Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዋሊያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ደካማ አቋምና ውስብስብ ችግሮች

የዋሊያዎቹ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ደካማ አቋምና ውስብስብ ችግሮች

ቀን:

በአይቮሪኮስት ለሚከናወነው የ2023 አፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛና አራተኛ የምድብ ጨዋታውን ያከናወነው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ በሞሮኮ በምድብ አራት የሚገኘው የጊኒ ብሔራዊ ቡድንን ገጥሞ፣ በሁለቱ ምድብ ጨዋታ 5 ለ 2 ተሸንፎ ወደ አገር ቤት ተመልሷል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በሁለቱ የምድብ ጨዋታ ላይ ደካማ እንቅስቃሴ ማሳየቱን በበርካቶች ዘንድ አልተወደደም፡፡

በተለይ ዋሊያዎቹ በሦስተኛው የምድብ ጨዋታ ጊኒን ሲገጥሙ ያሳዩት እንቅስቃሴ በዋና አሠልጣኙ ውበቱ አባተ ጭምር የተተቸ ሆኗል፡፡ ቡድኑ በመጀመሪያ ጨዋታው ያሳየው ደካማ እንቅስቃሴ፣ በሁለተኛው ጨዋታው በተወሰነ ደረጃ መሻሻል ቢኖረውም ከሽንፈት ግን መዳን አልቻለም፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በማጣሪያ ጨዋታው ያሳየውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በርካታ አስተያየቶች ሲዘነዘሩ የሰነበቱ ሲሆን፣ ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባሰናዳው ጋዜጣዊ መግለጫ አሠልጣኝ ውበቱ  ማብራራያ ሰጥተዋል፡፡

ከጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረበላቸው አሠልጣኝ ውበቱ፣ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ቡድኑ ወደ ሞሮኮ ሲያመራ በውድድሩ ነጥብ በማግኘት በውድድሩ ለመቆየት አቋም እንደነበረው አሠልጣኝ ውበቱ አብራርተዋል፡፡

‹‹በሁለቱም ጨዋታ ላይ ያሰብነውን ውጤት ማሳካት አልቻልንም፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ጨዋታ እጅግ መጥፎ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረግንበት ነበር፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ችለናል፡፡ በቀጣይ በጣም የጠበበ ዕድል ነው ያለን፤›› በማለት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ በሚያከናውናቸው ጨዋታዎች ላይ ወጥ የሆነ አቋም ያለማሳየቱ ችግር፣ በፕሪሚየር ሊጉ በክለቦች የሚስተዋሉ የችግሮች ነፀብራቅ መሆኑም ተወስቷል፡፡

በዚህም በሊጉ ላይ ወጥ አቋም የሚያሳዩ ክለቦች ውስን መሆናቸው እንዲሁም ወጥ አቋም ያላቸውን ተጫዋቾች ማግኘትም አዳጋች እየሆነ መምጣቱን አሠልጣኙ ይናገራሉ፡፡ በተለይ ከተክለ ሰውነት፣ ከሥነ ልቦናና የመጡበት የተለመደ አካሄድ የብሔራዊ ቡድኑ ወጥ የሆነ አቋም እንዳይኖረውና የተፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ተፅዕኖ ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

ይህም በየውድድሩ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ሲጎዱ እንደነበርና ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላም የተጎዱ ተጫዋቾች መኖራቸውን ለችግሩ ማሳያ እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት ብሔራዊ ቡድኑ ምርጥ 11 ተጫዋቾችን ማጣቱን አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ባለፈው ሁለት ዓመታት የተለያዩ ውድድሮችን ጨዋታ ሲያደርግ ወጥ አቋም የሚያሳዩ ተጫዋቾች በማጣቱ፣ በኢትዮጵያ ሊግ የሚገኙትን በርካታ ተጫዋቾች ጥሪ እያደረገ ሲሞክር መክረሙ ተጠቅሷል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ያስተናገደውን ሽንፈት ተከትሎ፣ በቀጣይ ከማላዊና ከግብፅ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ስለሚኖረው የማጣሪያ ጨዋታ፣ ማድረግ ስለሚገባው ዝግጅት ተነስቷል፡፡ ቡድኑ የገጠመው ሽንፈት በዓለም በእግር ኳስ ጨዋታ ሊገጥም የሚችል መሆኑ የሚያነሱት አሠልጣኝ ውበቱ፣ በገጠማቸው ሽንፈት ተሸማቀው እንደማይቀሩና በተጫዋቾች ሥነ ልቦና ላይ ተሠርቶ ለቀሪ ጨዋታዎች ለመሰናዳት ማቀዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል አሠልጣኙ ዋሊያዎቹን ከተረከቡ በኋላ ‹‹ስኬታማ ነኝ ብለው ያስባሉ?›› ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ብሔራዊ ቡድኑ ትክክለኛ መደላደል ላይ እንደማይገኝና በርካታ ሊመቻቹ የሚገባቸው መሠረተ ልማቶች አለመኖራቸውን አብራርተዋል፡፡

‹‹ቡድኑን ተረክበን መሥራት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ፣ ከኒጀር ጋር የመጀመሪያ ጨዋታ ክስ ካደረግንበት ድረስ የተለያዩ ሒደቶችን አልፈናል፤›› ሲሉ አሠልጣኝ ውበቱ አስረድተዋል፡፡

አሠልጣኙ ባለፈው ሁለት ዓመታት በአፍሪካ ዋንጫና በቻን ውድድር ውስጥ መገኘት በራሱ ስኬት እንደሆነ ያስረዱት ዋና አሠልጣኙ፣ በአንፃሩ በውድድሩ የተስተዋሉት ስህተቶችን መታረምና መሻሻል እንደሚገባቸው እናምናለን ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑን ለማሠልጠን ከተረኩቡ ሁለት ዓመታት የሞላቸው አሠልጣኝ ውበቱ፣ ‹‹ከኃላፊነታቸው ይለቃሉ ወይስ አይለቁም?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፣ የሁለት ዓመታት ኮንትራት መፈራረማቸውን አስታውሰው፣ የመልቀቅ ውሳኔ በእሳቸው ፍላጎት ብቻ የሚወሰን አለመሆኑንና ከቀጠራቸው አካል ጋር ተወያይተውና ተማክረው የሚወሰን እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ብሔራዊው ቡድኑ ከጊኒ ጋር ባደረገው ጨዋታ፣ የተቀያሪ ወንበር ላይ የነበሩት ተጫዋቾች፣ ቡድኑ ላይ ግብ ሲቆጠር ሲስቁ መስተዋላቸውን ተከትሎ፣ ተጫዋቾቹ የአገራቸው ሰንደቅ ዓላማን አንግበው እንደመሠለፋቸውና አገራቸውን ከመውደድና አለመውደድ ጋር ተያይዞ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡

አሠልጣኙ ምላሽ ሲሰጡም፣ በጨዋታው ወቅት እሳቸው ጨዋታውን ለመከታተል ተቀያሪ ወንበር ላይ ለተቀመጡት ተጫዋቾች ጀርባቸውን ሰጥተው ጨዋታውን ሲመለከቱ እንደነበር አውስተው፣ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ ቅጽበታዊ ክስተት እንደሆነና አገርን ከመውደድና ካለመውደድ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹አገርን መውደድ በአንድ ጀምበር የሚፈጠር ነገር አይደለም፡፡ ተጨዋቾችን ከሥር መሠረቱ ሲመጡ እንዲሁም በክለብ ውስጥ እያለፉ ሲሄዱ የሚገነባ ነው፤›› በማለት አሠልጣኙ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ቡድኑ ላይ ጎል ሲቆጠር ወይም የቡድኑ እንቅስቃሴ ደካማ ሲሆን የሚደሰት ሰው አብሮን ነበር ብዬ ለማሰብ ይከብደኛል፡፡ በቡድን ውስጥ አይደለም በክስተቱ የሚደሰት ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም፡፡ ይህ የእኔ ስሜት ነው፡፡ የግለሰብን ስሜት ማወቅ ያስቸግራል፤›› ሲሉ አሠልጣኝ ውበቱ ስለሁኔታው ገልጸዋል፡፡

አሠልጣኙ ሲያክሉም፣ ማንኛውም ተጫዋች በብሔራዊ ቡድን ሽንፈት የሚስቅ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ለብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ጥልቅ ፍላጎት ያላቸው ተጫዋቾች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

ዋሊያዎቹን ለማሠልጠን ኃላፊነት የተረከቡት አሠልጣኝ ውበቱ፣ በአጠቃላይ 35 ጨዋታዎችን ያደረጉ ሲሆን፣ 10ሩ ጨዋታዎች የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም 25 የውድድር መርሐ ግብር ጨዋታዎች ሲሆኑ፣ ዋሊያዎቹ ማሸነፍ የቻሉት 6 ጨዋታዎችን ብቻ ነው፡፡

በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ አራት ከግብፅ፣ ጊኒና ማላዊ ጋር የተደለደለው የዋሊያዎቹ ስብስብ፣ በ3 ነጥብና በግብ ተበልጦ በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከግብፅና ከማላዊ ጋር ቀሪ የምድብ ጨዋታዎች ይቀሩታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...