Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ቀን:

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ወገኖች ቁጥር በርካታ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም  በመሆኑ ከአዕምሮ እክል ጋር የተያያዘውን ክስተት ለመቋቋም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የግል ማዕከሎች ተመሥርተው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

ማዕከላቱ በወርኃ ሚያዝያ (አፕሪል) የሚታሰበውን 16ኛውን ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ወር አስመልክተው  በሳምንቱ አጋማሽ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ  የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪያቸውን  አቅርበዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በኦቲዝምና ተዛማጅ በሆኑ የአዕምሮ እክል ዙሪያ የሚንቀሳቀሱት ድርጅቶች ይበልጥ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ ማኅበራቸውን ‹የኢትዮጵያ ኦቲዝም ሶሳይቲ› ለማቋቋም መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ስምምነት ላይ የደረሱትም ከአዲስ አበባ ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል፣ ነህምያ ኦቲዝም ማዕከልና ምሉዕ ፋውንዴሽን፤ ከአዳማ ከተማ ቤተል አዳማ ማዕከል፣ ከሐዋሳ ከተማ ብራይት ኦቲዝም ማዕከል ናቸው፡፡

የማኅበሩ ዕውን መሆን ማዕከላቱ በየግላቸው ያካበቱትን ልምድ፣ አቅምና ዕውቀት በማስተባበር ያሉትን ችግሮች በአንድነት ለመቋቋም አቅም ይፈጥርላቸዋል። ከዚህም ባሻገር አገልግሎቱ ባልተዳረሰባቸው  አካባቢዎች ለማዳረስ ትልቅ አቅም የሚፈጠር መሆኑም ተገልጿል።

የኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል ዳይሬክተር ወ/ሮ እሌኒ ዳምጠው እንደገለጹት፣ የሶሳይቲው መቋቋም ማዕከላቱ በየግላቸው የሚያካሂዱትን እንቅስቃሴ በተጠናከረና በተሳለጠ አኳኋን ለማንቀሳቀስ፣ በኦቲዝምና ተያያዥ በሆኑ የአዕምሮ ዕድገት እክል ላይ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ለመገናኘትና ትስስር ለመፍጠር፣ ሥልጠና፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማከናወን ያስችላቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የፈጣሪ ቁጣ ወይም መጥፎ መንፈስ በሚል የተሳሳተ አመለካከትና አረዳድ ከማኅበረሰቡ ተገልለው፣ ታስረውና ቤት ተዘግቶባቸው ያሉትን ልጆችና ቤተሰቦቻቸውንም በመድረስ የድርጅቶቹ በአንድ ጥላ ሥር መሰባሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የኒያ ፋውንዴሽንና ሌሎች መሰል ድርጅቶች የዓመታት ጥረት ከሚዲያዎች አጋርነት ጋር ተደምሮ መሰል የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ከመቅረፍ አኳያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ መሻሻል ማምጣት የተቻለ ቢሆንም እንደ አገር በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ጥራት ያለው አካቶ ትምህርት ከኦቲዝም ጋር ለሚኖሩ ሁሉም ሕፃናትና ወጣቶች›› በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በሚከበረው ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ግንዛቤ ቀን አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለጹት በጤና፣ በትምህርት፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የኦቲዝም አገልግሎት ለመደገፍ እያሳዩ የሚገኘውን በጎ መነሳሳት ማዕከሉ ያደንቃል፡፡

ነገር ግን ድጋፉ ዘላቂና ተከታታይነት ያለው እንዲሆን እንዲሁም ተቋማዊና በተዋረድ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች በፖሊሲ ደረጃ መወሰድ በሚገባቸው ዕርምጃዎች ዙሪያ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የኦቲዝም መከሰት ምጣኔ በከፍተኛ እየጨመረ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 በዓለም አቀፉ የበሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል (ሲዲሲ) ከ11 የተደራጀ የኦቲዝም ጥናት መረጃ ማዕከላት በተሰበሰቡ የጥናት መረጃዎች ውጤት እንደሚያመለክተው፣ አዲስ ከሚወለዱ ሠላሳ ሦስት ሕፃናት መካከል አንዱ ከኦቲዝም ሁኔታ ጋር ይወለዳል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው እንደተወሳው፣ ይህ አስደንጋጭ የጥናት ሪፖርት ውጤት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ባልተሰጠባቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ምን ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

የጆይ ኦቲዝም ማዕከል ለረዥም ዓመታት የተሃድሶና የቴራፒ ድጋፍ ሲያደርግላቸው የነበሩ 12 የኦቲዝምና የአዕምሮ ዕድገት እክል ያለባቸው ልጆች ተመርቀው በድርጅቱ ውስጥ በቋሚ ሠራተኝነት ተቀጥረው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በመርዳት ላይ መሆናቸውን ነው ዳይሬክተሯ ያመለከቱት፡፡

ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኦቲዝምና የአዕምሮ ዕድገት እክል ያለባቸው ልጆች የተሃድሶ ትምህርትና እንክብካቤ ከተደረገላቸው መሥራት፣ መለወጥና ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር የመረዳት አቅም ያላቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

እንደ የምሉዕ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ኃይሉ አገላለጽ፣  መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአዕምሮ ጤና ችግሮች ትኩረት በመስጠት የተነሳ ብሔራዊ የአዕምሮ ጤና ስትራቴጂክ ቀረፆ እየተገበረ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን ስትራቴጂው ለኦቲዝምና ተያያዥ ለሆነው የአዕምሮ ዕድገት እክል ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም፡፡

ኦቲዝምና ተያያዥ የሆነው የአዕምሮ ዕድገት መዛባት፣ የነርቭ የአዕምሮ ሥርዓት ዕድገት እክል መሆኑን ገልጸው፣ እክሉ ግን ዕድሜ፣ ፆታና አካባቢ ሳይለይ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ሊከሰት እንደሚችል፣ ተላላፊ ከሆኑ በሽታዎች ይልቅ አሳሳቢነቱ በጣም የከፋ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የኦቲዝም ቀን በዓለም ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲከበር የተወሰነው እ.ኤ.አ. በ2007 ሲሆን፣ ዓላማውም የኦቲዝምና ተዛማጅ የአዕምሮ ዕድገት ዕክል ያለባቸው ወገኖች መሠረታዊ መብትና ነፃነታቸው እንዲጠበቅና ተገቢው አፅንኦት እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ሕይወታቸው የተሻለና ትርጉም ያለው እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ለማድረግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...