Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሴቶች እምብዛም በአመራርነት የማይገኙበት የፖለቲካ ተሳትፎ

ሴቶች እምብዛም በአመራርነት የማይገኙበት የፖለቲካ ተሳትፎ

ቀን:

በኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ በፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነትና ኃላፊነት ላይ ያላቸው ሚና እምብዛም አይደለም፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያላቸው የመምራት እድልም እንዲሁ፡፡

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና አመራርነት ማሳደግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ ያህሉን የሚይዙ ሴቶችን መወከል ነው ቢባልም፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከሚኒስቴሮች ድረስ በመሪነትና በውሳኔ ሰጪነት ብዙም ተሳትፎ የላቸውም፡፡

ይህ በእነዚህ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ባሉባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም ተመሳሳይ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ፓርቲዎች ውስጥም በሴት የሚመራ  የለም፡፡

ሴቶች በፖለቲካ መሳተፍ አለባቸው፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው ሊቀረፍላቸውና በአጠቃላይ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ሊረጋገጥ ይገባል በሚል የሚሠራው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)፣ ችግሩንና መፍትሔውን ያመላክታል፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም ግብአ ይሆናል ያለውን አመላካች  ጥናት አቅርቧል፡፡

ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ፓርቲያቸውን ወክለው በተመራጭነት እንዲወዳደሩ፣ የተመረጡ ሴቶች በተወከሉበት ምክር ቤትና በፖለቲካ ፓርቲያቸው የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረትና በቀጣይም ይህንን ለማጎልበት ይረዳ ዘንድ በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎና የሚያጋጥሙ ውስንነቶች ዙሪያ የተጠናውን ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ፆታ መምህርትና አማካሪ እመዛት መንገሻ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እመዛት (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በተለይ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እያደገ ነው፡፡ ከ20 ዓመታት ወዲህ ያለው ሲታይም፣ ከ45 በመቶ እስከ 48 በመቶ መራጮች ሴቶች ናቸው፡፡ በተመራጭ ደግሞ የዛሬ 20 ዓመት 2.4 በመቶ የነበረው አሁን ላይ 38.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህ በክልሎች 40 በመቶ ድረስ አድጓል፡፡

ሆኖም ሴቶች ፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፉ ሦስት መሰናክሎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው አባታዊ የሆነ ሥርዓት ሲሆን፣ ሁለተኛው የፖለቲካ ባህሉ ጨቋኝ መሆኑ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው እክል መሆናቸውን ጥናቱ ያሳያል፡፡

አባታዊ የሆነ ሥርዓትና የፖለቲካ ባህሉ ጨቋኝ መሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገለጽ ሲሆን፣ በራሱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚስተዋል እክልም አለ፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ወደ ፓርቲው ለማስገባትም ሆነ ከመጡ በኋላ የበላይ ለማድረግና ወደ ውሳኔ ሰጪነት ደረጃ ለማምጣት ብዙም ሲሠሩ አለመታየታቸውም  ሌላው ችግር ነው፡፡ ሴቶች በኅብረተሰቡ ደረጃ ያላቸው የ50 በመቶ ውክልናም  በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የለም፡፡

የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግና ሌሎች ፖሊሲዎች ሴቶች ለከለከሉም ሆነ መገለልን ሊገለሉ እንደማይገባ ያስቀምጣል፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይም አፈርማቲቭ አክሽን አለ፡፡ ነገር ግን ይህና ሌሎች ሕጎችና የፖሊሲ ማዕቀፎች ሲታዩ ትኩረት የሚያደርጉት ፆታ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሴቶች ተመሳሳይ ፍላጎት ችንዳላቸውና ተመሳሳይ ቦታ ላይ እንዳሉ አድርጎ እንዲታዩ የሚያደርግ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡ 

እንደ ዶ/ር እመዛት፣ በጥናቱ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶች ብዝኃነት ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ሴት ይህን ያህል፣ ወንድ ይህን ያህል ብሎ ከማስቀመጥ በዘለለ ሴቶች ምን ዓይነት የትምህርት ዝግጅት አላቸው፣ ከየትኛው ብሔር መጥተዋል፣ ሃይማኖታቸው፣ የሶሽዮ ኢኮኖሚክ ሁኔታቸው የሚለውን አያሳይም፡፡

በ2013 ዓ.ም. በነበረው ምርጫ የዕጩዎች ዝርዝር ላይ ሴቶች የመጡበትን ስብጥር ያሳያል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤቶች 21 በመቶ ሴቶች ሲሆኑ፣ 79 በመቶ ወንዶች መሆናቸው ያልተመጣጠነ እንደነበር ያሳያል፡፡

በየክልሎቹ የነበሩት የሴት ተወዳዳሪዎች ቁጥር ዝቅተኛው 14 በመቶ ሲሆን፣ ትልቁ 36 በመቶ ነው፡፡ በአፋር፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እስከ 20 በመቶ ሴት ተወዳዳሪ አቅርበው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ 21 በመቶ ሴት ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡

ከተወዳደሩት ሴቶች 59 በመቶ ያህሉ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ያላቸውና በማስተርስ ደረጃ የጨረሱ፣ የኮሌጅ ትምህርት የሌላቸው 22 በመቶ መሆናቸው ሴቶችን የወከሉት የተማሩት ክፍሎች ናቸው የማለውን ያሳያል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ትንሽ ዝቅ ቢልም፣ አብዛኛው ሴት ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ትምህርት ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

ይህ ሴቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከገቡም በኋላ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡና ፖለቲካው ውስጥ ሚና እንዲኖራቸው መማራቸው ቅድሚያ ያሰጣቸዋል፡፡ ይህም ሁሉም ሴቶች እኩል አይገለሉም የሚለውንና የተማሩ ሴቶች የተሻለ የፖለቲካ ተሳትፎ አላቸው የሚለውን እንደሚያሳይ ዶ/ር እመዛት ጠቁመዋል፡፡

ሴቶች ወደ ፖለቲካ እንዲመጡና ከመጡ በኋላ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የመጡበት ክልል፣ ያላቸው ማኅበራዊ ደረጃ (በተለይ የትምህርት ደረጃ)፣ ሃይማኖት፣ ዕድሜና የጋብቻም ይወስናቸዋል፡፡

በተለይ የተማሩ ሴቶች በራሳቸው ፈቃድ ወደ ፖለቲካ የሚመጡበት ሁኔታ ቢኖርም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ወደ ፓርቲያቸው በሚመለምሉበት ጊዜ ትምህርት፣ ሃይማኖት፣ ብሔር የሚያዩበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡

ሴቶች ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ከገቡ በኋላ ምን ታዝበዋል?

ሴቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከገቡ በኋላም የአባታዊ ዓይነት ልምድ ማየታቸውን አመላካች ጥናቱ አሳይቷል፡፡ አባታዊ አመለካከት በተለይ ወጣት ሴቶችን የማያበረታታ ዕድሜና ፆታ በአንድ ላይ ሲታይ ደግሞ፣ ወጣት ሴቶች ከፖለቲካ የሚገፉበት በሌላ በኩል ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠቀሙበት ሆኖ ታይቷል፡፡

የጋብቻ ሁኔታም ፖለቲካ ውስጥ ከገቡ በኋላ በፖለቲካው ለመዝለቅ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ወጣትና ያልወለዱ ከሆነ የተሻለ ተሳትፎ አላቸው፡፡ ያገቡና የወለዱ ሲሆኑ ፖለቲካን ጥለው እስኪወጡ የሚያደርስ የቤተሰብና የማኅበረሰብ ጫና እንደገጠማቸው ዶ/ር እመዛት ጠቁመዋል፡፡

ሴቶች ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከገቡ በኃላ የትምህርት ደረጃቸው ወደ ላይ እንዲወጡ አሊያም ባሉበት እንዲቀሩ ምክንያት ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራር ደረጃ ሆነው የተገኙትም ከፍተኛ ትምህርት የተማሩና በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ያሉ ናቸው፡፡ መማር በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳትፎአቸው እንዲያድግ ቢያደርግም፣ የሴቶችን ጉዳይ ለማንሳት የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩም ተስተውሏል፡፡

የኢኮኖሚ ደረጃ ሌላው በጥናቱ የታየ ሲሆን፣ የራሷ የገቢ ምንጭ የሌላት ሴት በተለይ ተቀጥራ የምተሠራ ሴት ችግር እንደሚገጥማት ታይቷል፡፡

ምን መደረግ አለበት?

እንደ ጥናቱ፣ ሴቶችን ከቁጥር በዘለለ ብቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ሁሉም ሴቶች አንድ ናቸው ብሎ በፆታ ከፍሎ የማስቀመጥ ልማድን መቀየርና ሴቶችን በትምህርት፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ደረጃዎች ማየት ያስፈልጋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ መንግሥት ሴቶችን የሚመለምሉት ከታች በመሆኑ፣ ሴቶችን የሚመለምሉ ሠራተኞች ሴቶች ሁሉ ተመሳሳይ ፍላጎትና ደረጃ  እንዳሌላቸው  እንዲረዱ መሰራት አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን እንዳሉት፣ ጥናቱ ብቻውን ለውጥ የማያመጣ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ችግሩን ዓይተው ውሳኔ ለሰጡባቸውና ችግሩን ለመቅረፍ ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ 

ጥናቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥርዓተ ፆታ ፣ የጥበቃና የፀረ ጥቃት ፖሊሲ እንዲኖራቸው፣ ካላቸው ደግሞ ወቅታዊ ሁኔታን መሠረት በማድረግ ማሻሻያ እንዲያደርጉ የሚያመለክት መሆኑንም ወ/ሮ ሳባ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሴቶች ጥያቄ ሙሉ በሙሉ እንዳልተፈታ፣ በተለያየ መንገድ የሴት ልጆች መብቶች እንደዚሁም የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳሉ፣ ይህንንም ለመቅረፍ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሚዲያ ጋር በተለይም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ አስመልክቶ በጥብቅ መሥራት እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡

በኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲ ስተዲስ (አይስኤስ) የተጠናው ጥናት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሴቶች ውክልና፣ አካታችነትና ብዝኃነት የሚል ሲሆን፣ ጥናቱ አሁን ያለው እክል ካልተፈታና ከአሁኑ የሚመለከታቸው አካላት ተወያይተው መፍትሔ ካላስቀመጡ ሴት ፖለቲከኞች፣ መራጮችና ለወደፊቱ በፖለቲካው ዘርፍ መሳተፍ የሚፈልጉ ሴት ወጣቶችን  ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ውጤታማ እንደማያደርገው አክለዋል፡፡

ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥና የሴቶች መብት እንዲጠበቅ እየሠራ የሚገኘው ኢሴማቅ፣ ባለፉት አራት ምርጫዎች የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ፣ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ፓርቲያቸውን ወክለው በተመራጨት እንዲወዳደሩ፣ የተመረጡ ሴቶች በተወከሉበት ምክር ቤት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ በተወከሉበት ምክር ቤት እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲያቸው ውስጥ የአመራር ሚና እንዲኖራቸው ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...