Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበትግራይ ክልል ከ22 ሺሕ በላይ መምህራን ለሁለት ዓመታት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተገለጸ

በትግራይ ክልል ከ22 ሺሕ በላይ መምህራን ለሁለት ዓመታት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተገለጸ

ቀን:

  • በሰሜን ኢትዮጵያ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ወደ ትምህርት አልተመለሱም

በትግራይ ክልል በኮቪድ ወረርሽኝና ለሁለት ዓመት በዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለሦስት ዓመታት ከትምህርት የተገለሉ 22,500 መምህራን፣ ለሁለት ዓመታት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ዓለም አቀፍ የሕፃናት አድን ድርጅት አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ሚያዚያ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል 85 በመቶ ትምህርት ቤቶች ከባድ ወይም ከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ሁሉም የሕዝብ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ አስታውቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም የሰላም ስምምነት ቢፈረምም፣ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አልቻሉም ብሏል፡፡

ድርጅቱ የመማር ማስተማር ሒደቱን ለማስጀመር ተጨማሪ የገንዘብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልጾ፣ በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

በሕፃናት አድን ድርጅት በወጣው አኃዛዊ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ 16 ሕፃናት መካከል አንዱ ከትምህርት ገበታ የተገለለ ነው፡፡ የድርጀቱ መረጃ ኢትዮጵያን ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀውስ ካስተናገዱ አገሮች አንዷ ያደርጋታል ብሏል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር፣ በሕፃናት አድን ድርጅትና በዩኒሴፍ የሚመራው የትምህርት ክላስተር በሰሜን ኢትዮጵያ ማለትም በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን በጥናቱ ስለመረጋገጡ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከትምህርት ቤት የራቁ ሕፃናት ለመብት ጥሰቶችና ብዝበዛ፣ አንዲሁም ጥቃት የመጋለጥ ዕድላቸው ይጨምራል የሚል ሥጋት እንዳለውም ድርጅቱ አስታውቋል፡፡

የ13 ዓመት ታዳጊና በአማራ ክልል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነቸውን ተማሪ ለአብነት የጠቀሰው የሕፃናት አድን ድርጅት፣ ሕፃኗ በአካባቢው በተነሳው ጦርነት ሳቢያ ቤተሰቦቿ ቤታቸውንና አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ በመገደዳቸው ለአንድ ዓመት ትምህርቷን አቋርጣ እንደነበር ገልጿል፡፡ ነገር ግን አሁን ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ከቻሉ ጥቂት ልጆች አንዷ መሆኗም በመግለጫው ተካቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ለኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ሰብዓዊ ዕርዳታ ጥያቄ ለማሟላት ያስፈልጋል ብሎ ከጠየቀው የገንዘብ መጠን 18.4 በመቶ የሚሆነው ብቻ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለመደገፍ ተጨማሪ 3.26 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል።

በኢትዮጵያ የሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታዩት የከፋው ስለመሆኑና ግጭት፣ ረሃብና የአየር ንብረት ቀውሱ ተፅዕኖ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀላቸው በኢትዮጵያ የሕፃናት አድን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዣቪየር ጁበርትን የጠቀሰው መግለጫ አስረድቷል፡፡

በዚህም ምክንያት፣ ‹‹ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕፃናት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንደተገደዱና በግጭቱ የተጎዱ ወይም የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ማደስና ደመወዝ ላልተከፈላቸው መምህራን ለሥራቸው ክፍያና ማበረታቻ እንዲሰጣቸው ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ዳይሬክተሩ መናገራቸው ተጠቅሷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2022 ድርጅቱ በሕይወት አድን የምግብ አቅርቦት፣ በመጠጥ ውኃ ድጋፍ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች ባደረገው ሕክምናና ሌሎች አገልግሎቶች ከ7.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን እንደደረሳቸው አስታውቋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሃለፎም፣ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረሰባቸው ውድመት ባሻገር ብዙዎቹ የተፈናቃዮች ካምፕ እንጂ ልጆች ሊማሩባቸው አይችሉም ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶቹ ሕንፃቸውም፣ መጻሕፍቶቻቸውም የወደሙ መሆኑን፣ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የተፈናቀሉ ስለሆኑ ትምህርት ቤቶቹ ከካምፕነት ወደ ትምህርት ቤት ተቀይረው፣ የተቃጠሉ መጻሕፍትም ካልተገኙ ወደ ትምህርት ለመመለስ ከባድ ነው ብለዋል፡፡

ከተቋማት ውድመት ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲፈቱ በሒደት ነገሮች እንደሚለወጡ የተናገሩት ኃላፊው፣ አሁን ግን አንድም ተማሪ በትምህርት ላይ አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...