Wednesday, May 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የቡና አፈላል ወግና ሥርዓቱን በዓለም አቀፍ መድረክ የማብቃት ትልም

የኢትዮጵያ ባህል፣ እሴትና ወግ ከሚያንፀባርቁ ነገሮች መካከል የቡና አፈላል ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡ በተለይም በበዓላት ወቅትም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት ዘመድ ከዘመድ ጎረቤት ከጎረቤት ጋር ትስስር የሚፈጥሩበትና እርስ በርስ ሐሳባቸውን የሚወያዩበት የዕለት ከዕለት መገለጫ መሆኑ ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነውን ይህንን የቡና ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዋርካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እየሠራ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ ሰአዳ ሙስጠፋ የማኅበሩ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የማኅበሩን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዋርካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንዴት ተመሠረተ?

ወ/ሮ ሰአዳ፡- ዋርካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተመሠረተው በዚህ ዓመት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ሥራ ለመሥራት የዛሬ ሁለት ዓመት ጥናትና የተለያዩ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ተቋሙም የተመሠረተበት ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ የቡና ባህላዊ እሴቶች ከማኅበረሰባዊ ጥቅም አኳያ በመቃኘት አዎንታዊ የአገር ግንባታ ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ነው፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላል እሴቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ለመገንባት ትልቁን ድርሻ ይወጣል፡፡ በባህላዊ የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት እሴቶች ዙሪያ በሚገኘው ማኅበረሰባዊና አገራዊ ጥቅም ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ለመሆን ዘርፈ ብዙ ሚናዎችን ይጫወታል፡፡ በሌላ በኩል የቡና ባህል እሴቶች ከሚያበረክቱት ጠንካራ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር በማስተሳሰር ለአገር ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ ለማበርከት ሰፊ ሥራዎችን ይሠራል፡፡

      ከሁሉም በላይ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላል ሥርዓት ግንዛቤ መፍጠርና ባህላዊ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሻገር ያላለሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡ በተለይም ‹‹የኢትዮጵያ የቡና ባህል ቀን ፌስቲቫል›› በሚል የአገሪቱን የቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት በሰፊው ለማስተዋወቅና በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንዲሁም በየዓመቱ የሚከበር ዓመታዊ በዓል ሆኖ እንዲቀጥል ኅዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ለመሥራት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የዚህ በዓል መከበርም ለቱሪስት ዘርፍ፣ ለአገር ገጽታ ግንባታና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ይኼም ከሆነ የተለያዩ ክልሎችን የቡና አፈላል ባህልን ማሳየትና ማስተዋወቅ ከተቻለ ዩኔስኮ ላይ ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ እንደዚህ ከሆነ የኢትዮጵያ ባህል ወደ ፊት አንድ ዕርምጃ ከፍ እንዲል ተቋማችን የበኩሉን ይወጣል፡፡  

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል?

ወ/ሮ ሰአዳ፡- ዋርካ ኮፊ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ሰፊ እነቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በርከት ያሉ ባህሎችና እሴቶች ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን ይኼንን የቡና አፈላል ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅም በላይ ለዓለም ለማሳየት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ ለመሥራት የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ የቡና አፈላል ሥርዓትን ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በዓሉንም ዓመታዊ ከማድረግ በዘለለ ክልሎች እርስ በርስ የቡና አፈላል ሥርዓታቸውን ልምድ የሚለዋውጡበት መድረክ ይፈጠራል፡፡

እንደዚህ ከሆነ የኢትዮጰያ የቡና ባህል እሴቶች ከሚያበረክቱት ጠንካራ የሆነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር በማስተሳሰር የአገር ገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ ማስፋት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ የቡና አፈላል ሥርዓትንም ለዓለም ለማስተዋወቅና የቡና ምርታችንን ተደራሽነትን ለማስፋት ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ ይሆናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ማሳካት ከተቻለ የኢትዮጵያ የቡና አፈላል ሥርዓትን ዩኔስኮ ላይ ማስመዝገብ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች አንፃር የተለያዩ የቡና ምርቶች ባለቤት መሆኗ ቢታወቅም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷ ላይ ግን ክፍተቶች እንዳሉ ይወሳል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ተቋሙ ምን ይሠራል?

ወ/ሮ ሰአዳ፡- እንዳልከው ኢትዮጵያ የብዙ ቡና ምርት ባለቤት ናት፡፡ ይሁን እንጂ ያላትን ምርቶች ከማስተዋወቅና ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ከማግኘት አንፃር ሰፊ ክፍተቶች አሉባት፡፡ እንደ አገር ያሉንን ነገሮች ዋጋ ባለመስጠታችን የተነሳ የቡና አፈላል ሥርዓታችን ዩኔስኮ ላይ እንዳይመዘገብ አድርጎታል፡፡ በተለይ ክልሎች እርስ በርስ የቡና አፈላል ሥርዓታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ አለመኖሩ ዘርፉ ላይ ክፍተት ፈጥሮብናል፡፡ በተቋሙም በቀጣይ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና መፍትሔ ለመስጠት ሰፊ ሥራ የሚሠራ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ከጥንት ጀምሮ የነበረ የቡና አፈላል ሥርዓታችንን ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ትልቅ ሚና የምንጫወት ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ የቡና ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስታወቅ ተቋሙ በየወሩ ፌስቲቫሎችን ያዘጋጃል፡፡ ይኼ ከሆነም የኢትዮጵያ የቡና ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበት መንገድ ይፈጠራል፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ወ/ሮ ሰአዳ፡- በእርግጥ የመጀመርያ የቡና ማፍላት ፌስቲቫል ቅዳሜ መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል አካሂደናል፡፡ ይኼንንም ፌስቲቫል ዓመታዊ በዓል በማድረግና ለቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የበኩላችንን እየተወጣን ይገኛል፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልን የቡና ማፍላት ሥርዓታችንን ዩኔስኮ ላይ የምናስመዘግብ ይሆናል፡፡ የቡና ማፍላት ሥርዓታችንም ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አምስተኛ ሆኖ ከተመዘገበ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ወርኃዊ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ይኼንንም ማድረግ ከቻልን ቡናችንን ኤክስፖርት ከማድረግ ውጭ የአፈላል ሥርዓታችንን ለዓለም የምናስተዋውቅበት መንገድ ይፈጠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ በየዓመቱ የቡና አፈላል ሥርዓት ፌስቲቫል እንደሚያካሂድ ነግረውናል፡፡ በፌስቲቫሉ የሚሳተፉትን እንዴት ትመርጣላችሁ?

ወ/ሮ ሰአዳ፡- እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መናኸሪያ ናት፡፡ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው የሆነ የቡና አፈላል ሥርዓት አላቸው፡፡ ነገር ግን የቡና አፈላል ሥርዓታቸው ምን እንደሚመስል አብዛኞቹ አያውቁም፡፡ ይኼንን ለማሳየት ፌስቲቫል ማካሄድ ትልቅ አማራጭ በመሆኑ ፌስቲቫሉን ማካሄድ ችለናል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ያካሄድነው ፌስቲቫል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን መረጣ ያከናወነው ከአዲስ አበባ ነው፡፡ በአዲስ አበባም በአሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የተለያዩ ባህሎችን ወክለው የሚሠሩ ተቋሞችን በማግኘታችን አጋጣሚውን በቀላሉ ለመጠቀም ችለናል፡፡ በቀጣይም ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የራሳቸውን ባህል የሚያንፀባርቁ የአፈላል ሥርዓት የሚከተሉ ሰዎችን የምንመርጥ ይሆናል፡፡ ይህንንም ማድረግ ከተቻለ ሰዎች እርስ በርስ የሚተዋወቁበት መንገድ መፍጠር ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

አማራ ኢንሹራንስ ኩባንያን በሁለት ቢሊዮን ብር ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

አማራ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ሊቋቋም መሆኑ...