የሕዝብ አስተዳደርና ፖሊሲ ባለሙያው እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ናቸው፡፡ ሲሳይ ሳህሉ በወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከዋና ዕንባ ጠባቂው ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ከአምስት ዓመታት በፊት የተካሄደውን የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ ተከትሎ በዴሞክራሲ ተቋማት ዘንድም ትልቅ የሚባል የሪፎርም ሥራ እንደተከናወነ ይነገራል፡፡ በዕንባ ጠባቂ ተቋም ይህ ለውጥና ሪፎርም እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር እንዳለ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠበቂ ተቋም በኢትዮጵያ ካሉት የዴሞክራሲ ተቋማት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እንግዲህ በመርህ ደረጃ ተቋማት በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃም ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሥራቸውን መሥራት እንዳለባቸው ነው የተቀመጠው፡፡ ከዚያም ባለፈ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ሊኖር ይገባል፡፡ የሚሠሩት ሥራ በአዋጅ ይወሰንላቸዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መርሆዎች መሠረት አድርገን ተቋሙን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች አከናውኗል፡፡ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ይሠራል ስንል የተቋሙ ሠራተኞች የራሳቸው የሆነ ብሔር፣ እምነት፣ አመለካከትና የዕድገት ዓላማ አላቸው፡፡ ነገር ግን የሚሠሩት ሥራ ከእነሱ ሃይማኖት፣ እምነት ወይም ርዕዮተ ዓለም ጋር የሚያገናኙበት ወይም ለሚከተሉት እምነትና አስተሳሰብ ቀድመው መሥራት እንደሌለባቸው መግባባት ተፈጥሮ፣ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች እንደ ተቋም በሁሉም ቅርንጫፍ የጽሕፈት ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሠሩ በዋነኛነት የተሠራ የለውጥ ሥራ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሌላው ተጠሪነታችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆነ ልምዱ እነዚህ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሆነን መሥራት እንዲችሉ በመቀመጡ ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ጫና ወይም ጣልቃ ገብነት አይኖርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከመንግሥት ወይም ከዥው ፓርቲ፣ እንዲሁም ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና አካላት ነፃና ገለልተኛ ሆነው ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሥራችንን እየሠራን ነው፡፡ ሌላው ከዚህ በፊት አስቸጋሪ መሰናክል የነበረው የምናቀርባቸውን ሐሳቦች የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ተቀብሎ መፈጸም ላይ መሠረታዊ ችግሮች ነበሩ፡፡ ይህ መሠረታዊ ችግር አሁንም ተግዳሮት ቢሆንም፣ በየዓመቱ በምናቀርባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች የሚፈጸሙት እያደጉ መጥተው አሁን 75 በመቶ ደርሷል፡፡ ተቋሙ ከዚህ በፊት በአዋጅ የተሰጡት ተግባራት ኃላፊነቶች ላይ ብቻ ነበር በትኩረት የሚሠራው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች፣ መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች የዜጎችን መብት የሚነኩ ከሆነ እነዚህ ጉዳዮች ትክክል አለመሆናቸውን በልዩ ልዩ መግለጫና በፕሬስ መግለጫ በመስጠት፣ እንዲሁም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በማሳወቅ ነፃና ገለልተኛ ሆነን እየሠራን ነው፡፡ ስለዚህ ከሞላ ጎደል ተቋሙ ለውጥ አካሂዶባቸዋል የሚባሉት ዋና ዋና ጉዳዮች እነዚህ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተደጋጋሚ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርጋቸው የጥናት ውጤቶች፣ ጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ የዜጎች መብት ሲጣሱ ወይም በደል ሲፈጸም ምክረ ሐሳብ ሲሰጥና ሲያጋልጥ ይሰማል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ይህን የዕንባ ጠባቂ ተቋም ተግባርና እንቅስቃሴን የሚፈርጁ አካላትም ይስተዋላሉ፡፡ ይህን ተቃርኖ እንዴት ይመለከቱታል?
ዶ/ር እንዳለ፡- ተቋሙ በተቻለው መጠን ከየትኛውም ዘር፣ ብሔር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ ፀድቶ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሥራውን እየሠራ ነው የሚገኘው፡፡ ስለዚህ እኛ የምንመዘነው ምን ያህል ነፃ ነን? ምን ያህል የብሔር፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት አለ ወይ? በሚሉት ጉዳዮች ተቋማችንን? እንመዝናለን፡፡ እኛ በእነዚህ ጉዳዮች ነፃና ገለልተኛ ሆነን ሥራችን እየሠራን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የተለያዩ አካላት የራሳቸው የሆነ አስተሳሰብ፣ እምነት ወይም የብሔር ፖለቲካ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሐሳባቸውን እናከብራለን፣ ነገር ግን ሐሳባቸው ትክክል ነው አይደለም የሚለውን ራሳቸው የሚመዝኑት ነው የሚሆነው፡፡ እኛ እየሠራን ያለነው ግን ነፃና ገለልተኛ ሆነን ሲሆን፣ ከዚያም ባለፈ ሥራዎችን በምንሠራበት መሥፈርት አማካይነት ነው ተቋማትን የምንመዝነው፡፡ እነሱ ግን በሚፈልጉት መንገድ መፈረጃቸው ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን መታወቅ ያለበት የሚፈልጉትን ማንኛውንም መረጃ ሆነ ማስረጃ ተቋማችንን ጠይቀውና እኛንም ዋቢ አድርገው ቢጠቅሱ ሚዛናዊ መረጃ መስጠት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መገናኛ ብዙኃን እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ከሰጡ በተሰጠው መረጃ ሕዝቡ የተዛባ አመለካከት እንዳይዝ መደረግ አለበት፡፡ አንድ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ወይም ግለሰብ የሰጠው አስተያየት ተቋሙን የማይወክል መሆኑን በመግለጽ፣ ኅብረተሰቡ የተዛባና የተሳሳተ መረጃ እንዲይዝና እንዳይደናገር መግለጫ እንሰጣለን፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ተቋሙን በፈለጉት መንገድ መፈረጅ መብት ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የተባለው ጉዳይ አለ? ወይም የለም? የሚለውን ወደ ተቋሙ መጥቶ ለማጣራት በራችን ክፍት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የሚያከናውናቸውን የዕለት ተዕለት ተግባራት በመገምገም ችግር በሚያስከትሉት ላይ ወቀሳ፣ መስተካከል ባለባቸው ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ መግለጫና ምክረ ሐሳብ ስትሰጡ ከመንግሥት አካላት የሚደርስባችሁ ጫና አለ?
ዶ/ር እንዳለ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሲቋቋም ዓላማው መንግሥትን መተቸት ነው፡፡ መተቸት ሲባል መንግሥት የሠራቸውን ጥሩ ጥሩ ሥራዎች የሚገልጽበት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አለ፡፡ ይህ ማለት ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መሥሪያ ቤት አይደለም፡፡. ስለዚህ ለሕዝቡ ቃል በገባው መሠረት እየሠራህ አይደለም፣ ወይም ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የሚለው እንዚህን ጉዳዮች ነው፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሥራህን እየሠራህ ስላልሆነ በማለት መንግሥትን የመተቸት ኃላፊነት ነው የተሰጠው፡፡ እንዳልከው እንደ ግለሰብ የተቋሙን ሥልጣንና ተግባር የማይረዱ ሰዎች እንደ እነዚህ ዓይነት ስሜቶችንና አስተያየቶችን ሲያንፀባርቁ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን የዴሞክራሲ ተቋማትን በተለይም የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከመልካም አስተዳደርና ከብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን እየነቀሰ፣ መንግሥትን ማጋለጥና መተቸት በአዋጅ የተሰጠው ዋነኛ ኃላፊነት ነው፡፡ እንዲያውም ተቋሙ መወቀስ ካለበት በተሰጠን ሥልጣን ልክ ሥራዎችን እየሠራን አይደለም በሚል ነው፡፡ በተሰጠን የሥልጣን ገደብ ልክ ለመራመድ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ምቹ ስላልሆነ፣ እኛም ያን የፖለቲካ ሁኔታ ግምት ውስጥ እያስገባን አንዳንዱ ጉዳይ ከመንግሥት አቅም በላይ ውጪ ሊሆን ይችላል በሚል፣ አንዳንዱ ደግሞ ለምሳሌ የውጭ ተፅዕኖ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የተለያዩ አካላት ፍላጎቶች ሊኖሩ ስለሚችሉና መንግሥት እነዚህን ጉዳዮች ማጣጣም አለበት በሚል አመክንዮ ሕገ መንግሥቱ በሰጠን ነፃነት ልክ ኃላፊነታችን ተወጥተናል ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም እኮ መንግሥት ሥራው ካልሠራና ተጠያቂ ካልሆነ፣ የሕግ የበላይነቱን ማስከበር ካልቻለ፣ ኅብረተሰቡ መንግሥትን ተጠያቂ ከሚያደርግበት አሠራር አንዱ የመተማመኛ ድምፅ (Vote of Confidence) መሰጠት አለብን ብለን ሕዝቡ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ለማድረግ አሁን ያሉት አጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አይፈቅዱም በሚል፣ ሕገ መንግሥቱ በሰጠንና አዋጁ ላይ በተቀመጠው ሥልጣን መሠረት ከዓለም አቀፍ ልምዶች ተነስተን መሥራት በሚገባን ልክ አልሠራንም የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ በመንግሥት ላይ የመተማመኛ ድምፅ የመስጠት ሥልጣን አላችሁ?
ዶ/ር እንዳለ፡- እስከዚያ ድረስ የሚያደርስ ነፃነት አለን፡፡ ሕገ መንግሥቱም ላይ በደንብ ተቀምጧል፡፡ የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ወይም ምክር ቤቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጣም ብሎ ኅብረተሰቡ ሲያምን የመተማመኛ ድምፅ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ከእያንዳንዱ የምክር ቤት አባላት ጀምሮ ሥልጣን ላይ ባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች አሁን ካለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕድገት አኳያ የሚባለውን ለመፈጸም ምን ምቹ ሁኔታ አለ? ለምሳሌ አንድ የክልልነት ጥያቄ ለመመለስ እየተጠየቀ ያለው በጀት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚያቀርባቸውን ምክረ ሐሳቦችን አስፈጻሚው ለመቀበል ያለው አዝማሚያና እንቢተኝነት ምን ይመስላል?
ዶ/ር እንዳለ፡- ልዩነቶች አሉ፡፡ እኔ ወደ እዚህ ተቋም ስመጣ ከተሰጡ የመፍትሔ ሐሳቦች የተፈጸሙት 42 በመቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፈው በ2014 ዓ.ም. ተቋማችን ከሰጠው ምክረ ሐሳብ 75 በመቶ ያህሉ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህ ሲባል አንዳንድ አስፈጻሚ አካላት በተለይ የከተማ አስተዳደር አካላት የእንቢተኝነት አዝማሚያ አለ፡፡ ሞገደኝነቱ ግን ሕግን መሠረት አድርገው ሳይሆን አንደኛ የተቋሙን ሥልጣንና ተግባር ባለመገንዘብ፣ ሁለተኛ ደግሞ እነሱ የያዙት ሥልጣን የሕዝብ ሥልጣን መሆኑን ስለማይገነዘቡ እንዲህ ዓይነት ሞገደኝነቶችን ያሳያሉ፡፡ እኛ የምናቀርባቸው የመፍትሔ ሐሳቦች ሕዝቡን ወክለን ከዜጎች ጥቅም አንፃር ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እዚያ ወንበር ላይ ሲቀመጡ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊያስከብሩ መሆኑን የማይረዳ፣ ወይም ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ሥልጣን አድርገው የሚረዱ ግለሰቦች አሉ፡፡ እንደ ሥርዓት ግን ተቋማችን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ነው የሚሠራው፡፡ ከየትኛውም ወገን በፀዳ መንገድ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የምታስታውሱ ከሆነ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፓርላማውን እንደፈለጉ ያሽከረክሩት እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ ያ ሁኔታ አሁን ላይ የለም፣ መሻሻሎች አሉ፡፡ ነገር ግን ቅድም እንዳልኩህ የእኛ ተቋምም ሆነ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት የበለጠ ሥራቸውን መሥራት የሚችሉት የፖለቲካው ሁኔታ የተሻለ ሲሆን ነው፡፡ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ሲችል፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሆዎች ሲኖሩ፣ መንግሥትም ለሕዝብ ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፣ እነዚህ ተቋማት ሥራቸውን ይበልጥ የሚተገብሩ ይሆናል፡፡ ነገር ግን መንግሥት እነዚህ ጉዳዮችን መፈጸም ሳይችል ሲቀር ተቋማቶቻችን መሰናክል ያጋጥማቸዋል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ ሲኖር ተቋማት የበለጠ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት አምስት ዓመታት በቀጠለው የዝናብ እጥረት በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ድርቅ ተከስቷል፡፡ ድርቁ በዚህ ዓመትም ተባብሷል፡፡ ይህን የተረዱ አንዳንድ ተቆርቋሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ችግሩ ሊፈጠር የቻለው ከመንግሥት ቅድመ ጥንቃቄ ጉድለት ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ ችግሩ እየተባባሰ በዚህ ዓመትም እየተሰጠ ያለው ምላሽ በሚገባው ልክ እንዳልሆና ፍትሐዊ አለመሆኑንም ሲናገሩ ይስማሉ፡፡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሊል ይችላል?
ዶ/ር እንዳለ፡- እንግዲህ በአጠቃላይ ከድርቅ ጋር ተያይዞ በሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ባለፉት አምስት ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ የድርቅ አደጋ ተከስቷል፡፡ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት በሦስቱም ክልሎች መደበኛ ቁጥጥር አካሂደን ነበር፡፡ ከዚያም በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት በመጀመሪያ ዙር በባሌ ዞን ሁኔታው ምን እንደሚመስልና መንግሥት ለድርቁ ምን መልስ እየሰጠ ነው የሚለውን፣ ድርቁ የከፋ አደጋ ከማድረሱ በፊት መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ምን ምን ይመስላሉ የሚለውን ዋና ዋና ይዘቶችን የያዘ የቁጥጥር ሥራ ሠርተናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን በሦስቱም ክልሎች ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከድርቁ ጋር ተያይዞ ያለው መሠረታዊ ችግር በኮሚሽን ደረጃ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር፣ እንዲሁም ብሔራዊ ፖሊሲ አለ፡፡ ስለዚህ ኮሚሽኑም ሆነ ፖሊሲው የተቋቋመበት ሦስት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት፡፡ እነሱን ስትመለከት አንደኛው ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ መከላከል፣ ሁለተኛው አደጋ ከተከሰተ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መቀነስና ሦስተኛው ችግሩ ከተከሰተ ለአደጋው አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት የሚሉት ናቸው፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት አለ፡፡ ይህ ሥርዓት ዋነኛ ተልዕኮው ተፈጥሮአዊ ወይም ሰው ሠራሽ አደጋዎች ቢፈጠሩ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሥርዓት መሠረት ከዓመት ዓመት ዝናብ የማይዘንብ ከሆነ፣ ችግሩን ቀድሞ በመረዳት መፍትሔ በመስጠት ረገድ ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት በቅንጅት የሚሠራው በመዋቅር በመሆኑና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ከዚህ ሁኔታ አኳያ ምን ሁኔታ ላይ ነች የሚለው እየተገመገመና የመፍትሔ ሐሳብ እየተሰጠበት መሄድ አለበት፡፡
አንድ ምሳሌ ብነግርህ በ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. ከግብርና ምርት ምን ያህል ኩንታል ልናመርት እንችላለን የሚለውና የምግብ ፍላጎታችን ምን ያህል ነው የሚለውም ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እጥረቱን ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህን እጥረት በዕርዳታ ወይስ ከአገር ውስጥ የምርት ክምችት መሙላት የሚለውን አስቀምጦ የሚሠራበት አሠራር ይተገበራል፡፡ ምናልባት አንዳንዴ ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥን ወይም የጎርፍ አደጋን ቀድመህ ላትተነብየው ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት የነበረው ሁኔታና ክስተቱ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ የት የት አካባቢ ላይ የጎርፍ አደጋ እንደሚከሰት፣ ድርቅ በየስንት ዓመቱ እንደሚከሰት ቅድመ ትንበያ አድርጎ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች መሥራት ላይ ክፍተት አለ፡፡ ሁለተኛ አደጋ ከተከሰተ በኋላ በድርቅ ምክንያት ሕፃናት የምግብ አጥረት ያጋጥማቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን ጉዳይ መቀነስ የሚቻልባቸው አሠራሮች አሉ፡፡ ድርቅ የሚከሰት ከሆነ እንስሳትን ድርቅ የሌለበት አካባቢ ለጊዜው እንዲቆዩ የሚደረግበት ሁኔታ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎችን የመውሰድ ክፍተቶች ደግሞ ታይተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ሲነሳ የነበረው ችግር የሰብዓዊ ዕርዳታ አገልግሎት በአግባቡ አለመድረስና የሚሰጠው ዕርዳታ ከሚፈለገው ሕዝብ ቁጥር ጋር በቂ አለመሆን፣ ለእንስሳት የሚቀርበው መኖ ጭምር በቂ አለመሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህ በሦስቱም ሒደቶች ክፍተቶች ነበሩ፣ ወይም አሉ፡፡ ሌላኛው ክፍተት ግን የቅንጅት ክፍተት ሲሆን፣ አገሪቱ የምትከተለው የፌደራሊዝም ሥርዓት ቢሆንም ዜጎቿን ግን የፌዴራልና የክልል ተብሎ ክፍፍል የለም፡፡ ስለዚህ የፌዴራሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሚጠየቅበት ጊዜ ክልሉ አላሳወቀኝም የሚል ነገር እንሰማለን፡፡ ነገር ግን እንደ አገር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት ከወረዳ እስከ ፌዴራል በመዋቅር ደረጃ በተዋረድ መረጃው ስለሚይደርስ፣ ይህንን ደግሞ የሚመለከተው የፌዴራል መንግሥቱ የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ነው፡፡ ነገር ግን የፌዴራሉ በክልል፣ የክልሉ ደግሞ በፌዴራሉ ሲያሳብቡ ይታያሉ፡፡ ስለዚህ ተቀናጅቶና ተወያይቶ መሥራት ላይ ውስንነቶች አሉ፡፡ የጀመርነውን ሁለተኛ ዙር ዳሰሳ ሲጠናቀቅ መንግሥት ለድርቁ ምን ምላሽ እየሰጠ ነው የሚለውን መረጃ ለሕዝቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- በመረጃ ነፃነት ላይ ያለው ለውጥ ምን ይመስላል? የመንግሥት አካላት መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠታቸውን እንዴት ይመለከቱታል? ተቋማችሁስ በዚህ ረገድ በሚጠበቅበት ልክ እየሠራ ነው ማለት ይቻላል ወይ?
ዶ/ር እንዳለ፡- ይህ ጥያቄ የእኛን ተቋም ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ተቋማት ያመለክታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትችት በምናቀርብበት ጊዜ ለየተቋማቱ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ምንድነው የሚለው ነገር በግልጽ መታወቅ መቻል አለበት፡፡ ለተቋማቱ ከተሰተጠው ሥልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት አንፃር አልተሳካላችሁም፣ ወድቃችኋል የሚል ትችት ቢቀርብ ሕጋዊ ሊሆን ይችላል፡፡ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ከማስተግበር አንፃር ለተቋማችን የተሰጠን ሥልጣን አንደኛው ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ግንዛቤ በየመንግሥት ተቋማቱ ላሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ነው የምንሰጠው፡፡ ሁለኛው የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ነው፡፡ ለዚህም የመረጃ ነፃነት አዋጅ አለ፡፡ ይህንን አዋጅ ለማስተግበርና ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ የሕግ ድጋፎች፣ መመርያዎችና ደንቦች ማዘጋጀት አለ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በየተቋማቱ ላሉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር እስከ መጨረሻ ድረስ ሄደን ኃላፊነታችንን ተወጥተናል የሚል ግምገማ የለንም፡፡ ነገር ግን ግንዛቤ ማግኘት ለሚገባቸው ሁሉም አካላት ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ከእኛ ተቋምም አልፈን ከሌሎቹ ተቋማት ጋር ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በመሆን በትብብር ለሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ከዚህ አኳያ እኛ ጋ የሚታዩ ጉድለቶች የሉም፡፡
በአጠቃላይ ይህንን አዋጅ ለማስተግበር ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አሉ፡፡ ፓርላማው የራሱ የሆነ ኃላፊነት አለበት፣ ዕንባ ጠባቂም እንዲሁ ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን የመረጃ ነፃነት አዋጅን የሚያስተገብሩ ደግሞ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ናቸው፡፡ አስፈጻሚ አካላት መረጃ በመስጠትና ባለመስጠት መካከል ያለውን መሠረታዊ ችግር መጠየቅ ያለበት አስፈጻሚ አካሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት ለምሳሌ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ለሚዲያ ተቋማት መረጃ የማይሰጡት ከግንዛቤ ችግር ነው ከተባለ፣ ዋና ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሊጠየቅ ይገባዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ሁሉም የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ለዜጎች መረጃ መስጠት እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ አንድ ግለሰብ ሚኒስትር ሆኖ ሲሾም መጀመሪያው የተሰጡትን ሥራዎች ማከናወን አለበት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እንደ ድልድይ ሆኖ ሕዝብንና መንግሥትን ያገናኛል፡፡ ድልድይ ሆኖ ሲባል የኮሙዩኒኬሽን ሥራዎችን መሥራት አለበት ማለት ነው፡ ስለዚህ አንደኛ እሱ ዜጎች የሚፈልጉትን መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ እንደ ተቋምም መረጃ ሊሰጥ የሚችል የሥራ ክፍል የማዋቀርና የማደራጀት ኃላፊነት አለበት፡፡ ለምሳሌ የግብርና ሚኒስቴር ስንሄድ ተቋሙ መረጃ ካልሰጠ ሚኒስትሩ ተጠያቂ ነው ማለት ነው፡፡ ወደ ሕዝብ ግንኙነት ጣቱን መቀሰር የለበትም፡፡ ምክንያም የሚኒስትሩ ኃላፊት በመሆኑ፣ ሕጉ ላይ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ እናውቃለን፡፡
አንድ የመገናኛ ብዙኃን መረጃ ሲያዛባ ይጠየቃል፡፡ ነገር ግን አንድ የመንግሥት አካል ግን መረጃ ሳይሰጥ ሲቀር ምንም አይደረግም፡፡ እናም አንድ አካባቢ ላይ የሚከሰት ክፍተት አለ፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ ስለ ሐሳብ ነፃነትና የመረጃ ነፃነት በምናወራበት ጊዜ የመንግሥት ባህሪ ዴሞክራቲክ መርሆዎችን ሊላበስ ይገባል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ዜጎች የመሰብሰብ፣ የመሠለፍና የመቃወም ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው ሲታዩ የመንግሥት ፈቃደኝነት የማይታይበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በመርህ ደረጃ ግን መንግሥት ፈቃጅም ከልካይም አይደለም፡፡ የእኔን ሐሳብ መንግሥት የሚገድብበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት የለውም፡፡ የእኔ ሐሳብ የሌሎችን ሕዝቦች ወይም የሌሎች ዜጎችን መብት እስካልነካ ድረስ፣ የሌሎችንም ሰላምና ደኅንነት እስካልነካ ድረስ፣ አንተ የተናገርከው እንዲህ አስበህ ነው ወይም እንዲህ ዓይነት ጉዳት ለማድረስ አቅደህ ነው ብሎ የእኔን ሐሳብ የመከልከል ምንም ዓይነት መብት የለውም፡፡ ነገር ግን እኛ ያለነው አፍሪካ ውስጥ በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ነውና አሁን ያለው የሐሳብና የመረጃ ነፃነት በመንግሥት ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው የሚል ግምገማ ነው ያለን፡፡
ሪፖርተር፡- ለመገኛኛ ብዙኃን መረጃ የማግኘት ችግር ድሮም የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ መሻሻሎች ታይተው ነበር፡፡ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በዚህ ረገድ ያለውን የለውጥ ዕድገት መጨመርና መቀነስ እንዴት ይገመግመዋል?
ዶ/ር እንዳለ፡- በኢትዮጵያ ያለው ልምድ የመንግሥት ባህሪ ሲታይ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ጊዜ በተለይ እስከ 1989 ዓ.ም. የሌለ የሚዲያ ዓይነት አልነበረም፡፡ በቅርቡ ደግሞ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ የተፈጠሩ የሚዲያ ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ሲታይ ሚዲያዎች በነፃነት ሐሳባቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ነገር ግን መንገሥት ሥልጣን ላይ እየቆየ በሄደ ቁጥር የዜጎች የሐሳብና የመረጃ ነፃነት እየቀነሰ ነው የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ሁኔታው መንግሥታት ወደ ሥልጣን ሲወጡ ሁሉም ዓይነት ለውጥ የሚመጣበትና በሽ በሽ የሚሆንበት ሁኔታ ነው የሚኖረው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲቆይ እነዚህ እየቀነሱ የሚሄዱበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አሁን ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ከጦርነቱ ወዲህ ሚዲያዎችም ኃላፊነት አለባቸው፣ መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ኃላፊነት የሚጎድልባቸውም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ኃላፊነት የሚጎድልባቸው ሚዲያዎች ምንም ዓይነት ሐሳብ ቢሰጡ መንግሥት ማድረግ ያለበት ትክክል አለመሆናቸውን ማሳየት እንጂ፣ ማሰሩ ወይም መከልከሉ ውጤት አያመጣም ማለት ነው፡፡ አንድን ሰው ብታስረው ሐሳቡን ልታስረው አትችልም፡፡ አስተሳሰቡ ደግሞ ብዙ ሰዎች የሚጋፉት ሊሆን ይችላል፡፡ የብዙ ሰዎች ሐሳብ ከሆነ ደግሞ መንግሥት ሊቆጣጠረው የሚችለው ጉዳይ ስላልሆነ፣ እንዲያውም በተሻለ ነፃ ቢደረግ ሐሳቦች በስፋት ይመጣሉ፡፡ እንዲያውም በእነዚህ ሐሳቦች ዜጎች ምን ዓይነት ስሜት አላቸው የሚለውን እየተከታተለ መንግሥት ሥራውን ቢሠራ ዴሞክራሲውም ያድጋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብም እየተቀራረቡ የሚሄዱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ የተፈጠረው የኑሮ ውድነትና የሕዝቡን ስሞታ ዋና ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዴት ይመለከተዋል?
ዶ/ር እንዳለ፡- አንዴ ድምፃዊ ሃጫሉ የተናገረው ንግግር ነበር፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍራሽ ሲሆን፣ እዚህ ፍራሽ ላይ መተኛት የሚችል መንግሥት ነው ያጣችው አገሪቱ›› የሚል ንግርር ከመሞቱ በፊት ተናግሮ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እያለ ያለው አስተዳድሩኝ እኮ አይደለም፣ ግዙኝ ነው፡፡ በቅርቡ በኬንያና በሱዳን እየተከሰተ ያለውን ሁኔታ እያየን ነው፡፡ ከኑሮ ውድነት አንፃር መሠረታዊ ችግራችን የፖሊሲ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ዓለም አቀፋዊ ችግሮችና ተፅዕኖዎች የሉበትም ማለት አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን አገሮች ደግሞ በኢኮኖሚያቸው የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል የተለያዩ ዕርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ አንደኛ የእኛ ኢኮኖሚ መሠረታዊ የፖለሲ ችግር አለበት፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የተቆጣጣሪ ተቋማት ችግር ነው፡፡ የኑሮ ውድነት የሚከሰተው እኮ በተመረተውና በሚፈለገው ምርት መካከል ያለው ልዩነት ሳይጣጣም ሲቀር ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ያለውን ክፍተት መሙላት ነው ያለብን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኑሮ ውድነት በተመለከተ እኛ የምንጠቀመው የምርት መጠን ይታወቃል፡፡ ያ ማለት እያንዳንዳንች ቤት ውስጥ ዘይት፣ ስኳር ጤፍና መሰል መሠረታዊ የሚባሉ የፍጆታ ምርቶች የፍላጎት መጠን በደንብ አይቶ፣ ከሚመረተው ምርት ጋር ማጣጣምና ልዩነቱን መሙላት ቢቻል መፍትሔው ቀላል ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቆጣጣሪ ተቋማት ይህን እያደረጉ አይደሉም፡፡ የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል አንዳንዴም የልማት ሥራዎች ታጥፈው ድጎማ የምታደርግበት አሠራር ትዘረጋለህ፡፡ ጤፍ በታኅሳስ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ አራት ሺሕ ብር አካባቢ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ሰባት ሺሕ ብር ገብቷል፡፡ በሦስት ወራት ውስጥ እዚህ ደረጃ ላይ ያደሰረው ምንድነው የሚለውን ነገር ስታይ፣ የምርቱን እንቅስቃሴ አስፈጻሚ አካላት ስለገደቡት ነው፡፡ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይዘዋወር ስለተደረገ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ሰው ሠራሽ ችግሮች አሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የውጭ ችግር በተለይ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ጫና አሳድሯል፡፡ ብዙ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው የሚሰጡት ምላሽ ከኢኮኖሚ አኳያ የተመዛዘነ ነው የሚለውን እጠራጠራለሁ፡፡ ምክንያቱ በቂ ምላሽ አይደለም፡፡ እንዲያውም ውጫዊ የማድረግ አዝማሚያ አለ፡፡ ከዚያ ይልቅ ግን የኢትዮጵያውያን የመግዛት አቅም ይታወቃል፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ የግሉ ሠራተኛ፣ ከተሜውም፣ ገበሬውም ሁሉም መግዛት የሚችሉትን የፍላጎት መጠን ማወቅ ይቻላል፡፡ ይህ ከታወቀ ደግሞ መንግሥት እንዴት አድርጎ ጣልቃ ገብቶ ማስተካከል ይችላል የሚለውን ነገር በመመርያ ወይም በፖሊሲ በየጊዜው እየመረመረ፣ እያደገ የሚሄደው የዋጋ ንረት ባለበት እንዲቆም ሊያደርጉ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊ አማራጮች አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ዕርምጃዎች ከመውሰድ አንፃር ክፍተት ያለ ይመስለኛል፣ ግን ጥናት ያስፈልገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የዋጋ ንረቱ በአጭሩ ካልተገታ የሕዝቡ ምሬትና እሮሮ ምን ዓይነት የፖለቲካ ጫና ሊፈጥር ይችላል?
ዶ/ር እንዳለ፡- መንግሥት እንግዲህ ይህ ችግር ምን ሊፈጥር ይችላል ብሎ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ስለዚህ ሰው መብላት ካልቻለ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ‹‹የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል›› እንዳሉት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሕዝብ መሪውን ከመብላቱ በፊት መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡
ሪፖርተር፡- የመንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ምን ይመስላል ይላሉ?
ዶ/ር እንዳለ፡- በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በአጠቃላይ 15 መሥሪያ ቤቶች ለይተን፣ ከመልካም አስተዳዳር መመዘኛዎች አንፃር ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ከእኛ በተሻለ ለእነዚህ ችግሮች ሲቪል ሰርቪስን ብትጠይቅ የተሻለ ነው፡፡ እኔ አንድ መረጃ ለማምጣት ወረዳ ብቻ ሦስትና አራት ቀናት ነው የሚፈጅብኝ፡፡ ያውም የምፈልገው መረጃው አለ ወይስ የለውም የሚለውን ለማወቅ ማለት ነው፡፡ የታደለ በኦንላይን ዓይቶ በቀጥታ መረጃ ይሰጥሃል፣ ወይም ራስህ ታገኘዋለህ፡፡ አሁን መንግሥት የመዋቅራዊ ለውጥ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ይህ የመዋቅራዊ ለውጥ ግን የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሽል አይደለም፡፡ ዓላማው ተቋማትን ለመመሥረትና አላስፈላጊ የሆኑትን ደግሞ ሰብሰብ ለማድረግ ነው በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን አገልገሎት ላይ ለውጡ አይታይም፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እንዲሰቀል፣ የኦሮሚያ ክልል መዝሙርም እንዲዘመር ሲደረግ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ድርጊቱ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው ያላችሁበትን ምክንያት ቢያብራሩልኝ?
ዶ/ር እንዳለ፡- ኢሕገ መንግሥታዊ ነው ያልነው በግልጽ ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር እንደምትከተል በሕግ ተቀምጧል፡፡ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሆነች ብቻ ተደንግጓል፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግሥት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ስለዚህ ባለቤቷ ማነው ከተባለ የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ የፌዴራል መንሥት አባል የሆኑት ደግሞ ሁሉም ክልሎች ናቸው ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ለየትኛውም ክልል አልተሰጠችም የሚል ነው መግለጫችን፡፡ ይህም ሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ ስለተቀመጠ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ የአዲስ አበባ የሥራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አማርኛ ነው ሲባል ግን የከተማ አስተዳደሩ አቅም በፈቀደ መጠን አሥርም ሃያም ቋንቋዎችን መጠቀም ይችላል፡፡ ይህ ግን የከተማ አስተዳደሩ አስተዳደራዊ ወጪዎቹን መሸፈን ከቻለ የሚከለክለው የለም፡፡ እኛም ይህን ያልነው ከሕገ መንግሥቱ አልፎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር በግልጽ የሚያስቀምጠው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- መግለጫ ካወጣችሁ በኋላ ጉዳዩን ተከታተላችሁት? ወይስ ቆሟል?
ዶ/ር እንዳለ፡- ይህን ጉዳይ መከታተተል ወይም አለመከታተል የእኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ በመግለጫችን እንዳየኸው ሕዝብ የሚቀበለውና የሚያምነው ከሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተርም የሚለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብን ፍላጎት መሠረት አድርጎ ፖሊሲ፣ አዋጅና መመርያ እንዲያወጣ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህን በሚያደርግበት ግን ኅብረተሰቡን ሊያሳትፍና ፍላጎቱን ግምት ውስጥ አስገብቶ ውሳኔ ሊወስን ይችላል ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከተቀበለውና ከተስማማ ሌሎች ክልሎችም እስካልተቃወሙ ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ነገር ግን መታወቅ ያለበት የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የአንድ ክልል አይደለችም፣ ወይም ለአንድ ክልል አልተሰጠችም፡፡ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ አዲስ አበባ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ መቀመጫው አዲስ አበባ ከሆነና የኦሮሚያ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው ትምህርት ቤቶች ካሉ ኦሮሚኛ ማስተማር፣ ባንዲራ ማውለብለብ ክልላዊ መዝመር ማዘመር ይቻላል፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ከተማ ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግሥቱ ነው ሲባል ይህች ከተማ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ነች ማለት ነው፡፡ የነዋሪዎቹም ስብጥር ኅብረ ብሔራዊ ቢሆንም ድርጊቱ ግን ይህንን መሠረታዊ መርህ የሚጥስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ የሚባል አዲስ ከተማ ሲያዋቅር በርካታ ቤቶችን ሕገወጥ በሚል አፍርሷል፣ አሁንም እያፈረሰ ነው፡፡ ድርጊቱን በሚመለከት ተቋማችሁ መግለጫ አውጥቷል፣ የመግለጫው አንድምታ ምንድነው?
ዶ/ር እንዳለ፡- የሸገር ከተማ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚያስተዳድራት ከተማ ናት፡፡ ነገር ግን ወደ ቤት ማፍረስ ሲሄዱ እንደ ተቋም አንድ ሰው ሕጋዊና ሕገወጥ የሚባለው ተርታ ለመግባት ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እና ውሳኔው ወቅታዊ አይደለም በሚል ነው ያወጣነው፡፡ ይህን ስንል የሸገር ከተማ አስተዳዳር ገና ከመመሥረቱ በፊት ቤት የማፍረስ ሥራ ውስጥ ተገብቷል፡፡ ሁለተኛ የከተማ አስተዳደሩ ከተመሠረተና ወደ ሥራ ከገባ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ማነው ሕጋዊ፣ ማነው ሕገወጥ የሚለውን በመለየት ማለትም ሕገወጥ ስንል ከእነሱ አመክንዮ በመነሳት ማለት ነው በዚያ ረገድ ተለይቶ የተሠራ ሥራ አይደለም፡፡ ሰው ጎዳና ላይ የሚያድረው በማጣቱ እንጂ ሕጋዊ ወይም ሕገወጥ ስለሆነ አይደለም፡፡ ጎዳና ላይ መውጣት ሕገወጥነት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሕገወጥነት የሚለውን ከእነሱ ትርጉም እንዋስና ሕጋዊ ማነው ሕገወጥ ማነው፣ የሚለውን በጥናት ተመሥርቶ ነበር መከወን የነበረበት፡፡ እንግዲህ መመርያው የሚለው ከ2005 ዓ.ም. በኋላ የተሠሩ ቤቶች መፍረስ አለባቸው ነው፡፡ ነገር ግን ከ2005 ዓ.ም. በፊት የተሠሩ ቤቶች ላይ ጥናት ተደርጓል የሚለውን ስናይ በቂ ጥናት ተደርጓል ወይስ አልተደረገም ለሚለው፣ እኛ ባለን መረጃ መሠረት በቂ ጥናት አልተደረገም፡፡ ለምሳሌ ከ17 ዓመታት በፊት የተሠራ ቤት ፈርሷል፡፡ ሁለተኛ የሸገር ከተማ በሚዋቀርበት ወቅት በርካታ ቦታዎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የነበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ በሚሄዱበት ጊዜ የእነዚሀ ቤቶች መረጃና ማስረጃ የሚኖረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡
ለምሳሌ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ወደ ኦሮሚያ ክልል የገቡ አሉ፡፡ የእነዚህ ቤቶች መረጃ ያለው ግን አዲስ አበባ ነው፡፡ ነገር ግን መረጃው ከአዲስ አበባ ወደዚያ ሳይሄድ የፈረሱ ቤቶች አሉ፡፡ ሌላው ጉዳይ ውሳኔው የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም የሚል ግንዛቤ ነው ያለን፡፡ ፖለቲካ ስንል ምን ማለት ነው? ከጦርነት የወጣነው በቅርብ ነው፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የፈለሱ ዜጎች አሉ፡፡ በውስጥ ተፈናቃይ ከዓለም አንደኛ ነን፡፡ ዩክሬንን ስታይ በጦርነት ምክንያት በልዩ ሁኔታ ከእኛ ትበልጠናለች፡፡ ስለዚህ አስተዳዳራዊ ቢባልም ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔ በምትወስንበት ጊዜ ደግሞ ያሉት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምንድናቸው የሚውን ነገር ከግምት ውስጥ አስገብተህ ነው፡፡ አገራችን ውስጥ ብዙ ተፈናቃዮች አሉ፡፡ እነዚህ ተፈናቃዮች ዕርዳታ ይፈልጋሉ፡፡ ወደድንም ጠላንም ኃላፊነቱ ያለው መንግሥት ትከሻ ላይ ነው፡፡ እንግዲህ የተሳሳተው ግንዛቤ ብዙ ተፈናቃዮች በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ካሉ ይህ የተፈናቃዮች ችግር የእነዚህ ክልሎች ችግር ብቻ አድርጎ የመውሰድ ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የተከሰተው የቦረናና የጉጂ ድርቅን ስታይ ሁሉም ሰው እንደምናየው ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ በዚህም የመንግሥት አስፈጻሚውና በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ዕሳቤ የተለያየ መሆኑን ታያለህ፡፡ ስለዚህ በርካታ ተፈናቃዮች ባሉባት አገር የተፈናቃዮችን ቁጥር መጨመር ተገቢ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ሕገወጥነትን መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ነው በሚል ነበር ማስተባበያ ሲሰጥ የነበረው እኮ?
ዶ/ር እንዳለ፡- እኛም ሕገወጥነትን አናበረታታም፣ ለሚዲያዎችም ስንገልጽ ሕገወጥነትን እያበረታታን አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ዜጎች ሕጋዊ መንገድ ስለጠበባቸው ነው ወደ ሕገወጥነት የሄዱት፡፡ ማንኛውም ዜጋ አገሬ ነው ብሎ ነው በሄደበት ቦታ ከአርሶ አደሩ ቦታ ገዝቶ ቤት ሠርቶ የሚኖረው፡፡ እነዚህ ዜጎች የገበሬ መሬት አይሸጥም ቢባልም ከገበሬም ገዝተው ነው፡፡ የሚገርመው እኮ መሬቱን የሸጠው አርሶ አደሩ የንብረት መብት አለው፡፡ ያንን ንብረት የማስተላለፍ መብት አለው፡፡ ከዚያ አንፃርም መታየት አለበት፡፡ ስለዚህ የአንተ መግዛትና መሸጥ ሕገወጥ ነው ከተባለ አርሶ አደሩ ግን ወደ እዚህኛው ወገን የማስተላለፍ መብት አለው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሰጠው መብት ነው፡፡ ለቤተሰቡ ወይም ለሚያውቀው ሰው የማስተላለፍ፡፡ ሁለተኛ ዜጎችን ማፈናቀል የመንግሥት መብት ነው ወይ? የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ሲታይ አጠቃላይ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህ ግን ግምት ውስጥ ያልገባና የተቻኮለ ውሳኔ ነው በሚል ነው የኦሮሚያ ክልልን ወይም የሸገር ከተማን የምንሞግተው፡፡ ቢያንስ ጊዜያዊ መጠለያ ልታዘጋጅላቸውና ማወያየት ትችላለህ፡፡ የተሰጠው የማስጠንቀቂያ መልዕክት በቂ ነው ወይስ አይደለም የሚሉትን ግምት ውስጥ አስገብተህና ዜጎችን አማክረህ ውሳኔ ብትወስን፣ ከዜጎቹ ከራሳቸው እኮ መፍትሔው ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለሆነም ውሳኔው በጥድፊያ የተደረገና ብዙ አማራጮችን ያላየ ነው በሚል ነው መግለጫ ያወጣነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ ከንቲባዋን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታና የፖሊስ ኃላፊዎች፣ ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለው የሚመጡ ዜጎች ለከተማዋ የደኅንነትና የፀጥታ ሥጋት መሆናቸውን አውስተው ነበር፡፡ የዕንባ ጠባቂ ተቋም ይህንን እንዴት ያየዋል?
ዶ/ር እንዳለ፡- እንዲህ ዓይነት ነገሮች ላይ ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች የማኅበረሰብ አንቂዎች መረዳት ያለባቸው፣ በውይይት ወቅት ብዙ ሐሳቦች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ የውይይቱ ዓውድ ደግሞ ሰዎችን ወዳልተፈለገ ትንታኔና ዕይታ ሊወስድ ይችላል፡፡ ስለዚህ የተናገሩትን ነገር ምንድነው የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እኛም በምክር ቤቶች ውስጥ በሚነሱ ሐሳቦች ላይ በመነሳት ትችት መስጠት ተገቢ ነው ብለን አናስብም፡፡ ግለሰቡ ከምንም ይነሳ ከምንም ሐሳቡ ትክክል እንዳልሆነ እንዲህ ብሎ በማስቀመጥ መገምገም ይቻላል፡፡ በምክር ቤቶች በሚወጡ ውሳኔዎች አስተያየት መስጠትም ሆነ ሌሎች የምርመራ ሥራዎች ማድረግ እንደሌለብን አዋጃችን ላይ ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ከተማ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ዋና ከተማ ነች፡፡ ስለዚህ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ የመውጣትና የመግባት መብትና ነፃነት አለው፡፡ አስፈላጊ ከሆነም የመኖር መብት አለው፡፡ የትኛውም የመንግሥት አስፈጻሚ አካል በብሔሬ፣ በሃይማኖቴ ወይም በሌላ መሥፈርት አውጥቶ አዲስ አበባ መግባት ወይም መኖር አትችልም የሚል መመርያ ሊያወጣ አይችልም፡፡
ከዚያ ውጪ መንግሥት ማሰብ ያለበት ዜጎች ወደ አዲስ አበባ ለምን ይመጣሉ የሚለውን መገምገም አለበት፡፡ እንደሚታወቀው ዜጎች በአራቱም አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ይህ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ አማራጭ የሥራ ዕድል ስላለ ነው፡፡ ፈልሰው ከሚመጡበት አካባቢ ደግሞ የተሻለ የሥራ ዕድል ስለሌለ ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ፖሊሲ ከተማ ተኮር ከሚሆን ይልቅ ገጠሩ አካባቢ ያለው ሰው ተራጋግቶ እንዲኖር ማድረግ አለባት፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልል መንግሥታት ይህን የማሟላት ኃላፊነት አለባቸው፡፡