Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከደቡብ እስከ ትግራይ የዘለቀው የባህላዊ ቅርሶች ገጽታ ስነዳ

ከደቡብ እስከ ትግራይ የዘለቀው የባህላዊ ቅርሶች ገጽታ ስነዳ

ቀን:

በመንግሥቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ አገላለጽ፣ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጅብል ካልቸራል ሄሪቴጅ) የሕዝብን ያለፈ ሕይወት በአሁን በኩል አድርገው ከመጪው ጋር በማገናኘት የማንነትና የባለቤትነት ስሜትን ስለሚሰጡ እጅጉን አስፈላጊ ናቸው፡፡ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታም ያላቸው ከመሆኑም ባለፈ፣ ማኅበራዊ ትስስርን የሚረዱ፣ ግለሰቦች የአንድ ማኅበረሰብና በአጠቃላይ የኅብረተሰቡ አካል እንዲሆኑ እንዲሰማቸው ይረዳል፡፡

ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል የቃል (አፋዊ) ታሪክ ይገኝበታል፡፡ ከግለሰቦችና ከቡድኖች የሚገኙ ታሪካዊ መረጃዎችን ከመሰብሰብ ባለፈ፣ ተጠብቀው እንዲቆዩ ወጎችና ልምዶች፣ የጋራ ዕውቀቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ይደረግበታል፡፡

ዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የሚመዘገቡብት፣ የሚሰናዱበት ኢንቬንቶሪ ማኑዋል (መመርያ) ለአባል አገሮቹ አስተላልፏል፡፡

ከዚህ አኳያ የዩኔስኮ አባል የሆነቸው ኢትዮጵያ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን በመመዝገብ ላይ ትገኛለች፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (አሁን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን) አማካይነት ባለፉት አሥር ዓመታት የ76 ብሔረሰቦች የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን ቆጠራና ምዝገባ (ኢንቬንቶሪ) አካሂዷል፡፡

ኢንቬንቶሪው በአምስቱም የኢንታንጅብል ባህላዊ ቅርሶች ምድብ (አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎች፣ አገረሰባዊ ትውን ጥበባት፣ ማኅበራት ሥነ ሥርዓት፣ ክዋኔና ፌስቲቫል፣ ስለተፈጥሮና ዓለም ዕውቅና ትግባራና ትውፊታዊ የዕደ ጥበብ ዕውቀቶችና ክህሎቶች) ውስጥ የሚመደቡ ልዩ ልዩ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን ያካተተ ነው፡፡

ምዝገባና ስነዳ

የቅርስ ባለሥልጣን የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ማድረግ የጀመረው በ2002 ዓ.ም. ሲሆን፣ የመጀመርያው ቅጽ መጽሐፍ ትኩረትም በደቡብ ክልል በሚገኙ ብሔረሰቦች ላይ ነው፡፡ በተከታታይ ዓመታት አንትሮፖሎጂና የፎክሎር ባለሙያዎች በተለያዩ ክፍላተ አገር ባደረጉት የመስክ ጥናቶች መሠረትም፣ በተከታታይ ዓመታት 73 ብሔረሰቦች የሚመለከቱ ባህላዊ ቅርሶች በስምንት ቅጽ በመጻሕፍት ታትመዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኙ የሦስት ብሔረሰቦች (ትግራይ፣ ኢሮብ፣ ኩናማ) የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን የሚዳስሰው ቅጽ 9 መጽሐፍ የታተመው በ2012 ዓ.ም. ነው፡፡

በኅትመቱ ቀዳሚ ቃል እንደተገለጸው፣ ኢንቬንቶሪው የተከናወነው የቅርሱ ከዋኞች ወደሚኖሩበት የተለያዩ ወረዳዎች በመሄድ፣ የመጀመርያ ደረጃ መረጃ በማሰባሰብና በኢንቬንቶሪ ማኑዋሉ መሠረት በማጠናቀር ነው፡፡

ከክልሉ ስፋት አንፃርም በተለያዩ ዞኖች ውስጥ የሚከወኑ ተመሳሳይ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችም ተካተዋል፡፡  ቅርሶቹ የሚመሳሰሉ ቢሆንም፣ አንዳንዶቹ  ከቦታ ቦታ መጠነኛ ልዩነቶች የሚስተዋሉባቸው ሆነው ሲገኙ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያላቸውን ገጽታ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡

የቅርስ ምዝገባ የመጀመርያው ደረጃ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ተግባር ነው የሚለው ባለሥልጣኑ፣ በመጽሐፉ የተካተቱ ቅርሶች፣ ባህላዊ ትውፊቶች የሕዝቡን ማንነት፣ ባህልና ትውፊት አጠቃላይ የያዙ በመሆናቸው ስለብሔረሰቡ ይበልጥ ለማወቅና ለመረዳት ይረዳል ብሏል፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለቅርሶቹ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ቅርሶቹ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኙ ከማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በተለይ ደግሞ ክዋኔያቸው እየተዳከመ የመጡና የመጥፋት ሥጋት የተጋረጠባቸው ቅርሶች በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር የኅትመቱ ፋይዳ የጎላ በመሆኑ፣ በፍጥነት የክብካቤ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶች ለይቶ ወደ ተግባር ለመግባት ይረዳል፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ኢንቬንቶሪ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬት በምዝገባ ማኑዋል በመታገዝ፣ የቅርስ ምዝገባ ሥራን ወጥ በሆነ መንገድ ሲያከናውን መዝለቁን፣ የሥራ ክፍሉ የ76 ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ላይ ኢንቬንቶሪ ማከናወኑን የኅትመት ውጤቶቹም ለኅብረተሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ ማድረጉን ገልጿል፡፡

የትግራይ፣ የኢሮብና የኩናማ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን የያዘው ቅጽ 9 መጽሐፍ ተዘጋጅቶ መታተሙን አስመልክቶ፣ በወቅቱ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሙሉጌታ ፍሥሐ (ዶ/ር)፣ ለኅትመቱ በጻፉት ቀዳሚ ቃል ሥራው የየብሔረሰቡን ማንነት፣ ባህልና ትውፊት አካቶ የያዘ በመሆኑ ስለብሔረሰቦቹ ይበልጥ ለማወቅና ለመረዳት እንደሚረዳ፣ የቅርሱ ባለቤት በሆነው ኅብረተሰብ ዘንድም ስለቅርሶቹ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምርና ቅርሶቹ ትኩረት እንዲያገኙም ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ትግበራቸው እየተዳከመ የመጡና የመጥፋት ሥጋት የተጋረጠባቸው የብሔረሰቡ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች፣ በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት አግኝተው ተጨማሪ ጥናቶች እንዲካሄዱባቸው፣ የቅርስ ክብካቤ ሥራ እንዲከናወንባቸውና ለምተው የቱሪዝም መስህብ አካል እንዲሆኑ ይረዳል፡፡

ሌላው ደግሞ የዚህ መጽሐፍ ታትሞ መሠራጨት አንደኛው ብሔረሰብ ስለሌላኛው ብሔረሰብ አጠቃላይ ባህላዊ እሴቶች መረጃ እንዲያገኝና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር የሚረዳ በመሆኑ በሕዝቦች መካከል ያለውን የባህል ውይይት፣ ተግባቦትና መማማር ከፍ ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡

የቅርስ ምዝገባ ሥራው ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በጋራ የሚከናወን ተግባር መሆኑን ያመለከቱት፣ ኅትመቱ በተዘጋጀበት ወቅት የቅርስ ኢንቬንቶሪ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ደሳለኝ አበባው፣ በ2002 ዓ.ም. በተዘጋጀው የኢንቬንቶሪ ማንዋል በመታገዝ ኢንታንጅብል ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ሲከናወን መቆቱየንና የምዝገባው ውጤትም ባለሥልጣኑ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አሳትሞ ማሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ከቅርስ ምዝገባ ሥራ አስቀድሞ ከክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ የቅርስ ባለሙያዎች ስለቅርስ ምዝገባ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ከሥልጠና በኋላ የኢቬንቶሪ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ኢንቬንቶሪው የተከናወነው በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ ሲሆን የማዕከላዊ፣ የሰሜን ምዕራብ፣ ምሥራቃዊ፣ ደቡብ ምሥራቅ፣ ደቡባዊ ዞኖችና የመቐለ ከተማ ይገኙበታል፡፡  

ሆኖም ግን ይህ የኢንቬንተሪው ውጤት ከሀብትና የጊዜ ውስንነት አኳያ ሁሉንም የትግራይ  የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች አካቶ አልያዘም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይህን የኢንቬንቶሪ ኅትመትን መሠረት በማድረግ የየአካባቢው ማንነት መገለጫ የሆኑና ያልተካተቱ ቅርሶችን በመለየት መመዝገብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...