Thursday, June 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ዘ ዊኬንድ›› – የማንነት አሻራ ከቤላ እስከ ካናዳ

በአበበ ዘገዬ (ፕ/ር)

ወላጆች ልጆቻቸውን አሳድገው፣ አስተምረውና ለወግ ለማዕረግ ያደርሳሉ፡፡ ልጆችም የራሳቸውን ቤተሰብ መሥርተው የራሳቸውን ልጆች ለእናትና አባቶቻቸው ደግሞ የልጅ ልጅን ያፈራሉ፡፡ ልጅ እንደ መውለድ ሁሉ የልጅ ልጅ ማየት ደግሞ መታደልና የደስታ ምንጭ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለአንዲት እናት በኋላም የልጅ ልጅ አይታ አያት ስለሆነች፣ ብሎም የእናትነት ኃላፊነቷን ተወጥታ የአያትነት ክብርንና ኃላፊነትን በማግኘት በዓለም መድረክ ታዋቂ የሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ካናዳዊ አቀንቃኝን ያበረከተች እናትና አያት እንተርክላችኋለን፡፡ ለመሆኑ ይህ በአያት አድጎ አሁን ከዓለም ቁንጮ ዘፋኞች መካከል የደረሰ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ማነው በኢትዮጵያ ባህልና ሥነ ምግባር አሳድጋ ለዚህ ያበቃች አያትስ ማን ናት?

ቅድመ ታሪክ

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከሆኑ በኋላ በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፋ አድርገዋል፡፡ የተደረገው ጥረት ለወንዶች ተማሪዎች ብቻ ያመቻቸ ስለነበር ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ተልከው የመማር ዕድል አልነበራቸውም፡፡ በኋላም እቴጌ መነን ሴት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ መኳንንቱ እያሳመኑ እንዲሁም ደግሞ የእሳቸውን ዓላማ በመደገፍ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲልኩ የመጀመርያው የሴቶች ትምህርት ቤት ተቋቋመ፡፡ በዚያን ጊዜ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ሆነው ከውጭ ዜጎች የተሾሙት ማዳም ካሪኮይስና ማዳም ጋሪጉ ሲሆኑ፣ ትምህርት ቤቱ በጣልያን ወረራ ምክንያት ተዘጋ፡፡ ከዚያም በኋላ የተሾሙት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ሲሆኑ፣ ከ1936 ዓ.ም. እስከ 1948 ዓ.ም. ድረስ በተከታታይ ለአሥራ ሁለት ዓመታት በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ አድማስ እየሰፋ ከሠለጠኑ በኋላ ብቃታቸው እየተረጋገጠ ሰርተፊኬት ያገኙና በልዩ ልዩ ሙያ እየተሰማሩ አገራቸውን ያገለግሉ ነበር፡፡ የአሁኑ ባለታሪካችን አቤል ተስፋዬ ወይም በሙያዊ መጠሪያው ‹‹ዘ ዊኬንድ›› (The Weekend) አያት ወ/ሮ ወሰኔ ኃይሌ በዚያን ጊዜ ከነበረው የትምህርት ሥርዓት ከተማሩ ሴቶች መካከል ናቸው፡፡

የአሁኑ አቤል ተስፋዬ አያት ወ/ሮ ወሰኔ ኃይሌ ማን ናቸው? ለአቤል ተስፋዬስ አሁን ላለበት ማንነትና ለልጅነት አስተዳደጉ ምን አስተዋጽኦ ነበራቸው? የሚለውን ጥያቄ እያነሳን በቅደም ተከትል እናስነብባችኋለን፡፡  ወ/ሮ ወሰኔ ኃይሌ ከአባቷ ከአቶ ኃይሌና ከእናቷ ከወ/ሮ የሺ አስፋው በአዲስ አበባ በፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ በተለምዶ ፈረንሣይ አቦ እየተባለ በሚጠራው ሠፈር ተወለደች፡፡ በኋላም ወላጅ እናቷ ሻለቃ ዘገዬ የምሩን በትዳር ሲያገቡ ወሰኔ ከወንድሞቿ ዓለማየሁ ኃይሌ፣ አሥራት ኃይሌ፣ ተፈራ ኃይሌ ጋር ወደ እናቷ ዘንድ መጣች፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ በእቴጌ መነን የልጃገረድ ሴቶች ትምህርት ቤት ገባች፡፡ አብረዋት ከተማሩት ተማሪዎች መካከል ወ/ሮ አንቺንለማ ግርማ ይገኙበታል፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታዋ በትጋት በመማር ትምህርቷን አጠናቃ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ማሠልጠኛ ሠልጥና በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤት በመቀጠር በሃምሳ አምስት ዓመት ዕድሜዋ ጡረታ እስከወጣች ድረስ አገልግላለች፡፡ ወሰኔ በጣም የሚማርክና ልዩ የሆነ የድምፅ ቅላጼ ነበራት፡፡ በዚህ የተነሳ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁጥር ስምንት ዓለም አቀፍ ኦፕሬተርነት ተመድባ ለማገልገል በቅታለች፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ዝነኛው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሳተመው ዓመታዊ መጽሔት በሥራቸው ላይ ሆነው ፎቶግራፋቸውን ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

ወ/ሮ ወሰኔ በትምህርት ራሷን አሻሽላ ለራሷና ለአገርዋ አስተዋጽኦ ካደረገች በኋላ ጡረታ ስትወጣ በኢትዮጵያ ባህል በተለመደው የአያትነት ክብር የልጅ ልጆቿን ለማሳደግና ለመንከባከብ ለልጆች እንዲሁም፣ በልጅ ልጅ ተከቦ መኖርን ታድላለች፡፡ በዚያው በውጭ አገር እየኖረች የልጇ ልጅ የሆነውን አቤል ተስፋዬን የእህቶቿን ማለትም ሚሚ (ዘውድነሽ) ዘገዬ፣ ትዕግሥት ዘገዬ፣ ልጆች እንዲሁም፣ የወንድሞቿን ልጆች እየረዳች ታሳድግ ነበር፡፡

አቤል ተስፋዬ የተወለደው እ.ኤ.አ. የካቲት 16 ቀን 1990 በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ ሲሆን ዕድገቱም በዚያው ነበር፡፡ የስድስት ዓመት ሕፃን ሳለ ወላጅ አባቱ አቶ ተስፋዬ መኮንን ትዳሩን ፈትቶ ሌላ በማግባቱና ልጆች በመውለዱ አባቱን በቅጡ አያስታውሰውም፡፡ የአቤል ወላጅ እናት ቤተሰቦቿን ለማስተዳደር ልዩ ልዩ ሥራዎች በመሥራት ጥረት ታደርግ ነበር፡፡ አቤልንም እስከ ወጣት ዕድሜው ድረስ አያቱ ወ/ሮ ወሰኔ አሳድጋዋለች፡፡ የአማርኛ ቋንቋንም አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ በዚያን ጊዜም ቢሆን የእነ አስቴር አወቀን፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ማህሙድ አህመድ፣ የሙላቱ አስታጥቄን፣ የጃዝና ብሉዝ ጨዋታዎችንና ሌሎችንም የአገር ቤት ሙዚቃዎች አዘውትረው ማዳመጥ ይወዱ ስለነበር የወጣቱ አቤል ድምፃዊነት የመጣው ከእሳቸው እንደሚሆን አሳማኝ ነው፡፡ ቀጥሎም የፖፕ ንጉሥ በሆነውን የማይክል ጃክሰን ሙዚቃ እየተሳበ በመምጣቱ ለፖፕ ሙዚቃ ልዩ ፍቅር አድሮበታል፡፡ አቤል በዚህ ሁኔታ ከአያቱ ከወ/ሮ ወሰኔ ጋር አብሮ ሙዚቃ እያዳመጠና ወደ ቤተ ክርስቲያንም እየሄደ አገልግሎት እየሰጠ በማደጉ አሁን ለደረሰበት የሙዚቃ ሕይወቱ ጉልህ ተፅዕኖ ፈጥሮበታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2007 በአሥራ ሰባት ዓመት ለጋ ዕድሜው ትምህርቱን አቋርጦ ሲወጣ አያቱ ወሰኔ አብራው ነበረች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 ደግሞ ወደ ሙዚቃው ዓለም ጭልጥ ብሎ የገባው ወጣቱ አቤል ዝናን በማትረፍ በአሜሪካና በአውሮፓ እየተዘዋወረ ኮንሰርቶችን አቅርቧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ስሙ በቢል ቦርድ ሰንጠረዥ በመውጣት ለግራሚ ሽልማት በቅቷል፡፡ ምንም እንኳ ስለራሱ መናገር እምብዛም የማይፈልገው አርቲስት አቤል ተስፋዬ ከሙዚቃው ሕይወቱ ባሻገር በበጎ አድራጎት ሥራም በመሳተፍ ይታወቃል፡፡ ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2014/15 ለዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቶሮንቶ የግዕዝ ትምህርት ተጠናክሮ እንዲሰጥ ሃምሳ ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ለግሷል፡፡ በተጨማሪም ለራያንሲያክረስት ፋውንዴሽ ለሕፃናት ሆስፒታል መርጃና በአትላንታ የጥቁሮች ሕይወት ማሻሻያ በሚል ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺሕ ዶላር አበርክቷል፡፡  

የአቤል የሙዚቃ ተሰጥኦ በጥረቱና በልምዱ የዳበረ ቢሆንም፣ የድምፅ ለዛውና የሙዚቃ ዝንባሌው ከአስተዳደጉና ከቤተሰቡ ጋር ይገናኛል፡፡ የአቤል ተፈራን አያት ጨምሮ የእናቱን አክስቶችና የአያቱን እህቶች የድምፅ ተሰጥኦ ምን ይመስል እንደነበር  በአሜሪካ የሚኖሩት የአቤል እናት አጎት ለዮናስ ዘገዬ (ዶ/ር) እንደዚህ ይገልጹታል፡፡  ‹‹የወሰኔ የዘፈን ዝንባሌ ምንጭ ከመርሐ ቤቴ ከሚወለዱት አያቷ ከወ/ሮ ወርቅነሽ ደስታ  ሲሆን፣ እሳቸው በዘመድ ሠርግና በበዓላት በቤት ውስጥ ሲዘፍኑና እስክስታ ሲወርዱ በማየቷ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከታኅሣሡ ግርግር ከ1953 ዓ.ም. በፊት በወ/ሮ ተቀባሽ ልጅ ሠርግ አጋጣሚ ላይ ወ/ሮ ወርቅነሽ ትንሹን ዮናስ ዘገዬን አስከትለው ሠርጉን ለመታደም ወደዚያው ሄዱ፡፡ በሠርጉ ላይ አያቱ ሲዘፍኑ በማየቱ እስከዛሬም ድረስ ያንን ግሩም ድምፃቸውን ያስታውሳል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ወ/ሮ የሺ አስፋው ለልጃቸው ሠርግ ወደ ፔንሲልቫንያ መጥተው ሳለ በሠርጉ ላይ ዘፍነው ነበር የተቀረፀው የቴፕ ክር አሁንም ድረስ እቤታቸው እንደሚገኝ ዮናስ (ዶ/ር) ይገልጻል፡፡ 

በኢትዮጵያዊ ቤተሰቦች ያለው ጠንካራ የቤተሰብ ቅርርብ በልጆች አስተዳደግ ላይና የሰብዕና ግንባታ ላይ የጎላ አበርክቶት ሲኖረው በተለይ ሴት አያቶች ለልጆቻቸው የሚያደርጉት እንክብካቤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ በዘመናዊ ዓለም ልጆችን በሞግዚት ማሳደግ የተለመደ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አያቶች የልጅ ልጆቻቸውን በማሳደግ የልጆቹን ጤንነት ለመጠበቅ፣ በሥነ ምግበር ለማነፅ ብዙ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ እንደ አባባሉ “አያት ጋር ያደገ ልጅ” እስኪባል ድረስ አያቶች የልጅ ልጅን አቅብጠው እንደሚያሳድጉ የታመነበት ነው፡፡ አቤል እስከ ወጣት ዕድሜው ሁለንተናዊ ሰብዕናውን ቀርፃ ባሳደገችው አያቱ ወ/ሮ ወሰኔ ኃይሌ እጅ መታነፁ ቁም ነገሮች በእሱ ሕይወትና ስኬት ዙሪያ የማንነት አሻራ እንዲያጠነጥን አስችሎታል፡፡ የልጆችን ተሰጥኦ ወላጅ ሲደግፍላቸው ልጆች ህልማቸውን ሊከተሉና ዕውን ያደርጋሉ፡፡ በተቃራኒው ቤተሰብ በልጆች የልጅነት ምኞትንና ፍላጎትን ካልደገፈ ልጆች ከተሰጧቸው ርቀው ድካም የተሞላበት ሕይወት ሊመሩ ይችላሉ፡፡ አቤል በወጣትነት ዕድሜው ይህንን የመሰለ ምኞቱን፣ ልምዱንና ፍላጎቱን ያልተወበት ምክንያት ህልሙን ራዕዩን ባለመከልከል ሲቻላቸውም በመደገፍ የረዳችው አያቱ ወ/ሮ ወሰኔ ኃይሌ ናት፡፡

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቤተሰብ ሙዚቃ እንደ አላስፈላጊ ብሎም ዓላማን የሚያሰናክል ተግባር ተደርጎ በሚታይበት ጊዜ ሙዚቀኛነትን እንደ ራዕይ ይዞ መቀጠልና ውጤታማ መሆን ከባድ መሆኑን ብዙ በሙያው ያለፉ ሙዚቀኞች ይናገራሉ፡፡ ወሰኔ ሙዚቃን እንደ ነውርና አላስፈላጊ አድርገው ከሚያዩ ሰዎች መካከል አልነበረችም፡፡ እሷም ብትሆን በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረችበት ወቅት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በእቴጌ መነን የልደት ቀን፣ በንጉሡ የዘውድ በዓል ቀን እንዲሁም ሚያዝያ 27 የነፃነት ቀን የትምህርት ቤቱ ልጃገረዶች ተሰብስበው እየዘመሩ ቤተ መንግሥት እንጉሡ ፊት ቀርበው ምሥጋና ይሰጡ ስለነበር ከሴት ዘማሪዎቹ መካከልም አንደኛው ነበረች፡፡ የእሷ ልምድና አመለካከት በምታሳድገው የልጅ ልጅ አቤል  ተስፋዬ ሕይወት ውስጥ እንዲንፀባረቅና የጥበብ ዝንባሌውን ከማንም ሰው በፊት በቀላሉ ለመገንዘብ አስችሏታል፡፡ በእርግጥ ይህች ሴት ለልጅ ልጇ ወጣት አቤል ተስፋዬ ምን ሚና ነበራት ብለን ስንፈትሽ ምላሹን አሁን አቤል የደረሰበት ደረጃ ይሆናል፡፡

አቤል ተስፋዬ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሚዲያ ከሰጠው ቃለ መጠይቅ በዩቲዩብ ከተለቀቀው (እ.ኤ.አ. በታኅሣሥ 8 ቀን 2018) ስለቤተሰቦቹ የሚከተለውን ብሏል፡- ‹‹ቤተሰቦቼ በተለይም እናቴ/አያቴ እኔን ስለአገሬ ባህልና ማንነት እንድገነዘብና እንድኮራ አድርጎኛል፡፡ በተለይም ትምህርት አቋርጬ ፍላጎቴ ወደ ሙዚቃ ማዘንበል ከልጅነት ዕድሜዬ አንስቶ ታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ዘፋኞች በማዜም ጭምር ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ በልጅነት ዕድሜዬ አንድ የምወደውን ነገር ሳደርግ ሁሉ እናቴ/አያቴ ደስ እያላት ታበረታታኝም ነበር፡፡››

ይህ በዓለም የዝና ቁንጮ የደረሰው አቤል ተስፋዬ ስሙ ከኢትዮጵያ ጋር የሚነሳው፣ ብሎም የአንጋፋ ኢትዮጵያውያን ዘፋኞችን ድምፅና ሙዚቃ በሙዚቃዎች መሀል እየጨመረ ኢትዮጵያን ለሌላው ዓለም የሚያስተዋውቀው በአያቱ ምክንያት ነው፡፡ ልጆች የሚወለዱት አንድ ውስን መንደር ሲሆን፣ ነገር ግን በህልማቸው በጥረታቸውና በበጎ አበርክቶቻቸው ዓለምን ይደርሳሉ፡፡ በማያውቋቸው መንደሮች ይኖራሉ፣ በብዙ በአካል በማያውቋቸው ሰዎች ልቦች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ይህ እንዲሆን የወላጆች ሚና ከፍተኛ ሲሆን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ አያቶችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው <[email protected]> ማግኘት ይቻላል፡፡   

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles