ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የተመረቁት አቶ መሐመድ አብራር፣ የጉራጌ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለውና የሕግ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ የቀረበ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ማኅበረሰቡን የማንቃት ሥራ ሲሠሩ ቢቆዩም፣ የጉራጌን ጥያቄ በተደራጀ መንገድ ለማስመለስ ይረዳል ያሉትን ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲን ለጉራጌ እንታገላለን ከሚሉ ሰዎች ጋር ተሰባስበው መመሥረታቸውን ይናገራሉ፡፡ የጉራጌ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ መንግሥትን የተከተለና በሕገ መንግሥቱ ሊፈታ የሚችል ቀላል ጥያቄ ሆኖ እያለ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጉዳዩ ተወሳስቦ የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት ለምን እንደሆነ በሰፊው ያብራራሉ፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ በቅርቡ ስለተመሠረተው ጎጎት ፓርቲ እንቅስቃሴ፣ ስለጉራጌ የክልልነት ጥያቄና መንግሥት ጥያቄውን በተመለከተ ስለተከተላቸው አቋሞችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሪፖርተር ዩቲዩብ ስቱዲዮ ተገኝተው ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ሰፊ ቆይታ እንደሚከተለው የሚቀርብ ሲሆን፣ ቆይታውንም በሪፖርተር ቲዩብ በአውዶ ቪዡዋል ማግኘትም ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡– ጎጎት ማለት ምንድነው?
አቶ መሐመድ፡- ዘመነ መሣፍንት ይባል በነበረው በዋናነት 18ኛው ክፍለ ዘመን በየቦታው የጎበዝ አለቃና መከፋፈል የበዛበት ነበር፡፡ የጉራጌ ማኅበረሰብም ከውጭም ከውስጥም በሚገጥመው ፈተና አንድ ሆኖ ህልውናውን ጠብቆ መኖር የተቸገረበት ጊዜ ነበር፡፡ በውስጥ በግጦሽ፣ በእርሻና በወሰን የተለያዩ ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ ከውጭ ደግሞ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን አቅቷት በየመሣፍንቱ ተከፋፍላ ስለነበር ጥቃቶች ያጋጥመው ነበር፡፡ ይህን መሠረታዊ የህልውና ችግር ለመፍታት ደግሞ የጉራጌ አባቶች መሰባሰብ ጀመሩ፡፡
በዋናነት ሰላውዳ በሚባሉ አባት መሪነት ከተለያዩ የጉራጌ አካባቢዎች የመጡ አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎች በአንድ ቦታ ተሰባስበው ለሰላም፣ ለፍትሕና ለአንድነት በጋራ ለመቆም ቃል ኪዳን አሰሩ፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና ውጫዊ አደጋዎችን በጋራ ለመመከት የተገባ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህ ቃል ኪዳን ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት በትንሹ ለአምስት ጊዜ እየታደሰ በቤተ ጉራጌ ሕዝቦች መካከል ሲወራረስ የዘለቀ ነው፡፡
አባቶቹ ይህን ቃል ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የገቡበት ቦታ ደግሞ ጎጎት የሚባል ተራራ ነው፡፡ ጎጎት የምሥራቅና የምዕራብ ጉራጌ ሕዝቦች አማካይ ላይ የሚገኝ የቦታ ስም ሲሆን፣ በሒደት ግን የዚህ ቃል ኪዳን መጠሪያም ሆኗል፡፡ የጉራጌ ሕዝብ ተመሳሳይ የህልውና አደጋ ተፈጥሮበታል በተባለ ጊዜ ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ጉባዔ እየጠራ ቃል ኪዳኑን እያደሰ ነው የኖረው፡፡ ትልቁ የጎጎት ቃል ኪዳን የተገባው በጣሊያን ወረራ ጊዜ በ1928 ዓ.ም. አካባቢ የተደረገው ነው፡፡ በወቅቱ ታላላቅ የጉራጌ አርበኞች የመሩት ቃል ኪዳን ተገብቶ ነበር፡፡
እኛም ይህን ቃል ተውሰን የፓርቲ ስም ያደረግነው፣ ጉራጌ አሁን የገጠመውን አደጋ የውስጥ ችግሮችን ፈትቶ በጋራ በመቆም ለማለፍ የምናደርገውን ጥረት ይወክላል ብለን ነው፡፡ የጎጎት ጽንሰ ሐሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ጉራጌ ከሌሎች ጋር ተባብሮም ሆነ ተወዳድሮ ጥቅሞቹንና ደኅንነቱን የሚያረጋግጥበት ተሞክሮን የሚሰጥ በመሆኑ ነው ወደኋላ ተመልሰን ከታሪካችን የተዋስነው፡፡
ሪፖርተር፡– ጎጎት የቦታ ብቻ ሳይሆን የጉራጌ አንድነትን የሚያንፀባርቅ የቃል ኪዳን ስም ማለት ነው?
አቶ መሐመድ፡- በትክክል፡፡ ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ የተባልነው ለዚያ ነው፡፡ ጎጎት እርስ በእርስ የሚደረጉ ሽኩቻዎችን አቁሞ በአንድነት መሠለፍ ይጠይቃል፡፡ ማኅበረሰቡ አንድነት እንዳይፈጥር የሚደረጉ የተለያዩ አሻጥሮች አሉ፡፡ እነሱን አክሽፎ በአንድነት መቆም ይጠይቃል፡፡ የጥንት የጉራጌ አባቶች ብቻ ሳይሆኑ የአሁኑም ጉራጌ የጎጎት ቃል ኪዳን ያስፈልገዋል፡፡ ፓርቲው የጉራጌን ሥነ ልቦና የተላበሰ መሆን ይገባዋል፡፡ የጎጎት አስተምህሮ ደግሞ በአገር ደረጃም ቢሆን አገር በቀል የሆነ እንደ ጎጎት ያለ ቃል ኪዳን ያስፈልጋል፡፡ የጎጎት አስተምህሮ ለአገሪቱም ይጠቅማል እንላለን፡፡
ሪፖርተር፡– አገር አቀፍ ፓርቲ መሆናችሁን ትናገራላችሁ፡፡ በሌላ በኩል በብዝኃነት ስም አገር ከሚያፈርሱ፣ በአንድነት ስም ለመጨፍለቅ ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር አንተባበርም ትላላችሁ፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ አቋማችሁን የበለጠ ቢያብራሩልን?
አቶ መሐመድ፡- ጎጎት ሌሎችን አያሳትፍም ባይባልም፣ በዋናነት የጉራጌ ማኅበረሰብን የሚወክል ነው፡፡ የጉራጌ ማኅበረሰብ ማኅበራዊ ሥሪት ይታወቃል፡፡ ጠንካራ ሠራተኛ ሕዝብ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ በሰፊው ተሠራጭቶ የሚኖር ነው፡፡ የሌሎችን ጥቅም ሳይነካ የራሱን ማንነት አክብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ደግሞ በብዝኃነትና በአንድነት መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ጎላ ብለው የወጡ ብዝኃነተቶች አሉ፡፡ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ ወዘተ ተብለው የሚገለጹ ብዝኃነቶች መኖራቸው በኢትዮጵያ ሀቅ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያ በሚባል ሉዓላዊ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ያላቸው ማኅበረሰቦች በአንድነት መቆማቸው ጠቃሚ ነው፡፡ እንደ አገር ብቻ ሳይሆን በተናጠል ለእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ህልውናም አንድነቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ማንነቱ የተለያየ መሆኑ የማይካድ ሀቅ እንደሆነው ሁሉ፣ አንድነቱም ለረዥም ጊዜ ይዘነው የመጣነው ሀቅ ነው፡፡
በአንድነት ቆሞ የውጭ ጥቃትን የመከላከሉ ብቻ ሳይሆን፣ በጋራ ሆኖ ክፉውንም ደጉንም የማለፉ ጉዳይ የማይካድ የኢትዮጵያ ሀቅ ነው፡፡ አሁን ላይ ጎልቶ እየወጣ ያለው የኢትዮጵያ ችግር ግን በአንድ በኩል ብዝኃነቱን ያለመቀበል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ታሪክም ሆነ የሚያስተሳስር ነገር እንደሌለ ሁሉ አንድነቱን የመቃወም ነው፡፡ ሁለቱ የፖለቲካ አሠላለፍ ደግሞ ፍፁም የሚቃረንና ከተጨባጩ የኢትዮጵያ ሀቅ የራቀ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ጉራጌ የተባለ ሚዛኑን በጠበቀና ሁለቱንም አቀራርቦ ባቀፈ መንገድ ነው የምንጓዘው፡፡ አንዱን ትቶ ሌላውን የመያዝ ዓይነት ፖለቲካ አንቀበልም፡፡ ብዝኃነት አስጠብቆ አንድነትንም ማስቀጠል ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህም ብዝኃነት ተጠብቆ እንዲቆይና እንዲለማ እንደግፋለን፡፡ ይህ ደግሞ በአገራዊ አንድነት ውስጥና ማዕቀፍ ውስጥ ሊሆን ይችላል ብለን እናምናለን፡፡
ሪፖርተር፡– የጉራጌ ቋንቋ፣ ባህል፣ ማኅበራዊ እሴትና ማንነት አደጋ ላይ ወድቋል፣ እየተሸረሸረ ነው ትላላችሁ፡፡ በተጨባጭ እንዴት ነው ይህ እየሆነ ያለው?
አቶ መሐመድ፡- እንደ ጉራጌ እንድናወራ የሚያደርገን የጎጎት መምጣት አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱና በሥራ ላይ ያለው መንግሥታዊ አሠራር እንደ ጉራጌ መታየትን አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ያደረገ ነው፡፡ በመታወቂያ ጉራጌነቴ እየታየ ነው የምኖረውና በየዕለቱ አገልግሎት የማገኘው፡፡ ጉራጌ ለሚባል ማኅበረሰብ የራሱ መኖሪያ ብሎ የተከለለ ወሰን የሰጠውም ይህ ሕገ መንግሥታዊ አሠራር ነው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ውስጥ እንደሚኖር አንድ ማኅበረሰብ በሕገ መንግሥቱ የተፈቀዱለትን መብቶች ጉራጌ ልክ እንደ ሌላው ማኅበረሰብ አግኝቶ መኖር አለበት፡፡
ራሱን በራሱ ማስተዳደሩ፣ በቋንቋው መገልገሉ፣ ከአገራዊ ሀብት ተጠቃሚ መሆኑ ሁሉ ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡ የጉራጌ ሕዝብ የሚገባውን ድርሻ ማግኘት አለበት፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ለማካተት ጥረት ሲደረግ ይታያል፡፡ ጉራጊኛ ግን በዚህ ደረጃ የታሰበበት አይመስልም፡፡ የሥራ ቋንቋ የመሆን አንዱ መመዘኛ ‹‹በምን ያህል ጂኦግራፊያዊ የቆዳ ስፋት ቋንቋው ይነገራል?›› የሚል ነው፡፡ ጉራጌ በሰፊው የአገሪቱ ክፍል የሚገኝ ቢሆንም፣ ቋንቋው ግን ለሥራ ቋንቋነት ግምት ውስጥ ሲገባ አይታይም፡፡
ሌላውን ትተን በተሰጠው የወሰን አስተዳደር ውስጥም ጭምር ቋንቋው ችግር ገጥሞታል፡፡ በዞኑ ራሱ የትምህርት፣ የሥራ፣ የንግግር፣ የሥነ ጽሑፍና የሌላም መገልገያ ቋንቋ በሰፊው አልሆነም፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ቋንቋውን በትክክል የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር ቀንሰዋል፡፡ ቋንቋው አደጋ ገጥሞታል የሚለው የፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ወሬ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ኢንስቲትዩት ጥናት አደጋ ውስጥ ገብተዋል ከተባሉት መካከል ጉራጊኛ አንዱ ነው፡፡
ይህ ፕሮፖጋንዳ ለመሥራትና የብሔር እንቅስቃሴን ለማስጮህ የሚነሳ ሳይሆን በገለልተኛ አጥኚዎች ጭምር የሚታወቅ ሥጋት ነው፡፡ አንድ ቋንቋ የትምህርት፣ የሥራ፣ የሚዲያ፣ የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እንዲሆን ካልተደረገና ጥበቃ ከሌለው ዕጣ ፈንታው ምን ሊሆን እንደሚችል ተገማች ነው፡፡ ጉራጊኛ እያጋጠመው ያለውም ይህ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ጉራጌ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ እሴቶቹንና ባህሉን በማጋራት የሚታወቅ የጎላ ተፅዕኖ ያለው ማኅበረሰብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ምግቦቹ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወደዳሉ፣ ሙዚቃውም ሆነ ጭፈራው ብዙዎችን የሚስቡ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ማኅበረሰቡ ማኅበራዊ እሴቱ እየተናደ ነው፣ ባህሉም ችግር ገጠመው ለማለት ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ አይጠይቅም?
አቶ መሐመድ፡- የምናወራው ነገር ከመጥላትና ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር በተያያዘ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ጉዳዮች በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም ሆነ በባህላዊ ገጽታዎች ጉራጌ ምንም ሚና የለውም ለማለት አይደለም፡፡ ጉራጌን ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይወዱታል፣ ይጠሉታል፣ ወይም ያርቁታል ከሚልም የመነጨ አይደለም፡፡ በባህል፣ በሙዚቃው፣ በምግቦቹም ሆነ በሌሎች መንገዶች የሚገለጹ ተፅዕኖዎች ጉራጌ ሊኖረው ይችላል፡፡
ነገር ግን እኛ ምንለው ከዚህ በላይ በሚገባው ልክ ሚና ይኑረው ነው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ የራሱ የመንግሥት ጥናት እንደሚያመለክተው 20 በመቶው የጉራጌ ተወላጅ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ያለው ሕገ መንግሥታዊ አሠራር ደግሞ ሁሉም ነገር በብሔር እንዲታይ ወይም ስለብሔር እንድናወራ የሚያስገድድ ነው፡፡ በየትም ቢሆን ሁሉም ነገር ሲሠራ ለምሳሌ በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ምን ያህል ጉራጌ፣ ምን ያህል ደግሞ ኤክስ፣ ዋይ፣ ዜድ የተባሉ ብሔሮች አሉ ተብሎ ነው የሚለካው፡፡ የተለያዩ ብሔሮች ምን ያህል ሹመት አገኙ፣ ኮታ ደረሳቸው እየተባለ ነው በሁሉም መስክ ንፃሬ የሚታየው፡፡
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሀብትም ሆነ የሥልጣን ድርሻ የሚወሰነው ከብሔር አንፃር ነው፡፡ ይህ እስኪሆነ ድረስ ደግሞ ጉራጌ አሁን ካለው በተሻለ ድርሻ ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉራጌ ድርሻውን እንዳያገኝ ደግሞ ውጫዊ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ምክንያቶች መኖራቸው አይካድም፡፡ ሁሉንም ችግር ውጫዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ ለምሳሌ ከባህል፣ ከቋንቋና ከመሳሰሉት ጋር ችግር ገጥሞታል ስንል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሆን ብሎ ሊያከስመው ስለፈለገ የሚል አተያይ በግሌ የለኝም፡፡ ባለው የዞን መዋቅር ውስጥ ቋንቋውን ማሳደግ የሚችልበት ምቹ ዕድል አለው፡፡
ስለዚህ ሁሉንም ዓይነት ችግር ከአደረጃጀት ጥያቄ ጋር ማያያዝ አንችልም፡፡ አንዳንዶቹ ውስጣዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ምንም ቢባል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በታሪክ ካየን በሥነ ቃል የዳበረና በጣም የተደራጀ ቋንቋ ነበረው፡፡ ሌሎች ማኅበረሰቦች ቋንቋቸውን የሥራና የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ለማድረግ ሲሠሩ፣ መዋቅሩ ምንም ይሁን ምን ጉራጌን የሚያስተዳድሩ አካላት ይህን አለማድረጋቸው ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ ትውልዱ እየተማረበት እንዲያድግ ዕድሎች አልተመቻቹም፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ዞኑን ያስተዳደሩ ወገኖች የሚጠበቅባቸውን ባለመሥራታቸው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡
ሌሎች ቋንቋዎች እንደሆኑት ሁሉ የጉራጌ ቋንቋም በአገሪቱ የተሻለ ቦታ ላይ መድረስ መቻል ነበረበት፡፡ ሌሎቹ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ጥናትና ምርምር የሚደረግባቸው ቋንቋዎች ሆነዋል፡፡ ጉራጊኛ ግን በአፍ መፍቻ ደረጃ የትምህርት መስጫ ቋንቋ ስለመሆኑ እየተነጋገርን ነው፡፡ የማንነት ዋና መገለጫዎች ከሆኑት አንዱ የሆነው ቋንቋ አለማደጉና አደጋ ላይ መውደቁ ደግሞ የሚያሳስብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– የክልልነት ጥያቄው ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የተነሳ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ጥያቄው የበለጠ ገፍቶ እየመጣ ይመስላልና ጉዳዩ በምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው?
አቶ መሐመድ፡- ምናልባት በዞኑ ምክር ቤት ፀድቆ የቀረበበት ካልሆነ በስተቀር፣ ጥያቄው እንኳን ረዘም ያለ ጊዜን አስቆጥሯል፡፡ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በተዋቀረበት ጊዜ የጉራጌ 33 ተወካዮች ስብሰባውን ረግጠው በመውጣት ተቃውመዋል፡፡ ጉራጌ መጨፍለቅ የለበትም፣ የራሱ አስተዳደር ይኑረው በሚል ነው ይህን ያደረጉት፡፡ በጊዜው ሌሎቹ ካገኙት በተቃራኒው ግልጽ የወጣ አፈናና አድሏዊነት በመኖሩ ነበር አደረጃጀቱን አንፈልግም ያሉት፡፡
ሥርዓቱ ጉዳዩን ቢያፍነውም ለረዥም ጊዜ ተዳፍኖ የቆየው የሕዝቡ ጥያቄ፣ የአፈና ሥርዓቱ ተወግዶ አዲስ መንግሥት ሲተካ የዞኑ ምክር ቤት ጥያቄ ሆነ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሚያስቀምጠው መሠረት አንድ የዞን ምክር ቤት ያፀደቀውን የአደረጃጀት ጥያቄ፣ የክልል ምክር ቤቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር ተነጋግሮ ያስፈጽማል ነው የሚለው፡፡ የሲዳማም ሆነ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ሲፈጠሩ የተደረገው ይኼው ነው፡፡ አሁን እየተደራጀ ባለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር ክልልም ከዚህ የተለየ አካሄድ አልታየም፡፡
ነገር ግን ጉራጌ ጥያቄውን ባቀረበ ወቅት ብዙ ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄዎች በደቡብ ክልል ተፈጥረው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የክልሉ ምክር ቤትና የፌዴራል መንግሥቱ ጥያቄውን መመለስ አንችልም ነው ያሉት፡፡ አብዛኛውን የደቡብ ክልል ጥያቄ የፈጠረው ግን ራሱ የብልፅግና መንግሥት ነበር፡፡ እንደ ሲዳማ፣ ጉራጌ ያሉ ጠንካራ ጥያቄ ይዘው የቀረቡትን ለማጨናገፍ ይፈለግ ስለነበር፣ ጥያቄዎቹ በሁሉም አቅጣጫ እንዲፈጠሩ ተደረገ፡፡ እናንተ ጋ ብቻ አይደለም ሁሉም ስለጠየቀ መመለስ ይከብዳል ለማለት ይፈለግ ነበር፡፡ ደቡብ ክልል 55 ብሔረሰቦች ናቸው ያሉት፡፡ ብልፅግናዎች ስላልታያቸው እንጂ በወቅቱ 55 የብሔር አደረጃጀት ጥያቄዎች እንዲፈጠር ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ የሰላም አምባሳደሮች የሚባል ኮሚቴ ተቋቋመና እንዲያጠና ተመደበ፡፡ ነገሩ ቀድሞ የተመቻቸ ነገር ነበር፡፡ ወደ ሦስት ቦታዎች ሄዱ፡፡ ዛሬ ደቡብ ኢትዮጵያ ተብሎ የተዋቀረው ያኔ ኦሞቲክ በሚል ክላስተር ክልል ሊዋቀር አመቻቹ፡፡ ጉራጌ የሚገኝበትን አሁን ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተባለውን ደግሞ ሸዋ ክላስተር ክልል ብለው ሊያዋቅሩ አዘጋጁ፡፡ ሦስተኛው ደቡብ ምዕራብ ተብሎ ነው ክልል ሆኖ የወጣው፡፡
ሪፖርተር፡– እዚህ ላይ ጥናቱን ካደረጉት ሰዎች ነው? ከጥናት አጠናኑ? ወይስ ከጥናቱ ይዘት ነው ችግር ያለው ነው የምትሉት?
አቶ መሐመድ፡- ከይዘቱ፡፡ ጥናት ተጠና እንዲባል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመደበ፡፡ የሰላም አምባሳደሮች የተባለ አቶ አባዱላ የመሩት ቡድን በደቡብ ክልል በሦስት አቅጣጫዎች ተንቀሳቀሰ፡፡ ይዞት የተመለሰው ደግሞ ሲዳማ የሌለበት ደቡብ ክልል በሦስት ክልሎች መደራጀት ይችላል የሚል ድምዳሜ ይዞ ተመለሰ፡፡ ይህ ራሱ ቡድኑ ያቀረበው የጥናት ሪፖርት ያስቀመጠው ነው፡፡
ሪፖርቱ እንዳመለከተው ከሆነ በጉራጌ ዞን በጥናቱ ከተሳተፉ ወደ 400 ከሚሆኑ ሰዎች መካከል፣ ከጉራጌ ውጪ የሆነ አዲስ አደረጃጀት እንፈልጋለን ያለ ሕዝብ እንደሌለ አስቀምጧል፡፡ ይህን ኮሚቴውም ሳይክድ በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ጥናቱን ከማድረጋቸው በፊት የወሰኑት በመሆኑ ከጥናቱ ግኝት በተቃራኒ ጉራጌ በክላስተር ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ወስነዋል፡፡ ይህንን ዕቅዳቸውንም ዞኑ እንዲያፀድቅ ገፍተው አመጡት፡፡
የጉራጌ ዞን ግን ሐሳቡን በድምፅ ብልጫ ውድቅ ነው ያደረገው፡፡ ከነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የጉራጌ ጥያቄ እንደ ሌሎቹ ሳይሆን የተለየ ጥያቄ ሆኗል፡፡ በሌሎቹ አካባቢዎች መንግሥት ያለው በክላስተር ክልል የመደራጀት ዕቅድ ከሞላ ጎደል እንዲፈጸም ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በጉራጌ ግን ውሳኔው ውድቅ ነው የተደረገው፡፡
ሪፖርተር፡– ጉራጌ ለምን አልተቀበለውም?
አቶ መሐመድ፡- ጉራጌ አዲስ ጥያቄ አይደለም ያቀረበው፡፡ ብልፅግና የላካቸው የሰላም አምባሳደሮች ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢሕአዴግ ተሃድሶ ላይ ነኝ ባለበት ወቅትም ጥናት አደረግኩ ብሎ ነበር፡፡ የደቡብ ክልል ከመደራጀቱ በፊት ክልል ሰባት በሚል ጉራጌ አሁን በሚባለው የሸዋ/ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክላስተር ክልል ልክ የሆነ ተመሳሳይ ጂኦግራፊ ባለው ክልል ኖሯል፡፡ አሁን ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብለው እንዳመጡት ሁሉ ከ1983 እስከ 1987 ዓ.ም. በነበረው የሽግግር መንግሥት ጊዜም ክልል ሰባት ተብሎ ተደራጅቶ ነበር፡፡ ይህ አይሆንም ተብሎ ደግሞ ማዕከሉን ከሆሳዕና ወደ ሐዋሳ ወስደው በደቡብ ብሔሮች ክልል ውስጥ ከተቱት፡፡
ማዕከሉ ሐዋሳም ሆኖ በ1992 ዓ.ም.፣ በ1997 ዓ.ም.፣ በ2002 ዓ.ም. በተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦበታል፡፡ የጉራጌ ተወካዮች ተቃውመዋል፣ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ጥያቄም ነው፡፡ ክላስተሩ ድጋፍ እንዲያገኝ በመንግሥት ብዙ ቅስቀሳ፣ ማባበያ፣ ማስፈራሪያና አፈና ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ ጥረት ምክር ቤት ላይ ቢቀርብም የዞኑ ምክር ቤት ግን ውድቅ ነው ያደረገው፡፡ ስለዚህ ከነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የጉራጌ ጥያቄ እንደ ሌሎቹ ሳይሆን የተለየ ጥያቄ ነው፡፡ የጉራጌ ጥያቄ የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ መሆኑ የሚረጋገጠው ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደ ብቻ ነው፡፡
የአንድ ዞን ትልቁ የሥልጣን አካል የዞን ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ አንድ ውሳኔን ካፀደቀ በኋላ ሊመጣ የሚችለው ነገር ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ስለሚያስገድድ ሕዝበ ውሳኔው መደረጉ ግዴታ ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የቀረበ የቆየ ጥያቄ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. ነው በምክር ቤት የፀደቀው፡፡ የምናወራው የሕገ መንግሥት ጉዳይ ነው፡፡ የሪኮመንዴሽን፣ የጥናት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት፣ ወዘተ የሚባሉት ነገሮች ሁሉ ከሕገ መንግሥቱ በታች ነው፡፡
መጀመሪያ ክልል ጠየቀ እንቢ አሉ፡፡ ክላስተር ተቀበል አሉት እሱንም ውድቅ አደረጉት፡፡ ምክር ቤት እኮ ማለት የጎጎት፣ የተቃዋሚ ወይ የሌላ አባላት የሞሉበት አይደለም፡፡ የራሱ የመንግሥት ሰዎች የሞሉበት ነው፡፡ ከ96 የምክር ቤት አባላት አብላጫዎቹ የራሱ የብልፅግና ተወካዮች ነው፡፡ የራሱ ሰዎች ያፀደቁትን እሺ አይቀበለው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱን ምን ሊያደርጉት ነው? እነሱ ውድቅ ካደረጉት በኋላ ፍላጎታቸውን በኃይል ለመጫን ካልሆነ በስተቀር ለምን ይታገላሉ?
ግልጽ የሕገ መንግሥት ጥያቄ ነው እየተጠየቀ ያለው፡፡ የብልፅግና መንግሥት ክላስተር ክልል የማደራጀት የፍላጎቱን ለማስፈጸም ብቸኛው አማራጩ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት የክላስተር ክልል ነው የሚያዋጣው ያለውን ሐሳብ በስፋት ማኅበረሰቡ እንዲቀበለው ያስተምር፣ ይቀስቅስ ወይም ያስርፅ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክላስተር አይበጅም የሚሉ ኃይሎች ሐሳባቸውን በነፃነት እንዲያራምዱና ተቀባይነት እንዲያገኝ ሜዳው ይፈቀድላቸው፡፡ በስተመጨረሻ ግን ሕዝቡ ከሁለቱ የራሱን ፍላጎት በካርዱ እንዲመርጥ ሕዝበ ውሳኔ ይደረግ፡፡
ሪፖርተር፡– ሌላ አማራጭና መንገድ መፈለግ አይቻልም? ለምሳሌ ኢትዮጵያ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ክልል ለመፍጠር የሚፈቅድ አለመሆኑን መንግሥት ይናገራል፡፡ በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩትን ሰምተውታል፡፡ አዳዲስ ክልሎች እየተፈጠሩ በጀቱን በተለይም ደመወዙን መሸፈን እየከበደን ነው ብለዋል፡፡ በትንሹ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ የሌለው አካባቢ ክልል ቢሰጠው ገቢ አመንጭቶ በራሱ ደመወዝ ለመክፈል ይቸገራል ብለዋል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም አገሪቱ በጦርነት ማግሥት ላይ ትገኛለች፣ ሰላምና መረጋጋትም ርቋታልና የክልልነት ጥያቄውን አመቺ ጊዜ እስኪፈጠር ጋብ ማድረግ አይቻልም?
አቶ መሐመድ፡- የመጀመሪያው መንግሥት ማድረግ ያለበት ነገር ሕገ መንግሥቱን መጣሱን በግልጽ ማመን ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሥቱን በትክክል መፈጸም ያልቻለበትን ምክንያት ማቅረብ አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱን እየጣስክ መልሰህ ደግሞ በግድ ተቀበሉኝ ልትል አትችልም፡፡ የጉራጌ ክልል የመሆን ጥያቄ መመለስ የነበረበት በ2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ የዞኑ ምክር ቤት 2011 ዓ.ም. አፅድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አስገብቷል፡፡ ይህ በአንድ ዓመት ሊፈጸም የሚገባ ቢሆንም፣ በ2012 ዓ.ም. ደግሞ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታውን አስገብቷል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ደግሞ ክላስተር ክልል ተቀበሉ የሚለውን ውድቅ ካደረገ በኋላም ያንን ውሳኔ ከቃለ ጉባዔ ጋር ለፌዴሬሽን ምግር ቤት አስገብቷል፡፡
ይህንን ሁሉ ውሳኔ ምን አድርገውታል የሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠው መብቱ ተነፍጓል፡፡ ለሌሎች የተፈቀደውን ተከልክሏል፡፡ ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ መብት ይከበር የሚል ነው፡፡ ይህን ማድረግ አልቻልንምና ሌላ አማራጭ ይታይ ቢባል እንኳ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡
ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ክልል በገቢ ራሱን ለመቻል ያስፈልገዋል የተባለውም ጉዳይ የማይመስል ሐሳብ ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የሰማነው በፓርላማ ነው፡፡ የተቋቋሙት ክልሎች ብዙዎቹ ስድስት ሚሊዮን አይሞሉም፡፡ እነሱ ሊፈርሱ ነው፡፡ ክልል መሆን የበጀት ወጪን የሚጨምርበት አሳማኝ አመክንዮ የለም፡፡ ድጎማውም ቢሆን በተለየ መንገድ ሳይሆን ባለው አሠራር የሚደረግ ነው፡፡
ሀብቱ የሚከፋፈለው በብሔር ኮታ ነው፡፡ በክልል፣ በወረዳም ሆነ በዞን መዋቅር አንድ አካባቢ ቢሆን በቀመሩ መሠረት ነው የሚያገኘው፡፡ አሁን ግን ባለበት ያልቆመ ወይ ከነበረበት መዋቅር ወደ ታች ያልወረደ ተጨማሪ የበጀት ድልድል አያገኝም የሚል ፍላጎት ያላቸው ነው የሚመስለው፡፡
ሪፖርተር፡– ከወረዳ ወደ ዞን፣ ከዞን ወደ ክልል ሲታደግ ቢሮክራሲያዊ ወጪውም በዚያው ልክ ይሰፋል፡፡ አዳዲስ መዋቅር ስለሚፈጠር የደመወዝ ወጪ ይጨምራል የሚል ሥጋት መሆኑን አውስተዋል እኮ?
አቶ መሐመድ፡- አንድ ክልል ሲደራጅ ጥቅሞችና ጉዳቱን አስልቶ ነው፡፡ ከፌዴራል መንግሥቱ የሚጠበቀው አሠራሩ በሚፈቅደው መሠረት ለዚያ ክልል በቀመሩ መሠረት በጀት መስጠት ነው፡፡ ክልሉ በራሱ መንገድ አብቃቅቶ መጠቀም ይችላል፡፡ ጉራጌን በተመለከተ ቤሳ ቤስቲን አይጠይቅም፡፡ ጉራጌ ክልል ባለመሆኑ ያጣው ብዙ ነው፡፡ በጉራጌ ዞን 1,000 ካሬ መሬት ማግኘት አትችልም፡፡ አካባቢዬን ላልማ ካልክ ሐዋሳ ተመላልሰህ ደጅ መጥናት አለብህ፡፡ በጉራጌ እጅግ ደም ያፋሰሱ የወረዳነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ክልል ካልተሄደ ዞኑ መመለስ አይችልም፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚችልበት የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይል፣ አስተዳደራዊ አሠራር የመፍጠር አቅም የጉራጌ ማኅበረሰብ ያነሰው አይደለም፡፡ የጉራጌ ሕዝብ አልተማረም፣ መሬት የለውም፣ ታሪክ የለውም፣ አካባቢውን የመምራት አቅም የለውም ለማለት ካልተሞከረ በስተቀር፣ ከሌሎች ክልል ከሆኑ አካባቢዎች የሚያንስበት አንዳችም ማሳመኛ ማቅረብ አይቻልም፡፡
ሪፖርተር፡– እንደ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ያሉ ከጉራጌ ማኅበረሰብ የወጡ አንጋፋ የፖለቲካ ሰዎች ጭምር የክልልነቱን ጥያቄ ሲቃወሙት ተመልክተናል፡፡
አቶ መሐመድ፡- እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ አቋማቸውን አከብራለሁ፡፡ የሚያራምዱትን የብሔር ፖለቲካ አፍራሽ ነው የሚል አካሄድ ለረዥም ጊዜ ይዘው መጓዛቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሐሳባቸውን ወደ ጉራጌ ይዘው ወርደው የተሸነፈ ሐሳብ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ባለፈው ምርጫ አንፃራዊ ነፃ ፉክክር በታየበት የጉራጌ ዞን ምርጫ የእሳቸው ኢዜማ ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ ኃይሎች፣ ጉራጌ ዞን በተሻለ ሰላምና ነፃነት ገብተው ለመፎካከር ችለው ነበር፡፡ ሆኖም በሰፊው ተንቀሳቅሰው ዞኑ ካለው 13 የፓርላማ ወንበሮች ሁለት ብቻ ነው ማሸነፍ የቻሉት፡፡ ሕዝቡ አስተሳሰባቸውን ስላልገዛውም ሆነ በሌላ ምክንያት አሸናፊ አልሆኑም፡፡
እሳቸው የብሔር ፖለቲካ አልደግፍም የሚል አቋም እያንፀባረቁ ቢሆንም፣ ነገር ግን የብሔር ፓርቲ ሥርዓትን እያገለገሉ ነው ያሉት፡፡ ጉራጌ እያቀረበ ያለውን የክልል ጥያቄ ለማደናቀፍ ከብልፅግና ጋር እየሠሩ ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድም ከፍተኛ ውግዘት እየደረሰባቸው ነው፡፡ የክልል ጥያቄን ከብሔር እንቅስቃሴ ጋር አገናኝተውታል፡፡ የብሔር ፖለቲካን የሚፀየፉ ከሆነ አሁን ያለውን በብሔር የተደራጀ መንግሥት እያገለገሉ ነው፡፡ ብልፅግና የብሔር ድርጅት ነው፡፡ ወልቂጤ በተካሄደው መድረክ ላይ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጎን የተቀመጡት የባህል አልባሳት የለበሱ የብልፅግና ከፍተኛ አመራሮችም የኦሮሞ፣ የአፋርና የሶማሌ ከሰመሳሰሉ ብሔሮች የመጡ ናቸው፡፡
ጉራጌ ክልል መሆኑ አይደለም የብሔር ብሔርተኝነትን የሚፈጥረው፡፡ በዞንም እያለ እኮ በመታወቂያ የተጻፈ ጉራጌ የሚል የብሔር ማንነት ተሰጥቶታል፡፡ ዛሬ እየጠየቀ ያለው ጉራጌ የሚባለው አስገዳጅ አደረጃጀት በመኖሩ፣ በዞኑና ከዞኑ ውጪ ያለውን ጉራጌ ተወላጅ አደራጅቼ ልንቀሳቀስ የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን እነሱ ጉራጌ ለ30 ዓመታት እንደተሄደው በፖለቲካም በኢኮኖሚም እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ሳይኖረው ይቀጥል እያሉ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ የክልልነት ጥያቄውን ከብሔር እንቅስቃሴ ጋር ያገናኙበት መንገድ ፍፁም ትርጉም የማይሰጥ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ሕገ መንግሥቱና አስተዳደራዊ መዋቅሩ ጉራጌን ጉራጌ ብሎ አስቀምጦታል፡፡ ከዞንነት ወደ ክልልነት ማደጉ ልክ አዲስ ትርጓሜ ያሰጠው ይመስል ተገቢ አይደለም ማለቱ ትርጉም የለውም፡፡ እሳቸው አይዲዎሎጂያቸውን ነው እየተከላከሉ ያሉት፡፡
ሆኖም እሱንም በሚጣረስ መንገድ በቅርቡ ኢዜማ ከአብን ጋር ለመሥራት ተስማምቷል፡፡ እሳቸው በብሔር የተደራጀ ፓርቲን እያገለገሉ ነው፡፡ ድርጅታቸው ኢዜማ ደግሞ ከብሔር ፓርቲዎች ጋር እየተባበረ ነው፡፡ ፍላጎታቸው እንዲህ ነው ብሎ ለመረዳት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ንግግራቸውና ሥራቸው የጉራጌን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚነጥቅ ዓይነት ነው፡፡ ፓርቲያቸውን ይወክላል አይወክልም የሚለውን ስገምት፣ ከፓርቲያቸውም ሆነ ከራሳቸው አመለካከት ጋር የሚገጥም አይመስለኝም፡፡ ጉራጌ ክልል ሲሆን ምን እንዳስፈራቸው ራሳቸው ይወቁት፡፡ በአጠቃላይ ሦስት ጉራጌን የተመለከቱ መድረኮች ላይ ተገኝተዋል፡፡ በእነዚህ መድረኮች የተናገሯቸው ንግግሮች ደግሞ እንደ ንግግር ችግር የለባቸውም፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ከሚጠይቀው ጋር የማይገናኝ ነገር ነው የተናገሩት፡፡ ጉራጌ በክልልነት ልደራጅ ነው ያለው፡፡ አዲስ ማንነት ይኑረኝ ሳይሆን የበለጠ ልልማ፣ ተደማጭነት ይኑረኝ፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ልሁን ነው ያለው እንጂ፣ አዲስ የብሔር ማንነት አልጠየቀም፡፡ ለዚህ ጥያቄ እንቅፋት ሆነው ለምን እንደሚቆሙ አልገባኝም፡፡
ሪፖርተር፡– መንግሥት ጉራጌ አጀንዳ ተቀባይ አይሁን ይላል፡፡ ሕዝቡ የኅዳር አህያ መሆን እንደሌለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ምን ምላሽ አላችሁ?
አቶ መሐመድ፡- ጉራጌ የማንም አጀንዳ ተቀባይ ሆኖ አያውቅም፡፡ ንግግሩ ሕዝቡን ለማስፈራራትና ጥያቄውን እንዲተው ለማሸበር ታስቦ የተነገረ ይመስለኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማንም በተሻለ መረጃው ስለሚኖራቸው የጉራጌ ሕዝብ የማን አጀንዳ ተቀባይ እንደሆነ ራሳቸው ግልጽ ቢያደርጉት ጥሩ ነው፡፡ በዚህ መሰሉ ነገር ጥያቄውን ማስቆም ግን አይቻልም፡፡