በዋግ ኸምራ ብሔሰብ ዞን የምትገኘው አበርገሌ ወረዳ ከሕወሓት ታጣቂዎች ነፃ ወጥታለች መባሉ ሐሰት መሆኑን፣ የዞኑ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ ጋሻው አንተነህ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹አሁን ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከበድ ያለ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከአገር ሸንጎ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነሱ ናቸው ሰላም እንደሆነ የሚያወሩት፡፡ እኔ ደርሼ እስከመጣሁበት ዓርብ መጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ የአገው ሸንጎዎች ናቸው አካባቢውን እየረበሹና እየበጠበጡ ያሉት፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹ወረዳው ከሕወሓት ታጣቂዎች ነፃ እንደወጣ የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ገልጿል፤›› ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ገና ነው ነፃ አልወጣም ውሸት ነው፤›› የሚል ምላሽ ሃምሳ አለቃ ጋሻው ሰጥተዋል፡፡
የአበርገሌ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን፣ ‹‹ከሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሕዝብ ተለይታ የነበረችው የአበርገሌ ወረዳ ዋና መዲና ‹‹ንየር አቑ›› ከተማ እነሆ! ዛሬ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. የነፃነት ካባዋን ለበሰች፤›› ሲል አስታውቋል፡፡
‹‹ቀጣይ ተግባር መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመልሶ ማቋቋም ሥራና ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ማቅረብ እጅግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ሃምሳ አለቃ ጋሻው በበኩላቸው፣ ‹‹አካባቢው ነፃ ወጥቷል ለማለት አያስደፍርም፣ ፃግብጅና አበርገሌ ወረዳ ላይ ሚሊሻዎች አሉ፣ የሚችሉትን እየታገሉ ነው፡፡ ከዚያ በዘለለ ግን ነፃ ነው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የተለየ ነገር እንዳለ ሲጠየቁም፣ ‹‹አሁን በወረዳው የተለየ ነገር ያለው፣ በአካባቢው ያለው ንብረት አልቋል፡፡ ማንም ምንም ዘርፎ ሊወስደው የሚችል ነገር የለም፤›› ያሉት ሃምሳ አለቃ ጋሻው፣ ስለዚህ ማኅበረሰቡ ወደ አካባቢ ሲመለስ፣ ቢጠግብም ባይጠግብም ለጊዜው እንኳን በዕርዳታም ቢሆን በራሱ ሲተዳደር ብቻ ነው ነፃ ነው ሊባል የሚችለው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እየረበሹ ያሉት የአገው ሸንጎዎች ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ነገር ግን ነፃ ነው ብሎ ለማውራት ይከብዳል፡፡ ርቀት ላይ ሆነን የምናየውና በቦታው ሆነን የምናየው በብዙ ፐርሰንት ይለያያል፤›› በማለት አክለው ተናግረዋል፡፡
‹‹የአገው ሸንጎ ምንድነው እየተገበሩ ያሉት፤›› ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ‹‹ከብልፅግና ጋር ተያይዞ፣ ብልፅግና አይመራውም አካባቢውን መመራት ያለበት በእኛ ነው፤›› የሚል መሆኑን ሃምሳ አለቃ ጋሻው ገልጸዋል፡፡
‹‹በነገራችን ላይ አሁን ከሁለት እየተከፈሉበት ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ግማሾቹ ድጋፍ ያላቸው ወደ ትግራይ ክልል ነኝ ይላሉ፡፡ ድጋፍ የሌላቸው ደግሞ ራሳቸውን ችለው እኛ ነን የምንመራው ይላሉ፡፡ በአካባቢ ያለው ነገር በጥቅሉ ዝም ብሎ ውንብድና ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹የውንብድና ሥራ ስለሆነ እየተሠራ ያለው፣ ይህንን ደግሞ መንግሥት መቶ በመቶ መቅረፍ ስላልቻለ፣ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይልም እየተበታተነ ስለሆነ፣ የሕወሓት ታጣቂዎች የሚፈልጉትን ነገር እያደረጉ ነው፤›› ሲሉ ሃምሳ አለቃ ጋሻው ተናግረዋል፡፡
አክለውም፣ የሕወሓት ታጣቂዎች ያገኙትን ከመውሰድ አልተቆጠቡም፡፡ ሰላም አለ ብሎ ያለው አካልም አንድም ከሕወሓት መካከል፣ ወይም ጤናኛ አይደለም ብለዋል፡፡
‹‹50 መኪና መከላከያ ወደ አካባቢው ስለመጣ ነፃ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሕወሓት ታጣቂዎች በአበርገሌና በፃግብጅ ወረዳ ያደረሱት ሰብዓዊ ጉዳት እንዳለ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሃምሳ አለቃ ጋሻው፣ ‹‹ያደርሳሉ፡፡ እንግዲህ ሕወሓት እዚያ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ጋር ነው ትልቁ ጥላቸው፡፡ በተለይ አበርገሌ ወረዳ ድንበርም ስለሆነ በጣም አስቸጋሪ ቦታ ነው፡፡ ሕወሓት የእነሱ እንደሆነ የሚያምኑበት ስለሆነ፣ አበርገሌን ወረዳም ተቆጣጥረው ይዘውታል፤›› ብለዋል፡፡