Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የልብ ቀዶ ሕክምና አላቂ ዕቃዎች አለመኖር ባለሙያዎችን ወደውጭ አገር እንዲኮበልሉ ይዳርጋቸው ይሆን?

የልብ ቀዶ ሕክምና ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ፣ ከሕይወት ጋር የተያያዘና እጅጉን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም በጥሩና በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የበኩሉን ዕገዛ ያደርጋል ተብሎ የታመነበት የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር ተቋቁሟል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ደጁማ ያደታ (ዶ/ር)፣ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ፣ በልብ ቀዶ ሕክምናና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር አመሠራረት፣ በዚህም አባላቱ ያገኙት ጥቅምና ለልብ ቀዶ ሕክምናው ማኅበሩ ያለውን ፋይዳ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ደጁማ፡- የኢትዮጵያ የልብ ማኅበር በ2014 ዓ.ም. መስከረም ተቋቋመ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ2,200 በላይ አባላት አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የልብ ሕመም ያለባቸው ናቸው፡፡ የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎቹም በማኅበሩ የታቀፉ ናቸው፡፡ ሕሙማኑ በማኅበር መደራጀታቸው ተገቢውን እንክብካቤና ለሕመማቸው የሚረዱ ቁሳቁሶችን ከተለያዩ ተቋማት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የልብ ሕክምናን በተመለከተ ለሚያነሱት የመብት ጥያቄዎች ተገቢው መልስ እንዲያገኙ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ እንዲሻሻል ከአጋር ድርጅቶች ጋር መሥራት የተሻለ መሆኑን ለመገንዘብ ችለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የልብ ታካሚዎችን አብሮነትና መረዳዳትን እንዲያዳብሩ ለማድረግ፣ ተመሳሳይ ከሆኑ ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት፣ ስለልብ ሕመምና ስለሕክምናው ለኅብረተሰቡ ተገቢውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችላቸውን አካሄድ አመቻችቶላቸዋል፡፡ በማኅበር መደራጀታቸው ያስገኘላቸው ሌላ ጥቅም ለልብ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለማመቻቸት፣ የሚጠቀሟቸውን መድኃኒቶች በአግባቡና በሰዓቱ ለመውሰድ ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማግኘት በማኅበር መደራጀታቸው ረድቷቸዋል፡፡ በአጠቃላይ የልብ ቀዶ ሕክምና ፍትሐዊና ግልጽ በሆነ መንገድ ሲከናወን በቅርብ ሆነው የማየትና የመታዘብ ዕድል አጋጥሟቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ከማኅበሩ እንቅስቃሴ ወጣ እንበልና ከልብ ጋር ተያያዥነት ስላላቸው በሽታዎች እንነጋገር፡፡ ለልብ በሽታ መንስዔዎች ምንድናቸው?

ዶ/ር ደጁማ፡- ስለመንስዔዎቹ ከመናገሬ በፊት የበሽታዎቹን ዓይነትና የሽፋን መጠናቸውን አጠር ባለ መልኩ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ በሽታዎችን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ተላላፊ የሆነ (ከሰው ወደ ሰው የሚላለፍ) በሽታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ነው፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው አደጋ ነው፡፡ የእያንዳንዳቸው የሽፋን መጠን ሲታይ ደግሞ ተላላፊ በሽታ 53 በመቶ፣ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ 39 በመቶ፣ አደጋ ሰባት በመቶ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል በሕክምና መከላከል የሚቻለውና በታዳጊ አገሮች የተንሰራፋው ተላላፊ በሽታ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የእናቶችንና የጨቅላ ሕፃናትን በሽታዎች እንዲሁም በምግብ እጥረት የሚከሰቱ በሽታዎችን ሁሉ አጠቃሎ ይይዛል፡፡ ይህም ሲጠቃለል ‹‹ኮምኒክብል ማትርናል፣ ኒዎኖታል ኤንድ ኒውትራሽናል ዲዝዝ›› ይባላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ተላላፊ ያልሆነው በሽታ ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ብዙ ቢሆኑም 45 በመቶ ያህሉን የያዘው የልብ ድካም በሽታ ነው፡፡ ይህም በሽታ እንደማንኛውም በሽታ በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው ከውልደት በኋላ የሚመጣ የልብ በሽታ (አኳየርድ ኸርት ዲዝዝ) የሚባል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በውልደት አብሮ የነበረ ወይም ተያይዞ የሚመጣ የልብ በሽታ (ሮማቲካል ኸርት ዲዝዝ) ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ያለው አኳየርድ ኸርት ዲዝዝ ሲሆን፣ ይህም ከጉሮሮ ጋር ግንኙነት ያለው የልብ በሽታ ያስከትላል፡፡ ቀጥሎ ከደም ግፊት ጋር ያለው የልብ በሽታ ሌላው ጫና መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከአኗኗርና ካለመንቀሳቀስ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ኮሌስትሮል የደም ቧንቧን ይዘጋል፡፡ ይህም ለልብ በሽታ መንስዔ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለልብ ቀዶ ሕክምና መሟላት የሚያስፈልጋቸው ነገሮችና እንደ ቁልፍ ችግር ተብሎ የተለየው ምንድነው?

ዶ/ር ደጁማ፡- የልብ ቀዶ ሕክምናን ለማከናወን ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነርሱም ቤት/ቦታ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና ለቀዶ ሕክምና እንደ ግብዓት የሚያገለግሉ አላቂ ዕቃዎች ናቸው፡፡ ከቦታ ወይም ከቤት አንጻር ያለው ሁኔታ ሲታይ አዲስ አበባ ውስጥ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ አምስት ጤና ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የመንግሥት ጤና ተቋማት ናቸው፡፡ እነርሱም ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታልና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ናቸው፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ የሚገኘውና መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ወይም በኢትዮጵያ የሕፃናት ልብ መርጃ ማዕከል የሚንቀሳቀሰው የሕፃናት ልብ ሕክምና ማዕከልና ሌሎች ሁለት የግል ጤና ተቋማት እንደዚሁ የልብ ቀዶ ሕክምና ያደርጋሉ፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይልን በተመለከተ በየጊዜው እየሠለጠኑ የሚወጡ በቂ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ዓይነት ባለሙያዎች ቁጥር ወደፊትም እየጨመረ ይሄዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ እንደ ቁልፍ ችግር ወይም ማነቆ ሆኖ የታየው ለግብዓትነት የሚጠቅሙ የአላቂ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረትና ከነአካቴውም አለመኖር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ባለሙያዎቹ ብዙ መሥራት እየቻሉ እጥረቱ ወይም የአላቂ ዕቃዎች አለመኖር ጥቂቱን ብቻ እንዲሠሩ በተረፈ የቀረውን ጊዜ ያለሥራ እንዲያባክኑ አድርጓቸዋል፡፡ አቅርቦቱ ካለ ግን ብዙ ታካሚዎችን መርዳት ይቻል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ አላቂ ዕቃዎች እጥረት ወይ ማጣት መንስዔው ከምን የመጣ ነው?

ዶ/ር ደጁማ፡- መንስዔው አላቂ ዕቃዎቹ በጣም ውድ ከመሆናቸው የተነሳ አስመጪዎች ትርፍ የለውም ወይም አያዋጣንም ከሚል እምነት ዕቃዎቹን ከማስመጣት መቆጠባቸው ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው በይበልጥ ጫና ለሚያሳድሩ በሽታዎች ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአላቂ ዕቃዎች አቅርቦት ትኩረት እንደተነፈገው ነው የሚታየው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አላሳደረም?

ዶ/ር ደጁማ፡- በእርግጥ አሳድሯል፡፡ አንድ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ እስከ ሰብ ስፔሻሊቲ ድረስ በአገር ውስጥ ቢሠለጥንም፣ ሙያውን ወይም ብቃቱን የሚያሳድገው ደግሞ በተግባር ወይም በሥራ በሚያከናውነው የቀዶ ሕክምና ሥራ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥራ አልፎ፣ አልፎ ብቻ ከመጣና ጭርሱንም ከሌለ ወደኋላ መቅረትን ያስከትላል፡፡ ከዚህ አኳያ በአገር ውስጥና በእሥራኤል በቂ ሥልጠና የወሰዱ አንድ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሠለጠነበትን ሙያ በአላቂ ዕቃዎች ዕጦት ሳቢያ በሚፈለገው መልኩ ሥራ ላይ ባለማዋሉ የተነሳ አገር ለቆ ወደ ውጭ አገር መሄድ ግድ ሆኖበታል፡፡ ይህም ለአገር ትልቅ ኪሣራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም አግባብ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ለልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የአላቂ ዕቃዎች እጥረትና አለመኖር ሐኪሞችን ወደ ባዕድ አገር እንዲኮበልሉ ዳርጓቸዋል ለማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ እንዳለ ሆኖ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በየሳምንቱ ስንት የልብ ቀዶ ሕክምና ያካሂዳል?

ዶ/ር ደጁማ፡- አሁን ባለው ሁኔታ የልብ ማዕከሉ ከሞላ ጎደል የተወሰኑትን በወር ይሠራል፡፡ ግን አሁን በአላቂ ዕቃዎች ዕጦት ሳቢያ እየሠራ ያለው በልብ ክፍልፋዮች መካከል ያሉትንና በተፈጥሮ የመጡ የልብ ቀዳዳዎችን የመጠገንና የበቀሉ ነገሮችን የማስወገድ ሁኔታ ነው፡፡ በስም የተጠቀሰው ሆስፒታል ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2022፣ 105 የልብ ቀዶ ሕክምና አከናውኗል፡፡ ይህም በሳምንት ሲታይ ከአንድ ግፋ ሲል ደግሞ ከሁለት አይዘልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠባበቁት ከ12,000 በላይ ናቸው፡፡ ሳይመዘገቡ ቤታቸው ተቀምጠው የቀሩ ሲታከልበት የአገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር አሁን ከተያዘው በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ሪፖርተር፡- አላቂ ዕቃዎች የተባሉትን ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ደጁማ፡- አላቂ ዕቃዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ቫልቭ፣ የልብ ባትሪና የቀዶ ሕክምናው ሲጀመር ወይም በሒደት ላይ እያለ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ልብ አራት ክፍልፋዮች አሉት፡፡ እነርሱም በግራና በቀኝ፣ ቀጥሎ ደግሞ በላይና በታች ናቸው፡፡ እነዚህ ክፍልፋዮች ደም እንደ ልብ የሚያዘዋውሩ የተፈጥሮ ቫልቮች አላቸው፡፡ ሮማቲካል ዲዝዝ በእነዚህ ቫልቮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ሰው ሠራሽ በሆነ ቫልቭ መቀየር ወይም መተካት አለባቸው፡፡ የተዘረዘሩት የተፈጥሮ መሣሪያዎች፣ ቫልቮችና የልብ ባትሪ ሲጎዱ በሰው ሠራሽ መተካት አለባቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ዋጋቸው በጣም ውድና ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ስለበሽታዎች ጫና ሲነገር ይሰማል፡፡ በሽታዎች ያስከተሉትን ጫና ማን ነው የሚመዘግበው?

ዶ/ር ደጁማ፡- ‹‹ግሎባል በርደን ኦፍ ስተዲስ ግሩፕ›› የተባለና መቀመጫውን በአሜሪካ አገር የሚገኝ አንድ ዓለም አቀፍ አካል አለ፡፡ ይህ አካል የተቋቋመው በ1990 ነው፡፡ ተቋሙ በየአገሩ የራሱ የሆነ ተመራማሪዎች አሉት፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎችም በየዓመቱ ወይም በተወሰኑ ጊዜ በየተመደቡበት አገር ያሉትን የበሽታ ጫናዎችን እየመዘገቡ ከተነተኑ በኋላ የደረሱበትን ውጤት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሠሩትን ወይም የደረሱበትን ውጤት በ2019 ሪፖርት አድርገዋል፡፡ አንዳንድ አገሮችም ሪፖርቱን ለፖሊሲ ግብዓት ይጠቀሙበታል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የበሽታ ጫና የሚመዘገቡት በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተመደቡትና የግሩፑ ተጠሪ የሆኑ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ውጪ በየክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎች የልብ ቀዶ ሕክምና ክፍሎች በምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

ዶ/ር ደጁማ፡- በትግራይ ክልል መቀለ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል ብቻ ነው የልብ ቀዶ ሕክምና ክፍል ያለው፡፡ የቀሩት ክልሎች ሁሉ ይህ ዓይነት አገልግሎት የላቸውም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...