የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የተቋቋመው በወቅቱ በነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ይዞታ ዳር ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ዳሩ መሀል ሆኗል፡፡ ድርጅቱም እስካሁን ድረስ በተቋቋመበት ቦታ ላይ ሆኖ የአቅሙን ያህል አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ አቶ ሰይድ እንድሪስ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በድርጅቱ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለኅብረተሰቡ ዘመኑን የዋጀና ጥራቱን የጠበቀ ሥጋ በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ያቀደው ነገር አለ?
አቶ ሰይድ፡- የአዲስ አበባን ኅብረተሰብ የሥጋ ፍላጎት በመጠኑም ቢሆን የማርካት አስተዋጽኦ አላቸው ተብሎ እምነት የተጣለባቸው ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቄራዎችን ለመገንባት የሚያስችሉ ጥናቶች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ቋሚ ቄራው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዕርድ አገልግሎት መስጪያ አዳራሽ፣ ለቢሮ ሥራና ለሌሎችም የሚያገለግሉ ክፍሎችንና ለደንበኞች ሥጋ የሚሸጥበት መደብርን ያካተተ ነው፡፡ ተንቀሳቃሹ ቄራ ደግሞ ከተሽከርካሪው ጋር የተያያዘ የእንስሳት ማረጃ ክፍል ያሉት ሲሆን፣ ተረፈ ምርቱን ሰብስቦ ለአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሚያስረክብበት አካሄድ ተመቻችሎታል፡፡ የቋሚው ቄራ ሕንፃ ጥናት ተጠናቆ ወደ ግንባታ ፈቃድ ተገብቷል፡፡ የተንቀሳቃሽ ቄራው ጥናት ግን ገና በሒደት ላይ ነው፡፡ ሕንፃው የሚገነባው በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ሲሆን፣ የዕርድ አገልግሎት መስጪያው አዳራሽ ግን በየትኛው አካባቢ ቢሠራ ይሻላል የሚለውን ለይቶ ለማወቅ እየተጠና ነው፡፡ ለሕንፃው ግንባታ ከንድፍ እስከ ቁጥጥር ድረስ ለሚያስፈልገው ሥራ ድርጅቱ ከኮንስትራክሽን ሱፐርቪዥን ድርጅት ጋር የ16 ሚሊዮን ብር ውል ገብቷል፡፡ የተንቀሳቃሹ ቄራ ለኢትዮጵያ እንደ አዲስ ቢታይም፣ ቻይናን ጨምሮ በአውሮፓና በአፍሪካ የሚገኙ አንዳንድ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ ጥሩ ውጤት አስገኝቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ከቋሚ ቄራ ይልቅ ተንቀሳቃሹ ቄራ ብዙ ትኩረትን እየሳበ መጥቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅቱ መሀል ከተማ ውስጥ ስለሆነና የሚያወጣውም መጥፎ ጠረን ለጤና ጠንቅ በመሆኑ ከከተማዋ አውጥቶ በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት ታስቦ ነበር፡፡ ለግንባታውም ከፈረንሣይ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ መገኘቱ በተደጋጋሚ ተገልጾ ነበር፡፡ እስካሁን ግን ምንም የታየ ነገር የለም፡፡ ለምንድነው?
አቶ ሰይድ፡- ቄራን ከከተማ በማውጣት ችግሩን አንፈታውም፡፡ መሆን ያለበት በዓለም ያሉትን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ ቄራን ማዘመን ነው፡፡ ሽታ ወይም መጥፎ ጠረን የሚጠፋው ምንም ዓይነት ነገር ባለመጣል ነው፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ ከሚታረዱት እንስሳት ከእግር ጥፍር ጀምሮ ምንም የሚጣል ነገር የለም፡፡ ነገር ግን መቀቀል ሒደት ወቅት መጥፎ ጠረን ያለው ሽታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህንንም ሽታ ሊያስቀር የሚችል የሽታ መቆጣጠሪያ ማሽን ተገዝቶ ለበርካታ ዓመታት ያህል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የመቆጣጠሪያው ማሽን ከጊዜ ብዛት የተነሳ አርጅቶ በመበጣጠሱ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል፡፡ እንደገና ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ እንዲቻል አስፈላጊ የሆኑ የመለዋወጫ ዕቃዎች ተገዝተው ቀርበዋል፡፡ ማሽኑ በተፈበረከበት ኩባንያ ውስጥ የሚሠራ መሃንዲስ መጥቶ የመገጣጠሙን ሥራ እንዲያከናውን እየተጠበቀ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የግንባታው ጉዳይስ?
አቶ ሰይድ፡- እንደተባለውም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የቀድሞ ወረዳ አንድ አሁን ወረዳ 14 ወደ 20 ሔክታር የሚሆን የማስፋፊያ ቦታ ተሰጥቶን፣ ለዚህም የፈረንሣይ መንግሥት 70.5 ሚሊዮን ዩሮ በአነስተኛ ወለድ ለማበደር ፈቃደኝነቱን አሳይቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመንግሥት ለውጥና ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ተግባራዊ ሳይሆን የሦስት ዓመት የጊዜ ገደቡን በማሳለፉ የፈረንሣይ መንግሥት የሰጠው የጊዜ ገደብ ስላለፈ ውሉ ይቋረጥልኝ የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ በአነስተኛ የወለድ ክፍያ የተፈቀደው ገንዘብ እንደ ሀገር ሲታይ ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ ገንዘቡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ እንዲውል ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የጥራትና ምርታማነት አመራር (ካይዘን) ወይም ፈጠራ፣ አዲስ አስተሳሰብንና ስኬታማነትን የሚያበረታታ እንዲሁም ጥራትና ምርታማነትን በመፍጠር ውጤታማ የሚያደርግ ሥራ በድርጅቱ መተግበሩ ያስገኘውን ውጤት ሊያስረዱን ይችላሉ?
አቶ ሰይድ፡- በድርጅቱ የካይዘን ትግበራ የተካሄደው ከ2013 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህም ከፍተኛ መሻሻሎችን አስመዝግበናል፡፡ የካይዘን ትግበራ ከመከናወኑ አስቀድሞ አንድ ቅቅል ለመቀቀል እስከ ሁለት ሰዓት የሚፈጅበት ጊዜ ነበር፡፡ ከትግበራው ወዲህ ግን ወደ 45 ደቂቃ ወርዷል፡፡ ሠራተኛው ሥራውን ቶሎ እንዲጨርስ አስችሏል፡፡ ለዚህ ይውል የነበረው የነዳጅ መጠን እንዲቀንስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል፡፡ ከትግብራው በፊት ከዕርድ አገልግሎት፣ ከተረፈ ምርት፣ ከቆዳና ሌጦ ኮሚሽንና ከልዩ ልዩ ገቢዎች በዓመት ይገኝ የነበረው ገቢ ሁለት ወይም ሦስት ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከትግበራው ወዲህ ግን በዘንድሮው በጀት ዓመት ማለትም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ገቢው ወደ 30 ሚሊዮን ብር፣ የዕርድ ቁጥሩም ድርቁ የተወሰነ ጉዳት ማስከተሉ እንዳለ ሆኖ ወደ አምስት በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የቄራዎች ድርጅት በ1949 ዓ.ም. ሲቋቋም በቀን ለ300 ሠንጋዎች የዕርድ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን 4,500 ሠንጋዎችን ያርዳል፡፡
ሪፖርተር፡- በቴክኖሎጂ የታገዘው የሠራተኛ ቁጥጥር ምን ያህል ገንዘብ ከወጪ አድኗል? ለሠራተኛውስ ምን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል?
አቶ ሰይድ፡- የሠራተኛ መግቢያና መውጫ ሰዓት መቆጣጠሪያ በቴክኖሎጂ የታገዘና የአሻራ ሥርዓት መሆኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን የካርድ ፊርማ አስቀርቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ሠራተኞች ፊርማቸውን በመመዝገብያ ላይ የሚያኖሩት በወረፋ ሲሆን፣ ይህም ጊዜ ይፈጅ ነበር፡፡ ከካይዘን ትግበራው ወዲህ አሻራ ለማሳረፍ የሚወስደው ጊዜ የማይክሮ ሰከንድ ብቻ ሆኗል፡፡ በዚህም ለካርድ መግዣ በየወሩ ይወጣ የነበረ ከ324,000 ብር በላይ ከወጪ ለማዳን ተችሏል፡፡ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለሠራተኞቹም በካይዘን ትግበራ ዙሪያ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱን በተዝረከረከና በተዘበራረቀ ሁኔታ ላይ የነበሩ ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጪያ መሣሪያዎችና ሰነዶች ሥርዓት እንዲይዙ አድርጓል፡፡ የሲሲቲቪ ካሜራ መገጠሙም የካይዘን ትግበራው ካስገኛቸው ጠቀሜታዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገልግሎት አሰጣጣችሁ ላይ እንደ ችግር የምታነሱት ጉዳይ አለ?
አቶ ሰይድ፡- በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትልቅ እንቅፋት የሆነው ሕገወጥ የእንስሳት ዕርድ ነው፡፡ ችግሩ ሊከሰት የቻለውም ቄራዎች ተደራሽ ባለመሆናቸውና በተለያዩ ቦታዎችና ወረዳዎች የእንስሳት መሸጫ በሮች በመከፈታቸው ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመወጣት ገበያውንና ቄራውን የማስተሳሰር ሥራ ይከናወናል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለትንሳዔ በዓል ዝግጅታችሁ ቢገልጹልን፡፡ ምን ያህል ሠንጋ ለበዓሉ ይታረዳ? ለዚህስ ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት አድርጋችኋል?
አቶ ሰይድ፡- ለትንሳዔ በዓል እስከ 3000 ለሚሆኑ ሠንጋዎች የዕርድ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ልዩ ልዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከዝግጅት ሥራዎቻችን መካከልም ሥጋ በብልት ለየደንበኞች (ልኳንዳ ነጋዴዎች) ለሚያጓጉዙ 67 ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ መገጠሙ ይገኝበትል፡፡ ተሽከርካሪዎችም ሰርቪስ ተደርጎላቸው ለስምሪት ዝግጁ ሆነው በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ሠራተኞችም እረፍት ማድረጋቸውና በዓመት ሁለት ጊዜ የጤና ምርመራ ማድረጋቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ላይ የተጫነው ጂፒኤስ አሽከርካሪው ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ሲያሽከረክር፣ ቁልፍ አጥፍቶ ወደ ሌላ ቦታ ሲሄድ፣ በአንድ ልኳንዳ ቤት ሥጋ ለማራገፍ ወይም ለማስረከብ ከተወሰነው ሰዓት በላይ ካቆመና ሌላም አላስፈላጊ ሥራ ካከናወነ ለአመራሩ አካል ወዲያውኑ ያሳውቃል፡፡ በተረፈ ዕርድ በብዛት የሚከናወነው ከትንሳዔ በዓል ይልቅ በዓብይ ፆም መያዣ ቀን ነው፡፡ በትንሳዔ በዓል ሰው በየቤቱ በግ ያርዳል፡፡ በየሰፈሩም ቅርጫ ሥጋ ይቀራጫል፡፡ በዓብይ ፆም መያዣ ላይ ግን ሁሉም ሰው ከልኳንዳ ቤት ሥጋ ይገዛል፡፡