Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየበዓል ገበያ ቅኝት

የበዓል ገበያ ቅኝት

ቀን:

በዓላት በተቃረቡ ወቅት ሻጭ ንብረቱን ገዥ ደግሞ ጥሬ ብሩን በመያዝ ገበያ ላይ ለመገናኘት ይሰናዳሉ፡፡

ብዙ ጊዜ አንገብጋቢ የሚባል ትልቅ ጉዳይ ካልገጠመ በስተቀር ገበሬ ሰንጋውን በግና ፍየሉን፣ እንዲሁም ጤፍና ቅቤውን ወደ ገበያ አውጥቶ የሚሸጠው በዓላትን ተንተርሶ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ በዓላትን ጠብቀው እንዲደርሱ ታስበው የሚዘሩ አዝዕርቶች በአርሶ አደሩ ዘንድ የተለመዱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

ታዲያ ለበዓል ተብለው የተዘጋጁት ሁሉ ቀናቸውን ጠብቀው የእስልምናም ሆነ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደ እምነታቸው በሚያከብሯቸው ትልልቅ በዓላት ሰሞን በገበያው ይቀርባሉ፡፡ የኅብረተሰቡ ግርግርም የተለየ ድባብን ይዞ ይመጣል፡፡

በዓል ሊከበር ከሳምንት ያላነሰ ጊዜ ሲቀረው አርሶ አደሩም የበዓል ዕለት ዳጎስ ያለ ገንዘብ አገኝበት ይሆናል ያለውን ምርት ይዞ ወደ ገበያ ሲወርድ፣ ከአርሶ አደሩ በቅናሽ ዋጋ በመግዛት ወደ ከተሜ ዘንድ ቢደርስ የተሻለ ትርፍ                                                                                                                   ይገኝ ይሆናል በማለትም አርሶ አደሩና ጅምላና ቸርቻሪ ነጋዴው ሁለቱ ባለ ጉዳዮች በአንድ መድረክ ተገናኝተው ይከራከራሉ፣ ጨምር ቀንስ ይባባላሉ፣ በገዥም ሆነ በሻጭ መካከል ሁለቱን ለማስማማት በሽምግልናም ይሁን በድለላ ጣልቃ በመግባት በዚህ ዋጋ ሽጥ በዚህ ዋጋ ግዛ በማለት የሚያስማሙ ሰዎችም በገበያው ላይ ይታያሉ፡፡

ገበያው ከወትሮው በተለየ በገዥም፣ በሻጭም፣ በአሻሻጭም ይደምቃል፡፡ በሠንጋና በሙክት፣ በዶሮና በዕንቁላል፣ በአጠቃላይ በዓሉን በዓል በዓል በሚያስመስሉ ነገሮች ሁሉ ገበያው ይደራል፣ ይጨናነቃል፡፡

አርሶ አደሩ ያደለበውን በግና ፍየል በዓልን ምክንያት አድርጎ መብላት ቢፈልግም፣ ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ስለሚኖሩበት የጎደለውን ለማሟላት ወደ ገበያ እንደሚያወጣቸው ሁሉ፣ ገበያ ገብቶ ዋጋውና ኪሱ ሰማይና ምድር ሸማች ከሚሆኑበት በዓላት ባልመጡ ብሎ የሚያማርር ጥቂት አይደለም፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ነገሮች ዋጋቸው ጣራ እየነካ አልቀመስ ብሎ ኪስን ቢፈታተኑም፣ ‹‹ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም›› በማለት በአቅም እንደ ቤቱና እንደ ኪስ ለማክበር መሞከር አይቀርም፡፡

ከፊታችን በድምቀት ለሚከበረው የትንሳዔ በዓል ሁሉም በየአቅሙ ለማክበር ሲንቀሳቀስ ይስተዋላል፡፡ መንግሥት በበኩሉ በመዲናዋ ለሚገኘው ሕዝብ በቂ የሆነ የሥጋም ሆነ የእህል አቅርቦትን እያቀረበ እንደሚገኝና እንደሚያቀርብ ይናገራል፡፡

በቀጣይ ለሚከበሩት ታላላቅ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት የፆም መፍቻ በዓላት በተለያዩ የመዲናዋ የገበያ አካባቢዎች ምን ቀርቧል የሚለውን ሪፖርተር ተዘዋውሮ ምልከታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ በሳሪስ አካባቢ ባደረገው የገበያ ቅኝት አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ከ37 እስከ 40 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ነጭ ሽንኩርት አንድ ኪሎ ከ210 እስከ 220 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ባሮ ሽንኩርት አንድ ኪሎ ከ40 እስከ 45 እየተሸጠ መሆኑንና አብዛኛው ሸማቾች የሚፈልጉት የቀይ ሽንኩርት ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረው እየተወደደ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሸማቾች ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአበሻ ዶሮ ከ1‚200 እስከ 1‚700 ድረስ እየተሸጠ ሲሆን፣ የፈረንጅ ወይም ደግሞ ክልስ ተብለው የሚጠራው ዶሮ ከ1‚000 እስከ 1‚600 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በተመሳሳይ የሐበሻ ዕንቁላል ከ12 ብር ከሃምሳ ሳንቲም እስከ 13 ብር ድረስ እየተሸጠ ሲሆን፣ የሐበሻ ዕንቁላል ከ11 ብር ከሃምሳ ሳንቲም እስከ 12 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የሸኖ ለጋ ቅቤ አንድ ኪሎ ከ790 ብር እስከ 800 ብር በመሸጥ ላይ ነው፡፡ መካከለኛ የሚባለው ቅቤ 600 ብር እየተሸጠ መሆኑን ሪፖርተር ለማየት ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የበዓል ዕለት አብዛኛው ሰው እንደ ማባያ የሚጠቀሙት አይቤ አንድ ኪሎ ከ390 ብር እስከ 400 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡

በሳሪስ አካባቢም የሚገኙ አብዛኛው ነጋዴዎች የፋሲካ በዓል ከሌሎች በዓሎች የተለየ ስለሚያደርገው የተለያዩ ምርቶችንና ለምግብነት የሚውሉ ግብዓቶችን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በሌላ በኩል የቁም እንስሳት ማለትም ፍየልና በግ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በዚህ መሠረት መካከለኛ በግ ከ7‚000 እስከ 9‚000 ብር ድረስ እየተሸጠ ሲሆን፣ ትልቅ የሚባለው በግ ከ12‚000 እስከ 15‚000 ብር ድረስ ይጠራበታል፡፡ ትንሽ የሚባለው በግ ደግሞ ከ5‚000 ብር ጀምሮ ነው፡፡ በሌላ በኩል ጠቦት ወይም ትንሽ የሚባለው ፍየል ከ6‚000 እስከ 7‚000 እየተሸጠ ሲሆን፣ መካከለኛ የሚባለው ደግሞ ከ8‚000 እስከ 13‚000 ሺሕ ብር ድረስ ነው፡፡ ትልቅ የሚባለው ፍየል ከ14‚000 እስከ 17‚000 ሺሕ ብር ድረስ ይጠራበታል፡፡

በላፍቶ ገበያ አነስተኛ በግ ከ4‚500 ብር እስከ 6‚000 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ መካከለኛ በግ ደግሞ ከ7‚000 እስከ 8‚000 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ሙክት የሚባለው በግ ከ10‚000 እስከ 15‚000 ብር ድረስ ሲጠራበት፣ መካከለኛ የሚባለው ፍየል ከ8‚000 እስከ 11‚000 ሺሕ እየተሸጠ መሆኑን ሪፖርተር ለመመልከት ችሏል፡፡

ትልቅ የሚባለው ፍየል ደግሞ ከ13‚000 እስከ ከ17‚000 ሺሕ ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡ በላፍቶ ገበያ ተሰማርተው የሚገኙ ነጋዴዎች በሰሜኑ ክፍል መንገድ በመዘጋቱ የተነሳ ፍየልና በግ በብዛት ማስገባት አለመቻላቸውንና በብዛት የያዙትም ከሦስት ወር በፊት ያመጧቸው ከብቶች መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በበግና በፍየል ላይ ዋጋ ጨምረው ለመሸጥ መገደዳቸውን ማኅበረሰቡም ይኼን በመረዳት ከሌሎች ቦታዎች ጋር ዋጋዎችን በማነፃፀር እንዲገዛ ጠቁመዋል፡፡

በየካ ሾላ ገበያ ቅኝት ባደረግንበት ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሰዓት ገበያው የተቀዛቀዘ ነበር፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች እንዳሉንም፣ ሸማቹ ይህንንም ያህል እየሸመተ አይደለም፡፡ በገበያው የወላይታ የሚባለው ዶሮ ከ700 ብር እስከ 800 ብር እንደሚሸጥ ነጋዴዎች ነግረውናል፡፡

አንድ የሀበሻ እንቁላል 12 ብር ሲሆን፣ የፈረንጅ ደግሞ አሥር ብር ይሸጣል፡፡

ቅቤ የበሰለው በኪሎ 700 ብር፣ መካከለኛ 800 ብር ለጋ የሚባለው ደግሞ 850 ብር እንደሆነም ነግረውናል፡፡

የከብት ንግድ ከሚካሄድባቸው የአዲስ አበባ ገበያዎች አንዱ በሆነው ሸጐሌ ገበያ ቅኝት ባደረግንበት ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ገበያ አለመቆሙን ታዝበናል፡፡

ሪፖርተር የገበያ ቅኝቱን ያደረገው ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በመሆኑ የበዓል ገበያው ባይደራም፣ በእሑድ ገበያ የሚነግዱ ነጋዴዎች በዓልን አስመልክቶ በተለያዩ ሥፍራዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ሽያጭ እያከናወኑ መሆኑን ተመልክቷል፡፡

በተመስገን ተጋፋውና በአበበ ፍቅር

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...