Tuesday, July 23, 2024

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል መንግሥታት አመራሮችን ይዘው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ግፊቱ እየጨመረ የመጣውን የጉራጌ ዞንን የክልልነት ጥያቄ ለማርገብ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ከማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ውይይቱን ሲከፍቱ፣ ‹‹የክልልነትና የአደረጃጀት ጥያቄ ብዙ እንደሆነ አውቃለሁ፤›› ሲሉ የተንደረደሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸው ቢቻል የክልልነት ጥያቄ እንዲዘገይ ጊዜ መግዛት መፈለጉን ተናግረዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ፣ መንግሥታቸው ያዋቀረውን በክላስተር የመደራጀት አማራጭ የጉራጌ ዞን እንዲቀበለው ጥረት አድርገዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዞኑ የራሱ ክልል ይኑረው የሚለውን ውሳኔ ኅዳር 17 ቀን 2011 ነበር ያፀደቀው፡፡ ይህ ውሳኔ ወደ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ እንዲሁም ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በየደረጃው እየተገፋ ቢቀርብም ምላሽ አለመገኘቱን ነው ጥያቄውን ለማስመለስ የሚንቀሳቀሱ አካላት የሚናገሩት፡፡

ሲጀመር በማኅበራዊ አንቂዎችና የጉራጌ ክልልነት ጥያቄ ያገባናል በሚሉ ግለሰቦች ወደፊት የመጣው ዞኑ፣ በክልልነት ይደራጅ የሚለው ጥያቄ ዛሬ ዛሬ የፖለቲካ ፓርቲ ትግልን የወለደ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች፣ በመደበኛ እንቅስቃሴ አድማዎችና በሰላማዊ ሠልፎች የታጀበው ዞኑ በራሱ ክልል ይደራጅ የሚለው እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይዘቱም ሆነ ግለቱ እየተለወጠ የመጣ ይመስላል፡፡ በርካታ ዜጎች በዚህ ጥያቄ መዘዝ መታሰራቸው፣ እንዲሁም የወልቂጤ ከተማ የውኃ አቅርቦት ጥያቄን ተንተርሶ የሰዎች ሕይወት ማለፉ ሳይቀር የጉራጌ ዞን ትኩሳት የበለጠ እየጨመረ መምጣቱን አመላካች ሆኗል፡፡

ዞኑ ከኅዳር 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገ በሚመስል ሁኔታ በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲወድቅ መደረጉም፣ ጥያቄው የፈጠረው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን የሚጠቁም እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በክልል ብቻ ሳይሆን በፌደራል ደረጃ የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ጭምር የጉራጌን ክልልነት ጥያቄ ሽፋን ያደረገ ሕገወጥ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑ ተደጋግሞ መገለጹም ቢሆን፣ የጉራጌ ጉዳይ በጥሞና መያዝ ያለበት ከበድ ያለ የፖለቲካ ትኩሳት ማሳያ ተደርጎ ሲቀርብ ይታያል፡፡

ከሰሞኑ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የክልል መሪዎች በጉዳዩ ላይ ሕዝብ ለማወያየት ጥረት ሲያደርጉ መታየታቸው ለችግሩ መፍትሔ ያመጣል ተብሎ ቢገመትም፣ ነገር ግን ጠብ የሚል ውጤት አለመገኘቱን ነው የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች የሚናገሩት፡፡

በቅርቡ የተመሠረተው ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ የጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ ሳህሌ፣ ከፍተኛ አመራሩ ወደ ወልቂጤ ባይሄድ የተሻለ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹አዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ከተደረገው ስብሰባ ወልቂጤ ቢሄዱ ሊገጥማቸው የሚችለው ነገር ጥሩ እንዳልሆነ ይገመት ነበር፡፡ ራሳቸው በደገሱት ስብሰባም ላይ ቢሆን ሕዝቡ ከጠበቁት ውጪ የክልልነት ጥያቄውን ደጋግሞ ሲያነሳም ነበር፡፡ የሕዝቡን ወሳኝ ጥያቄ ላይመልሱ ከሆነ እዚያ ድረስ መሄዱ ትርጉም እንደሌለው እንዴት ሊገባቸው እንዳልቻለ እስገርሞኛል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ መላኩ የወልቂጤው ስብሰባ ምንም ዓይነት ውጤት የማያመጣ እንደሆነ ቀድሞ የተገመተ መሆኑን ያክላሉ፡፡ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ከጉራጌ ዞን የተወከሉ አንድ የደቡብ ክልል የሥራ ኃላፊም ቢሆን ይህንኑ ሐሳብ በሌላ መንገድ አስተጋብተውታል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉራጌ ሲመጡ የነበረው የሚዲያም ሆነ የሕዝቡ አጀብ ከፍተኛ ነበር፡፡ አሁን ግን በተቃውሞ ቤቱ በመቀመጥ ስሜቱን ገልጾላቸዋል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ አገሪቱ በሕግ የምትመራ ቢሆን ኖሮ የተጠየቀው ጥያቄ በሕግ አግባብ ነበር የሚመለሰው የሚሉት አስተያየት ሰጪው፣ ጥያቄው ሕጉ የሚጠይቃቸውን መሥፈርቶች አሟልቶና በዞን ምክር ቤት ጭምር በአብላጫ ድምፅ ፀድቆ የቀረበ ሕጋዊ ጥያቄ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹የጉራጌ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ መከልከሉን ከሰሞኑ መንግሥት ካደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ተረድቶታል፡፡ ጉራጌ ዞንን በተመለከተ እኔ ነኝ የማውቅልህ እየተባለ መሆኑ ታይቷል፡፡ ከሰሞኑ የተደረጉ ውይይቶች ትግሉ ከማን ጋር መሆን እንዳለበት የአካባቢው ሕዝብ እንዲረዳ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ የክልልነት ጥያቄውን ማን እንደከለከለ ተረድቶታል፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

የጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሐመድ አብራር በበኩላቸው፣ መንግሥት ጥያቄውን ለማስቀየርም ሆነ ለማስቆም እያደረገ ያለው ጥረት እንደማይሳካ ነው የሚናገሩት፡፡

የሰሞኑ ስብሰባዎች ሰዎች ተመልምለውና ምን እንደሚናገሩ ረዥም ዝግጅት ተደርጎባቸው የተካሄዱ መሆናቸውን አቶ መሐመድ ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ኅብረተሰቡ ግን ይህን ሁሉ አልፎ የክልልነት ጥያቄውን አስተጋብቷል፡፡ በመንግሥት ሚዲያዎች ኤዲት አድርገውና ቆራርጠው ቢያቀርቡትም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደውም ሆነ በወልቂጤ በተደረገው ስብሰባ የክልልነት ጥያቄያችን ይመለስ የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን በቅርበት አውቃለሁ፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

አቶ መሐመድ አክለውም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ስብሰባውን ሲጀምሩ ብዙ የክልልነትትና የውኃ ጥያቄ እንዳላችሁ አውቃለሁ ብለው አስቀድመው አፍ ለማዘጋት ጥረት አድርገዋል፤›› ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም እሳቸው ሲመጡ አደባባይ ሳይበቃው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ የተቀበላቸው ሕዝብ ዛሬ አድማ አድርጎ ቤቱ ተቀምጦ መዋሉ ብዙ መልዕክት አለው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ማክሰኞ፣ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበራቸው የፓርላማ ውሎ፣ የክልልነት ጥያቄዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡

‹‹የፖለቲካ ሰዎች መንገድ ይሠራልሃል፣ ልማት ይመጣልሃል፣ ወዘተ እያሉ የክልልነት ጥያቄን ይቀሰቅሳሉ፡፡ አንድ ክልል ሲፈጠር ደግሞ ዞን፣ ወረዳ እያለ ወደ ሌሎችም የአደረጃጀት ጥያቄዎች ይስፋፋል፡፡ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ አገሪቱን ሲረከብ በአገሪቱ የነበረው 230 ሺሕ የመንግሥት ሠራተኛ ነበር፡፡ አሁን ወደ 2.6 ሚሊዮን አድጓል፡፡ ሁሉም ወገን የራሱን መዋቅር ካልፈጠረና ካልተሾመ በስተቀር የሕዝብ መብት የተከበረ አይመስለውም፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ ‹‹ባጠናነው ጥናት በአንድ ክልል ውስጥ ቢያንስ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ ከሌለ፣ ገቢ ሰብስቦ ቢያንስ የራሱን ደመወዝ ወጪ ችሎ ህልውናውን ለመቀጠል እንደሚቸገር አረጋግጠናል፡፡ ክልል ከተሆነ በኋላ ደስታው ሳምንት ሳይቆይ የደመወዝ ጥያቄ ለፌዴራል መንግሥት ይቀርባል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ ካለው ገቢ ውጪ ከየትም አምጥቶ በጀት ሊያከፋፍል አይችልም፡፡ የበጀት ቀመር የሚሠራው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በጀት ቀመሩ የሚሠራው እናንተው ጋ ነው፡፡ የእኛ ሥራ እሱን ማስተዳደር እንጂ አዲስ ክልል በተፈጠረ ቁጥር በጀት አብሮ መስጠት እንቸገራለን፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የክልልነት ወይም የመዋቅር ጥያቄ እያነሱ ያሉ አካባቢዎች በተናጠል ሳይሆን በጋራ ተሰብስበው ቢመለስላቸው ከወጪ፣ ከኢኮኖሚ ሁኔታና ከበጀት አንፃር አመቺነት እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉራጌ ለብቻው ክልል ከሚሆን ይልቅ ከተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳ ጋር በጋራ ሆኖ ክልልነት እንዲያገኝ እንደሚፈልጉ በወልቂጤው ስብሰባም ሆነ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ደጋግመው አውስተዋል፡፡ መንግሥታቸውም የጉራጌ ዞን ከሃዲያ፣ ከስልጤ፣ ከከምባታ ጠምባሮና ከሀላባ ዞኖች፣ እንዲሁም ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በአንድነት ተሰባስቦ በሸዋ ክላስተር ክልል እንዲደራጅ ፍላጎት እንዳለው ደጋግሞ ግልጽ አድርጓል፡፡

ይህንን የክላስተር ክልል አደረጃጀት ደግሞ በጉራጌ ዞን ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ይህ ጉዳይም አሁን ከመንግሥት ጋር ላለው አለመግባባት መነሻ ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የጉራጌ ማኅበረሰብ የክልልነት ጥያቄ ያገባናል ያሉ ፖለቲከኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችና የሲቪክ ማኅበራት የመንግሥትን አቋም እየተቃወሙ ናቸው፡፡ መንግሥት ግን በተለያዩ መንገዶች የክላስተር አደረጃጀቱን ለማስፈጸም ጥረት ከማድረግ ሲቆጠብ አልታየም፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የተባባሰ ፍጥጫ ፈጥሮ ተጨማሪ አገራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

አቶ መላኩ ደግሞ፣ ‹‹የጉራጌ ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ሊስማማ ቀርቶ ቀድሞ ተቃውሞ ቤቱ ቁጭ ብሏል፡፡ ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ብልፅግና የክላስተር ክልል ምክረ ሐሳብ ብሎ ያመጣውን መፍትሔ የዞኑ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ውድቅ አድርጎታል፡፡ ይህን ሐሳብ የተቃወሙ የጉራጌ ማኅበረሰብ ተወካዮችን መንግሥት አስሯል፡፡ የመብት ጥሰትም እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ አሁን ልክ እንደ አዲስ የክላስተር አደረጃጀትን ካልተቀበላችሁ የሚባለው የተለመደ ጨዋታ እንጂ መፍትሔ አይደለም፤›› በማለት ነው የመንግሥትን አቋም የሚተቹት፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ መንግሥት አሁን ጥያቄውን የመመለስ አቅም እንደሌለው በተጨባጭ ማስረጃ ቢያቀርብና ማኅበረሰቡን ይቅርታ ቢጠይቅ እንኳ ለመቀራረብ የተሻለ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ጥያቄውን መመለስ ባለመቻላችን ብሎ ማድረግ በሚችላቸው ነገሮች ማኅበረሰቡን ቢክስ፣ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘምም ሆነ ፋታ እንዲያገኝ የተሻለ መንገድ በሆነ ነበር፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

በእሳቸው እምነት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችና በደነገገቻቸው የራሷ ሕጎችም ዋስትና የተሰጠውና ሊታፈንም የማይችል ጥያቄ ነው፡፡ ‹‹በሌሎች አካባቢዎች የመዋቅር ጥያቄዎች ደም አፋሳሽ ውጤት አስከትለዋል፡፡ ለምሳሌ በደራሼ የዞን ጥያቄን ተከትሎ 65 የልዩ ኃይልና 15 የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተገድለዋል፡፡ በኮንሶም ሆነ በሲዳማ የአስተዳደር ጥያቄዎች ደም አፋሰዋል፡፡ በጉራጌ ዞን ግን ጥያቄው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየቀረበ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን ከዚያ በተቃራኒው እንቅስቃሴውን በኃይል አዳፍኖ የራሱን ፍላጎት ለመጫን ነው ጥረት እያደረገ ያለው፤›› በማለት ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡

አቶ መሐመድ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉራጌ ጉዳይን በተመለከተ እያራመዱት ያለው አቋም ያልተገባ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ቤተ መንግሥት በነበረውም ስብሰባ እኔ ብፈልግ ኖሮ በአምስት ደቂቃ ክልል እሰጣችሁ ነበር ብለዋል፡፡ የእሳቸውን መፈለግ ወይም ማመን ከሕገ መንግሥቱም ሆነ ከዞኑ ምክር ቤትና ከሕዝቡ ፍላጎት በላይ አድርገው ተናግረዋል፤›› በማለት የእሳቸውንና የመንግሥታቸውን አቋም ተችተውታል፡፡

የጉራጌ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ የሚታፈነው ሆን ተብሎ በሚካሄድ በተጠና የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሻጥር እንደሆነ የጉራጌ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ይናገራሉ፡፡ ሕዝቡ የፖለቲካ ውክልና አጥቶ ለሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ድምፅ ሰጪ ብቻ ሆኖ እንዲቀር የታሰበበት መሆኑን ያክላሉ፡፡ በሌላ በኩል፣ ‹‹ሥራ ወዳዱና ታታሪው የጉራጌ ሕዝብ›› በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለፍቶ ያፈራውን ሀብት የራሱን አካባቢ ለማልማት እንዳያውለው ከመፈለግ በመነጨ የእኔ ነው የሚለው ክልል ሲነፈግ መኖሩንም ያስረዳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በወልቂጤው ስብሰባ፣ ‹‹የጉራጌ ማኅበረሰብ የኅዳር አህያ ከመሆን ይቆጠብ፤›› በማለት ጥያቄው የሌሎች አጀንዳ ሰጪ አካላት እጅ ያለበት መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

ይህን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አቶ መሐመድ፣ ‹‹በሕዝቡ ውስጥ የተለየ ፍራቻ በመፍጠር ጥያቄውን የማስቆም ሙከራ ነው፤›› ብለውታል፡፡ አቶ መላኩ በበኩላቸው፣ ‹‹የሚጠበቅና የመንግሥት የተለመደ የፍረጃ ፖለቲካ›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉት አስተያየት ሰጪ ግን፣ ‹‹ጉራጌ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ጨቦና ጉራጌ ጨቦ ተብሎ የራሱ አውራጃ ነበረው፡፡ በኋላም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ይካተት ሲባል ቀድሞ ተቃውሞ ነበር፡፡ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄው ከማንም በተውሶ የመጣ ሳይሆን፣ ቀድሞ የነበረና ለረዥም ጊዜ የቆየ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -