Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየዓለም ሻምፒዮናዎቹ ኢትዮጵያውያን በቦስተን ማራቶን ይጠበቃሉ

የዓለም ሻምፒዮናዎቹ ኢትዮጵያውያን በቦስተን ማራቶን ይጠበቃሉ

ቀን:

በዓለም የተለያዩ ከተሞች ከሚከናወኑ የጎዳና ላይ ውድድር አንዱ ነው፡፡ ውድድሩ መከናወን የጀመረበትን 127ኛ ዓመት ዘንድሮ ይደፍናል፡፡ ዓመታዊው ውድድር በዓለም ላይ ከሚከናወኑ ምርጥ ስድስት የዓለም አዋቂዎች የማራቶን ውድድሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. 1897 ላይ በ15 ተሳታፊዎች የተጀመረው የቦስተን ማራቶን ተሳታፊዎቹን 50 ሺሕ አድርሷል፡፡ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ጨምሮ በርካታ የዓለም የረዥም ርቀት አትሌቶች ከዓመት ዓመት የራሳቸውን አሻራ ማኖር ችለዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል እ.ኤ.አ. 2014 በሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ብዙነሽ ዴባ 2፡19፡59 በማጠናቀቅ፣ የውድድር ሥፍራውን ክብረ ወሰን መጨበጥ ችላለች፡፡ ብዙነሽ የክብረ ወሰኑ ባለቤት መሆን የቻለችው፣ በጊዜው አሸንፋ የነበረችው ኬንያዊቷ ሪታ ጄፕቶ ‹‹ዶፒንግ›› መጠቀሟን ተከትሎ ውጤቷ በመሰረዙ ነበር፡፡

የዘንድሮ የቦስተን ማራቶን ሰኞ ሚያዝያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡ በውድድሩ ላይ በርካታ ዕውቅ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያውያን የማራቶን የዓለም ሻምፒዮናዎችን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች በቦስተን ማራቶን እንደሚካፈሉ አዘጋጁ አስታውቋል፡፡

የ2019 የዶሃ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን አሸናፊው ሌሊሳ ዴሲሳና የ2022 የኦሪጎን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን አሸናፊዋ ጎይቲቶም ገብረ ሥላሴ ይጠበቃሉ፡፡

በኳታር ዶሃ ዓለም ሻምፒዮና በወንዶች ማራቶን 2፡10፡40 ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ማስገኘት የቻለው ሌሊሳ፣ በርካታ የቦስተን ማራቶን ውድድሮች ላይ መካፈል ከቻሉ አትሌቶች ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ አትሌቱ እ.ኤ.አ. 2013 ለመጀመርያ ጊዜ ከተሳተፈበት ጊዜ አንስቶ አራት ጊዜ መካፈል ችሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል በሁለቱ የወርቅ ሜዳልያን ሲያሳካ፣ በሁለቱ የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማጥለቅ ችሏል፡፡

ሌሊሳ የ2013 የቦስተን ማራቶን ባሸነፈበት ወቅት በዕለቱ በውድድሩ ላይ የቦምብ ፍንዳታ ማጋጠሙን ተከትሎ፣ በፍንዳታው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የወርቅ ሜዳልያውን ለከተማ አስተዳደሩ መለገሱ ይታወሳል፡፡

አትሌቱ በተለይ በአሜሪካ ከተሞች የሚከናወኑ በርካታ ውድድሮች በመሳተፍ የሚታወቅ ሲሆን፣ በኒውዮርክ ማራቶን አምስት ጊዜ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል፡፡ በዘንድሮው የቦስተን ማራቶን ከሚካፈሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ስሙ የተጠቀሰው ሌሊሳ፣ በርቀቱ ካዳበረው ልምድ አንፃር ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡

ሆኖም በውድድሩ ላይ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዘለለ የኬንያውያን አትሌቶች ጭምር የሚሳተፉበት ከመሆኑ አንፃር እንደ ወትሮው ቀላል እንደማይሆን ተገምቷል፡፡

በሌላ በኩል በሴቶች ውድድር በኦሪጎን የወርቅ ሜዳልያን ያጠለቀችው ኢትዮጵያዊቷ ጎይቲቶም ከፍተኛ ግምት አግኝታለች፡፡ አትሌቷ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2፡08፡11 ስኬት በፊት እንዲሁም በኋላ በተለያዩ የግል የማራቶን ውድድሮች ላይ መካፈል ችላለች፡፡

አትሌቷ በዓለም ሻምፒዮናው ከመሳተፏ አስቀድሞ የበርሊን ማራቶን ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፣ ከወራት በፊት በተከናወነው የኒዮርክ ማራቶን፣ እንዲሁም በቶኪዮ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ጎይቲቶም ቦስተን እንደሚካፈሉ ስማቸው ከተዘረዘሩ አትሌቶች መካከል አንዷ ብትሆንም፣ የቫሌንሺያ ማራቶን 2፡14፡58 በመግባት ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻለችው አማኔ በሪሶ ከፍተኛ ፉክክር ሊጠብቃት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ ኢትዮጵያዊቷ አፀደ ባይሳ በቦስተን ማራቶን የምትጠበቅ አትሌት ነች፡፡ አፀደ እ.ኤ.አ. 2016 በተካሄደው የቦስተን ማራቶን 2፡29፡19 በመግባት ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

አትሌቷ ከ2007 ጀምሮ ኢስታንቡል፣ ቺካጎ (2010፣ 2012) ፓሪስ፣ (2009፣ 2010) ማራቶን፣ እንዲሁም የፓሪስ 2010 ግማሽ ማራቶን ጨምሮ በርካታ ውድድሮች በማሸነፍ በጎዳና ሩጫ ልምድ አካብታለች፡፡

በዚህም ከፍተኛ ግምት ካገኙ ሴት አትሌቶች መካከል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች፡፡ በውድድሩ በርካታ ምርጥ የማራቶን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ስም ይፋ የሆነ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የዓለም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤቱ ኤሎድ ኪፕቾጌ ይገኝበታል፡፡

ኪፕቾጌ ከሰባት ወራት በፊት በርሊን ማራቶን 2፡01፡09 ካሸነፈ በኋላ በቦስተን ማራቶን እንደሚሳተፍ ታውቋል፡፡

አትሌቱ ዕውቅና ያልተሰጠውን በቬና በተከናወነው የማራቶን ውድድር 1፡59፡40 በመግባትና በዓለም አትሌቲክስ የተመዘገበውን በበርሊን ማራቶን 2፡01፡09 የዓለም ክብረ ወሰን በእጁ መጨበጥ የቻለ አትሌት ነው፡፡

በዚህም ዕውቅና ያገኘና ዕውቅና ያላገኘ የማራቶን ክብረ ወሰን መያዝ የቻለ ብቸኛው አትሌት ያደርገዋል፡፡

በሴቶቹም የኦሊምፒክ 5,000 ሜትር የሁለት ጊዜ የብር ሜዳልያ ባለቤቷ ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ የምትጠበቅ አትሌት ናት፡፡

በትራክ ውድድር የምትታወቀው ሔለን፣ አምና በኒዮርክ ማራቶን ስድስተኛ ሆና ካጠናቀቀች በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ማራቶን ትሳተፋለች፡፡

የቦስተን ማራቶን በበላይነት ለሚያጠናቅቅ አትሌት 150 ሺሕ ዶላር፣ ሁለተኛ ለሚወጣ 75 ሺሕ ዶላር፣ እንዲሁም ሦስተኛ ለሚወጣው 40 ሺሕ ዶላር መሰናዳቱን አዘጋጁ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...