Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉ‹‹እባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል››

‹‹እባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል››

ቀን:

በአያሌው አስረስ

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት አጠራጣሪና አስተማማኝ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ፣ የልዩ ኃይሎችን አደረጃጀት ለመለወጥ የተደረሰበት ውሳኔና የአማራ ክልል ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ሆኖ ልዩ ኃይሉ ቀዳሚ እንዲሆን መደረጉ ለጽሑፌ መነሻ ምክንያት ነው፡፡

ስብሐታውያን (የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት መሪዎች) እንደፈለጉ በሚዘውሩት የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በልዩ ልዩ መንገድ የሚገለጹ ተቃውሞዎች ቢኖሩም ይህን ያህል የሚያስደነግጡ አልነበሩም፡፡

- Advertisement -

አጎራባች በኦሮሚያ የሚገኙ ቀበሌዎችን አስተሳስሮ አዲስ አበባን ለማልማት የተወጠነው «የተቀናጀ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን» የቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ በተለይ በ2008 ዓ.ም. እየተባባሰ በመሄዱ በርካታ የፖለቲካ አቀንቃኞች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ ሄዶ የአማራና የደቡብ ክልሎችን አዳረሰ፡፡ የተከፋው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን ቅሬታ ለማሳየትና የኢኮኖሚ አቅምን ለማዳክም በፋብሪካዎች ላይና በመንግሥት ተቋማት ላይ እጁን አነሳ፡፡ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የግልና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች የእሳት እራት ሆኑ፡፡ አንዳንድ የግል የንግድ ተቋማት ሆቴሎችና ቡና ቤቶችም ዳፋው አልቀረላቸውም፡፡

በዚህ አመፅ የተሳተፉ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ ወገኖች በሕይወትና በአካል መስዋዕትነት ሲከፍሉ፣ ከ70 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እንደ ጦላይ፣ ብላቴን፣ ዝዋይ፣ ሸዋሮቢት በመሳሰሉ እስር ቤቶች እንዲታጎሩ ተደረገ፡፡ ወደ ሦስት ወራት የሚጠጋ ጊዜ ከታሰሩ በኋላ ተሃድሶ ተሰጥቷቸው «አይለምደንም» የሚል ቲሸርት እየለበሱ ‹‹ተመርቀው›› ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ሆነ፡፡

 ‹‹አይለምደንም›› ማለት የነበረበት መንግሥት፣ ከክፉ ምግባሩ ሊመለስ ባለመቻሉ አመፁ አሁንም ቀጠለ፡፡ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ አስገደደ፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በአዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ተተኩ፡፡ ከሥልጣን መወገድ የነበረበት ገዥ ፓርቲ ኢሕአዴግ ተመልሶ ሥልጣኑን ተቆጣጠረው፡፡ ያ ሁሉ መስዋትነት መጨረሻ ላይ ያመጣው ውጤት ስብሐታውያኑን (ትሕነግን) ከአራት ኪሎ ወደ መቀሌ መሸኘት ብቻ ሆነ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአካባቢ፣ በቋንቋና በብሔር ሳይለያይ ሕይወቱን፣ አካሉን፣ ንብረቱን የገበረበት አገር ደግሞ እስከ ዛሬም ድረስ ማገገሚያ ላጣችበት የኢኮኖሚ ጉዳት የተዳረገችበት የሕዝባዊ አመፁ ፍሬ ተመልሶ በሕዝብ ጠላቶች እጅ የወደቀው፣ በአገራችን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለመኖራቸው፣ በብሔር የተከፋፈሉ በመሆናቸውና ኅብረ ብሔራዊ ነን የሚሉትም ደካሞች በመሆናቸው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበልም ማለት ያስፈልጋል፡፡

ወደ መቀሌ የተሸኙት ስብሐታውያኑ (ሕወሓት) መቀሌን ምሽግና መደራጃ አደረጉት፡፡ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ለ27 ዓመታት በቆዩበት የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣንና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ክልሉ ያጋዙትን ሀብትና ንብረት ለጦርነት መዘጋጃ አደረጉት፡፡ በየቦታው የቀበሩትን መሣሪያ እያወጡ ወለወሉ፡፡

የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት እናቶችን፣ ታዋቂ ሰዎችና የሃይማኖት አባቶችን እንዲያግባቡት ቢልክም ስብሐታውያን የሚሰማ ጆሮ አጡ፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) (የአቶ ስብሓት ነጋ የእህት ልጅ መሆናቸውን ያዙልኝ) በሐሳባቸው ይገፉበት ዘንድ የሚያበረታታቸው በዛ፡፡ ፈረስ ከእነ ሙሉ ዕቃው በአደባባይም ሸልመው ግፋ በለው አሏቸው፡፡

በአንድ በኩል የፌደራል ኃይሎች፣ በሌላው በኩል ቀደም ሲል ባሠለጠኗቸውና ባስታጠቋቸው የቅማንት፣ የቤኒሻንጉል፣ ወዘተ ታጣቂ ኃይሎች ማዕከላዊ መንግሥቱን ስብሐታውያን እረፍት ነሱት፡፡ መከላከያ ውስጥ የነበሩ የአካባቢ ተወላጆችንም ‹‹ትግራይ ትፈልጋችኋለች›› ብለው መቀሌ እንዲገቡ አደረጉ፡፡ ሚሊሺና ልዩ ኃይል በማለትም መድፍ ተኳሽ፣ ታንክ ነጂ፣ ፈንጂ ቀባሪ፣ ወዘተ አሠለጠኑ፡፡ ጎን ለጎንም እግራቸው በረገጠበት አካባቢ የሚገኘውን የመንግሥትና የግል ንብረት እየነቀለ ወደ ትግራይ የሚጭን፣ መጫን የማይቻለውን የሚሰባብርና የሚያወድም ኃይል በበቂ አዘጋጁ፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት ላይ በሚከፍቱ ጦርነት እስከ ሦስት ሚሊዮን ሰው ሊሞትባቸው እንደሚችል፣ በመጨረሻ እነሱ አሸናፊ እንደሚሆኑ አቅደው ወደ ጦርነት ገቡ፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ላይ ‹‹መብረቃዊ ጥቃት›› ስብሓታውያኑ ከፈቱ፡፡ የፌደራል መንግሥቱ 44 ሺሕ ያህል ጦር ይዞ 250 ሺሕ ጦር ካላቸውና አሸባሪ ካላቸው ጋር ውጊያ ገጠመ፡፡ በ17 ቀናት ውስጥም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የመቀሌ ከተማንና ሌሎችን አካባቢዎች በእጁ አስገባ፡፡ እነ አቶ ስብሓት ነጋ ከተደበቁበት የተምቤን በረሃ ተይዘው እየተጎተቱ ወጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የእነ ስብሓትን ቡድን ‹‹ዱቄት›› መሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ስሜት ገለጹ፡፡ አሸናፊነቱን ያረጋገጠው የፌደራሉ መንግሥት በሙሉ ነጋ (ዶ/ር) የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር ትግራይ ላይ አቋቋመ፡፡

ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ለተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራሉ መንግሥት ሊያደርገው የሚገባውን ድጋፍ በበቂ አላደረገም የሚል ክስ የነበራቸው ቢሆንም፣ እሳቸው ራሳቸው ግን የስብሓታውያን አጀንዳ አስፈጻሚ መሆናቸውን የሚገልጹ ወገኖች በየጊዜው ቅሬታቸውን ከማሰማት አልቦዘኑም ነበር፡፡ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ኃላፊነት የያዙ ሰዎች እየተገደሉ ባለበት ጊዜም፣  ሙሉ (ዶ/ር) እየሠሩት ያለውን አሻጥር እየጠቀሱ ለመንግሥት መረጃ የሚሰጡ ክፍሎች ቢኖሩም የፌዴራሉ መንግሥት ግን የሕዝቡን ጩኸት መስማት አልችል ብሎ ችግሩ እየተባባሰ ሄደ፡፡

የፌደራሉ መንግሥት ወደ ክልሉ ሲገባ ድጋፉን የለገሰው ተራው የትግራይ ሕዝብ እየሆነ ባለው ነገር እያዘነ ሄደ፡፡ እንዳሰበውና እንደጠበቀው ሊሆን ባለመቻሉ እየጨነቀው ፊቱን ወደ ስብሓታውያኑ አዞረ፡፡ አንዳንዱ ‹‹ድረሱልን›› የሚል የሐሰት ጥሪ በማቅረብ መከላከያ ሠራዊት በስብሓታውያን ጦር እንዲጠቃ አደረገ፡፡ በዚህ የተማረረው ማዕከላዊ መንግሥት ምክንያቶቹን ደርድሮ ሠራዊቱን ከትግራይ አወጣ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በግልጽ አማርኛ መንግሥት ከጎኑ የቆመውን የትግራይን ሕዝብ ከዳው የሚያሰኝ እንደ ነበር መግለጽ ግድ ነው፡፡ ዋና ዋና ወታደራዊ ቦታዎችን ይዞ መቆየት እንደነበረበት የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡

‹‹ዱቄት ሆነዋል›› የተባሉት ስብሓታውያን እንደገና አንሰራርተው የአፋርና የአማራ አካባቢዎችን ወረሩ፡፡ ከምሥራቅ እስከ ሰሜን ጫፍ ያለውን አገር የጦር ሜዳ አደረጉት፡፡ በወልዲያ – ደሴ መስመር እስከ ደብረሲና ዘልቀው ገቡ፡፡ ‹‹የምን ድርድር ይልቅስ እጃችሁን ስጡ›› የሚል መልዕክት ለሠራዊቱና ለፌደራሉ መንግሥት መሪዎች አስተላለፉ፡፡ አጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ በገሐድ ታየ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ጦር ግንባር የዘመቱትና የስብሓታውያኑን ጥቃት መቀልበስ የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊት በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ገሰገሰ፡፡ መቀሌ በከበባ ውስጥ ገባች፡፡ ስብሓታውያኑ መቀሌ ከተማ ውስጥ ሆነው ከተማዋን መዋጊያ ሊያደርጓት እንደፈለጉ አሳዩ፡፡ መንግሥትም የከበባ ቀለበቱን እያጠበበ መሄዱን ቀጠለ፡፡ ከተማዋን ለመያዝ ግፋ ቢል ከሳምንት የበለጠ ጊዜ እንደማይወስድበት እየታመነ መጣ፡፡

በሳተላይት መረጃ በመስጠትና በአውሮፕላን በድብቅ የጦር መሣሪያ በማስገባት ስብሓታውያንን ሲያስታጥቁ የቆዩት ምዕራባውያን የተኩስ አቁም እንዲደረግና ድርድር እንዲጀመር መወትወት ያዙ፡፡ ጫፍ ላይ የደረሰውን ጦርነት ጨርሶ በሙሉ አሸናፊነት መቆም የነበረበት መንግሥት የድርድር ጥያቄውን ተቀብሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጓዘ፡፡

መንግሥት ‹‹ድርድሩ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሳይሆን ከአንድ አመፀኛ ቡድን ጋር ነው፡››  ብሎን እንደነበር ልብ እንበል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ሲደርስ ስብሓታውያኑን ያየበትና የያዘበት መንገድ ግን ከአንድ አቻ አካል ጋር የሚደረግ ያስመሰለ መሆኑ ታይቷል፡፡ የስብሓታውያኑ ዓርማ ከኢትዮጵያ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጎን ቦታ እንዲሰጠው ማድረግ በራሱ ለእኔ የተሸናፊነት ማሳያ ነው፡፡ የመንግሥት ተደራዳሪዎች ተቃውሞ አለማሰማታቸውም ሌላው መሸነፍ ነው፡፡

ስብሓታውያኑ በመሩት ጦርነት በአፋርና በአማራ ክልሎች ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት፣ የመሠረተ ልማትና የተቋማት ወድመት ደርሷል፡፡ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የትግራይ ወጣት በጦር ሜዳ እንዲረግፍ ያደረጉ፣ እነሱ በቀሰቀሱት ጦርነት እስካሁን ቁጥራቸው በውል ባልታወቀ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በአፋርና በአማራ ሚሊሺያና ልዩ ኃይል፣ እንዲሁም በአማራ ፋኖ ላይ ሞትና የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ስብሓታውያኑ በማይካድራ ከ1,500 በላይ አማራዎችን በዘራቸው ለይተው እንዲገደሉ በማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀለኞች መሆናቸውንና የወንጀል ሸክማቸው የከበደ መሆኑን የመንግሥት ተደራዳሪዎች ያሰቡት፣ የተገነዘቡት ስለመሆናቸው የሚያሳይ ድርድር ውስጥ የገባ ጭብጥ ስለመኖሩ ሲታይ ደግሞ ይበልጥ የሚያሳዝን ይሆናል፡፡

በድርድሩ በአገር ላይ በሠሩት በደል ልክ ስብሓታውያኑ ወንጀላቸውን እንዲሸከሙ ማድረግ ባይቻልም፣ ትጥቃቸውን ሙሉ በመሉ እንዲፈቱና በክልሉ ምርጫ ተካሂዶ የክልል መንግሥቱ እስከሚቋቋም ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር የመመሥረት ሥልጣን ለፊዴራል መንግሥት መሰጠቱ መልካም ነው – ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ እንዲሉ፡፡

የከፋው ግን ስምምነቱ ከተደረገ ሦስት ወራት ያለፈው ቢሆንም፣ በስምምነቱ መሠረት ትጥቃቸውን መፍታት የነበረባቸው ስብሓታውያኑ አሁንም 95 በመቶ ከነበረ ትጥቃቸው ጋር መገኘታቸው፣ ታጣቂዎቻቸው መሣሪያቸውን አውርደው ወደ ሥልጠናና ወደ ተሃድሶ ጣቢያ መግባት ሲኖርባቸው እስከ አሁንም ከእነ ትጥቃቸው መሆናቸው፣ ድርድሩ የለበጣ ነበር እንዴ? ብሎ የሚያስጠይቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ጄኔራል ታደሰ ወረደ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ታጥቀው መነሳታቸውን ካስታወቁ በኋላ ተግባራዊ ተደርጎ አቶ ጌታቸው ረዳ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሆነው ሲሾሙ፣ እሳቸውም በቅርቡ 27 አባላት ያሉት ልዩ ካቢኔያቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል ለውይይት በቀረበው የመመሥረቻ ሰነድ ላይ 55 በመቶ የሚሆነውን የሥልጣን ቦታ የስብሓታውያኑ የፖለቲካ ድርጅትና የወታደር ኃይላቸው እዲይዙት ተደርጓል፡፡ 15 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በክልሉ ለሚገኙ ተቃዋሚዎች የተመደበ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የቀሪው 30 በመቶ ባለቤቱ ባይገለጽም ማን እንደሚይዘው የታወቀ ነው፡፡ ምክትል አስተዳዳሪ ተብለው የተሰየሙት ደግሞ ሌተና ጀኔራል ታደሰ ወረደና ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ እንዲይዙት መደረጉም ተገልጧል፡፡ ይህ የሆነውና እየሆነ ያለው ‹‹በፊዴራሉ መንግሥት ዕውቅና›› መሆኑንም ሹመታቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የፀደቀላቸው አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል፡፡

ይህ ማለት ተሸናፊዎቹ ስብሓታውያን ተመልሰው አሸናፊ እየሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ የአገሩን አንድነት ለማስከበር ከመንግሥት ጎን ቆሞ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት የከፈለው ሕዝብ ድካም ገደል እንዲገባ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ ስብሓታውያኑ እንደገና አገግመውና ተደራጅተው ለሦስተኛ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ እንዲፈጽሙ ሁኔታዎች እየተመቻቹላቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ድርጊት ራስ ይዞ ኡኡ የሚያሰኝ አይሆንም?

የኢትዮጵያ ሕዝብ ድካምና መከራ እንዲበዛበት የሚያደርጉት የታወቁት ጠላቶቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ማድረግ ያለባቸውን በሰዓቱና በቦታው የማያደርጉና ማድረግ የማይፈልጉ የራሱ መሪዎችም ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሃም በላይና (ዶ/ር) ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ቆም ብለው ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የፖለቲካ ተደራዳሪው ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ ወታደራዊ ድርድሩን በኬንያ ናይሮቢ የመሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያመጣንለት ምንድነው ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው፡፡

መሪዎቻችን በደቡብ አፍሪካና በኬንያ የተደረሰውን ስምምነት ወደ መሬት ማውረድ ባልፈለጉ ቁጥር፣ በጦር ሜዳ የተሰው ወገኖቻችንን ደም በእነሱ እጅ እንደፈሰሰ ከመቁጠር ሕዝብን የሚያግደው ነገር ያለመኖሩን እንዲገነዘቡልን እፈልጋለሁ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ ማሳሰብ የምፈልገው የወገኖቻችንን መስዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን፣ የትግራይ በአጠቃላይም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለሌላ ችግር የሚጋለጥበት መንገድ እንዳይከፈት ነው፡፡

ገጣሚ ዮናስ አድማሱ በአንድ ወቅት የጨነቀ ነገር ገጥሞት የተጠቀመበት ምሳሌ ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ›› የሕዝቡን ሕይወት፣ ሀብትና ንብረት መታደግ ያለበት መንግሥት ጉዳዩን እንደ ቀላል ሲያየው መመልከትን ያህል የሚያስጨንቅስ ምን ነገር አለ? ነገሮች እየተበላሹና ከመስመር እየወጡ ሲሄዱ፣ ‹‹ መንግሥት ሆይ ሰነፍ እረኛ አትሁን›› ብሎ መጮህ ግድ ያልሆነ ምን ግድ ይሆናል?

ሌላው የወቅቱ አሳሳቢው ችግራችን የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ በመንግሥት የተላለፈው ውሳኔ ነው፡፡ ስብሐታዊያን ከበፊት ጀምሮ የልዩ ኃይላቸውን ሲያደራጁ ባለ ታንክ ሲያደርጉ፣ ሌሎች ግን በክላሽ እንዲወሰኑ አድርገው ነበር፡፡ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ሳይደረግና እነሱ ትጥቃቸውን ሳይፈቱ፣ እነ ጌታቸው ረዳ ሥልጣን መያዛቸው አማራን ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ እንደከተተው ይታወቃል፡፡

በራያም ሆነ በወልቃይት አካባቢዎች ስብሐታውያን ኃይላቸውን እያስጠጉ ለመሆናቸው መረጃ መኖሩ፣ እንዲሁም ተጨማሪ ጦር እየመለመሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ዘመኑ የመረጃ በመሆኑ ከመንግሥት ያላነሰ መረጃ በሕዝብ ውስጥ መዘዋወሩ፣ መንግሥትም ለመታመን እየከበደው መምጣቱ፣ ልዩ ኃይሉን ወደ ሌሎች መዋቅሮች ማስገባት ማለት የራሱን የዕዝ ሰንሰለት ማሳጣት መሆኑ፣ በሁሉም ክልሎች በእኩል ጊዜ አለመጀመሩና የአማራ ልዩ ኃይል መጀመሪያ መደረጉ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ስለዚህ መንግሥት በአማራ ክልል ለተነሳበት ተቃውሞ ቦታ ሰጥቶ መፍትሔ እንዲፈልግ እንደ አንድ ዜጋ አሳስባለሁ፡፡ ‹‹እባብ ያየ በልጥ ይበረግጋል›› እንደሚባለው ከዚያ ሁሉ ዕልቂትና ውድመት በኋላ ተመልሶ አገርን ችግር ውስጥ መክተት ተገቢ አይደለም እላለሁ፡፡

ፈጣሪ ቸር ወሬ ያሰማን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...