Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየትግራይ ክልል ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ካቆሙበት እንዲቀጥሉ ጥያቄ ቀረበ

የትግራይ ክልል ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ካቆሙበት እንዲቀጥሉ ጥያቄ ቀረበ

ቀን:

በሰሜኑ ጦርነት ተቋርጦ የነበረው የትግራይ ክልል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንደገና ለማስጀመር የተለያዩ ሐሳቦች እየቀረቡ እንደሆነ የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በዚህም በጦርነቱ ምክንያት በተለያዩ ውድድሮች ላይ ሲካፈሉ የነበሩ ክለቦች እንደገና ወደ ውድድር መመለስ የሚችሉበት መንገድ ለመፈለግ፣ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር እየተመካከረ እንደሆነ የትግራይ ክልል ስፖርት  ኮሚሽነር አቶ ተክላይ ፈቃዱ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ከሆነ ከጦርነቱ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሲሳተፉ የነበሩት ስሁል ሸረ፣ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም መቐለ ሰብዓ እንደርታ እግር ኳስ ክለቦች ውድድራቸውን ካቆሙበት እንዲቀጥሉ ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ ተክላይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በፕሪሚየር ሊጉ ከሚካፈሉ ክለቦች ባሻገር በሱፐር ሊግ ሲሳተፍ የነበሩ የአክሱምና የሶሎዳ እግር ኳስ ክለቦች ወደ ውድድር እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ተክላይ ገልጸዋል፡፡

ክለቦቹ እንደገና ወደ ውድድሩ እንዲመለሱ ለማድረግ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ከትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝቶ ከመከረ በኋላ፣ የበጀት ችግሩን ለመፍታት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የክለብ፣ የፕሮጀክት እንዲሁም የስፖርት ማዕከላት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠ ሲሆን፣ በርካታ የክለብ ተጫዋቾች ወደ ሠራዊቱ መቀላቀላቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህም ባሻገር በክልሉ የነበሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አብዛኛዎቹ መውደማቸውን ተከትሎ፣ ስፖርተኞቹ መበተናቸውን አቶ ተክላይ ለሪፖርተር አውስተዋል፡፡

በክልሉ ውድመት ያጋጠማቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የጥናት ዳሰሳ ተደርጎባቸው መለየታቸውን የሚያነሱት አቶ ተክላይ፣ በተፈለገው ጊዜ ለጊዜያዊው አስተዳደር እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥት ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አልሸሸጉም፡፡

በክልሉ ከሚዘወተሩት ስፖርቶች አንዱ ብስክሌት ሲሆን፣ የመስፍን ኢንዱስትሪያል፣ የትራንስ ኢትዮጵያ፣ የመሶቦ ሲሚንቶ፣ እንዲሁም የሳባ እምነበረድ የብስክሌት ክለቦችን ወደ መደበኛ ውድድር ለመመለስ ከፌዴሬሽኖች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በአንፃሩ አብዛኛው ስፖርተኛ ለጦርነት ሠራዊቱን በመቀላቀሉ በፕሪቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት ጠብቆ ስፖርተኛው ወደ ቀድሞ ክለቡ እንዲመለስ የማድረግ ሥራ እንደሚጠበቅ አቶ ተክላይ አብራርተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኘው የማይጨው የስፖርት ማሠልጠኛ ማዕከል ውድመት እንደረሰበት የተገለጸ ሲሆን፣ በማዕከሉ የነበሩት 40 አትሌቶች መበተናቸውን ተከትሎ ማዕከሉን አድሶ፣ እንደገና አትሌቶችን በመመልመል ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡

የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር መልካም ግንኙነት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጾ፣ በቅርቡም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሁሉንም ፌዴሬሽኖች ያካተተ ጉዞን ወደ መቐለ በማድረግ ለመወያየት ማቀዱን ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ የተደረገለት የትግራይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በርካታ ድጋፎች እንደሚደረግለት ቃል ቢገባለትም፣ እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጋቸውን አቶ ተክላይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በክልሉ መደበኛ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር በቂ በጀት የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት ከፌዴራል መንግሥቱ ድጋፍ በዘለለ፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ባለሀብቶች እንዲሁም አትሌቶች ሀብት የማሰባሰብ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት በክልሉ ያለውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የአጭር፣ መካከለኛና ረዥም ጊዜ ዕቅድ መዘጋጀቱ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ለሁለት ዓመታት ምንም ዓይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ሳያስተናግድ የቆየው ክልሉ፣ በቅርቡ በመቐለ ስታዲየም መጠነኛ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በመቐለ ስታዲየም ሦስት ፕሮጀክቶች የእግር ኳስ ልምምድ ማድረግ መጀመራቸው ተጠቁሟል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ከሆነ፣ ጥያቄዎቹ እየጨመሩ መምጣታቸውንም አልሸሸጉም፡፡

በመቐለ ከተማ ስፖርታዊ ልምምድ ከማድረግ ፍላጎት ባሻገር፣ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ስፖርታዊ ክንውኖችን ለማድረግ ፍላጎት መኖሩ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ማስተናገድ እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡

ከወራት በፊት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው አትሌቲክስ፣ ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ የክልሉ ፌዴሬሽን የመጀመርያ ዙር የዳሰሳ ጥናት ማድረጉ አስታውቆ ነበር፡፡

ክልሉ በጥናቱ መሠረት የደረሰበትን ውጤት ተንተርሶ፣ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳነ ተክለ ሃይማኖት ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...