Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በጎደለ ሙላ የሚሉት ጨዋታ!

ከመገናኛ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። የአኗኗራችን ጉዳይ የበዓል ገበያ ታክሎበት ሆዱን ባር ባር የሚለው፣ ክፍት ያላት፣ ሥጋት ሰቅዞ የያዘው፣ ግራ ግብት ያላት፣ በአጠቃላይ ሁሉም በስሜታቸው ውስጥ ሆነው ጎዳናውን ይራመዱበታል። ለዚህ ነው በየመንገዱ እንደ ሐሳባችን ሙቀትና ቅዝቃዜ የምንራመደው። ‹‹አይ መፈጠር፣ አይ ከቶም መኖር…›› ይላል አንዱ ግራ የገባው። በመሆንና ባለመሆን ስሜት ውስጥ ሁሉም የጥረቱን ሳይሆን የዕድሉን ሊሰበስብ፣ የዘራውን ሳይሆን ያልጠበቀውን ሊያጭድ፣ አንዳንዴም የተሰፈረለትን ሊዘግን በፍርኃት ሐዲድ ላይ እየተጓዘ ቀኑን ይጠባበቃል። ነገር ግን ተፈጥሮ የመምረጥን ነፃ ፈቃድ ባትቸረን በዚህ ሁሉ አዋኪ ኑሮ መሀል ምን ይውጠን ነበር? የተንጠለጠሉ ተስፋዎች በይሆን አይሆን የጥያቄ ማዕበል እየተናጡ ነገን እንድናይ ይገፉናል። ዘንድሮ የሚደግፍና ከኋላ የሚገፋ ባይመናመን ኖሮ እኮ ብዙ እንጓዝ ነበር። ድንበር ተሻጋሪ ሀኬት፣ ስግብግብነትና ምቀኝነት በቁም አስሮን የሌላውንም የራሳችንንም በረከት ይቀማናል። በግሳፄና በምክር አልከስም የሚሉ ባህሪዎቻችን እየበዙ ብዙ ያስተዛዝቡናል። ትዝብትና ጎዳና መቼ ተለያይተው ያውቁና!

በአካባቢው ወደ ጉዳዩ የሚብከነከነው ብዙ ነው። ከዚያ መሀል ነው ረጅም ርቀት ተጓዡ አንገቱን ታክሲ ውስጥ የሚያስገባው። ወያላው በጓደኞቹ ተከቦ ያሻውን ወሬ እያነሳና እየጣለ ይጣራል። ምናለበት እንዲህ የሚጠበቅባቸውን ማድረግ የማይረሱ ቢበዙልን? ‹‹አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ምን አደረግኩላት ብለህ ጠይቅ›› የሚል ጥቅስ ከፊት ለፊታችን ተለጥፎ ያዩ ሁለት ተሳፋሪዎች ጨዋታ ጀመሩ። ‹‹አሁን አንተ ለዚህች አገር ምን አደረክላት?›› ይለዋል አንደኛው። ያኛው ይመልሳል፣ ‹‹ቀድሞ ነገር አንድ ነገር ለማድረግስ ቢሆን ዝም ተብሎ መሰለህ? አሁን ምናለበት እንዲህ ያለውን ጥቅስ ስንረዳ እንደወረደ ባይሆን? አይ የትምህርት ጥራት መውረድ። ፈቃድ ሲኖርህ እኮ ነው አንድ ነገር የምታደርገው…›› ብሎ ይመልስለታል። ‹‹እንዴ ለአገር በጎ ነገር ለማድረግ ደግሞ ፈቃድ ካልተሰጠ አይሆንም ተባለ እንዴ?›› ብሎ አንድ በተባራሪ ወሬውን የሰማ ይጠይቃል። ‹‹አዎ!›› አለ ስለፈቃድ የተናገረው ተሳፋሪ በስላቅ። ‹‹ሰው ባለመደማመጥ ቁምነገሩን ከአሰስ ገሰሱ መለየት ትቷል ጃል…›› ይላል። አንዱ ታዛቢ መሳይ፣ ‹‹በፈቃድ ወረፋ ተይዘን ለመኖር ሌላ ፈቃድ እንዳያስፈልገን እንጂ ሌላውስ ዕዳው ገብስ ነው…›› ሲል ለጨዋታ ያህል የተነሳ መሆኑ ተነገረው። ‹‹እና ለአገር አስተዋጽኦ ለማበርከት ምን ቢያስመርርህ ነው እንዲያ የምትለው?›› ብሎ ወደ ሁለቱ የወሬው ጀማሪዎች አፈጠጠ። የዘንድሮን ዓይን በመፍጠጥና በማልቀስ የሚስተካከለው ያለ አይመስልም!

ኑሮ አንዳንዴ እንደሚታክተን አዕምሮን ማሰብ ቢታክተው ከተማችን የዕብዶች መናኸሪያ መሆኗ ባላጠያየቀ ነበር። ‹‹አይ አንቺ አገር መቼ ይሆን በልቶ ማደር ልጆችሽን በሐሳብ አዙሪት እየናጠ መድፋቱን የሚተዋቸው?›› እያሉ አንድ አዛውንት ተሳፋሪ ሲገቡ፣ የተነጋገርንበትን ሳይሰሙ እንዲያ ማለታቸው እያስገረመን ተመለከትናቸው። ለካ ከመንገዱ ዳር ምንም እህል ባለመቅመሱ ምክንያት በቁመቱ ልክ የተጋደመ የስኳር ታማሚ ዓይተው ኖሯል። ታማሚው ቀና አድርገው የሚጠጣ ነገር ለመጋት የሚሞክሩ መንገደኞች ይረባረባሉ። ‹‹ምናለበት ከውድቀት በፊት ብንረባረብ?›› ቢል አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹እውነት ነው፣ ይኼኔ አንድ ጉርሻ ማግኘት ባይችል ነው…›› ብሎ አጠገቡ ያለው መለሰ። አመላችን ሆኖ ካለቀ መድረስ ይቀናናል። ‹‹አቅርቡኝ ጠይቁኝ ብዬ ስለፈልፍ ሰሚ ስላጣሁኝ፣ በድኔን አትንኩት ስሞት አትቅበሩኝ…›› ያለው ማን ነበር!

ታክሲዋ ስትሞላ ፈጠን የሚለው ልጅ እግር ወያላ ሲሮጥ መጣ። በሩን እየዘጋ ሾፌሩን ‹‹ሳበው!›› አለው። ሾፌሩ ይኼኔ የዘነጋው ነገር ትዝ ብሎት፣ ‹‹እንዴ አንተ ልጅ የመንጃ ፈቃድህን ነገር እንዴት እያደረግክ ነው?›› ብሎ ጠየቀው። ሁላችንም የሚመልሰውን ልንሰማ ጆሯችንን አሰገግን። ‹‹ታውቃለህ? እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ እስከ 30 ሺሕ ተፈታኝ አለ ብለው ከሁለት ወር በኋላ ቀጠሩኝ። አይገርምህም ግን? እኔማ አንዳንዴ መስመሩ ሲጨናነቅ የዚህ ሁሉ ሰው መንፈስ ጭምር እንጂ፣ የምናየው መኪና ሁሉ አልተላለፍ ብሎ አይመስለኝም…›› አለው። ‹‹ዘንድሮ እኮ መኪና ማለት ጫማ በለው። ቅንጦትነቱ ድሮ ቀረ። እናንተን ተማምነን ታዲያ ልንኖር ነው?›› ሲል አንድ ተሳፋሪ ተንኮለኛው ወያላ፣ ‹‹ከጫማም ኤክስፖርት ስታንዳርድ ጫማ የሚባል አለ። መኪና ሁሉ እኩል መኪና አይደለም…›› ሲለው፣ ‹‹ወይ ጉድ፣ ‹‹ተኖረና ተሞተ የሚባለው እኮ የተተረተው ለእኛ መሰለኝ…›› ሲለው በቅሬታ ፈገግታ የተሞሉ ፊቶች ታዩ። ከፊል ደመናማ እንደሚሉት!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀምራለች። በሰፊው የቀበና ጎዳና ላይ መፍሰስ ስንጀምር፣ ‹‹መቼም ይኼ መሠረተ ልማት እንደዚህ ሁሉም ቦታ ቢሆን ደስ ይል ነበር፣ ግን ምን ያደርጋል…›› አለ አንድ ጎልማሳ ተሳፋሪ በቅሬታ ስሜት። ‹‹ምነው… ምነው… ደህና ረስተነው የነበረውን ነገር ባታስታውሰን?›› አለች አንዲት ሴት። ‹‹እንዴት?›› ቢላት ጎልማሳው? ‹‹የቤት ጉዳይን ነዋ፣ ባለፈው ሰሞን አከራዬ ልጄ ልትወልድ ስለምትመጣ ልቀቂ ብሎኝ ትናንት ባለአንድ ክፍል ኮንዶሚኒየም አገኘሁ። አሁን ሔጄ ዋጋ ብነጋገር አሥር ሺሕ ብር አይሉኝ መሰላችሁ? ኧረ የጉድ ዘመን…›› ብላ እንባ ተናነቃት። ከአስፋልት እስከ መኝታ ቤታችን ቅሬታችን በዝቷል። ‹‹እና ምን ተሻለሽ?›› ቢላት አጠገቧ የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹ምነው ወንድሜ ምን ተሻለን በል እንጂ? ‘የአንዱ ቤት መቃጠል ለሌላው ሙቀትና ብርሃን ነው’ ያሉትን የአገርህን ጸሐፊ አታውቃቸውም? ለነገሩ የዘንድሮ ልጆች ከአገራችሁ ይልቅ የባዕድ አጨብጫቢ መሆን ትወዳላችሁ…›› ብለው አዛውንቱ ድንገት ተናገሩ። በመንገድ አድርገን ስለቤት አውርተን፣ በአገር ምርትና በአገር ሰው ስለመኩራት እስክናወራ ታክሲያችን ጉዞዋ እንደቀጠለ ነው። ሕይወት እንዲህ ናት!

 ‹‹ወራጅ!›› አለ አንድ መንገድ ላይ የገባ ተሳፋሪ። ታክሲዋ ስትቆም፣ ‹‹ወይ ጉድ…›› ይላል ከኋላ ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች አንዱ። ‹‹ሰው ምነው እንዲህ ሐሞቱ ፈሰሰ? ከእዚች እዚች ለመሄድ ነው የተሳፈረው?›› ሲል አንደኛው፣ ‹‹በቃ በዓመት አንዴ ታላቁ ሩጫን ትሮጣለህ፣ በየዕለቱ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ሰው ታወራለህ…›› ብሎ ቀለደ። ‹‹ለመሆኑ አንተ ያልሮጥከው ኑሮዬ ራሱ ታላቅ ሩጫ ነው ብለህ ነው?›› አለው ጮክ ብሎ። ‹‹ታዲያስ፣ ከዘንድሮ ኑሮ የበለጠ ምን ታላቅ ሩጫ ይኖራል? በልቶ ለማደር አሥር ሺሕ ማይልስ የሚማስን ሰው አሥር ኪሎ ሜትር ብርቅ አይሆንበትም…›› ብሎ በነገር ነካ አደረገው። ታዲያ ቀልድ መሆኑን ሁለቱም ለማሳወቅ ትከሻቸውን ቸብ ቸብ ይደራረጋሉ። ‹‹ይሁንና ግን መሮጥ ነበረብህ። አንጀት የሚያርስ የፖለቲካ ፓርቲ በጠፋባት አገራችን በዓመት አንዴ በሚሰጥህ እንዲህ ያለው ዕድል ተጠቀመህ ጉሮሮህ እስኪሰነጠቅ ያሻህን በተናገርክ ነበር…›› አለው ድንገት የጨዋታውን ፍሬ ነገር ወደ ፖለቲካ እያሸጋገረ። ‹‹የመናገር ነፃነት በሕገ መንግሥት በፀደቀባት አገር ለመናገር ብዬ ለምን ቀን ልጠብቅ?›› አለው ወዳጁ ትንሽ ኮስተር ብሎ። ‹‹አይ የአንተ ነገር፣ እኛ እንደሆንን አሳምረንና ሥርዓት ጠብቀን የመናገር ልምድ የለንም። እንደ ወረደ ያምረናል። ይኼ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መብታችን መሰለኝ?›› አለው። እንደ ወረደ ከሚባለው ‹‹ቡና›› እና ‹ንግግር›› ዋጋው ከፍ ያለው የትኛው ይሆን! 

ታክሲያችን ከምኔው ቀበናን አልፋ መንገዱን እያገባደደች እንዳለች ስናይ ሁላችንም ተደናገጥን። ‹‹የጤና ይሆን?›› አለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ዝምተኛ ተሳፋሪ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹በጣም ፈጥነን ነዋ የደረስነው፣ አሥር ደቂቃ መቼ ፈጀብን?›› ብሎ መደነቁን ቀጠለ። ታክሲዋ አንድ ሰው ጭና ወዲያው ለማውረድ ከመቆሟ በቀር ጉዟችን አልተቋረጠም ነበር። ስለትራንስፖርት ዕጦት እያማረረች ስታወራ የነበረችው ሴት፣ ‹‹እኔስ የናፈቀኝ ነገር እንዳህ ያሰብነው ሥፍራ በፍጥነት መድረስ ነው። በረባ ባረባው መጓተት ሰለቸን…›› አለች ምርር ብሏት። ‹‹ማን የማይፈልፈግ አለ ብለሽ ነው? ችግሩ እኮ መንገዱ ነው። በፍጥነት ለመሮጥ ምን አቀበት ቢሆን ሊጠረግ ይገባዋል። አገር የምትቀናው በተጠረገ ጎዳና ዜጐቿ ሳያርፉ ለመሮጥ ሲቻላቸው ነው…›› ብሎ. ‹‹…አለበለዚያ ሳያልፍልን በኑሮ ውድነትና በሰላም ዕጦት እየተጠበስን ሳያልፍልን ማለፋችን አይቀሬ ነው…›› ሲል ተናገረ። አይቀርም!

ታክሲያችን ግንፍሌን ተሻግራ ወደ ወወክማ አቅጣጫ ስታመራ አራት ኪሎ መድረሳችንን አወቅነው፡፡ አራት ኪሎ የመንግሥት መቀመጫ በመሆኗ ሁሌም ስሟ ከምንም ነገር በላይ ገዝፎ ይታወቃል፡፡ በስተግራ በኩል የፓርላማው ሕንፃ ሁነኛ ምልክት የሆነው ሰዓት ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ‹‹ምነው የፓርላማው ወሬ በዛሳ?›› አሉ አዛውንቱ፡፡ አጠገባቸው የተቀመጠው ጎረምሳ፣ ‹‹ሁሌም የሚወራው ስለፓርላማው ውሎ አይደለም ወይ?›› አላቸው፡፡ አዛውንቱ ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ ‹‹የለም ወጣቱ ጥያቄዬ አልገባህም…›› አሉት፡፡ ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እስቲ በደንብ አስረድተው ይጠይቁና?›› አላቸው፡፡ አዛውንቱ ሳቅ እያሉ፣ ‹‹ጥያቄዬማ ፓርላማው ባለፈው ሰሞን በአንድ ጥያቄ ምክንያት እንደዚያ ግሎ ደጁን ጭምር ማጋሉ ማለቴ ነው፡፡ እኛ ጭምር አይደለን እንዴ በፓርላማ አባሉና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄና መልስ ትንታኔ ውስጥ የከረምነው?›› ሲሉ ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹ትንታኔያችን እስከሚያልቅ ድረስ ቆመን ስለማንጠብቅ…›› ብሎ ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን እየተሳሳቅን ወደ ጉዳያችን ስንበታተን በጎደለ ሙላ የመሰለው ጨዋታችንም አበቃ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት