በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳና ጀነራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ በርካታ ተከሳሾች ክስ ዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓም ተቋረጠ።
ፍትሕ ሚኒስቴር ዛሬ ከሰዓት እንዳስታወቀው፣ በፌዴራል መንግስትና በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) መሃከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት ከግጭቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት በተመለከተ ያለውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታሳቢ ባደረገ መልኩ፣ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ስለሆነም በወንጀል ተጠርጥረዉ ክስ ቀርቦባቸዉ የነበሩ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮችን ክስ በማቋረጥ ጉዳያቸዉ በቀጣይ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ እንዲታይ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በመሆኑም በተገለፀው አግባብ ከዚህ ጋር በተያያዘ ቀርቦ በክርክር ሂደት ላይ ይገኙ የነበሩ የወንጀል ክሶች በአዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6 (3) (ሠ) መሰረት የተነሱ መሆኑን አሳውቋል።