Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመረጃ መስጠት የማይችሉ አካል ጉዳተኞች ፎቶግራፍ ብቻ በማቅረብ ብሔራዊ መታወቂያ ሊሰጣቸው ነው

መረጃ መስጠት የማይችሉ አካል ጉዳተኞች ፎቶግራፍ ብቻ በማቅረብ ብሔራዊ መታወቂያ ሊሰጣቸው ነው

ቀን:

በአካል ጉዳት ወይም በሌላ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የባዮሜትሪክ መረጃ መስጠት የማይችሉ የዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች፣ ከፊት ገጽታ ፎቶግራፍ ውጪ ሌላ መረጃ ማቅረብ ሳይገደዱ ብሔራዊ መታወቂያ እንደሚያገኙ የሚደነግግ አዋጅ ፀደቀ፡፡

በፀደቀው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ላይ እንደተደነገገው የባዮሜትሪክ (የጣት አሻራ፣ የዓይን ብሌንና የፊት ገጽታ ምሥል) መረጃ ምዝገባ በሚከናወንበት ወቅት፣ በአካል ጉዳት ምክንያት ተመዝጋቢዎች ሌሎች መረጃዎች መስጠት አለመቻላቸው በብሔራዊ መታወቂያ መዝጋቢው ተቋም ከተረጋገጠ፣ ከፊት ገጽታ ፎቶግራፍ ውጪ ሌላ መረጃ አስገዳጅ አይሆንም ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በጤና፣ በዕድሜ ወይም በሌላ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት መዝጋቢው አካል ምዝገባ በሚያደርግበት ቦታ መምጣት የማይችሉ ተመዝጋቢዎች ባሉበት ቦታ ወይም አመቺ በሆነ ቦታ በመገኘት ምዝገባ ሊያደርግ እንደሚችል፣ በፀደቀው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ተደንግጓል፡፡

ሐሙስ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ባፀደቀው ረቂቅ አዋጅ፣ ሕፃናት ዲጂታል መታወቂያ ስለሚያገኙበት ሁኔታ የተሻሻለ ድንጋጌ ወጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት በዲጂታል ሥርዓት ለመመዝገብ የተመዘገበ ወላጅ፣ አሳዳጊ፣ ሕጋዊ ሞግዚት ወይም ሌላ ማንኛውም ሕጋዊ አካል የሕፃኑን ዴሞግራፊክ መረጃ ብቻ በመመዝገብ ሕፃኑ መታወቂያ መውሰድ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

የሕግና የፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሰው ሀብት፣ የሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡት ሪፖርት ከመፅደቁ በፊት ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በሰፊው ተወያይቷል፡፡

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዕፀገነት መንግሥቱ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ወጥና አስተማማኝ የአገሪቱ ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት ሥርዓት በመዘርጋትና የተመዝጋቢዎችን መረጃ በመያዝ፣ የዲጂታል መታወቂያ አጠቃቀም ሥርዓትን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

መታወቂያውን በመጠቀም በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋና የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት እንዲኖር አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ተብሏል፡፡

የምክር ቤት አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በአዲስ አበባ በነዋሪነት 10 እና 15 ዓመታት የሆናቸውና የነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸው ነዋሪዎች እንደሚገኙ፣ ስለሆነም በረቂቅ አዋጁ ላይ የመኖሪያ ቦታ በሚል የተገለጸው ልዩ ትርጓሜ ካልተሰጠው እንዴት ይታያል የሚለው ይገኝበታል፡፡

ከወንጀል ተጠያቂነት ጋር ተያይዞም የቀረበው የገንዘብ ቅጣት መጠን አነስተኛ ስለሆነ ከበድ ሊል ይገባል የሚለው ሌላው በምክር ቤቱ አባላት የቀረበ ጥያቄ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል ሲሠራበት የቆየው የወሳኝ ኩነቶች አዋጅ አዲስ ከወጣው አዋጅ ጋር እንደማይጋጭ ታይቷል ወይ የሚል ጥያቄም ተሰንዝሯል፡፡

ወ/ሮ ዕፀገነት ከቋንቋ ጋር ተያይዞ በዲጂታል  መታወቂያ ማስረጃ ላይ የሚገለጹ የግል መረጃዎች በፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ በአማርኛ፣ እንዲሁም ምዝገባ በሚካሄድበት ክልል የሥራ ቋንቋና በእንግሊዝኛ እንደሚሆን ገልጸው፣ የውጭ አገር ዜጎችም ነዋሪ መሆናቸው እስከተረጋገጠ እነሱም መታወቂያውን እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንግሊዝኛ እንደ አማራጭ ሆኖ ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን አስገዳጅ እንዲሆን ተደርጎ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ቅጣቱም ዝቅተኛው እርከን አሥር ሺሕ ብር መደረጉ አነስተኛ እንደማይባል ተናግረዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንድ ነዋሪ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ መቀመጡን ያስረዱት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፣ ከዚያ ጋር በማይጣረስ ሁኔታ በአዲሱ አዋጅ ውስጥ መሥፈሩን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...