Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንክ ቆጣቢዎችን ከአደጋ የሚጠብቅ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ተቋቁሞ ሥራ ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድን (Deposit Insurance) ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ በንግድ ባንኮችም ሆነ በአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ለሚቆጥበው ወይም ለሚያስቀምጠው ማኅብረሰብ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፣ በባንኮች ላይ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ላይ የመውደቅ አደጋ ቢያጋጥም፣ አስቀማጮች ካሳ የሚያገኙበት ሥርዓት እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ የተቀማጭ ገንዘብ መድን ፈንድ ወደ ሥራ መግባቱን የተናገሩት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ በባንኮች በፋይናንስ አደጋ ምክንያት ኃላፊነታቸውን መወጣት በማይችሉበት ወይም በሚወድቁበት ወቅት ዋስትና ለተገባላቸው አስቀማጮች ክፍያ መፈጸም የፈንዱ መሠረታዊ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል።

የተቋቋመው ፈንድ ይህንን መሠረታዊ ዓላማ ለማሳካት የሚረዱት የተለያዩ ተግባራትን እንደሚያከናውንም አስረድተዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ ከባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ዓረቦን መሰብሰብ ሲሆን፣ የሚሰበሰበውን ዓረቦን የማስተዳደርና መልሶ ኢንቨስት የማድረግ ኃላፊነት እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

የፈንዱ ገንዘብ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ሒሳብ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን፣ አባል የሚሆኑት ባንኮችና የማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ፈንዱ የሚያወጣውን መነሻ ዓረቦን መክፈል ይጠበቅባቸዋል። አባል ከሚሆኑት የፋይናንስ ተቋማት ከሚሰበሰበው ዓረቦን በተጨማሪ መንግሥት ፈንዱን ለማስጀመር የሚውል የሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚመድብ ታውቋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መርጋ ዋቅወያ፣ የፈንዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሾማቸውንም ዋና ገዥው አቶ ማሞ ምሕረቱ አስታውቀዋል።

ፈንዱን በበላይነት የሚመሩ አምስት የቦርድ አባላትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሾማቸውን ከብሔራዊ ባንክ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ ያመለክታል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ቦርዱን በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተሾሙ ሲሆን፣ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ መርጋ ዋቅወያ፣ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጃ ዘበነ፣ እንዲሁም የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ከበደ በቦርድ አባልነት ተሾመዋል።

የዓለም ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የየፋይናንስ ዘርፍ ጤናማነትን አስመልክቶ ባካሄደው ጥናት በኢትዮጵያ ሊያጋጥም የሚችልን የፋይናንስ ደኅንነት አደጋ ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓትም ሆነ የችግር ጊዜ አያያዝ ዝግጅት አለመኖሩን ይፋ አድርጓል። እንደ ዓለም ባንክ ጥናት በአንድ አገር የፋይናንስ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ቢያንስ የተቀማጭ ዋስትና፣ የፋይናንስ ተቋማት መልሶ ማገገሚያና የመፍትሔ ሐሳቦችን ማፍለቂያ ማዕቀፍ ማዘጋጀትን ይጠይቃል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፍ ደኅንነት ሥርዓትን ለማበጀት የተወሰነ ጥረት መጀመሩን የሚገልጸው የዓለም ባንክ፣ ከተጀመሩት ጥረቶች አንዱ የተቀማጭ ኢንሹራንስ ፈንድን ማቋቋም እንደሆነ ይገልጻል።

በአግባቡ የሚሠራ የተቀማጭ ኢንሹራንስ ፈንድ ማቋቋም ቆጣቢዎችን ወይም አስቀማጮችን ካልታሰበ አደጋ የሚጠብቅ በመሆኑ አስቀማጮች በሥጋት ምክንያት ገንዘባቸውን ለማውጣት በአንድ ጊዜ ወደ ፋይናንስ ተቋማት እንዳይተሙ የሚከላከል መሆኑን ይገልጻል። በተጨማሪም በፋይናንስ ተቋማት የደኅንነት ችግር ምክንያት አስቀማጮችን አደጋ እንዳይደርሰባቸው ለመጠበቅ የሚወጣውን ወጪ ከመንግሥት ወደ ፋይናንስ ዘርፉ የሚያሸጋግር መሆኑንም ይጠቅሳል።

በኢትዮጵያ የባንኮች ሥራ ዘርፍ ትልቅ የገበያ ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ በአገሪቱ ከሚገኙት ባንኮች ጠቅላላ ሀብት ውስጥ 59 በመቶ፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ 60 በመቶ ገደማው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች