Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁሉም ክልሎች የታየው የጤፍ ዋጋ ጭማሪ የመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበትን ማሻቀቡ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመጋቢት ወር በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች የታየው የጤፍ ዋጋ ጭማሪ ወርኃዊ የምግብ ዋጋ ግሽበትን እንዲያሻቅብ ማድረጉን፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በተጠናቀቀው ወር ከሰብል እህሎች በተለይም የጤፍ፣ እንዲሁም የአትክልና ፍራፍሬና የጥራጥሬ ምርቶች ዋጋ ጭማሪ እንዳሳየ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የተጋነነ የጤፍ ዋጋ ጭማሪ መደረቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስና ማሽላ በመሳሰሉት እህሎች ዋጋ ላይ በመጋቢት ወር ጭማሪ በመታየቱ የወሩ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር 32.8 ከመቶ ተመዝግቧል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር 34.2 በመቶ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በመጋቢት የጤፍ ዋጋ ጭማሪ በሁሉም ክልሎች የታየ ቢሆንም ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች በሆኑት ልብስና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫትና የአሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንዲሁ ጭማሪ መታየቱ ተጠቁሟል፡፡

የመጋቢት ወር አጠቃላይ ዋጋ ግሽበት መጠን የመጨመሩ ምክንያት ምግብ የሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ላይ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የታየው የዋጋ ግሽበት መጠን መጨመር መሆኑን፣ የስታስቲክስ አገልግሎት የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ሪፖርት ያሳያል፡፡

የመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በ5.7 ነጥብ ከመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የምግብ የኢንዴክሱ ክፍሎች በተመሳሳይ በ7.0 ነጥብ ከመቶ ጭማሪ ተመዝግቦባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት 3.9 ነጥብ በመቶ ያሻቀበ ሆኗል፡፡

ልክ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በኢትዮጵያም ማሳሰብ ከጀመረ መከራረሙን በተደጋጋሚ የሚናገሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ ለረዥም ዓመታት ሳያቋርጥ የቀጠለው የዋጋ ግሽበት የኑሮ ውድነትን እየወለደ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ ውጤቱ ወዴት ያመራል የሚለው ጉዳይ ደግሞ አሳሰቢነቱ የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

 የዋጋ ግሽበት ብዙ ጊዜ ከሚባባስባቸው አንዱና ዋናው ምክንያት በዓላት መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ በዓላትን ተከትለው የሚመጡ የዋጋ ጭማሪዎች በተለይም የምግብ ዋጋ ግሽበትን ከፍ እንደሚያደርጉት ያስረዳሉ፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ከዚህ ቀደም ይፋ ያደረገው የጥር ወር የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በጥር 2015 ዓ.ም. በነበሩ ሁለት ታላላቅ የሃይማኖት በዓላት ምክንያት የምግብ የኢንዴክሱ ዋጋ ግሽበት በመጠኑ ጨምሮ ነበር፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በተያዘው የሚያዚያ ወር በክርስትናና በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቅት የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት በመኖራቸው፣ እንዲሁም ከሰሞኑ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች በሚመረትባቸው አካባቢዎች ያጋጠመው የፀጥታ ችግር የምርት አቅርቦት ፍሰቱን ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ እያሻቀበ ያለውን የዋጋ ግሽበት ሊያባብሰው እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች