ሁለት መቶ ስድሳ ሦስት ሠዓሊያን እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ሥዕላቸውን ለግብይት የሚያቀርቡበት ‹‹ዘ ቢግ አርት ሴል›› የተሰኘ ዓመታዊ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ሊካሄድ መሆኑን ፕሮሎግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አስታወቀ፡፡
ተቋሙም ይህንን የገለጸው፣ ሐሙስ መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፣ በሥዕል ዓውደ ርዕዩም ከአምስት ሺሕ በላይ ጎብኚዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
የዋት ስዊት ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ራሔል ብርሃኔ እንደገለጹት፣ በሚቀጥለው ሳምንት የሰንበት ሁለት ቀናት በሒልተን አዲስ አበባ በሚካሄደው የሥዕል ዓውደ ርዕይ ላይ የሚሳተፉ ሠዓሊያን ሥዕላቸውን በፈለጉት ዋጋ መሸጥ ይችላሉ፡፡
በተለይ የሥዕል ዓውደ ርዕዩን ለየት የሚያደርገው ከጥበብ ሥራዎች በተጨማሪ ጥበብ አፍቃሪያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚገናኙባቸው የመጠጥና የምግብ ኮርነሮች ያሉት ሲሆን፣ ለልጆች ልዩ የወጫወቻ ሥፍራም እንደተዘጋጀላቸው ወ/ሮ ራሔል አስረድተዋል፡፡
የሥዕል ዝግጅቱም አርቲስቶች ሥራቸውን እንዲሸጡ ዕድል ከመስጠቱም በላይ ሥዕሎቹን ለመጎብኘት የሚታደሙት የሚከፍሉት የመግቢያ ሁለት መቶ ብር ለበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚውል አክለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ሠዓሊያን ብቻ ያቀርቡበት የነበረው ዓውደ ርዕይ ከሸመታ ጋር ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄደው ቅዳሜ መጋቢት 30 እና እሑድ ሚያዝያ 1 ቀን ነው፡፡