Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበጀት ከዝግጅት ጀምሮ ሊታሰብበት የሚገባ የአገር የደም ሥር ነው

በጀት ከዝግጅት ጀምሮ ሊታሰብበት የሚገባ የአገር የደም ሥር ነው

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

የምንገኝበት ጊዜ የመንግሥት በጀት ማፅደቂያም ሆነ ዓመታዊ አፈጻጸም መገምገሚያ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ግን በየመሥሪያ ቤቱ ገና የተያዘው የዓመት በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ሳይረጋገጥ፣ በተለምዶ ለቀጣዩ ዓመት በጀት ለማዘጋጀት መረጃ የሚሰበሰብበት ጊዜ ነው፡፡ የተያዘው በጀትም ሆነ የመጭው ዘመን በጀት በየደረጃው ለሕዝብና ለአገር አግባብ ባለውና በሥርዓት ጥቅም ላይ ይውል ዘንድ ስለጉዳዩ ከወዲሁ መነጋገር እንደሚያስፈልግ በማመን አንዳንድ ነጥቦችን ላስታውስ እወዳለሁ፡፡

እንደ አገር የመንግሥት በጀት ነገር ከተነሳ ካለፉት ዓመታት በተለየ፣ በአገር ደረጃ የበጀት አጠቃቀምና አካሄድ እንደሚስተዋል መታዘብ እየቻልን ነው፡፡ ቀዳሚው ነገር የፌዴራሉ መንግሥት በተለይም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በቀጥታ የሚያዝበት በዕርዳታም ሆነ በብድር የተገኘ ከፍተኛ ሀብት ለሜጋ ፕሮጀክቶች (ለቤተ መንግሥት ዕድሳትና ግንባታ፣ ለፓርኮችና ትልልቅ ልጆች ልማት…) እየዋለ መሆኑን ደጋግመን አዳምጠናል፡፡ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤትና በባለሀብቶች ተሳትፎ፣ ብሎም በረጂ አካላት “ተከናወኑ” የሚባሉ ተግባራትም ትንሽ አይደሉም፡፡

እንዲህ ያሉ አዲስ ዓይነት አካሄዶች ከሚያመጡት ውጤት አንፃር መልካም ስለመሆናቸው መናገር ቢቻልም፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ የበጀት አጠቃቀም ለማስፈን እንቅፋት እንዳይሆኑ ሥጋታቸውን የሚያስቀምጡ ወገኖች ግን እየተበራከቱ ነው፡፡ በተለይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ቋሚ ኮሚቴዎቹ ሳያውቋቸውና ሳይከታተሏቸው ገቢ ወጭ የሚደረጉ ሀብቶች ቢያንስ አጠቃቀሙን ለሐሜት እንዳያጋልጡት ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡

የወጪ ምርትን በማሳደግ ገቢን ለማሻሻል፣ የዕርዳታና ብድር አማራጮችን በማስፋት የበጀት ጉድለትን ለመሙላት መረባረብ ቸል እየተባለ በአገር ውስጥ ብድር፣ ካልበለፀገ ሕዝብ በታክስና ቀረጥ በገፍ ሰፊ ገቢ ለመሰብሰብና የተለጠጥን በጀት ለመሙላት መዳከርም በዜጎች ኑሮ ላይ ጫናና ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይጋብዝ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡ ነገሮችን በሚዛን የሰፈሩ መጓዝ ይበጃል፡፡ ለሁሉም ወደ ጉዳዬ ልመለስ፡፡ እንደሚታወቀው ‹‹በጀት›› የሚባለው በቁጥሮች አማካይነት የሚገለጽ፣ ለተወሰነ ጊዜ የሚዘጋጅ ዕቅድ ነው፡፡ በጀት የታቀደውን የሽያጭ መጠን (ብዛት) ግዥዎችን፣ ግብዓቶችን፣ ወጪዎችን፣ ንብረቶችና ዕዳዎችን የገንዘብ ፍሰቶችን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ የንግድ ድርጅቶችና ተቋሞች ሥራዎችን ወዘተ. መለኪያ ባለው ወይም ልኬታ በተበጀለት ሁኔታ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችንም ይይዛል፡፡

በሌላ አነጋገር በጀት ማለት በገንዘብ የተገለጸ ድርጅታዊ/መንግሥታዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሁሉም እንዳቅሙ ያቅዳል፡፡ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ቡድን፣ ድርጅት… መንግሥት የየራሱ ዕቅድ አለው፡፡ አንድ ሰው ብዙ ነገሮች ያስፈልጉታል፡፡ መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስ፣ ትራንስፖርት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ የመጠባበቅያ ተቀማጭ ወዘተ. ያስፈልገዋል፡፡ ይህን ለማሟላት ገቢ ያስፈልገዋል፡፡ ስንት ሰዓት ወይም ሳምንት ወይም ወር ሠርቶ ምን ያህል ገንዘብ ያገኛል? ከየትስ ያገኛል? ወይም አገኛለሁ ብሎ ያስባል? ገንዘቡ ሳይገኝ በፊት ጀምሮ ያቅዳል፡፡

ገንዘቡ ሲገኝ ደግሞ ከላይ ለተጠቀሱት የወጪ ርዕሶች በሚሆን መልኩ ይደለድላል፡፡ የወጪ ቋቶችን ማወቅና የሚያስፈልገውን በጀት መደልደል አንድ ትልቅ ሥራ ሆኖ ሳለ የበጀት አጠቃቀሙን በዲሲፒሊን መምራትና ማስፈጸም ግን የበለጠ ሥራ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሕዝብ ጥያቄን በፍትሐዊነትና በተጠያቂነት አግባብ መከወን እንዳለበት መንግሥት ተግባሩ ልዩ ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት የአገራችን የፌዴራል መንግሥት በጀት ከግማሽ የማያንሰው ለመደበኛ ወጪ የሚመደብ ነበር፡፡ እስከ 25 በመቶው ደግሞ ለክልሎች የሚደረግ የበጀት ድጋፍ ሲሆን፣ ቀሪው 25 በመቶ ገደማውም ለዘላቂ ልማት ግቦች እንዲሆን ይደለደል ነበር፡፡ ይኼ በሙሉ እንግዲህ ወጪ ነው፡፡

የበጀት ቀመሩ ዋንኛ ግብዓትም የወጪ መዘራዝሩ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ወጪ ለመሸፈን የግዴታ ከወጪው ጋር የሚመጣጠን ወይም የሚበልጥ ገቢ ማግኘት አለበት፡፡ ከየትኛው የገቢ ምንጭ? ምን ያህል? አገኛለሁ ብሎ እንዲያስብ የሚያስገድደውም ይኼው ነው፡፡ ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከውጭ አገር ዕርዳታና ብድር ከፍተኛ ሀብት መሰብሰብም ግድ ነው፡፡ መንግሥት ቀሪውን በጀት መሸፈኛ ገንዘብም ከአገር ውስጥ ብድር ለማግኘት ማቀዱ የተለመደ አሠራር ነው፡፡

ስለበጀት ወደ ዝርዝር ሲገባ ተግባሩ ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹‹ከአገር ውስጥ ከሚገኙ የገቢ ምንጮች›› የሚለውን ብቻ ብንመለከት ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች እናገኝበታለን፡፡

ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች ሲባል ከየትኞቹ ምንጮች ማለት ነው? ከግብርናው ዘርፍ፣ ከኢንዱስትሪው ዘርፍ፣ ከገቢና ከወጪ ንግድ ዘርፍ፣ ከአገልግሎት ዘርፍ፣ እያለ ይቀጥላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ‹‹የግብርናውን ዘርፍ›› ብቻ ብናይ፣ የእሱም ዝርዝሮች ብዙ ናቸው፣ በየምርቶች ዓይነትም ይዘረዘራል፣ ከቡና ስንት? ከቅባት እህሎች ስንት? ከቆዳና ሌጦ፣ ከቁም እንስሳት፣ አዝርዕት፣ ከመንግሥት ዘርፍ፣ ከግል ዘርፍ፣ እየተባለ በዝርዝር ይታያል፡፡

በጀት የአንድ ሳምንት ወይም የአንድ ወር ሥራ አይደለም፡፡ የዓመት ሙሉ ሥራ ነው፡፡ በጀት የወጪና የገቢ ዕቅዶችን ወደ ገንዘባዊ አኃዝ በመቀየርና በማስቀመጥ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡ የተቀመጡ ወጪዎችንና የተገመቱ ገቢዎችን ማለትም በጀቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችንና ተግዳሮቶችን ይለያል፡፡ ድንገት እንደሚመጣ ጦርነትና ድርቅን የመሰሉ ሀብት ፈላጊ ችግሮች ቀድሞ መዘጋጀት ባይቻልም፣ የቅድመ መከላከል ሥራ የሚሠራባቸው ተግባራት ሁሉ በጀት ፈላጊ ናቸው፡፡

በመሠረቱ በጀት የአገሪቱን ሀብት የመቆጣጠሪያ ሰነድ ነው፡፡ ምን ያህሉ ገንዘብ ምን ላይ ይውላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል፡፡ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው የልማት ዘርፎች ወይም ፕሮግራሞች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን ይለያል፡፡ መንገድ፣ ትምህርት፣ ግብርና፣ ውኃ፣ ጤና፣ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን፣ ሥራዎች የአገሪቱን ሀብት በፍትሐዊነት ይደለድላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተቆጣጣሪ አካላት አሉ፡፡ በየደረጃው ይህን የሀብት አጠቃቀም መምሪያ ሥርዓት አጠናክሮ መተግበር ካልተቻለ ግለሰቦች ያሻቸውን ከመፈጸም የሚያግዳቸው ከልካይ ሊኖር አይችልም፡፡

በጀት የአፈጻጸም መቆጣጠሪያ ነው ሲባል ሥራው በበጀቱ መሠረት አለመፈጸሙ በሌሎች ዘርፎችና በአጠቃላይ በጀቱ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ መመልከቻና ማስተካከያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የግድ የበጀት ብክነትን ወይም የገንዘብ መበላትን የሚከታተል ነው ማለት አይደለም፡፡ ‹‹በበጀቱ መሠረት አልተፈጸመም›› ማለት በጀቱ ‹‹ተበልቷል ወይም ወደ ግለሰቦች ኪስ ገብቷል›› ማለትም አይደለም፡፡

ማንኛውም ሥራ በተመደበለት በጀት መጠን ‹‹አልተሠራም›› ማለት በአብዛኛው የአፈጻጸም ብቃት ማነስን የሚያመለክት ነው፡፡ ለምሳሌ ዋናው ኦዲተር በየጊዜው የመሥሪያ ቤቶችን የበጀት አፈጻጸም ገምግሞ ሪፖርት ሲያቀርብ በአጠቃላይ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ አልተወራረደም፣ ይኼን ያህል ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዕቃ ወይም አገልግሎት ከግዥ መመርያና ደንብ ውጪ ተገዝቷል፣ ይህን ያህል ሚሊዮን ብር ሒሳብ አልተዘጋም፣ በጨረታ ደንብ መሠረት አልተከናወነም ሲል ሰምተናል፡፡

ትክክል ነው፡፡ ወደፊትም መባልም አለበት፡፡ የበጀት አፈጻጸም በሕጉ መሠረት ብቻ መሆን አለበት፡፡ ‹‹በሕጉ መሠረት አልተፈጸመም›› ማለት ግን ሁልጊዜ ገንዘብ ተበልቷል ማለትን አያመለክትም፡፡ አንዳንድ ሥራዎች አሉ፡፡ ከፍተኛ ሚስጥርነት ያላቸው በይፋ ቢወጡ ወይም ቢነገሩ የማይመለስ ጉዳት የሚያስከትሉ በባህሪያቸው በልዩ ሁኔታ መያዝ ያለባቸው ዘርፎች አሉ፡፡

ለምሳሌ የመከላከያ፣ የመረጃና ደኅንነት ወዘተ. ዓይነቶች አሉ፡፡ መከላከያ በጨረታ ወይም በግዥ ደንብ መሠረት የማይገዛቸው ብዙ መሣሪያዎች አሉ፡፡ የውጊያ አውሮፕላኖች፣ ሄሊኮፕተሮች፣ ፈንጂዎች፣ የተለያዩ ጠመንጃና የባዙቃ ጥይቶች፣ የአየር መከላከያ መሣሪያዎችና ግብዓቶቻቸው ሌላው ቀርቶ የደመወዝ ወጪን ለማመላከት የሠራዊቱን ቁጥርና አደረጃጀት የሥራ መደብና ሥምሪትን የሚመለከቱ መረጃዎች ይፋ ቢወጡ የሚያስከትሉት ጉዳትና ለጠላት የሚሰጡት ጠቀሜታ መታየት አለበት፡፡ መንግሥት እነዚህን መረጃዎች እንዲገልጽ አይገደድም፡፡ ማንም አገር  አያደርገውምና፡፡

ምክንያቱም እደዚህ ዓይነት ወጭዎች በሕዝቡ፣ በምክር ቤቶችና በኦዲተር መሥሪያ ቤት አልታወቁም ማለት፣ በመከላከያና በደኅንነት መሥሪያ ቤቶች አይታወቁም ማለት አይደለም፡፡ መከላከያ ያውቃቸዋል፡፡ በሌሎች መሥሪያ ቤቶችም ውስጥ ተመሳሳይ ውስብስብነት ሊኖር እንደሚችል ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ወጭዎችም ላይ ቢሆን ግን መንግሥት ቆጣቢ የሀብት አጠቃቀምን ከአገራዊ ህልውና ጋር እያመጣጠነ የመራመድ ግዴታ አለበት፡፡ ለሌብነት እንዳይጋለጥ አሠራሩን ማጥበቅም ግዴታ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ማለት ግን የመንግሥት በጀት በተለያዩ መንገዶች አይመዘበርም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ የመንግሥት የሥራ ዕቅድና የበጀት መጠን እየሰፋና እያደገ በሄደ ቁጥር ሙስናም በዚያው መጠን ያድጋል፡፡ በመቶ ቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ቀላል ገንዘብ አይደለም፡፡ ግማሽ ትሪሊዮን ብር እየተቃረበ ነው፡፡ የቀደመውን ጊዜ እንኳን እንተወውና ለዕርዳታና ለችግርኛ የተመደበ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሀብት እንኳን ሳይቀር በግለሰቦች ተቆርጥሞ እንደተበላ ታዝበናል፡፡ እናም በሕዝብ ሀብት መዘናጋት አይገባም፣ አይቻልም፡፡

በጀት የፖለቲካ መሣሪያነቱ የታወቀ ቢሆንም፣ ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ጥቂቶችን ለማስደሰት ወይም በሕዝበኝነት ስሜት ተነሳስቶ ለሚከናወን ተግባር በጀት መመደብም ሆነ ማባከን እንደ ነውር ሊቆጠር የገባል፣ ወንጀልም ነው፡፡ አሁን አሁን በአንዳንድ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት ቀጥታ ትዕዛዝና ኔትወርክ ውስጥ የገቡ የግዥ፣ የበጀትና የፋይናንስ ፈጻሚዎች ሕገወጥ አካሄዶች እንደሚስተዋሉም ይነገራል፡፡ እንዲህ ያሉ ግድፈቶችን በእንጭጩ ማረም ካልተቻለ ለውጥ ማስቀጠል አይቻልም፡፡

የመንግሥትን በጀት አሥልቶና ገቢ ወጭን አጣጥሞ ማዘጋጀት ትልቅና ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ሥራ መሆኑን ጠቅሰናል፡፡ ስለዚህ በየደረጃው ያሉ የዕቅድ ፈጻሚ ተቋማት የፀደቀውንና የተደለደላቸውን በጀት ወደ ጎን ትተው በዘፈቀደ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ በሰነዱ መሠረት እየሠሩ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ማድረግ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡

የሰነዱ ፍላጎት ማለት የአገሪቱና የመንግሥትና ሕዝብ ፍላጎት መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ማመንም ግዴታቸው ነው፡፡ ለድህነት ቅነሳና ለዘላቂ ልማት፣ ብሎም እንደ አቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ማበልፀግ የተመደበን በጀት ለቢሮ ማሳመሪያ፣ ለቅንጦት ተሽከርካሪና ለውጭ ጉዞ እየተዟዟሩ ማደፋፋትም ሊያስጠይቅ ይገባል፡፡ አንዳንዱ መሥሪያ ቤት በጀት በራሱ አቅም ያመነጭ ይመስል የተመደበለትን ሀብት ኃላፊዎቹ ለፈቀዱት ወገን በዕርዳታና ድጋፍ ስም የሚሰጡበት አካሄድም ለሕገወጥነት የተጋለጠ መሆኑን ነው ሙያተኞች የሚናገሩት፡፡

በሌላ በኩል በጀት ተመላሽ የማድረግ ፀባይም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ መንግሥት በጀት የሚሰጠው ፈጻሚ ድርጅቶች በየአካውንታቸው አስቀምጠው በዓመቱ መጨረሻ ላይ ተመላሽ እንዲያደርጉለት አይደለም፡፡ እንዲሠሩበት ነው፡፡ ቀደም ያለ ችግር ቢሆንም ‹‹በጀት ተመለሰ›› ማለት ‹‹ሥራ አልተሠራም›› ማለት ነው፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማስከተል አለበት፡፡ ሰበቡና ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የመንግሥትን ገንዘብ ወስዶ ዓመት ሙሉ አስቀምጦ መመለስ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡

አንዳንዶች ደግሞ ‹‹በጀት መመለስ ያስጠይቀናል›› በማለት በጀቱን ላለመመለስ ሲሉ ሰኔ ወር ላይ የማያስፈልገውን ዕቃ ጭምር እየገዙ የሚያበካክኑበት ልምድ ነበር/አሁንም አይጠፋም፡፡ የቢሮ ዕቃ ጠረጴዛና ወንበር፣ ኮምፒዮተር፣ መጋረጃ፣ የእንግዳ ፎቴ፣ ፍሪጅ፣ በመሸማመት ‹‹ገንዘብ ከሚመለስ›› በሚል ሰበብ በጀቱን አበካክነው ድራሹን የሚያጠፉበት አሠራር ነበራቸው፡፡ በእንዲህ ያለ ግዥ የሚፈጸመው ሌብነት ደግሞ ዓይን ያወጣ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ አካሄድ በጥፋት ላይ ጥፋት መፈጸሙ አይቀሬ ነው፡፡

በጀቱን ሳይሠሩበት ወዝፈው ማስቀመጣቸው ሳያንስ ይባስ ብለው በሰኔ ወር ቁሳቁስ ግዥ ማውደም ተገቢም አስፈላጊም አይደለም፡፡ ይህ የሰኔ ወር ግዥ አሁን አሁን የቀረ ይመስላል ወይም ጎልቶ አይሰማም፡፡ በጀት መመለሱ ግን ዛሬም አለ፡፡ ጉዳት አለው፡፡ ተወዝፎ የከረመው በጀት ሌሎች ብዙ ሥራዎች የሚሠሩበት ገንዘብ ነበር፡፡ መሥሪያ ቤቶች ገንዘቡን ለመመለስ የሚገደዱበት ሁኔታ ካለ መጀመርያ መጠየቅ አልነበረባቸውም፡፡

‹‹እንሠራበታለን›› ብለው ከጠየቁና ከተፈቀደላቸው ደግሞ በአግባቡ ሊሠሩበት ይገባል፡፡ ገንዘቡ ለአንድ ዓመት በብድር ቢሰጥ ስንት ትርፍ ያመጣ ነበር፡፡ ብሩ ተመለስ ቢባል እንኳ ሳይሠራበት ያለፈውን የዓመት ጊዜ ብክነት መመለስ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ጊዜ ወደፊት እንጂ ወደኋላን አያውቅምና፡፡ በተለይ እንደ ምንገኝበት ያሉ የኑሮ ውድንትና የተረጅንት ችግሮች የጎሉባቸው ወቅቶች ላይ ቅድሚያ የሰው ሕይወትን ለማቆየት የሚያግዝን ሀብት ሁሉ ሰብስቦ መወዘት እንደ ትልቅ ድክመት መቆጠሩም አይቀሬ ነው፡፡

በሌላ በኩል ዕቅድ ፈጻሚ ተቋማት ከተጠያቂነት ማምለጥ እንዲችሉ ከአቅማቸው በታች የሆነ ዕቅድ የሚያቀርቡበት ሁኔታም አለ፡፡ በትልቁ ማቀድ ይፈራሉ፡፡ የተለጠጠ ዕቅድ መሥራት ያለውን ጠቀሜታ አይረዱም፡፡ ትንሽ አቅደው ዓመቱን ሙሉ ዘና ፈታ ብለው ወጣ ገባ እያሉ መሥራትን ይመርጣሉ፡፡ ይህ በጣም ጎጂ ነው፡፡ ተቋማቱ ያላቸውን የሰው ኃይል፣ የማቴሪያልና የገንዘብ አቅም አሟጠው ለመጠቀም መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የበጀት ኮሚሽንና የተወራድ መሥሪያ ቤቶች ጥናት፣ ቁጥጥርም ሆነ ድጋፍ ስለማድረጋቸው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ግን ሊጀመር ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ብዙ ዕውቀት፣ ጊዜና ገንዘብ ወጥቶበት የተዘጋጀው በጀት ሁሉንም የመንግሥት ዕቅድ ፍላጎት በግልጽ ማሳየት አለበት፡፡ እንደ አስፈጻሚና ተቆጣጣሪ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝብም ለመረዳት የማያስቸግር፣ በዓለም ላይ ካሉት የበጀት አዘገጃጀት ሥልቶች (ላይን አይተም፣ ፐርፎርማንስ፣ ዜሮ ቤዝድ…) በተሻለና በተቀናጀ መንገድ ሊዘጋጅም ይችላል፡፡ ዋናውና ትልቁ ጉዳይ ግን ለፍትሐዊና ውጤታማ የበጀት አፈጻጸም መትጋት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ፈጻሚዎችና ራሱ ሕዝቡም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...