Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሆድና የሆድ ነገር

ሆድና የሆድ ነገር

ቀን:

(ክፍል ስድስት)

በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)

አቶ ባል – “ለዛሬ ገንፎ”   

ወ/ሮ ሚስት – “ለልክህ ድፎ”

ዜናዎች ወይም በአጠቃላይ መረጃዎች በጋዜጣ ላይ ከመታተማቸው፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከመሠራጨታቸው በፊት እንዴት እንደሚመረጡና ለሕዝብ የመድረስ ወይም አለመድረስ ዕድላቸው እንዴት እንደሚወሰን የሚነግረን ነቢብ (“ቲዎሪ”) “Gatekeeping” ይባላል፡፡ የዚያ ሚዲያ አዘጋጅ ወይም አርታኢ፣ የትኛው መረጃ ለእኛ መድረስ እንዳለበትና መድረስ እንደሌለበት የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንዲደርሰን ከወሰነው ዜና ወይም ሌላ መረጃ ውስጥ ባሉ ቃላትና ሐረጎች አገላለጽ፣ እንዲሁም በአንቀጾች ቅደም ተከተል ላይ ሳይቀር ይወስናል፡፡ በሌሌ አባባል መረጃው እንዴት ወይም በምን መልክ ሊደርሰን እንደሚገባ ሁሉ ይወስናል፡፡ እናም በዚህ ሒደት ውስጥ የእሱን ፈቃድ አግኝቶ የታተመውን ወይም የተሠራጨውን ብቻ ነው ከዚያ ሚዲያ ማግኘት የምንችለው፡፡ ከዚህ አንፃር  “Gatekeeping”ን የመረጃ ቃፊርነት፣ አርታኢውን “Gatekeeper” “የመረጃ ቃፊር” ልንለው እችላለን፡፡

የዚህ ነቢብ (Theory) የአመጣጥ መሠረቱ የቤት እመቤቶች ናቸው፡፡ ቤተሰቡ ዛሬም ሆነ ነገ ምን መብላት እንዳለበት፣ በቁርስ፣ በምሳና በእራት ወቅቶች ምን ዓይነት ምግብ መሠራትና መቅረብ እንዳለበት የሚወስኑት እነሱ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር Gatekeeper ናቸው፡፡ የምግብ ቃፊር መሆናቸው ነው፡፡

ሚስቶች አንዳንዴ ይኼን የምግብ ቃፊርነታቸውን በደንብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ቤት ባፈራው መጠን ቤተሰቡ የተለያየና የተመጣጠነ የምግብ ዓይነት እንዲያገኝ ከማድረግም አልፈው፣ የቤተሰቡ አባላት የምግብ ዓይነት ምርጫ እንዲጠበቅ እስከማድረግ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ማለትም ካልፈለጉ የተወሰነ ዓይነት ምግብ ደገምገም አድርገው ከማቅረብም አልፈው፣ የማንንም የምግብ ምርጫ ላይጠብቁ ይችላሉ፡፡ የቀፊርነት ሥልጣን ለመቼ ነው?

እዚህ ላይ የአንድን አባወራ ገጠመኝ ለአብነት እናንሳ፡-

ይህ አባወራ የምግብ ምርጫ ፍላጎቱን ሲናገር፣ ሚስቱ ምርጫውን አትጠብቅለትም፡፡ እንደ ነፍሰጡር ሴት የፈለገ ነገር አምሮት እንድታዘጋጅለት ቢጠይቃት፣ እንቅ ብትል አታዘጋጅለትም አምሮት፣ አምሮት ይወጣለታል እንጂ፡፡

ለቁርስ ገንፎ ካማረውና ከጠየቃት፣ ዳቦ ትጋግራለች “ለዛሬ ገንፎ” ሲላት፣ ለልክህ ድፎ” በማለት፡፡

በሌላ ጊዜ ንፍሮ ሲያምረው፣ “ለዛሬ ንፍሮ” ሲላት፣ ለልክህ ቆሎ” ትለዋለች፡፡

ከተወሰ ጊዜ በኋላ፣ የሚፈልገውን ምግብ ተቃራኒ እንድትሠራለት በመጠየቅ፣ የሚፈልገውን ምግብ መብላት እንደሚችል ሐሳብ መጣለት፡፡ እናም ሥራ ላይ አዋለው፡፡

ዳቦ መብላት ሲያሰኘው፣ “የኔዋ! ለዛሬ ገንፎ” ይላታል፡፡ “ለልክህ ድፎ” ትለዋለች፡፡ ድፎ ትደፋለች፡፡ ቢገምጡት፣ ቢበሉት የማይጠገብ ዳቦ ታቀርብለታለች፡፡

ቆሎ ሲያምረው፣ “ለዛሬ ንፍሮ” ይላል፡፡ “ለልክህ ቆሎ” በማለት ንፍሮ ትቀቅላለች፡፡ ንፍሮ ባስፈለገው ጊዜ፣ “የኔዋ ለዛሬ ቆሎ” ይላታል፡፡ “ለልክህ ንፍሮ” በማለት ገና ሲያዩት የሚያስጎመዥ ንፍሮ ታቀርብለታለች…  

 ገንፎ ሲፈልግ ደግሞ፣ “የኔዋ! ለዛሬ ድፎ” ይላታል፡፡ “ለልክህ ገንፎ” ትለዋለች፡፡ ገንፎ ታገነፋለች አፍ ውስጥ ለማጣጣም እንዲቻል ጭምር ለአመል ያህል ትንሽ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ ዘወር ዘወር ካደረጉ በኋላ ቶሎ ቶሎ ስልቅ ስልቅጥ የሚደረግ፣ “ምሳዬም፣ እራቴም እሱ በሆነ” የሚያስብል ገንፎ፡፡

ይኼኔ አቶ ባል፣ “ገንፎ በቅቤ፣ ይወዳል ቀልቤ” እያለ ገንፎውን መሰልቀጥ ነው፡፡ ታዲያ ይኼን የሚለው በሆዱ ነው፡፡ አለዚያማ “ነቄ” ካለች የምግብ ምርጫውን በሥልት የማስከበር ዕድሉ ተዘጋ ማለት ነው…

ስለገንፎ ከተነሳ አይቀር ስለእሱ ትንሽ ብናወራ አይከፋም፡፡ ገንፎ በአገራችን አንዱ በጣም ተወዳጅ ምግብ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የተወዳጅ ምግቦች ውድድር ቢካሄድ ማለትም በመጠይቅ አማካይነት መረጃ ቢሰበሰብ፣ ገንፎ ዕድ ቁጥር ላይ ገጭ የማለት ዕድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል ቢያንስ በወሎዬዎች አካባቢ፡፡ “እንዴት እንዲህ ልትገምት ቻልክ?” ካላችሁ፣ ወሎዬዎች ለገንፎ “የተቀኙለትን” የሚከተለውን ግጥም ተመልከቱ፡-

“ሰለሄ መለሄ

ጉሮሮ አይነሀሄ

ገብተህ ተለህለሄ”

ይሄን መጣጥፍ እየከተብኩ ባለበት ወቅት፣ በተለይ “ሰለሄ”፣ “መለሄ” እና “ተለህለሄ” የሚሉትን ቃላት ትርጉም ወይም ስርወ ቃል በተመለከተ የቋንቋ ምሁራንን ጭምር ብጠይቅም፣ ከአገባባቸው በመነሳት ለመግለጽ ከመሞከር ባለፈ፣ ትርጉማቸውን በእርግጠኝነት የሚያውቅ አላገኘሁም፡፡ እዚህ ባህር ዳርም፣ ወሎ አካባቢ የማውቃቸውን ሰዎችም “አፋልጉኝ” አልኩ፡፡ አልተሳካም፡፡

ሲጨንቀኝ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊና ሰብዓዊ ሳይንስ ኮሌጅ ባልደረባ ለሆነው መምህር ይማም ሙሀመድ የ”አፋልጉኝ” ማስታወቂያዬን በቴሌግራም አቀረብኩለት፡፡ የሚከተለውን መልስ ሰጠኝ፡፡

“‘ሰልሄ መልሄ’ ማለት፣ ‘ሰላላ-መላላ’ ከሚለው የመጣ ይመስላል፡፡ ‘አቅመ ቢስ፣ ቀጭን፣ ደካማ፣ በቀላሉ የሚሰለቀጥ’ ማለት ይመስለኛል፡፡” (በመሀል ያለው ፊደል ከ”ለ” ወደ “ል” መቀየሩ፣ ቃላቱ በሁለቱም መንገድ ሊጠሩ እንደሚችሉ አመላካች ነው፡፡)

የሰለሄ መለሄን የቃላቱን ትክክለኛ ስርወ ቃልም ሆነ ትርጉም በቀጥታ ማወቅ ባንችልም፣ ችግር የለመውም፡፡ ዋናው ነገር ሐሳቡ ገብቷችኋል ሰለሄ መለሄ ገንፎ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ወለዬዎች ምን ያህል እንደሚያቆላምጡትና እንደሚያሽሞነሙኑት፡፡ እኔም የምፈልገው እሱን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መምህር ይማም ስለ”ሰለሄ፣ መለሄ” የማላውቀውን አንድ ግጥምም ጀባ ብሎኛል፡-

“ሰለሄ መለሄ፣ የሴቶቹ ወንድም

እጅ ሲበዛበት፣ ቅቤ ሲያንስ አይወድም፡፡”

በግጥሙ ውስጥ ሴቶች መሞገሳቸውን ልብ በሉ፡፡ ለምግብ ቃፊርነታቸው የተሰጠ ዕውቅና ብቻ ሳይሆን፣ ሙገሳን ተገን በማድረግ ገንፎ ቶሎ ቶሎ እንዲያዘጋጁ የሚገፋፋ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ከሙገሳውና ከዕውቅናው ባሻገር ገንፎ መቼ መዘጋጀት እንዳለበትና ሊሟላ ስለሚገባው ነገር ቢያንስ በተዛዋሪ ይጠቁማል፡፡ ከቤት ውስጥ ብዙ ሰው ባለበት ወቅት ገንፎ ማዘጋጀት ጥሩ አለመሆኑን ይመክራል ለምን ከተባለ እጅ ይበዛበታልና፡፡ በሌላ በኩል ቅቤው ማነስ የለበትም፣ ቅቤው መብዛት ወይም ቢያንስ የተመጣጠነ መሆን አለበት የጣዕሙ ልክ የሚታወቀው እንዲያ ሲሆን ነውና፡፡

የ”ሰልሄ መልሄ”ን ትርጉም በምናፈላልግ ላይ በነበርኩበት ወቅት፣ “እንዲያው ለምን አልባቱ” በማለት ኢንተርኔት ላይ ለመፈለግ ሞከርኩ፡፡ የእኛ ነገር አብዛኛው ኢንተርኔት ዓለም ውስጥ የለም በተለይ ደግሞ በአማርኛ ተጽፎ፡፡ ሰለሄ መለሄ ገንፎ መሆኑን ብቻ የሚናገሩ ሁለት ወይም ሦስት ልጥፎችን አገኘሁ፡፡ እግረ መንገዴን “ኩችዬ በሚል የብእር ስም ስለሰለሄ መለሄ ግጥም የጻፈ ሰው አገኘሁ፡፡ ግጥሙ ትንሽ ፈገግ አስብሎኛል፣ ይሄውላችሁ፡-

“ለነቃ ጉሮሮ ለተቀየመ አንጀት ለጦዘ ጭንቅላት ለደከመው ጉልበት መድኃኒቱ አንተ ነህ ሰለሄ መለሄ ውረድ በላንቃዬ ግባ ተለህለሄ፡፡” (ኩችዬ 2004)

“ሰለሄ መለሄ፣ ጉሮሮ አይነሀሄ፣ ገብተህ ተለህለሄ” የሚለውን ግጥም እዚህ ያመጣሁበት ዓላማ አንድና አንድ ነው ሐበሾች ለአንድ ምግብ ያላቸውን ከልክ ያለፈ ፍቅር ወይም ፍላጎት ለመግለጽ ግጥም “እስከ መቀኘት”፣ ከዚያም አልፎ እንዴት ቃላት እንደሚያጥራቸውና አዳዲስ ቃላትን እስከ “መፍጠርም” ጭምር ሊሄዱ እንደሚችሉ ለማሳየት፡፡ መቼስ በሥራ ላይ ያሉት፣ የምንጠቀምባቸው የአማርኛ ቃላት ለገንፎ ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎትና ፍቅር በወጉ አልገልጽላቸው ቢሉ አይደል ቃላትን “ፈጥረው” ለመጠቀም የተገደዱት…     

ገንፎ ተወዳጅ ምግብ አድርገን ስንቆጥር ከሁሉም የምግብ ዓይነቶች “ደረጃዬ ተወሰደ” በማለት ሊከሰን ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ሊወጣ የሚችለው ማን እንደሆነ ይገባችኋል፡፡ አቶ ሽሮ! ስለዚህ ስለሽሮ ትንሽ ብናወራ ሚዛናዊ ከመሆንም አልፈን፣ የሽሮ ወዳጆችን ልናስደስት እንችላለን፡፡ ሽሮ ሲባል ያው እንጀራንም ይጨምራል፡፡ መቼም ሽሮ በዳቦ ማለታችን አይደለም፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ፣ ብዙዎቹ የሽሮ ወደጆች “ወራጅ አለ” ማለታቸው አይቀርም፡፡

የእንጀራ ነገር ለብዙ ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በጣም ብዙ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ሞታቸው ነው፡፡ የፈለገ “ምርጥ” የተባለ ምግብ ቢቀርብላቸውና ቢበሉ፣ እንጀራ ከሌለበት ምግብ ያልበሉ የሚመስላቸው ወይም የምግብ እርካታን የማያገኙ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡

ለማንኛውም እንጀራ በሽሮ ተወዳጅ ምግብ የመሆኑን ያህል፣ ሽሮው በጥሩ ሁኔታ መሠራት አለበት፣ ይህ ደግሞ ከመጀመርያው የሽሮ ዱቄቱን አሠራርና የቅመማ ሒደት ያካትታል፡፡ አለዚያማ በ1991፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወደ ግንባር የዘመቱት ወጣቶች “ከማይረባ ሽሮ፣ ይሻላል ሽራሮ” በማለት የገጠሙት ዓይነት ሁኔታ ይከሰታል፡፡ ሽሮ ከዱቄቱ ዝግጅት ጀምሮ በጥንቃቄና በተሟላ ቅመም ጭምር መዘጋጀት አለበት፡፡ እዚህ ላይ ተማሪዎቼ አንድ “ዲያስፖራ” ስለወጠወጠው የሽሮ ወጥ “ታሪክ” የነገሩኝ ቀልድ ጥሩ አብነት ነው ሽሮ ወጥ ተወዳጅ በመሆኑ እስከ “መዶስበር” ከመድረስም አልፎ ምን ዓይነት “መዘዝ” ሊያስከትል እንደሚችል ለመረዳት፡-

አቶ “ዳያስፖራ” በቅመም ያበደ የሽሮ ወጡን ይወጠውጣል፣ ትንሽ እንደ መብሰል ሲልም፣ ሌላ በቅመም ያበደ ነገር ጣል ያደርግበታል ንጥር ቅቤ፡፡ በመሆኑም አካባቢው በሽሮ ወጡ መዓዛ ይጥነገነጋል፡፡ በአካባቢው የነበሩ እናቶች ፈረንጅ የሽሮ ወጡ ሲሸታቸው ግራ ተጋቡ፣ ደነገጡም፡-

“ይህ ሽታ ምንድነው?” እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ፡፡

እርስ በርሳቸው ተፋጠጡ፡፡ ማንኛቸውም መልስ የላቸውም፡፡ እናም ጨነቃቸው፣ ሲጨንቃቸውም ወደ መላምት ገቡ፡፡

“አደገኛ የሆነ ኬሚካል እየተቀመመ እንዳይሆን?” ተባባሉ፡፡

እናም ወዲያው ነፃ የስልክ መስመር ላይ በመደወል ሥጋታቸውን ለፖሊስ አጋሩ፡፡ አራት ወይም አምስት የሚሆኑ የፖሊስ መኪኖች የአደጋ ምልክት ማስጠንቀቂያ የሆነ ድምፃቸውን እያናፉ ወዲያው ከች!… አቶ ኢትዮ ዳያስፖራ፣ “ይኼ ከባቄላ ዱቄት የተዘጋጀ ምግብ ነው፣ ቀምሼ ላሳያችሁ”፣ ምንትሴ ቅብጥርሴ ቢል፣ ለመለመን ቢሞክር ማን አባቱ ሰምቶት!…

ሰውነትን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ቱታ በለበሱ፣ ማስክ ባደረጉና ጓንት ባጠለቁ ሰዎች አማካይነት የአቶ ሽሮ ናሙና ከንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተወሰደ… አቶ ዳያስፖራም የላቡራቶሪ ውጤቱ እስከሚታወቅ ወደ ማረፊያ ቤት…

ደግነቱ የአቶ ሽሮ የምርመራ ውጤት ብዙ ጊዜ ሳይወስድ ታወቀ፡፡ የላቡራቶሪ ባለሙያዎቹ ፈረንጆች “ቢበሉትም፣ ባይበሉትም የማይጠቅም፣ የማይጎዳ” በማለት የምርመራ ውጤታቸውን አሳወቁ፡፡ (ለማንኛውም የሽሮ ወዳጆች እንዳትቀየሙ፣ እባካችሁ ቀልድን በቀልድ ውሰዱ፡፡)

በነገራችን ላይ፣ ሽሮ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ምግብ የመሆኑን ያህል፣ በድህነት በኩልም፣ ቢያንስ ምግብን በተመለከተ የመጨረሻው ወለል መለኪያ እሱው ነው፡፡ ብዙ ደሃዎች ከቤታቸው እንጀራ እያላቸው፣ ሽሮ ወጥ ለማብሰል ሽንኩርትም፣ ዘይትም፣ ምናልባትም ደግሞ የማገዶ እንጨትም ጭምር ሲያጡ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር፣ ሽሮውን በውኃ በጥብጠው በእንጀራ እያጠቀሱ መብላት ነው፡፡ ከዚህ በታች ያለው ድህነት ወይ ልመና ወይ ፆም ማደር ነው፡፡ (በክፍል ሰባት እንገናኝ)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...