የዓለም አትሌቲክስና ዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እ.ኤ.አ. 2024 በፈረንሣይ ፓሪስ እ.ኤ.አ. በ2024 በሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ የኦሊምፒክ ስፖርት ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
አዲሱ የኦሊምፒክ ውድድር የማራቶን የድብልቅ ዕርምጃ ውድድር (Marathon Race Walk Mixed Rely) የሚባል ሲሆን፣ 25 ቡድኖች እያንዳንዳቸው አንድ ወንድና አንድ ሴት በመሆን የሚካፈሉበት ነው፡፡ አዲሱ የውድድር ዓይነት ፓሪስ በኦሊምፒክ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ይካሄዳል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲሱን የውድድር ዓይነት ያሳወቀ ሲሆን፣ እያንዳንዱ አትሌት በ10 ኪሎ ሜትር ውስጥ ተለዋጭ የወንድና ሴት አትሌቶችን በመያዝ እንደሚሳተፉ አስታውቋል፡፡
ስፖርቱን ማራቶን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የተመረጠው ተወዳጅ መሆኑና ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጋር ያለውን ቁርኝት በመገንዘብ እንደሆነ የዓለም አትሌቲክስ በመረጃው አመልክቷል፡፡
ውድድሩ በማዕከላዊ ፓሪስ በሚገኘው ኤፍ ታወር ግርጌ የሚከናወን ሲሆን፣ በሦስት ሰዓታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ አትሌቶች በአዲሱ ስፖርት ዓይነት ለመካፈል የሚችሉበት አዲስ የማጣሪያ ውድድር መሥፈርት በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
በድብልቅ ሪሌይ ውድድሩ ወንዶችና ሴት አትሌቶች በአንድ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት ሲሆን፣ በጣም አዝናኝና በተመልካች ተወዳጅ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አግኝቷል፡፡ የ2024 ኦሊምፒክ ጨዋታን የምታስተናግደው ፓሪስ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው፡፡
ከሐምሌ 26 እስከ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚከናወነው የፓሪሱ ኦሊምፒክ ጨዋታ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች መርሐ ግብር ታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት በተለይ አትሌቶች ወደ ብሔራዊ ቡድን የሚመጡበት መሥፈርት የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም የኦሪጎን ዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎን ከግምት ያስገባ መስፈርት በቀዳሚነት ይታያል፡፡
አትሌቶች የሚመረጡት ባላቸው የብቃት ደረጃ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ 50 በመቶ አትሌቶች ያሉበት ወቅታዊ አቋም ሲሆን፣ ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ ደረጃ ያላቸው ብቃት እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የብቃት ደረጃ የመለየት ሥርዓቱን የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት አማይነት የፀደቀ ሲሆን፣ የብቃት መለኪያ ዝርዝሮች ሲቀመጡ፣ አትሌቶች የሚወዳደሩበትን የውድድር ዓይነትና ቁጥር ከግምት ያስገባ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ መርሐ ግብር መሠረት 23 የሴቶች የውድድር ዓይነትና 23 የወንዶች የውድድር ዓይነት፣ እንዲሁም 4 × 400 ድብልቅ ሪሌይና የከ35 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ውድድር እንመዲካሄድ ታውቋል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ይፋ ባደረገው የቅድመ የማጣሪያ ውድድር መርሐ ግብር መሠረት፣ 10 ሺሕ ሜትር የጥምር ውድድር ዕርምጃ እንዲሁም ድብልቅ ሪሌይ ከታኅሳስ 22 እስከ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ውስጥ የሚከናወኑ ሲሆን፣ ብቁ ሆነው የሚመረጡ አትሌቶች ወደ ፓሪሱ ኦሊምፒክ የሚያመሩ ይሆናል፡፡