Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በላይነህ ክንዴ ግሩፕ የፍራፍሬ ልማትን ተቀላቀለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በብላቴ በሎካ አባያ ወረዳ በተረከበው 550 ሔክታር መሬት ላይ በፍራፍሬና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በመመደብ ልማት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ 

በብላቴ ሎካ አባያ ወረዳ 550 ሔክታር መሬት የተረከበው ድርጅቱ፣  380 ሔክታር መሬት ላይ አትክልት ከማልማቱ አስቀድሞ የበጋ ስንዴ እያለማ የሚገኝ ሲሆን፣ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱን የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የእርሻ ዘርፍ አስፈጻሚ አንተነህ አብዋ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በሔክታር ከ30 እስከ 50 ኩንታል ለምግብ ፍጆታ የሚውል ስንዴ ለማልማትና ከዚህም በጥቂቱ ከ11,400 በላይ ኩንታል ስንዴ ለመሰብስብ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ከ600 በላይ ኩንታል ስንዴ ለዘር መጠቀማቸውን አብራርተዋል፡፡ 

ለዚህም ግሩፑ ለስንዴና ማዳበሪያ ግዥ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ያብራሩ ሲሆን፣ 400 ኩንታል ኤንቲኤስ፣ እንዲሁም 400 ኩንታል ዩሪያ መሬቱን ለማሰናዳት ማዳበሪያ መጠቀማቸውን አንተነህ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

የእርሻ ልማቱን ለማከናወን በአጠቃላይ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ከ20 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲሁም ወደ እርሻው የሚፈሰውን የወንዝ ውኃ ለመቆጣጠር 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ግድብ ገንብተዋል፡፡ 

የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የአባያ ሐይቅና የብላቴ ወንዝን ለእርሻው በዋነኛነት የሚጠቀም ሲሆን ዘመናዊ ፓምፖችን ለመጠቀም መሰናዳቱ ተጠቅሷል፡፡

በአንፃሩ በአካባቢው የዝናብ እጥረት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ከአባያ ሐይቅ እስከ እርሻው መዳረሻ ድረስ ሦስት ኪሎ ሜትር ያለውን ርቀት በፓምፕ ስቦ ለማምጣት መሠረተ ልማት መዘርጋቱን አንተነህ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የበጋ ስንዴ ማልማቱ ሲጠናቀቅ የአትክልትና የፍራፍሬ ልማቱ የሚቀጥል ሲሆን፣ አቮካዶ፣ ሙዝና ፓፓዬ ለማልማት የችግኝ ግዥ ፈጽሞ ለመትከል ዝግጅት ላይ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

መሬቱን ከተረከበ አራት ወራት ብቻ የሆነው የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ማልማቱንም ለማስቀጠል ከ40 ሔክታር መሬት በላይ አቮካዶ የተተከለ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ሙዝ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ እንዲሁም ፓፓዬ ለማልማት መታቀዱን ሥራ አስፈጻሚ አንተነህ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በዚህም መሬት ላይ ተጨማሪ ፍራፍሬዎችን ለማሰናዳት የችግኝ ማፍላት ሥራ እየሠራ ሲሆን፣ ለጊዜው ለ200 የአካባቢው ሠራተኞች፣ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ይኼም ቁጥር ወደ 500 ለማሳደግ መታቀዱ አንተነህ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን፣ ጉራጌ ዞን፣ ሲዳማ ክልልና ደቡብ ምዕራብ ክልል ላይ ሰፊ መሬቶችን ወስዶ እያለማ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በጉራጌ ዞን 5,000 ሔክታር መሬት፣ በወላይታ ዞን 1,000 ሔክታር መሬት፣ ደቡብ ምዕራብ 2,750 ሔክታር መሬት፣ እንዲሁም በሲዳማ ክልል 550 ሔክታር መሬት ተረክቦ የተለያዩ የግብርና ምርቶች እያለማ ይገኛል፡፡ 

በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአማራ ክልላዊ መንግሥት ቡሬ ከተማ የተገነባውና ፊቤላ ኢንዱስትሪያል የዘይት ፋብሪካ ከውጭ አገር የሚያስመጣውን የቅባት እህል ግብዓት በአገር ውስጥ ለመሸፈን እንዲያስችለው በጉራጌ ዞን የተረከበውን መሬት የሰሊጥ፣ የሱፍና የአኩሪ አተር ለማልማት ወደ ሥራ መግባቱን አንተነህ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ከደቡብ ምዕራብ የተረከበውን ከ350 እስከ 400 ሔክታር የሚሆነውን መሬት በቡና ምርት የተሸፈነ ሲሆን፣ ምርት ማምረት መጀመሩ ተጠቅሷል፡፡ በሌላ በኩል በወላይታ ዞን የተረከበውን መሬትም በቅባትና በጥራጥሬ እህል ለመሸፈን ማቀዱን አንተነህ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

እንደ የሥራ አስፈጻሚው አስተያየት ከሆነ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በጉራጌ ዞን ከተረከበው 5,000 ሔክታር መሬት 2,000 ሔክታር መሬት ተመንጥሮ፣ የቅባት እህሎችን ማለትም አኩሪ አተርና ሰሊጥ ማልማት መጀመሩን አውስተዋል፡፡ 

በሌላ በኩል በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር በአካባቢው ለምትገኘው መራሬ ከተማ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ለመዘርጋት የኮንክሪትና የእንጨት ፖል ዝርጋታ በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ እንተነህ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች