Tuesday, July 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ያልተስተዋለ ወረርሽኝ

በኤፍሬም ሰንበታ (ዶ/ር)

ይህንን መጣጥፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያት በኢትዮጵያዊነቴና በአስተዳደጌ በሚሰማኝ ኩራትና፣ እንደወረርሽኝ በፍጥነት እየተስፋፋ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ላይ ተፅዕኖ እያደረገ ያለ ሁኔታ አለ ብዬ በማመኔ ነው፡፡

ይኼውም ከበርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አንዱ ስለሆነው የአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም ስላለበት ሁኔታ ነው፡፡ ወረርሽኝና የአንድ ቋንቋ አጠቃቀም ምን ያገናኛቸው ይሆን? ለምትሉ፣ የቋንቋ ምሁር ባልሆንም እንዳብራራ ይፈቀድልኝ፡፡

ምንም እንኳን አብዛኛውን ሕይወቴን በትምህርትና በሥራ ያሳለፍኩት ከአገር ውጭ እየኖርኩና እንግሊዝኛ በመናገር ቢሆንም፣ የትውልድ አገሬ ማንኛውም ነገር ቋንቋዎቻችንን ጨምሮ ያሳሳኛል፣ ያሳስበኛልም፡፡ ስለዚህም ሊያሳስቡን ይገባል የምላቸውን አገር ነክ ጉዳዮች ዝም ብዬ ማለፍ ያዳግተኛል፡፡ አቅሜ በሚፈቅድልኝ መጠንም ለትውልድ አገሬ አስተዋጽኦ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከአሥራ አንድ ዓመታት በፊት እኔ ያገኘሁትን ትምህርት፣ የሥራና የኑሮ ልምድ ለአገሬ ሰዎች ለማካፈል ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት፡፡

የእኛ ቋንቋዎችን በሚመለከት ጉዳይ የምጽፍ እንደመሆኔ፣ የቋንቋ መሠረቴ ምን እንደሆነ መጥቀስ እወዳለሁ፡፡ የአባቴ አፍ መፍቻ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ሲሆን፣ የእናቴ ደግሞ አማርኛ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ቋንቋዎች በደንብ ይችሉ ነበር፡፡

በርካታ ቋንቋዎች ያሏት የቋንቋ ባለፀጋ አገር ውስጥ ተወልጄ በማደጌ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ግን አዲስ አበባ ውስጥ በማደጌ የተማርኩት አማርኛን ብቻ ስለሆነ፣ በዚህ ጽሑፍ የማስተላልፈው መልዕክት የማውቀውን አማርኛን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ሌሎቹ ሁሉ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሁላችን አክብሮትና እንክብካቤ የሚገባቸው የአገር ቅርሶችና ሀብት እንደሆኑ አምናለሁ፡፡

እኔን በጣም የሚያሳስበኝ እጅግ በሰፊው እየተለመደ የመጣው ተራ ሐሳብን እንኳን ለመግለጽ አማርኛ በቂ ያልሆነ እስከሚመስል ድረስ የእንግሊዝኛ ቃላትን እየተዋሱ ከአማርኛው ጋር ቀይጦ ማውራት ግዴታ ያህል ሆኖ መታየቱ ነው፡፡ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መጠን፣ ወጣቶችና አዛውንት፣ የተማረውና ምንም መደበኛ ትምህርት የሌለው፣ እንግሊዝኛ የሚችለውና የማይችለውም፣ በአገር ውስጥ የሚኖሩና ከአገር ውጭ ያሉም፣ አማርኛ ሲናገሩ የእንግሊዝኛ ቃላትን ጣል ጣል በማድረግ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሙጅር እያደረጉ ነው፡፡

የእንግሊዝኛ ቃላትና ስሞችም በግልና በመንግሥት ድርጅቶች፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ዝግጅቶች፣ የሰውን ስሞች ሳይቀር ተክተው በሰፊው በየቦታው ተሰግስገው ይታያሉ፡፡ የቋንቋ ሀብታም በሆነች አገራችን ይህንን ሁኔታ ሳስተውል ለምን ይሆን የሚል ጥያቄ አሳድሮብኛል፡፡ አስተሳሰባችንና ማንነታችን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖም ያሳስበኛል፡፡

የእንግሊዝኛ ቃላትን የመዋስ ከፍተኛ ዝንባሌ ምናልባት ዘመናዊነትን ያሳያል፣ አለዚያም የተማረ ያስመስላል የሚል አስተሳሰብ ይሆን? ወይም ከውጭ የሚመጣው የእኛ ከሆነው የተሻለ ነው የሚል አመለካከት ይሆን? መልሱን ከእኔ የተሻለ ብቃት ላላቸው የሥነ ልቦናና የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁሮች ትቼ፣ በየዕለቱ የማስተውላቸውንና የምሰማቸውን ላጋራችሁ እወዳለሁ፡፡

በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ የአንድ ስብሰባ ታዳሚ ነበር፡፡ ለስብሰባው ዋና ተናጋሪ አንድ የዶክተር ማዕረግ የነበረው ሰው ብዙ ቁምነገሮችን የያዘና ትምህርታዊ ንግግር አደረገ፡፡ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ የጥያቄና መልስ ጊዜ ሲጀምር ከታዳሚዎቹ አንድ አዛውንት የንግግሩን ይዘት ካደነቁ በኋላ፣ ተናጋሪውን ለምን እንደዚያ አላግባብ አማርኛንና እንግሊዝኛን እየደበላለቀ እንደተናገረ ጠየቁት፡፡ ተናጋሪውም ያልጠበቀው ጥያቄ ሆኖበትና አነጋገሩን በመገንዘብ ከኃፍረቱ ብዛት ላብ አሰመጠው፡፡

በለመደው ጉራማይሌ አነጋገርም የእሳቸውን ጥያቄ ለመመለስ ሲሞክር አፉ ተሳሰረበት፡፡ ከዚያ በኋላም የተጠየቁትን ጥያቄዎች መመለስ ዳገት ሆነበት፡፡ ልዩ ልዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኤጀንሲ፣ ኮሚሽን፣ ዳይሬክቶሬት፣ ወዘተ እየተባሉ ሲጠሩ ይታያሉ፡፡ በየጊዜው መረጃ የሚሰጠን የመንግሥት አካል ደግሞ ‹‹በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡ እነዚህን ስያሜዎች በትክክል የምንረዳ ስንቶቻችን እንሆን? እነዚህን ሊተኩ የሚችሉ የአማርኛ ቃላትስ ጠፍተው ይሆን? አንድ ጊዜ ደግሞ ለመብራት ወርኃዊ ክፍያ ለመፈጸም አቅራቢያዬ ወደነበረው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት ሄድኩና እንደገባሁ ያየኋት ለደንበኞች መረጃ ለመስጠት የተቀመጠች የምትመስል አንድ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ነበረች፡፡

እዚያ ስሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር የት እንደምከፍል ልጠይቃት ቀረብ ስል ጠረጴዛዋ ላይ የተቀመጠውን ስሟና የሥራ መደቧ የተጻፈበትን ምልክት አስተዋልኩት፡፡ በግዕዙ ፊደል ከስሟ ሥር ‹‹ከስተመር ኬር አድቮኬት›› የሚል ጽሑፍ አነበብኩ፡፡ ሥራው መረጃ መስጠት ለሆነ ሠራተኛ፣ ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ እንኳን የተለመደ የሥራ መደብ አጠራር አይደለም፡፡ ታዲያ ደንበኛን የሚረዳ ሳይሆን ግራ የሚያጋባ የእንግሊዝኛ አጠቃቀም እንዴት ተመረጠ በሚል ተገርሜ ሒሳቤን ከፍዬ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡

በቴሌቪዥን ዜና ሳዳምጥ በተደጋጋሚ ያስተዋልኩት ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞችና ሌሎችም በየቦታው፣ ገጠሩን ጨምሮ ለአካባቢው ሰዎች ንግግር ሲያደርጉ በተለመደው እንግሊዝኛ የተርከፈከፈበት አማርኛ ነው፡፡ በርከት ያሉ መጻፍና ማንበብ እንኳን የማይችሉ ሰዎች ያሉበት አገር ውስጥ እንዴት እንዲህ ዓይነት ስህተት ይሠራል? ንግግር ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ አዳማጩን ግንዛቤ ውስጥ መጨመር መሆኑስ ለምን ተረሳ? ለምን እያልኩ አጥብቄ እንድጠይቅ የተገደድኩት አብዛኞቹ የሚደባለቁት የእንግሊዝኛውን ቃላት መተካት የሚችሉ የተለመዱ የአማርኛ ቃላት በመኖራቸው ነው፡፡

በአማርኛ ስንጠቀምበት የኖርነው የምስጋና መግለጫ ‹‹አመሰግናለሁ›› ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በእንግሊዝኛው ‹‹Thank you›› ተለውጦ ይደመጣል፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት የንግድ ቤቶች ባህላዊ ምግብ ቤቶችን ጨምሮ በእንግሊዝኛ ቃላት የመሰየም ዝንባሌ በሰፊው መታየት ከጀመረ ከረምረም ብሏል፡፡ አንድ ያስገረመኝን እንደምሳሌ ለመጥቀስ፣ ‹‹ብራይት ሐውስ ክትፎ›› ነው፡፡ አዎ፡፡ ክትፎ ባህላዊው ተወዳጅ ምግባችን፤ በየሠፈሩ የሚታዩ የግል ትምህርት ቤቶችም ‹‹አካዳሚ›› ተብለዋል፡፡ ወደ ሰው ስሞችም ብንመለስ፣ ዳዊት አሁን ዴቭ፣ ሚካኤል ማይክ፣ ሳሙኤል ሳም፣ ኢየሩሳሌም ጀሪ፣ ወዘተ ሆነዋል፡፡

ሌላ ያስተዋልኩት ነገር ደግሞ የእንግሊዝኛ ቃላትን የምንጠቀም ከሆነ ምነው በቅጡ ብናደርገው የሚያስብል ነው፡፡ ለምሳሌ ብዙ ጊዜ ‹‹Communicate›› አደርገዋለሁ፣ እንዲሁም ‹‹Share›› አደርገዋለሁ ሲባል ይሰማል፡፡ ይህ እንግሊዝኛውን በተሳሳተ መንገድ መጠቀም ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አዲስ አበባ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ሥራና ከሥራ የሚያመላልሱት ሰማያዊ አውቶቡሶች ‹‹ፐብሊክ ሰርቪስ›› የሚል ምልክት ተጽፎባቸው ይታያሉ፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ጥያቄዎች ይመጡብኛል፡፡

የመጀመሪያው ለምን በግዕዙ ፊደል የተጻፉ የእንግሊዝኛ ቃላት መጠቀም አስፈላጊ ሆነ? ሁለተኛው ደግሞ አስፈላጊ ቢሆን እንኳን ለምን ትክክለኛ የእንግሊዝኛ ቃላት አልተመረጡም? ፐብሊክ ሰርቪስ የሚያመለክተው አውቶቡሶቹ ለሕዝብ አገልግሎት እንደሚሰጡ ሲሆን፣ እውነታው ግን እንደተረዳሁት ከሆነ አገልግሎት የሚሰጡት ለመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ነው፡፡

ይህስ ምነው ቢቀር ሊያስብል የሚችል የመጨረሻ ምሳሌዬ፣ በቅርቡ በሬድዮ የሰማሁት አባባል ነው፡፡ ይኼውም በአንድ ሐሳብ ዙሪያ በነበረ ውይይት አንድ ሰው እንዲህ አለ፣ ‹‹የዚህን ሐሳብ Positive እና Negative ጎኑን አይተን በምን way ልናስተካክለው እንደምንችል ማሰብ አለብን››፡፡

እስካሁን የጠቀስኳቸው ምሳሌዎች የሚያመለክቱትን ጉዳት በተጨባጭ ያስተዋልኩት ለሁለተኛ ዲግሪ ከሚማሩት ተማሪዎች ጋር በነበረኝ ቆይታ ነው፡፡ ይኼውም አብዛኞቹ ሐሳባቸው ባልተቀላቀለ አማርኛ መግለጽ አይችሉም፡፡ በእንግሊዝኛውም በጣም ይቸገራሉ፡፡

የእንግሊዝኛ ቃላት ምን ያህል በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ እየተደባለቁ እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ተስፋ የማደርገው ግን አማርኛ ላይ የሚታየውን ያህል እንደማይሆን ነው፡፡ ሁሉም ቋንቋዎቻችን የአገር ሀብቶች እንደመሆናቸው ልናጎለብታቸውና ልንንከባከባቸው እንደሚያስፈልግ አምናለሁ፡፡ አለዚያ አማርኛን ብንወስድ፣ በዚህ አካሄዱ ሊጠፋና እንደ ክሪዮል (ሃይቲ ውስጥ የሚነገር ቋንቋ) ሊሆን ይችል ይሆናል ብዬ እሠጋለሁ፡፡ ክሪዮል ፈረንሣይኛን ከነባር የአገሩ ቋንቋዎች ጋር በመደባለቅ የተፈጠረ ቋንቋ ሲሆን፣ ቋንቋ የሆነውም አጭር ሊባል በሚችል ጊዜ ነው፡፡

ዝግመተ ለውጥ ቋንቋዎችንም እንደሚነካ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው የውጭ ቃላት ወደ አንድ ቋንቋ እየገቡ የቋንቋው አካል የሚሆኑት፡፡ ይህ ያለ ነገር ስለሆነ አያሳስብም፡፡ የእኛ አያያዝ ግን ጉዳዩን ወደ ሌላ ጫፍ ወስደነው ቋንቋ ማጥፋት ደረጃ እንዳንደርስ የሚያሠጋ ነው፡፡ አንድ የእኛ የሆነ ቋንቋን ማጥፋት እኛነታችን በተወሰነ ደረጃ ማጥፋት ይሆን?

አንድ ቋንቋ ከተናጋሪው ሕዝብ ማንነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን የተረዳሁት ጣልያን አገር ሥራ ላይ ሆኜ ባሳለፍኩት ጊዜ ነበር፡፡ ይኼውም ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በእንግሊዝኛ በደንብ ብንግባባ እንኳን እነሱንና የአካባቢውን ሕዝብ የተረዳሁ የመሰለኝ በጣሊያንኛ ከእነሱ ጋር መነጋገር ስችል ነበር፡፡

በመጨረሻም ከቋንቋዎቻችን አንዱን አማርኛን ሲናገሩ የሚያስደስቱኝን ጥቂት ሰዎች ለምሳሌ ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ሐሳባቸውን በአማርኛ ሲገልጹ ውበትና ለዛ ባለው አነጋገር ሲሆን፣ የውጪ ቃል ቢዋሱ እንኳን በአማርኛ አቻ ለሌለው ሙያዊ ቃል ነው፡፡ ከእነዚህም አንዱ የአዕምሮ ሐኪሙ ፕሮፊሰር መስፍን አርዓያ ናቸው፡፡ መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁም ሌላው ናቸው፡፡ ሁለቱም የተወሳሰቡ ሐሳቦችን ለአድማጭ ግልጽ በሆነ መንገድ የውጭ ቃላትን አላግባብ ሳይዋሱ መናገር እንደሚቻል አሳይተውናል፡፡

ይህንን መጣጥፍ ስጽፍ የተመኘሁት ውጤት ቆም ብለን በቋንቋዎቻችን ዙሪያ ያለንን አካሄድ አስተውለን ወደሚያስፈልገው ማስተካከያ ሊመሩን የሚችሉ ውይይቶችን መቀስቀስ ነው፡፡ ተጀምረው ያሉ ውይይቶችም ካሉ ለማበረታታት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በኢትዮጵያዊነታችንና ባሉን እሴቶች ሊኖረን የሚገባንን ጤነኛ ኩራት ከማሳደግ አኳያ በትንሹም ቢሆን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles