Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ያለፉትን ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመዳሰስ የችግሮቹን መሠረታዊ ምንጮች አስረድተዋል። 

‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥቅሉ በአኃዝም ሆነ በመስተጋብር እያደገና እየሰፋ መጥቷል። የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በአጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) ብቻ ሳይሆን ከዓለም ጋር ባለው ትስስር ወይም መስተጋብርም እየሰፋ መምጣቱና፣ በተፈጠረው ትስስር መጠንም በሌላው ዓለም ያለው የኢኮኖሚ መናጋት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት አምጥቷል፤›› ብለዋል።

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ጊዜያት የኢኮኖሚ መናጋት መመታቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢኮኖሚ መናጋቱ መነሻ አንድ አካባቢ ቢሆንም አገሮች በሚፈጥሩት የኢኮኖሚ መስተጋብር ልክ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲያጋጥማቸው መቆየቱን አውስተዋል።

‹‹የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት መሠረቶች ሦስት ናቸው። አንደኛው ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ሲኖር ነው፣ ሁለተኛው የአሴት (የሀብት) ዋጋ መውረድ ነው፣ ሦስተኛው ደግሞ የገቢ መቀነስ ነው። በዚህ ላይ የዋጋ ንረት ሲጨመር መናጋቱን ለቁጥጥር አስቸጋሪ ያደርገዋል፤›› ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተፈራ ያለው አምስተኛው የኢኮኖሚ መናጋት ዓይነት እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አምስተኛው የኢኮኖሚ ችግር ከዚህ ቀደም ከነበረው ዓይነት የኢኮኖሚ መናጋት ጋር በባህሪውም በውጤቱም አንድና ያው እንዳልሆነ ገልጸዋል። አሁን ያለው አዝማሚያ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለና፣ ከፍተኛ የሠራተኛ መቀነስ ሒደትን በማስከተል ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሌላው እየታየ ያለ የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት አዝማሚያ የባንኮች መውደቅ መሆኑን ገልጸዋል። ታላላቅ የሚባሉት የዓለም ባንኮች መንኮታኮት መጀመር በቀጥታ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚያደቀው ሥጋታቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩልም ከውጭ ዕዳ ጫና ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መናጋት አሳሳቢ እንደሆነ አስረድተዋል።

‹‹ቀደም ሲል የውጭ ዕዳ የመክፈል ችግር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ኢኮኖሚዎች ብቻ ጉዳይ ነበር። አሁን ግን ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮችም በከፍተኛ ደረጃ እየተቸገሩ ነው። እነሱ መክፈል ሲቸገሩ ወደ እኛ የሚመጣው ሀብት ይቀንሳል፤›› ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ያለ ከፍተኛ የሸቀጦች የዋጋ ንረት ሌላው የአገሮች ራስ ምታት መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት አንዳንድ አገሮች የህልውና ችግር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ የኢኮኖሚ መናጋት ምልክቶች በዓለም ላይ በስፋት እየታዩ እንደሆነና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም በፈጠረው መስተጋብር ልክ የዚህ ክስተት ተጎጂ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት በዚህ ማብራሪያ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ግን፣ አሁን ባለው ነባራዊ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁኔታ አኳያ የቀረበውን ትንታኔ ለመቀበል እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ። 

የኢትዮጵያ ባንኮች ወይም አጠቃላይ የአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ክፍት ባልሆነበት ዓውድ ውስጥ፣ የተወሰኑ የአሜሪካ ባንኮች በመክሰራቸው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለጉዳት ይጋልጣል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በጣም ሩቅ እንደሆነ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን በጥንቃቄ ፈትሾ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ካልተጨበጠ የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ጋር ማስተሳሰር ትክክል እንዳልሆነም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ራሷን በስንዴ ምርት መቻል አቅቷት የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ስንዴ ከውጭ ስትሸምት መክረሟ ከዓለም የኢኮኖሚ መናጋት ምን ያገናኘዋል ሲሉም ሙግታቸውን በጥያቄ መልክ አቅርበዋል።

ከዚያ ይልቅ በመንግሥት የአመራር ውስንነት ስንዴ ኢምፖርት ማድረግ ውስጥ መገባቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳስከተለ በመጥቀስ ጉዳት ያሏቸውንም አመላክተዋል።

‹‹አንደኛ ውስን የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ከውጭ መግባት ላልነበረበት የስንዴ ምርት ማውጣት፣ የሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን ሲሻማ ነበር፡፡ ምክንያቱም ስንዴ ወሳኝ የማኅበረሰብ የምግብ ፍላጎት መሸፈኛ ምርት በመሆኑ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ቅድሚያ ይሰጠዋል። 

‹‹በሌላ በኩል ደግሞ ስንዴ ኢምፖርት ሲደረግ የዓለም የዋጋ ንረትንም አብሮ ይገባል፣ Imported Inflation የሚባለው ሁኔታ ይፈጠራል፣ በዚህ ላይ ደግሞ የብር የመግዛት አቅምን የማዳከም ፖሊሲ ታክሎበት የዋጋ ንረቱን በማባባስ ኢኮኖሚያዊ ችግር ይፈጥራል፤›› ብለዋል።

ባለፈው ዓመት መንግሥት የስንዴ ምርትን በአገር ውስጥ ለማምረትና ራስን ለመቻል ባደረገው ከፍተኛ ዘመቻ የተትረፈረፈ የስንዴ ምርት ማግኘት በመቻሉ፣ በዘንድሮ ዓመት ስንዴ ከውጭ ለማስገባት አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አለማባከኗን ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያረጋገጡትና የችግሩ ምንና የት ጋር እንደነበረ ያሳዩበት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል። 

እንዲያውም ለአገር ውስጥ ፍላጎት በቂ የሆነ የስንዴ ምርት ከተያዘ በኋላ የተረፈውን ወደ ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ ወይም እንደሚባለው ለዓለም የምግብ ፕሮግራም በዓለም የገበያ ዋጋና በመሸጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስንዴ ምርት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኘት በመቻሉ ላለፉት ዓመታት የነበረው የስንዴ ችግር መንስዔ አገራዊ እንጂ ውጫዊ እንዳልሆነ ምስክር ነው ብለዋል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃም መንግሥት የስንዴ ምርትና ማርታማነት በማሳደግ አዲስ የሸቀጥ ዓይነትን ከአገሪቱ የወጪ ንግድ ሸቀጦች ምድብ ውስጥ ለማስገባትና አዲስ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጭ ለመፍጠር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ባለፉት ስምንት ወራት 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጪ መላኩን አመልክቷል።

አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የስንዴ ዋጋ መሠረት፣ ባለፉት ስምንት ወራት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው 1.3 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ወደ 150 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ልታገኝ እንደምትችል ይገመታል።

‹‹የአገሪቱን የምግብ እህል ፍላጎት በአገር ውስጥ መመለስና ከዚያም አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንደሚቻል መንግሥት ከስንዴ ምርት ተሞክሮው የተረዳው እውነታ ሆኖ ሳለ፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ችግር መንስዔ ከዓለም የኢኮኖሚ መናጋት ጋር ማስተሳሰር ውጫዊ ምክንያት የመፈለግ ጥግ ማሳያ ነው፤›› ሲሉ ባለሙያው ይከራከራሉ። 

የውጭ ምንዛሪ ቀውሱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ባለው ትስስር የተፈጠረ አድርጎ ማቅረብም አሳሳች እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያው፣ ለዓለም ገበያ በቂ ምርት ማቅረብ የማይችል ኢኮኖሚ ያለው አገር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን የሚያሟላው በዕርዳታና ብድር እንደሆነ አስረድተዋል።

ከውጭ ብድር ጋር ተያይዞ የተሰጠውም ምላሽ ለኢትዮጵያ ተስማሚ አለመሆኑን የተናገሩት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ዕዳ መክፈል ባለመቻሏ፣ እንዲሁም ከሰሜኑ ግጭት ጋር ተያይዞ የውጭ ብድር ሽግሽግና የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ እንዳታገኝ ዕቀባ ተደርጎባት እንጂ፣ በዓለም የኢኮኖሚ መናጋትና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ባለው መስተጋብር የተፈጠረ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

‹‹የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ተፈጠረም አልተፈጠረ ተበዳሪ አገር ዕዳውን በወቅቱ መክፈል አለበት፣ ይህንን ማድረግ ካልቻለ አበዳሪ አገራትን እምነት ማግኘት አይችልም፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ብድር የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፤›› ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መናጋት ሲያጋጥም የውጭ ገዥዎችን የመግዛት ፍላጎት ያዳክማል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ጠንካራ ትስስር የፈጠሩ አገሮች ጉዳት ያጋጥማቸዋል ቢባል ትክክል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ችግር ይህ አይደለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ችግር ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የሸቀጥ ዓይነቶችን አለማስፋትና ያሉትም በሚፈለገው መጠንና የጥራት ደረጃ የሚመረቱ አለመሆናቸው፣ ከውጭ ምንዛሪ ቀውሱ ጋር ተያይዞ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በገጠመው የግብዓት ችግር ተወዳዳሪ አለመሆኑ፣ አገሪቱ ባለባት ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ምክንያት ተጨማሪ የውጭ ካፒታል ማግኘት አለመቻል የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እየጎዱ ያሉ ዋነኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን በመግለጽ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ችግርን ከዓለም የኢኮኖሚ መናጋት ጋር ማስተሳሰር አሳማኝ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአኃዝ አስደግፈው በሰጡት ማብራሪያም ሆነ ይህንን ተከትሎ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ የሚያሳየው እውነታ አገሪቱ ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ቅናሽ የታየበት ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ በ2015 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ 2.3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ በ8.1 በመቶ ቅናሽ ታይቶበታል።

በወጪ ንግድ አፈጻጸም ላይ ለታየው ቅናሽ ዋነኛው ምክንያት በወርቅ የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ነው፡፡ መረጃው እንደሚያመለክተው፣ በዘንድሮ ስምንት ወራት ከወርቅ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ65.1 በመቶ አሽቆልቁሏል። ከወርቅ በተጨማሪ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ አፈጻጸም በተመሳሳይ ዝቅተኛ መሆኑ ለአጠቃለይ የወጪ ንግድ ገቢ መቀነስ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች