አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ‹‹አለኝታ›› የተሰኘ የዲጂታል ብድር አገልግሎት የሚውል 500 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ‹‹አለኝታ›› በተሰኘው የዲጂታል ብድር አገልግሎት አምስት ዓይነት ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረጉን ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በአገልግሎቱ ማስጀመርያ ላይ ገልጿል፡፡
የአንበሳ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ተከሰተ እንደተናገሩት፣ ‹‹አለኝታ›› የተሰኘውን የዲጂታል የብድር ያለመያዣ የብድር አገልግሎት የሚቀርብበት ነው።
አገልግሎቱ በዋናነት የደመወዝ ብድር፣ ለራይድና ለታክሲ ሾፌሮች፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ፣ ለሞባይልና ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መግዣ ብድርና ለግብረ ሠናይ ድርጅቶች የዲጂታል የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የብድር አፈቃቀድ ሒደቱም የደንበኞችን የገቢ ሁኔታና የመመለስ አቅምን ባገናዘበ መንገድ የሚከናወን መሆኑን፣ ለዚህም አገልግሎት የሚሆን 500 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስረድተዋል፡፡
በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከደመወዝ እስከ ቀጣይ ደመወዝ ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል የአንድ ወር ብድር የሚያገኙበት አገልግሎት መሆኑን አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
የታክሲና የሜትር ታክሲ ሾፌሮች ደግሞ የሚያግጥማቸውን ወጪዎችን ለመሸፈን፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም በምርት ሒደት ወቅት ለአፋጣኝ የካሽ እጥረትን ለመቅረፍ እንዲችሉ፣ እንደ ሞባይልና ላፕቶፕ የመሳሰሉ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ለመግዛት የገንዘብ እጥረት ለገጠማቸው ደንበኞችም የብድር አገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
ከበጎ ፈቃደኞች አጋሮች ጋር በመተባበርም የፋይናንስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚሰጥ የቡድን ብድርም በ‹‹አለኝታ›› ከሚቀርቡ አገልግሎቶች መካከል አንዱ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ በባንኩ የቁጠባ ሒሳብ ያለው ማንኛውም ደንበኛ የ‹‹አለኝታ›› የብድር አገልግሎትን በማንኛውም ሰዓት ማግኘት እንደሚችል፣ በእጅ ስልክም የ‹‹አለኝታ›› መተግበሪያን በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል።
የ‹‹አለኝታ›› የመተግበሪያ አበልጻጊ የኳንተም ቴክኖሎጂ ሶሉውሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሶፎኒያስ እምቢበል፣ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ሥርዓት ለተለያዩ ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት የክፍያ መተግበሪያዎችን በማበልፀግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የብድር አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር የተደረገው ‹‹አለኝታ›› መተግበሪያ በቀጣይም እያደገ የሚሄደውን የደንበኞች ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት አዳዲስ የብድር አገልግሎቶችን እንዲያስተናግድ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
የኳንተም ቴክኖሎጂ ሥራ ከጀመረ ቅርብ ጊዜ ቢሆነውም፣ በተለይም የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ሁለገብ እንቅስቃሴ እያጠናከረ መሆኑን አቶ ሶፎኒያስ ገልጸዋል።
ድርጅቱ በተፈጠረው አጋርነት የባንኩን የዲጂታል ብድር አቅርቦት አሠራርን መሠረት በማድረግ ለደንበኞች ቀላልና ምቹ የሆነ መተግበሪያ ሥራ ላይ እንዲውል ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በርካታ የአገር ውስጥ የግል ባንኮች በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የዲጂታል ብድር አገልግሎቶችን እያስተዋወቁ ይገኛሉ። የዲጂታል ክፍያ በኢትዮጵያ እየተነቃቃ ቢሆንም፣ ከሰፊው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አኳያ በቂ እንዳልሆነና ገና በጅማሮ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡