- እኔ ምልህ፣ ቴሌቪዥኖቹ በሙሉ የለውጡ ጉዞ አምስት ዓመት ሞላው የሚሉት ምኑን ነው? የምን ለውጥ ነው?
- በቀላል አማርኛ አሁን ያሉት የለውጡ መሪ ወደ ሥልጣን የመጡበት አምስተኛ ዓመት ማለታቸው ነው።
- አምስት ዓመት ሞላቸው እንዴ?
- አዎ።
- ታዲያ አምስት ዓመት ከሞላቸው ለምንድነው ሦስት ዓመት ይቀረኛል የሚሉት? ምርጫ ሊያራዝሙ አስበው ነው እንዴ?
- እንደዚያ አይደለም።
- እ?
- የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት የእሳቸው አልነበረም።
- እንዴት ማለት?
- የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሥልጣን ዘመን ነበር። ነገር ግን በፈቃዳቸው ሥልጣን በመልቀቃቸው የለውጡ መሪ ተተኩ። በምርጫ ከተመረጡ ደግሞ ሁለት ዓመታቸው ነው።
- የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለምንድነው ሥልጣን የለቀቁት?
- ፈልገው ነው በፈቃዳቸው የለቀቁት።
- በፍላጎትማ ሥልጣን አይለቀቅም።
- ማንም አላስገደዳቸውም ስልሽ። ፈቅደው ነው የለቀቁት።
- ባለፈው ፓርላማ ላይ ሥልጣን እንዴት እንደሚለቀቅ በብርጭቆ ሲያስረዱን አልነበር?
- አዎ።
- እንደዚያ እንዳይሆን የለቀቁት።
- ማን?
- የቀድሞው መሪ።
- እንዴት?
- ውኃ የሞላው ብርጭቆው ውስጥ እንትን ገብቶ።
- ምን?
- ድንጋይ!
- በይ ሌላ ቦታ እንደዚህ እንዳትናሪ?
- እንዴት?
- ነገርኩሽ እንደዚህ ስትናገሪ እንዳልሰማሽ?
- እንዴት? ምን ተናገርኩ?
- ድንጋይ ለማለት የፈለግሽው ማንን ነው?
- እኔ ምሳሌውን ደግሜ ተናገርኩ እንጂ፣ አንተ የሰጠኸውን ትርጉም አላልኩም። ጨርሶም አላሰብኩትም።
- ይህንን የተናገርሽው ሌላ ቦታ ቢሆን ማንም ምክንያትሽን አይሰማም ነበር። አንጠልጥለው ነበር የሚወስዱሽ።
- ወዴት?
- ቃሊቲ ወይም ቂሊንጦ ነዋ። ይወረውሩሽ ነበር።
- ምንም ሳላጠፋ? ያላልኩትን ተርጉሞ ማሰር ይቻላል አንዴ?
- አይደለም ለአንቺ፣ ለእኔም ትተርፊኝ ነበር።
- በዚህ ንግግር ለዚያውም በእናንተው በሰጣችሁት ትርጓሜ ቃሊቲ የሚያስወርድ ከሆነማ በተቃራኒው ይሆናል?!
- ምኑ?
- ለውጡን በማጽናት ፈተናዎችን መሻገር የምትሉት።
- እንዴት ነው በተቃራኒው የሚሆነው?
- ቦታው ተለዋውጠው።
- ምኖቹ?
- ለውጡና ፈተናው።
- አልገባኝም?
- ለውጡን በማጽናት ፈተናዎችን መሻገር አይደል ያላችሁት
- እ?
- ፈተናዎችን በማጽናት ለውጡን መሻገር ይሆናል ማለቴ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጋር ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ቃለ መጠይቅ እያደረጉ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር የሰሜኑ ግጭት በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ያደረሰው መስተጓጎል ምን ያህል ነው።
- በጣም የሚገርመው በግጭት ውስጥ ሆነን እንኳን የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ እንጂ መስተጓጎል አልገጠመውም።
- እንዴት ሊሆን ቻለ? እስኪ ያብራሩልኝ?
- ለምሳሌ ባለፉት ስምንት ወራት ሦስት ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ተችሏል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ16 በመቶ ብልጫ አለው። ስለዚህ ዕድገት እንጂ ፍሰቱ አልተስተጓጎለም።
- ለመሳብ ከተቻለው የውጭ ኢንቨስትመንት ውስጥ ምን ያህሉ ወደ ኢንቨስትመንት ገብቷል?
- እሱ አሁን አይታወቅም።
- ታዲያ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
- አብዛኞቹ ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጥ ይቻላል።
- ዓምናም ሆነ ዘንድሮ መሳብ ከተቻለው ውስጥ እስካሁን ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ የሉም ማለት ነው? ወይስ መረጃው አልደረሰዎትም?
- መረጃውን በቀጣይ የምናየው ይሆናል። ነገር ግን ፅኑ ፍላጎት እንዳላቸው እርግጠኛ መሆን ይቻላል።
- ጥሩ። እስኪ ከአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ረገድ ያለውን አፈጻጸም እንመልክት። በግጭቱ ምክንያት የገቢ አሰባሰቡ አልተደናቀፈም?
- ይገርምሀል። በአገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢ በየዓመቱ እስከ 20 በመቶ ዕድገት የሚመዘገብበት ነው። በአጠቃላይ በዚህ ረገድ ጥሩ ስኬት ነው ያለው።
- የሚሰበሰበው ገቢ ከአጠቃላይ ጂዲፒው አንፃር ምን ያህል ነው?
- በገቢ ረገድ ያለው ትልቅ ችግር ከጂዲፒ ጋር ያለው ጥምርታ ነው። ከዓመት ዓመት በማሽቆልቆል ላይ ነው።
- አሁን ያለው የገቢና የጂዲፒ ጥምር ምጣኔ ምን ያህል ነው?
- ከአምስት ዓመታት በፊት 11 በመቶ ነበር።
- አሁን ያለውን ነው የጠየኩት?
- የዘንድሮው የሚታወቀው በዓመቱ መጨረሻ ላይ ነው።
- የስምንት ወሩን ማወቅ አይቻልም?
- ይቻላል ግን ሙሉ ሥዕሉን የሚገልጸው ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚሰበሰበው ገቢ ሲታወቅ ነው።
- እሺ ዓምና የነበረው ምጣኔ ምን ያህል ነበር?
- ስምንት በመቶ ነበር።
- የአፍሪካ አገሮች አማካይ ምጣኔ 18 በመቶ ነው። አሁን የነገሩኝ ቁጥር ግን በጣም ዝቅተኛ ነው። ኢኮኖሚው ቆሟል ወይም ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም ማለት ነው?
- የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን መዘንጋት የለብህም።
- የሕዝብ ቁጥር መጨመር ከአገር ወሰጥ ገቢ መቀነስ ጋር ምን ያገናኘዋል?
- ለምን አይገናኝም? ይገናኛል!
[ሚኒስትሩ ቃለ መጠይቁን ጨርሰው እንደወጡ ጋዜጠኛው ከአለቃው ስልክ ተደወለለት]
- እሱን ቃለ መጠይቅ አቆየው።
- ለምን? ጥሩ ቃለመጠይቅ እኮ ነው።
- የምልህን አድርግ። በተጨማሪም …
- በተጨማሪ ምን?
- የተጠራቀመ የዓመት ዕረፍት አለህ ተብሏል።
- ስለዚህ?
- ዕረፍት መውጣት አለብህ!