ባለፉት ዓመታት በተደረገው ርብርብ የኤችአይቪ ኤድስ ወረርሽኝን መቆጣጠር ቢቻልም፣ የሕፃናትና አፍላ ወጣቶች የኤችአይቪ መከላከል ምርመራና ሕክምና አገልግሎት ላይ ግን አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ የጤና ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡
የጤና ሚኒስቴር አዲስ በነደፈው አገር አቀፍ የሕፃናት ኤችአይቪ ፕሮግራም የማፋጠኛ ኢኒሽየቲቭ መሠረት፣ ኤችአይቪ ኤድስ ዳግም ወረርሽኝ እንዳይሆን እየተሠራ ነው፡፡
ሰሞኑን ኢንሽየቲቩ ሲገመገም የኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ያደታ እንደገለጹት፣ ሕፃናትን ከኤችአይቪ የመከላከሉ ሥራ ላይ ክፍተት መኖሩን ተከትሎ፣ አገር አቀፍ የሕፃናት ኤችአይቪ ፕሮግራም የማፋጠኛ ኢንሽየቲቭ የታቀደ ሲሆን ፕሮግራሙም አበረታች ጅምር አሳይቷል፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ፣ ኤችአይቪ ኤድስ ተመልሶ ወረርሽኝ እንዳይሆንም በንቃት መከታተልና ኢኒሽየቲቩን በባለቤትነት ይዞ ተጠያቂነት ባለው አኳኋን መሥራት ያስፈልጋል።
ፕሮግራሙን በማስተዋወቅና ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ማደራጀት፣ የጤና ተቋማትን ማጠናከር ብሎም ቅንጅታዊ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም ሳይናገሩ አላለፉም።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት መኰንን በበኩላቸው፣ ራሱን ከኤችአይቪ የሚጠብቅ ትውልድ ለማስረከብ ትውልዱ ላይ መሥራት እንደሚጠበቅ፣ ይህን ለማስፈጸምም ሕፃናትን የመመርመር ሥራ ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የኢንሽየቲቩ አጋር ድርጅቶች፣ ባለፉት ዓመታት በጤና ሚኒስቴር አመራር ሰጪነት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የኤችአይቪ ሥርጭትን ለመቆጣጠር በጋራ እየሠሩ መሆኑን በዚህም በርካቶችን መታደግና አዳዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽኖችን መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።
በኤችአይቪ ፕሮግራም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶች እጅግ በጣም ብዙ ቢሆኑም፣ ሕፃናትና ወጣቶች ላይ ያነጣጠሩ አገልግሎቶችን ማሳደግ የረዥም ጊዜ ፈተና ሆኖ መቆየቱንም ጠቁመዋል።
ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሕፃናትና ጎረምሶች ጉዳይን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢንሽየቲቩ አጋር ድርጅቶች መገለጻቸውንም ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡