በገብርኤላ አብረሃም (በብሄራዊ መታወቂያ ጽሕፈት ቤት ፖሊሲ አድቫዘር)
በዓለም ዙሪያ አንድ ቢሊዮን ሰዎች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ማስረጃ እንደሌላቸውና ከእነዚህም ውስጥ 81 በመቶ የሚሆኑት ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል የሚገኙ እንደሆኑ የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2018 ያወጣው ጥናት ያሳያል። ጥናቱ እንደሚያመላክተው በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች መሠረታዊ ከሆኑ የጤና፣ የትምህርት፣ የማኅበራዊ ጥበቃና የፋይናንስ አገልግሎቶች ይገለላሉ። የተጠናከረ የመታወቂያ ሥርዓት አለመኖር ዜጎችን ብቻ ሳይሆን፣ በተለያየ ምክንያት ከአገራቸው ተሰደው ወይም ፈልሰው በሌሎች አገሮች የሚገኙ ሰዎች፣ ከስደት ተመላሾች፣ ዜግነት አልባ ሰዎች፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች አገልግሎት እንዳያገኙ ተግዳሮት ነው።
በሌላ በኩል መንግሥት ለዜጎች በሚዘረጋቸው የማኅበራዊ ጥበቃ መርሐ ግብሮች ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ እንዲሁም መንግሥት የሚሰጣቸውን ሌሎች አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ ሲያደርግ እርስ በርሱ መናበብ የሚችል አገልግሎት መስጠት እንዲችል የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መሠረታዊ ነው። ይህን ትግበራ ለማረጋገጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ተቋቁም የሙከራ ምዝገባ፣ የሕግ ማርቀቅና ተቋማዊ ዝግጅቶችን የማጠናከር ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በዚህ ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የዲጂታል መታወቂያ አተገባበርን አስመልክቶ ስለምዝገባ፣ የማረጋገጥ አግልግሎት፣ ተቋማዊ ቅርፅ ስለማዘጋጀት፣ ስለመረጃ ደኅንነት (Data Security)፣ ስለመረጃ ግላዊነት አጠባበቅ (Data Privacy Protection)፣ እንዲሁም የወንጀል ተጠያቂነት ዝርዝር አንቀጾችን ያካተተ ሕግ ነው። አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል። እንዲሁም አዋጁ ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት ባገኙት ንድፍ (Design)፣ አካታችነት (Inclusion) እና አስተዳደር (Governance) መርሆች የተቃኘ ሕግ ነው። የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ሦስት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት አሉት፡፡ እነዚህም ነዋሪዎች፣ ተጠቃሚዎች፣ የማረጋገጥ አገልግሎት ሰጪዎችና መንግሥት ናቸው።
ነዋሪዎች
የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣ ምዝገባና የማረጋገጥ አገልግሎትን በተመለከተ በተመዝጋቢዎች ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ምዝገባ እንደሚከናወን አዋጁ የሚደነግግ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ተመዝጋቢዎች ከተመዘገቡ በኋላ መረጃዎቻቸውን በዘላቂነት መቆለፍ ቢፈልጉ ይህንንም አማራጭ ያካተተ ነው። ማንኛውም ተመዝጋቢ ከመመዝገቡ በፊት የፈቃድ መስጫ ፎርም መሙላት አለበት። በፈቃድ መስጫ ሰነዱ ላይ ተመዝጋቢው የሚሰጣቸው መረጃዎች ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ፣ እንዲሁም ምዝገባው ሙሉ ፈቃድ ላይ የተመሠረት ስለመሆኑ ይገልጻል። ተመዝጋቢዎች ሲመዘገቡ ብቻ ሳይሆን የማረጋገጥ አገልግሎት ሲያገኙም በሙሉ ነፃ ፈቃዳቸው ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ አዋጁ ይደነግጋል።
ተመዝጋቢዎች በምዝገባ ወቅት ባዮሜትሪክና ዴሞግራፊያዊ መረጃ መስጠት አለባቸው። በዚህም አግባብ የአሥር ጣት አሻራ፣ የዓይን አሻራና የተመዝጋቢው ፎቶ እንደ ባዮሜትሪክ መረጃ የሚወሰድ ሲሆን ሙሉ ስም፣ የትውልድ ቀን፣ የመኖሪያ አድራሻ፣ ዜግነትና ፆታ እንደ ዴሞግራፊክ መረጃ ይወሰዳል። አካታችነትን ለማረጋገጥ ዲጂታል መታወቂያ የሚሰጠው ለዜጎች ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎችም ጭምር በመሆኑ ስደተኞች፣ ፍልሰተኞች፣ የውጭ አገር ዜጋ ሠራተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት አላቸው። በተለያየ ምክንያት የጣት አሻራቸው የጠፋ ወይም አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአማራጭ የዓይን አሻራ በመስጠት መመዝገብ ይችላሉ፣ በዚህም አካታችንነትን ማረጋገጥ ይቻላል።
በምዝገባ ወቅት ተመዝጋቢዎች ማንኛውንም ማንነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብ መመዝገብ ይችላሉ። ይህም መታወቂያ፣ ፓስፖርት፣ የትውልደ ኢትዮጵያዊ ካርድ (Yellow Card)፣ የልደት ምስክር ወረቀት፣ የትምህርት ማስረጃ፣ የሥራ ፈቃድን ይጨምራል። ተመዝጋቢዎች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ሰነድ ማቅረብ ካልቻሉ ለዲጂታል መታወቂያ የተመዘገበና ልዩ ቁጥር ያለው ግለሰብ በሚሰጠው ምስክርነት መሠረት ሊመዘገብ ይችላል። በመሆኑም በተለያየ ምክንያት ማስረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ግለሰቦች ከመታወቂያ አሰጣጥ አገልግሎት እንዳይገለሉ በምስክር አማካይነት የሚደረግ ምዝገባ ያግዛል። በተጨማሪም የቅድመ ምዝገባ አገልግሎት በፕሮግራሙ በበይነ መረብ (register.fayda.et) መመዝገብ ይቻላል።
ተመዝጋቢዎች መረጃዎቻቸው ወደ ማዕከላዊ ዳታቤዝ ከገቡ በኋላ ባለ 12 አኃዝ ልዩ ቁጥር በስልክ መልዕክት የሚላክላቸው ሲሆን፣ እያንዳንዱ ተመዝጋቢ ያለው ቁጥር ከሌላ ተመዝጋቢ የተለየ ነው። ይህም አንዴ ጥቅም ላይ ከዋለ ለሕይወት ዘመን የማይቀየርና ደግሞ ጥቅም ላይ የሚውል ልዩ ቁጥር ነው። እንደ ግብር ከፋይ (TIN) እና መሰል መለያዎችም በልዩነት አንድ ለአንድ (1:1) ተያያዥ ይሆናል። ከስልክ መልዕክት በተጨማሪም በስልክ አፕልኬሽንና በመታወቂያ ካርድ ታትሞ ለዜጎችና ነዋሪዎች ለማቅረብ እየተሠራ ነው።
ተጠቃሚዎች
በዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ተጠቃሚዎች የሚባሉት በሥርዓቱ የተመዘገቡ ግለሰቦች ሳይሆኑ፣ ሥርዓቱን በመጠቀም ለደንበኞቻቸው ወይም ለተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ናቸው። የፋይናንስ ተቋማት በተለይም ባንኮችና የብድርና ቁጠባ ተቋማት፣ እንደ ሴፍቲኔት የመሳሰሉ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የመንግሥት ተቋማትም ሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች በመባል ይታወቃሉ። በተለይ በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ተጠቃሚዎች ደንበኞችን ወደ አገልግሎታቸው ለመመዝገብ በሚያደርጉት ጥረት የደንበኛህን ዕወቅ (KYC) ግዴታ ያለባቸው በመሆኑ፣ ይህን ግዴታቸውን ለመወጣትም ሆነ አስቀድሞ ለተመዘገቡ ደንበኞቻቸው ከማጭበርበር የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።
የማረጋገጥ አገልግሎት ሰጪዎች
አዋጁ ዲጂታል መታወቂያ የአንድን ግለሰብ ማንነት አረጋግጦ አገልግሎት ለመስጠት በራሱ ብቁና ሕጋዊ ማስረጃ መሆኑን ይደነግጋል። በመሆኑም ተጠቃሚዎች የተቀላጠፈ፣ አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ፣ ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የማረጋገጥ አገልግሎት በሚሰጡ የግል ድርጅቶች አማካይነት የማረጋገጥ አገልግሎት (Authentication Service) ሊሰጥ ይችላል። የማረጋገጥ አገግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በመንግሥት ዕውቅና የተሰጣቸው መሆን ይኖርባቸዋል። አዋጁ እነዚህ የማረጋገጥ አገልግሎት እንዲሰጡ ዕውቅና የተሰጣቸው አካላት የግለሰብ መረጃ ደኅንነትን የመጠበቅ፣ እንዲሁም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ብቻ የማጋራት ኃላፊነት አለባቸው።
መንግሥት
መንግሥት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መሪና ተቆጣጣሪ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚም ጭምር ነው። መንግሥት ለተጠቃሚ ዜጎች ሴፍቲኔትን የመሳሰሉ የማኅበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶች ሲሰጥ፣ ወደ ተጠቃሚዎች የሚተላለፈው ገንዘብ ሐሰተኛ የባንክ ሒሳቦችን በመክፈት ከመመዝበር በተጠበቀ መንገድ መተላለፍ እንዲችል የማረጋገጥ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል መንግሥት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ግንባታ አንቀሳቃሽ ነው። ምዝገባ በማከናወንና ሌሎች አካላት ምዝገባ እንዲያከናውኑ ፈቃድ በመስጠት፣ የባዮሜትሪክና የዴሞግራፊክ መረጃዎችን በማዕከላዊ ቋት ውስጥ በማስቀመጥ፣ ደኅንነቱን በማረጋገጥ፣ የማረጋገጥ አገልግሎት ለሚሰጡ አካላት ፈቃድ በመስጠት፣ የግል መረጃ ደኅንነት ጥበቃን የማረጋገጥ ኃላፊነት በመንግሥት ደረጃ በሚቋቋም ተቋም እንደሚከናወን አዋጁ ይደነግጋል። በተጨማሪም ተቋሙ የቅሬታን አቀራረብ ሥርዓት መዘርጋትና ቅሬታዎችን ማስተናገድ እንዳለበት ይደነግጋል። በተቋሙ ቅሬታ አቀራረብና አፈታት ቅር የተሰኘ ተገልጋይ ቅሬታውን ለፍርድ ቤት በማቅረብ ፍትሕ ማግኘት እንደሚችል አዋጁ ይጠቅሳል።
መደምደሚያ
የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ከዓለም አቀፍ በተለይም ከህንድ ልምድ በመማር የተዘረጋ ሥርዓት ሲሆን የዜጎችን የመታወቅ ሰብዓዊ መብት የሚያረጋግጥ፣ ተጠቃሚ አካላትን ከማጭበርበርና ከምዝበራ የሚጠብቅ፣ ጊዜና ሀብት ቆጣቢ፣ እንዲሁም አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ የመታወቂያ ሥርዓት ለመዘርጋት የፀደቀ አዋጅ ነው። የመታወቂያ ሥርዓቱ አዋጅ የተመዝጋቢዎችን ሙሉ ፈቃድ መሠረት ያደረገ፣ የግል መረጃዎችን ለመጠበቅ ገደቦችንና ክልከላዎችን ያስቀመጠ ነው።
የተመዝጋቢዎችን ማንኛውም መረጃ የሚይዙ አካላት መረጃውን ለሌላ ማንኛውም አካል ማስተላለፍም ሆነ፣ ተመዝጋቢው ከተመዘገበበትና የማረጋገጥ አገልግሎትን ከጠየቀበት ዓላማ ውጪ ለሌላ ማንኛውም ዓላማ መጠቀም አይችሉም። መዝጋቢ አካላት በአዋጁ ከተቀመጡት መረጃዎች ውጪ ማንኛውንም መረጃ መሰብሰብ አይችሉም፡፡ ይህም ተመዝጋቢዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በጤና ሁኔታ መገለል እንዳይደርስባቸው ይከላከላል። ለዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊ ከሆኑት መረጃዎች ውጪ የሰበሰበ አካል፣ እንዲሁም የተመዝጋቢዎችን መረጃ ከሕግ አግባብ ውጪ ለሦስተኛ አካል አሳልፎ የሰጠ አካል በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን አዋጁ ይደነግጋል።
የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ለአገሪቱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ እንዲሁም ለአሥር ዓመቱ የመንግሥት የልማት ዕቅድ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በአግባቡ የተተገበረ ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ላይ እስከ ስድስት በመቶ የሚደርስ ጭማሪ ያለው አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ በዚህም ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብቷንና የዜጎችንም የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
በተጨማሪም ለግሉ ሴክተር በር ከፋች እንደሚሆን ይታመናል፡፡ እንደ ህንድ ያሉ አገሮች የዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ አንስቶ በርካታ የዲጂታል አገልግሎት ሰጪዎች (Startups) ማበብ ችለዋል። ከዚህም ባሻገር መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የማረጋገጥ አገልግሎት ሥራ ወደ ገቢ ማስገኛ በመቀየር ገቢውን ማሳደግ ይችላል። ለዚህም መሠረት መጣል እንዲቻል የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡