Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናራስ ገዝ ይሆናሉ የተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ቻንስለር እንዲኖራቸው የሚያደርግ ረቂቅ...

ራስ ገዝ ይሆናሉ የተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ቻንስለር እንዲኖራቸው የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

ቀን:

  • ቻንስለሩ በሥራ አመራር ቦርድ ከሚቀርቡ ዕጩዎች መካከል የዩንቨርሰቲ ፕሬዚዳንት ይሾማል

የከፍተኛ ተቋማትን ራስ ገዝ በማድረግ ነፃ ሆነው ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል ተብሎ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ቻንስለር እንደሚኖረው የሚያብራራ አንቀጽ ተካትቶበት ለውይይት ቀረበ፡፡

መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ውይይት የተደረገበትና ስለራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመደንገግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዩኒቨርሲቲዎችን የአካዴሚክና የምርመር ነፃነት የሚሰጥ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በረቂቅ አዋጁ እንደተመለከተው፣ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደር ላይ ሳይገባ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲውን በሥራና መልካም ስም የሚያጎላ እንደ ከፍተኛ አምባሳደር የሚያገለግል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ቻንስለር ይኖራቸዋል፡፡

በረቂቁ ቻንስለሩ ለአምስት ዓመታት የሚሾም ሲሆን፣ በሥራ አመራር ቦርድ አቅራቢነት ለፕሬዚዳንትነት ከሚቀርቡ ሦስት ዕጩዎች መካከል የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት የመሾም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው ፕሬዚዳት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሾም ቻንስለር የሚሾም ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱ በውድድር ካሸነፈና የፖለቲካ ፓርቲ አባል ከሆነ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ለመልቀቅ የሚስማማ መሆን እንዳለበት በረቂቁ አንቀጽ 14 ተመላክቷል፡፡

ለፕሬዚዳንትነት የሚመረጡ ዕጩዎችን ለቻንስለሩ የሚያቀርቡት የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ሲሆኑ፣ የቦርድ አባላት የትምህርት ሚኒስትሩ ከመንግሥት ጋር በመመካከር እንደሚሰየሙ በረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 10 ላይ ተቀምጧል፡፡

በየዓመቱ የሚሰየሙት የቦርድ አባላት በትምህርት ሚኒስትሩ አማካይነት የሚሾሙ የቦርድ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢም የሚኖራቸው ሲሆን፣ የቦርድ አባላቱ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲውን የውስጥ መዋቅርና አደረጃጀት፣ የሰው ሀብት አስተዳደርና አሠራር መርሆዎች ያፀድቃል፡፡

ቦርዱ የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ከፍተኛ ድክመት አሳይተውም ሆነ በዲሲፕሊን ምክንያት አዋጁን ተከትሎ በሚወጣ መመርያ መሠረት ከኃላፊነት ማንሳትን ጀምሮ ዕርምጃ ይወስዳሉ፡፡  

በረቂቅ አዋጁ እንደተመላከተው የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ የተለዩ የኮሌጅና የኢንስቲትዩት ኃላፊዎች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ፣ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ፣ የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊ፣ የግዥ አስተዳደር ኃላፊ፣ የንብረት አስተዳደር ኃላፊና ሌሎች በቦርድ የሚለዩ አባላት ያሉበት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል ይቋቋማል፡፡

የዩንቨርስቲ ካውንስሉ ዋና ዓላማ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲውንና የአሃዶቹን አፈጻጸም መገምገም ሆኖ ሌሎች ኃላፊነቶች በቦርድ ሲሰጠው ይፈጽማል፡፡

በሌላ በኩል የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ የተለዩ የኮሌጅና የኢንስቲትዩት ኃላፊዎች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ፣ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ፣ የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊ የግዥ አስተዳደር ኃላፊና የንብረት አስተዳደር ኃላፊ ያሉበት ማኔጂንግ ካውንስል እንደሚቋቋም በረቂቁ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ የተለዩ የኮሌጅና የኢንስቲትዩት ኃላፊዎች አባላት ያሉበት ኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ እንደሚቋቋምም ያስቀምጣል፡፡

በረቂቅ አዋጁ እንደተመለከተው፣ የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ምንጮች፣  በስጦታ፣ በኑዛዜ፣ በአደራና በኢንዶውመንት መልክ የሚደረጉ ችሮታዎች፣ የተማሪዎች የምዝገባ ክፍያን ጨምሮ የትምህርት ክፍያ፣ ከፓተንት፣ ከፈጠራና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራ የሚገኙ ገቢዎች፣ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚገኙ ገቢዎች ናቸው፡፡

በተጫማሪም ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው ሊሠራቸው ከሚችላቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች የሚገኙ ገቢዎች፣ ከመንግሥት የሚሰጥ ድጋፍና  ከሌሎች ሕጋዊ ምንጮች የሚገኝ ገቢ መሆናቸው ተጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲው በሒደት ራሱ በሚያመነጨው ሀብት ወጪዎችን የሚሸፍንበትን ሥርዓት እየገነባ መሄድ ያለበት ሲሆን፣ በፋይናንስ ራሱን እስኪችል ድረስ በሒደት እየቀነሰ የሚሄድ የገንዘብ ድጋፍ ከመንግሥት የሚመደብለት ሲሆን፣ ማንኛውም ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ በቦርዱ ውሳኔ የንግድ ድርጅቶች ሊያቋቁም እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ የንግድ ድርጅቶች የራሳቸው የተለየ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ሆነው በንግድ ሕግና በሌሎች አግባብነት ባላቸው ሕግጋት መሠረት ይቋቋማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...