መልክ ለሚነሱ ለጥያቄዎቹ መፍትሔ የሚሰጥበት ሲሆን፣ ሌላው ከግብርና ሚኒስቴር ወይም ከሌሎች ተቋማት የቅድመ ማስጠንቀቂያ (ከተባይ፣ ከበሽታ፣ ከድርቅ ጋር በተያያዘ) በሞባይል መልዕክት የሚተላለፍበት ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዲጂታላይዜሽንን አርሶ አደሩ ደጅ ለማድረስ የስማርት ስልኮች፣ የተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞች፣ ተደራሽነቱ በሁሉም አካባቢዎች ባይሆንም፣ በቴሌቪዥንም የተለያዩ መልዕክቶችን እንዲተላለፍ እንደሚደረግ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የተለያዩ የማስተማሪያ ቪዲዮዎችን በማዘጋጀት በአርሶ አደር ማሠልጠኛ ተቋማት ለልማት ሠራተኞችና ለአርሶ አደሩ ትምህርቱ እንደሚዳረስ ተናግረዋል፡፡

በተወሰነ ሁኔታ የዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ለማዳረስ፣ በስልክ ጥሪ ማዕከላት የሚገኙ ባለሙያዎች መፍትሔ እየሰጡ መሆናቸውን መለስ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያያይዞም የግብርና ሚኒስቴርና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ ብሔራዊ ዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታን የተመለከተ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡

ኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታ ከዚህ ቀደም የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች በተሳተፉበት ውይይት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ፍኖተ ካርታው በግብርና ዘርፉ በተለይም በቴክኖሎጂ ረገድ ድርሻ ያላቸውና በተበታተነ መንገድ የሚሠሩ አካላትን አሰባስቦ አንድ ላይ እንዲሠሩ የሚያደርግ ይሆናል ተብሎ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ዓለም ከደረሰበት ሁኔታ ጋር እንዲጓዝ፣ እያደገ የመጣውን የግብርና መረጃ የሚመጥን ዕርምጃ ካልተደረገ፣ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ካልተዘረጋ፣ ከጊዜው ጋር መሄድ የሚያዳግት መሆኑን ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ማንደፍሮ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በፍኖተ ካርታው ላይ የሠፈሩ ጉዳዮችን መተግበር እንደተጀመረ፣ ነገር ግን ሁሉም በአንድ ጊዜ የሚጀመር እንዳልሆነና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው በቅድመ ተከተል እየተተገበሩ ናቸው፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዲጂታል አማራጭ ለአርሶ አደሩ የሚሰጠውን የኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ምንድን ናቸው የሚለውን መረጃዎች በመመዝገብ መጀመሩን፣ በሚፈለገውና አሁን ባለው መካከል ልዩነቱ ምንድን ነው የሚለውን በሦስት አንጓዎች መቀመጡ ተገልጿል፡፡

የውይይት መድረኩ ትልቁ ትኩረት ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ዲጂታይዝ ማድረግ፣ የዲጂታል አገልግሎት አርሶ አደሮች ባሉበት ቦታ ሆነው አጠቃላይ ስለሚሠሩት ሥራ፣ ከሠሩ በኋላ ስለምርታቸው፣ ስለገበያ መረጃ የሚያገኙበት የዲጂታል ኢትዮጵያ አካል ሆኖ፣ ከዘርፍ ደግሞ የዲጂታል ግብርና በሚለው ሥር የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት የተነደፈ ፎረም መሆኑን ማንደፍሮ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

 ፍኖተ ካርታው ከዓምና ጀምሮ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 መቼ ምን ይሠራል የሚለው፣ ከ30 የድርጊት መርሐ ግብሮች ላይ እየተቀዳ የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመንግሥት የአሥር ዓመታት ስትራቴጂ ዕቅድ ላይ ከተቀመጡት አራት ዓላማዎች በቤተሰብና በአገር ደረጃ የምግብና የሥርዓተ ምግብ ዋስትና ማረጋገገጥ፣ በገጠር ያሉ ወጣቶችና ሴቶች በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚሉት ተጠቃሾቹ መሆናቸውን የተናገሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው፣ እነዚህን ስትራቴጂ ግቦች ለማሳካት ትልቁ መሠራት ያለበት ግብርናን ዘመናዊ ማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች