Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበደቡብ ኦሞ ዞን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፍየሎችና በጎች ለገዳይ በሽታ መጋለጣቸው ተነገረ

በደቡብ ኦሞ ዞን ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፍየሎችና በጎች ለገዳይ በሽታ መጋለጣቸው ተነገረ

ቀን:

  • በሐመር ወረዳ በሦስት ቀናት ብቻ ከ7,000 በላይ እንስሳት ሞተዋል ተብሏል

ከሁለት ሚሊዮን በላይ በግና ፍየሎች ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ እንደተጋረጠባቸው፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምርያ ገለጸ፡፡ ለሦስት ዓመታት በተከታታይ ዝናብ ባለመኖሩ በዞኑ የሚገኙ እንስሳት በድርቁ እየሞቱ እንደነበር፣ ባለፈው ሳምንት ለሁለት ተከታታይ ቀናት ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት ምንነቱን ለማወቅ በምርመራ ሒደት ላይ የሚገኝ በሽታ በመከሰቱ፣ በተለይ በሐመር ወረዳ ፍየሎችና በጎች እየሞቱ ናቸው ሲል መምሪያው ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡

‹‹ከሦስት ዓመታት የድርቅ ወቅቶች በኋላ ባለፈው ሳምንት በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ዝናብ ዘንቧል፡፡ ይህን ተከትሎም በድርቁ ወቅት ሳር ፍለጋ ወደ ኬንያ ድንበር ሄደው የነበሩ በርካታ እንስሳት ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዝናቡ በዘነበ ማግሥት በበሽታና በጎርፍ የሞቱ እንስሳት አሉ፤›› ሲሉ፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መምርያ የእንስሳት ልማት ኃላፊ አቶ ዘማች በየነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹በሐመር ወረዳ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከባድ ዝናብ ዘንቧል፤›› ያሉት አቶ ዘማች፣ ከዘነበ በኋላ ግን ገና ምንነቱን ለማወቅ በምርመራ ላይ የሚገኝ በሽታ 1‚896 ፍየሎች፣ 2‚648 በጎች፣ በአጠቃላይ 4‚544 እንስሳት ገድሏል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ዝናብ መዝነቡ በድርቅ ለረጅም ጊዜ የተጎዱ እንስሳት ሳር እንዲያገኙ ይረዳል እንጂ እንዴት ገዳይ በሽታ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ለረጅም ጊዜ በድርቅ የቆዩ አካባቢዎች ዝናብ ሲያገኙ ከአፈሩ በእንፋሎት መልክ የሚወጣ የእንስሳት በሽታ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ከሞቱት እንስሳት ናሙና የመውሰድና የበሽታውን ዓይነት በላቦራቶሪ የመመርመር ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ፣ ናሙናው የእንስሳቱ ጭንቅላት ላይ ከፍተኛ ዕብጠትና አረፋ እንደሚያሳይ፣ ይህም ምልክት ከመዝነቡ ጋር ተያይዞ የመጣ በሽታ እንደሚሆንና በሽታው ተላላፊ እንደሚሆን በመሠጋቱ የሞቱት እንስሳት እንደተቃጠሉም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የእንስሳቱ የሞት መጠን በሐመር ወረዳ ብቻ የተከሰተ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች እንስሳት በበሽታው እንዳይሞቱ ሥጋት መፈጠሩን፣ አስረድተዋል፡፡

በወረዳው የሚገኙ ከ765 በላይ የቤተሰብ አባላት በዝናቡ ሳቢያ በሦስት ቀናት ውስጥ በበሽታና በጎርፍ ምክንያት ከብቶቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን፣ በጎቻቸውንና ዶሮዎቻቸውን እንዳጡ አቶ ዘማች አብራርተዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ ባለፈው ሳምንት በዘነበው ዝናብ በተከሰተ አደገኛ ጎርፍ በሰዎች፣ በእንስሳትና በመኖሪያ ቤት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ፣ የጉዳት መጠኑን ለመግለጽ ዳታውን ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡ በጎርፍ ምክንያት የሰው ሕይወትም እንዳለፈ፣ በርካታ እንስሳት እንደ ሞቱ፣ መኖሪያ ቤቶችም እንደ ወደሙና ነዋሪዎች እንደ ተፈናቀሉ ማወቅ ተችሏል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ከድርቁ ባሻገር በጎርፍና በበሽታ ከፍተኛ ጉዳት ማጋጠሙን ገልጾ፣ የጉዳት መጠኑን ለማወቅ ጊዜ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡

የግብርና መምርያው የእንስሳት ልማት ኃላፊው በበኩላቸው፣ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ በሐመር ወረዳ በበሽታ ከሞቱት 4‚544 በጎችና ፍየሎች በተጨማሪ፣ በሌሎች እንስሳትና በነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ አብራርተዋል፡፡

በድርቁ ምክንያት ከ15 ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸውን ያስታወሱት አቶ ዘማች፣ በተለይም በሐመር ወረዳ ድርቅ ካደረሰው ጉዳት ባሻገር ጎርፍ፣ የእንስሳት በሽታ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹በድርቁ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ባገኘነው መረጃ መሠረት 464 ከብቶች፣ 695 ፍየሎች፣ 390 በጎችና 1‚667 ዶሮዎች በድምሩ 3‚216 እንስሳት በጎርፍ፣ 4‚544 በጎችና ፍየሎች በበሽታ፣ በአጠቃላይ በቀናት ውስጥ 7‚760 እንስሳት ሞተዋል፤›› ብለዋል፡፡ የጉዳት መጠኑ በገንዘብ ደረጃ ስንት እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ አሁን ባለው የእንስሳት የገበያ ዋጋ አሥልቶ ማወቅ እንደሚቻልና በእነሱ በኩል ግን እስካሁን የገንዘብ መጠኑ እንዳልተሰላ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ካሉት ወረዳዎች መካከል ከፍተኛ የበግና የፍየል ክምችት የሚገኘው በሐመር ወረዳ መሆኑን፣ በተከሰተው በሽታ ሳቢያ ለጊዜው መደበኛ ክትባት ቢደረግም የመድኃኒት እጥረት ማጋጠሙን፣ የበሽታው ዓይነት በፍጥነት ካልታወቀ በወረዳው የሚገኙ ቀሪዎቹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍየሎች፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በጎች በአጠቃላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንስሳት በበሸታው ሊጠቁ እንደሚችሉ ሥጋት መፍጠሩንና እንስሳቱ ለጊዜው መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በተከሰተው ድርቅ በአጠቃላይ ከ28 ሺሕ በላይ እንስሳት መሞታቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ሰሞነኛው ዝናብ እያስከተለው ያለው ጉዳት ከፍተኛ ችግር እንደሚያስከትል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...