Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ ለሚገኙ የሶማሌላንድ ስደተኞች ድጋፍ 116 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሶማሌላንድ ስደተኞች ድጋፍ 116 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ

ቀን:

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ዋና ኮሚሽነርና አጋሮቹ፣ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ላሉ የሶማሌላንድ ስደተኞች የሕይወት አድን ድጋፍ ለማቅረብ 116 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስታወቁ፡፡

ሪፖርተር ከተመድ ባገኘው መረጃ መሠረት በሶማሌላንድ የተፈጠረው ግጭት ቆሞ ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለስ እስከሚችሉ ድረስ፣ የመጀመርያ ደረጃ ዕርዳታዎችንና የሕይወት አድን ድጋፎችን ለማድረግ የተጠቀሰው መጠን ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ስደተኞቹ በአገራቸው ሰላም ሰፍኖ የማይመለሱ ከሆነም ከዚህ የበለጠ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

ተመድ በመረጃው እንዳስታወቀው ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የትብብር ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶችም የኢትዮጵያን መንግሥት በማገዝ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያቀርቡ እንደተጠየቀ፣ ድጋፉ ሲገኝም ለአጋሮቹ በማከፋፈል ስደተኞቹ እንዲደገፉ እንደሚደረግ ተመድ አክሏል፡፡

እስከ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ 88 ሺሕ የሶማሌላንድ ስደተኞች ቢመዘገቡም፣ በባለፉት ሰባት ሳምንታት ግን ከ100 ሺሕ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንና በሶማሌ ክልል መሥፈራቸውን የተመድ መረጃ ይጠቅሳል፡፡

አብዛኞቹ ስደተኞች ሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን መሆናቸውን የገለጸው ተመድ፣ 3‚200 የሚሆኑት ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ለብቻቸው እንደተሰደዱ ጠቁሟል፡፡ ሕፃናቱን ከቤተሰቦቻቸው ማገናኘትና የምክር አገልግሎት እየተሰጣቸው እንደሆነም ገልጿል፡፡

‹‹የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ከ56 ሺሕ በላይ ሕፃናት የኩፍኝ ክትባት ለመስጠት ተዘጋጅቷል፤›› ሲል የተመድ የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር ለሪፖርተር በኢሜይል በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

ወደ ሕክምና ተቋም የሄዱ በኮሌራም ሆነ በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች ሪፖርት እንደሌለ የገለጸው መረጃው፣ አሥጊ የሆነ ሁኔታ ባለመኖሩ በሽታ አይከሰትም ማለት እንደማይቻል አስረድቷል፡፡ ‹‹የክልሉና የወረዳ ጤና ቢሮዎች ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመሆን ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተሉ ነው፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ በስደተኞች መካከል የሚከሰት ወረርሽኝ የሚኖር ከሆነ ወይም የመከሰት አዝማሚያ ካለ ሪፖርት እንዲደረግ እየተሠራ ነው፤›› ብሏል፡፡

መንግሥት 460 ሔክታር መሬት በሶማሌ ክልል በዶሎ ዞን ሚርቃን በሚባል ሥፍራ አዘጋጅቶ የስደተኞች መጠለያ በመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሆነም የተመድ መረጃ ያስረዳል፡፡ በዚህ ሥፍራ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ውስጥ መጠለያው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ፣ 12 ሺሕ ስደተኞችን እንደሚይዝ ተመድ ገልጿል፡፡

ስደተኞቹ በአሁኑ ጊዜ እየተጠለሉባቸው ባሉ አካባቢዎች ውስን የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች መኖራቸውንና ሕፃናት፣ ሴቶችና አዋቂዎችም በችግሩ ምክንያት እንደሚጎዱ ተገልጿል፡፡ ‹‹አብዛኛዎቹ አዳዲስ ስደተኞች በትምህርት ቤትና በሌሎች የሕዝብ መገልገያ ተቋማት እየተጠለሉ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ መጠለያ በማጣታቸው ውጭ ናቸው፤›› ይላል መረጃው፡፡

የተመድ ኤጀንሲ ከሆኑት አንደኛው የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር እ.ኤ.አ. በ2023 ስደተኞችን በሚመለከት በኢትዮጵያ ለሚሠራቸው ሥራዎች 370 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ እንደሚያስፈልገው ዕቅድ የያዘ መሆኑን እ.ኤ.አ. እስከ መጋቢት 14 ቀን 2023 ዓ.ም. ድረስ ግን ያገኘው ዘጠኝ በመቶውን ብቻ እንደሆነ ሪፖርተር የተመለከተው መረጃ ያሳያል፡፡

ተቋሙ ካቀደው የ370.7 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ ውስጥ 32.9 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው በተወሰኑ አገሮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የግል ድርጅቶች ነው፡፡ ዴንማርክ ከፍተኛውን ድርሻ ስትይዝ የለገሰችውም 4.5 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ጃፓን 4.4 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...