በገነት ዓለሙ
አገራችን ውስጥ ዴሞክራሲና ሻል ያለ ዓለም የሚታይበት ሥርዓት ለመመሥረት የተጀመረው ትግል ሁለት ዓመታት ብቻ ሳይሆን ብዙ የሰው ሕይወት፣ የአገር ሀብትና ንብረት ከፈጀ ጦርነት በኋላ፣ በፕሪቶሪያው የጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰላም ስምምነት አማካይነት የዘላቂ ሰላምን አቅጣጫ ይዞ ወደ እዚያ የሚወስደውን ጉዞ አንድ ሁለት ብሎ ጀምሯል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ራሱ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ይህ የሰላም ስምምነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ከመፈረሙ በፊት ባሳለፍናቸው ሁለት የጦርነት ዓመታት እንዳየነው፣ ለምሳሌ ሰኔ 2013 ዓ.ም. እና መጋቢት 2014 ዓ.ም. እንደሆነው ዓይነት የአንድ ወገን ብቻ የግጭት ማቆም ዕርምጃ አይደለም፡፡ የሰላም ስምምነት ነው፡፡ ስምምነቱ ኦፊሴል (ይፋ) ስያሜው ደግሞ ከዚህም በላይ ብዙ ነገር ይናገራል፡፡ በኢፌዴሪና በሕወሓት መካከል ግጭትን በቋሚነት በማቆም አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገ ስምምነት ነው፡፡
የስምምነቱን ረዥም ርዕስና መጠሪያ ራሱን ብቻ ዓይቶ መረዳት እንደሚቻለው፣ ስምምነቱ ዘላቂ ሰላም ላይ ዝም ብሎ ዘሎ መግባት ይቻላል አይይልም፡፡ ግጭት በማቆም፣ ግጭት የማቆምን ዕርምጃ ቋሚና ዘላቂ እያደረጉ በመሄድ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስደውን መንገድ ይይዛል፡፡ ዋናው ግብ ዘላቂ ሰላም ነው፣ ዘላቂ ሰላም ላይ ለመድረስ የተሻለ ሁኔታ መፍጠር፣ መሠረቱንም ማደላደል፣ ይህንንም መጀመርያ ከአስቸኳይና ቀስ እያለም ቋሚ እየሆነ ከሚቀጥል ግጭት ማቆም መነሳት ብሎ ይጀምራል፡፡
የስምምነቱ መግቢያ፣ ከመግቢያው ቀጥሎ የሚመጣው የስምምነቱ ግብ (አንቀጽ1)፣ በአንቀጽ 2 የተወሰነው ግጭትን በቋሚነት የማቆም የመርህ መሠረቶች፣ ወዘተ የሚያሳዩትና የሚያረጋግጡት ድሮም ቢሆን፣ ወደ ጦርነት ውስጥ ከመገባቱም በፊት ቢሆን ብቸኛው መንገድ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል መሆኑን ነው፡፡ የጠቃቀስናቸውን አንቀጾች አንዳንድ መሪ ቃሎች እንመልከት፡፡
- ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈቱት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ መሆኑን በማረጋገጥ፣
- ትግራይ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ ለግጭቱ ዘላቂና አካታች መፍትሔ ለማምጣት ቁርጠኛ በመሆን፣
- ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት (ከመግቢያው) ነውጥን የትግል መሣሪያ ማድረግን እንቢ ማለት (ግብ)፣
ይህንን የመሳሰሉት ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድን የሚያነጥፉት የስምምነቱ ሁኔታዎችና ውለታዎች የማዕቀፍ ግቢ ደግሞ የኢትዮጵያ (ኢፌዴሪ) ሉዓላዊነት የአገርና የግዛት አንድነት፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ ናቸው፡፡ አምስት ወሩን ጨርሶ ስድስተኛው ወር ውስጥ የገባው የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም፣ አሁን የሚገኝበት ወሳኝ ደረጃ በስም የጠቀሱትን የስምምነቱን ተዋዋይ ወገኖች ብቻ ሳይሆን፣ እነሱንም ጨምሮ የመላውን ቤተ ዘመድ ዴሞክራሲያዊነት፣ ለሕጋዊነት መገዛት፣ እንዲሁም ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኛ መሆንን የግድ ይፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ‹‹የቤተ ዘመዱ [ሁሉ] ይታያል ጉዱ›› የሚባልበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡
ጉዳዩን በዝርዝር ለመመልከት፣ ከሕወሓት ከራሱ ልጀምር፡፡ ሕወሓት ትጥቅ መፍታት አለበት፡፡ ፓርቲው ይህንን ማድረግ ያለበት ውል ስለገባ፣ ፕሪቶሪያ ላይ ስለፈረመ ብቻ ሳይሆን፣ ፓርቲ ስለሆነ፣ ፓርቲ ሆኖ ስለተመዘገበ (ተሰጥቶት የነበረውም ስያሜ ስለተነሳ) እንደ ማንኛውም ፓርቲና ድርጅት ወደ ሰላማዊ ተፎካካሪነት መለወጥ፣ ይህም ሰላማዊና ሕጋዊ ተፎካካሪነት የሚጠይቀውን ምግባርና ባህርይ መያዝ አለበት፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ፓርቲ ሆኖ መደራጀት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ መምጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሥልጣን የሚወዳደሩት የታጠቁ ፓርቲዎች አይደሉም፡፡ የሚቋቋሙት ፓርቲዎች በሙሉ በሕግ የታወቀና የተወሰነ ዴሞክራሲያዊ አመለካከትና ተመሳሳይ ድርጅታዊ የአሠራርና የአኗኗር መለኪያን ያለፉ እንዲሆኑ ሕግ የሚያስገድደው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የገንዘብ ‹‹ትጥቃቸው››ን እንኳን ከየት ያገኛሉ የሚባሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ሕወሓት ትጥቅ ፈታ የሚባለው ይህ የፕሪቶሪያው ስምምነት ያቋቋመው ግዴታ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በቀረበበት መልክ ደግሞ የአንዱን አካባቢ ሕዝብ ከአፈናና ከጥርነፋ ማላቀቅ ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ታጣቂዎች በአግባቡና በሕግ መሠረት ትጥቅ መፍታት አለባቸው፡፡ የጦር መሣሪያዎች ያለ ሸፍጥ መሰብሰብ ይገባቸዋል፡፡ የትም ቦታ የዘረጋው የአፈናና የጥርነፋ መረብ መበጣጠስ አለበት፡፡ በትግራይም በመላው ኢትዮጵያ ጭምር ለየትኛውም ቡድን ያላደረና የማያድር ለሙያው የታመነ የአካባቢ ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ግንባታ እየጠራ፣ እየተሳካና እያማረበትም የሚመጣው፣ ከሌሎች መካከል እነዚህ ሒደቶችና ክንዋኔዎች ሳይልከሰከሱ ተፈጻሚ ከሆኑ ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን የብዙ ፓርቲዎችን ነፃ ህልውና ይጠይቃል/ይፈልጋል እያልን፣ የፓርቲዎች መንግሥታዊ ገዥነትም ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበት አዲስ ምዕራፍ ይከፈት እያልን፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት አንቀጽ 6 አፈጻጸምን መጀመርያ በድል ማጠናቀቅ አለብን፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና አንጓ የሆነውን ‹‹DDR››ን በውጤትነት ያስከተለው የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት አንድ ብቻ ነው የሚለው ሕገ መንግሥታዊ ምሰሶ ነው፡፡ ይህ እውነትና ሕግ ጭምር ከእነ ሁለመናው ተቀበሉኝና አስፈጽሙኝ ሲል የኖረው ገና ከጦርነቱ በፊት፣ ጦርነት ውስጥም ከመግባታችን በፊትና ስለቲዲኤፍም መነጋገር ሳይጀምር በፊት ነው፡፡ ሲጀመርም እኮ 2010 ዓ.ም. የለየለት ትግል ዒላማ ገዥው ቡድን ራሱ አልነበረም፡፡ እኔ ብቻ ልክ ብሎ፣ የምገዛውም ለብቻዬ ነው ብሎ፣ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ በአስተሳሰብና በአሠራር ባህል ላይ ብልሽት ነበርና ትግሉ መንግሥታዊ አውታሩ ከሕወሓት ቡድን ይዞታነት እንዲላቀቅና የዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ችሮታነት እንዲያከትም በመታገል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ሕግ ይከበር፣ መንግሥት ሕጉን ያክብር፣ ሕገ መንግሥታዊ መብቶች አይረገጡ፣ መንግሥታዊ ሕገወጥነትና አጥፊነት ተጠያቂ ይሁን ማለትን የመሰለ ዛሬም ትናንትም የሚያዋጣና የሚቀድም የትግል ሥልት የለም፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በፌዴራል ወይም በማዕከላዊ መንግሥትና በክልል መንግሥታት የተዋቀረውና የመንግሥትንም ሥልጣን ለእነዚህ መንግሥታት ያከፋፈለው/ያደላደለው ሕገ መንግሥት መሠረት አገር የመከላከል የመንግሥት ሥልጣን የማነው? የፖሊስስ? የሚል ጥያቄ የሰላማዊ ትግል ጥያቄ ጭምር ሆኖ ሲነሳ ቆይቷል፡፡
ሕገ መንግሥቱ በዚህ ረገድ ግልጽ ነው፡፡ አገር የመከላከል የመንግሥት ሥልጣን የማዕከላዊው ማለትም የፌዴራሉ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ የፖሊስ ሥልጣን ግን የሁለቱም ነው፡፡ አንዱ ወይም የሌላው ብቻ አይደለም፡፡ የፌዴራል ወይም የክልል ሥልጣን የሚባሉ የፖሊስ ሥልጣኖች አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በተረቀቀበት ወቅት በነበረው የአርቃቂዎች ቋንቋ እንኳን የፖሊሲ አገልግሎት (Police Service) አላለም፡፡ የፖሊስ ኃይል ነው ያለው፡፡ እንዲያም ሆኖ ዛሬ ፖለቲካ አጀንዳችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ሰላማችንን ጤና የነሳው የልዩ ኃይል ነገር እንኳንስ ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ሌላው ሕግ ቋንቋ ውስጥም የሚታወቅ የሕግ ድጋፍ ያለው አይመስለኝም፡፡ ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ጊዜ የተረቀቀውና ሕግ የሆነው የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ፖሊስ ኃይል ብሎ ነገር ማለት ላይ አምፆ፣ የፖሊስ አገልግሎትን ከሲቪል ቁጥጥር ጋር ሲደነግግ በአገራችን ከሕገ መንግሥቱ ወዲህ የወጣው የፖሊስ ማቋቋሚያ ሕግ (የመጀመርያዎቹ ሁለቱ) መግቢያቸው ውስጥ ስለሲቪል ፖሊስ ቢያወሩም ወታደራዊ ማዕረግን ከማስቀረት በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ሻል ያለ ለውጥና ተጨማሪ እሴት ያመጣ ነገር አልበረም፡፡ ይልቁንም ወታደራዊ ማዕረጉን እንዲሁ ዝም ብሎ የተነጠቀው የፖሊስ ኃይል በተግባርም በትጥቅም ሚሊታራይዝድ እየሆነ መጣ፡፡ በልዩ ኃይል መልክ ደግሞ ‹‹እያማረበት›› ራሱን የቻለ ሠራዊት እየሆነ መጣ፡፡ የክልልን ልዩ ኃይል አደገኛና ኢሕገ መንግሥታዊ የሚያደርገው የልዩ ኃይል መኖር በራሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ በላይ የመከላከያ ሠራዊት አለ የሚል መልዕክት ስለሚያስተላልፍ፣ የመከላከያ ሠራዊትን የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ስለሚገዳደር ብቻ አይደለም፡፡
ሕገ መንግሥቱ ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል›› ይላል፡፡ በዚህም መሠረት ለሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 የተዘረዘሩ ዘጠኝና በዚያው አንቀጽ ንዑስ ቁጥር (3) (ሠ) መሠረት፣ በሪፈረንደም የተጨመሩ ክልሎች የፌዴራሉ መንግሥት አባላት ናቸው፡፡ ይህን የመሰለው የፌዴራል አካላት አከፋፈሉንና አካባቢያዊ ሥልጣንን የተወሰነ ማኅበረሰብ ርስት የመሬት ቅርጫ ማረጋገጫ ያደረገ ንቃትና የፖለቲካ አቋም አቋቁሟል፡፡ በዚህ ላይ ፓርቲያዊ አደረጃጀት ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የክልሎች አወቃቀርና ብሔርን መሠረት ያደረገ ፓርቲነትና ገዥነት ተደጋግፈው በየክልሉ ሕዝብን ቤተኛና ባይተዋር አድርጎ ለመከፋፈል መዘዝ ሆነዋል፡፡ ይህንን በመሰለ የአስተዳደር ምድር የሚደራጅ የታጠቀ ኃይል ደግሞ አድሏዊና አንጓላይ መሆኑ (በአንድ ክልል ውስጥ የእኔና የእኔ ያልሆኑ የሚላቸው መኖሩ፣ ከሌላው ክልል አንፃር ደግሞ ክልሌና ሌላው ክልል መባባል መኖሩ) አንድና ሁለት እንደሌለው ዓይተናል፡፡ በብሔርተኛ ወገንተኛነት የተሞላ ክልላዊ ታጣቂ ምን ያህል ደም አፋሳሽ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል እስኪሰቀጥጥ ድረስ ዓይተናል፡፡ በዚህ ምክንያት ድሮም ቢሆን ከአጀማመሩ ልዩ ኃይል ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ማዕከላዊው/ፌዴራል መንግሥት ሕግ ማስከበር ክልሎችም በሕግ ሥር ማደር ስላለባቸው ጥንትም ቢሆን ተከልከል በአዋጅ ሊባል የሚገባው ሥራ ነው፡፡
አሁን የተነሳውን ይህንን የተወዘፈ ሥራ ውስብስብ፣ አስቸጋሪና አገር አማሽ ያደረገው ከተለያየ አቅጣጫ ተረባርቦ አንድ ላይ የገጠመና እልም ያለ ችግር፣ እልም ያለ ‹‹ጫካ›› የፈጠረ ነገር ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ይህንን ‹‹እልም ያለ ጫካ፣ እልም ያለ ዱር›› ተብሎ ቢጠራስ ያልኩትን ነገር ፈረንጆች ‹‹ፐርፌክት ስቶርም›› ይሉታል፡፡ የተለያዩና በርካታ ክፉ ነገሮች አምሳያ የሌለው፣ ያልተለመደ ጥምረት ወይም አንድነት መሥርተውና ተዋህደው የፈጠሩት ነውጠኛ ማዕከል ማለት ነው፡፡ የምንገኝበት ጊዜ ሌላ የውዝግብ ርዕስ ሊጨመርበት አይገባም፡፡ የሰሜኑን ጦርነት ያስቆመው፣ ግቤ ዘላቂ ሰላም ነው የሚለው የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋና ዋና የፊርማው የጀርባ አጥንት የሆኑ አደጋዎችን ገና አላቀላጠፈም፣ አላጠናቀቀም፡፡ በተለይም ከምንነጋገርበት የልዩ ኃይል እንደገና/መልሶ መደራጀት የተባለው አዲስ የልፊያ አጀንዳ የጫረውን እሳት በተመለከተ፣ የስምምነቱ የአንቀጽ 6 (DDR) ነገር በደንብና በሚገባ እየተነገረ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ስለዚህ ስምምነቱ አፈጻጸም፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ትግራይ ውስጥ ስላለው ትክክለኛ እውነታ ጥርት ያለ መረጃ ማግኘት ችግር ነው፡፡ ብዙው ነገር፣ ምናልባትም ሁሉም ነገር ድብስብስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ (የፕሪቶሪያው ስምምነት ፈራሚዎችን በሚጠሩበት ስም/ስያሜ ለመጠቀም) ከፌዴራል መንግሥት ወገን ከሚገኘው መረጃ ይልቅ፣ ከሕወሓት ወግ የሚገኘው ወሬ/መረጃ ያመዝናል፡፡ ሕወሓት ትጥቅ ስለመፍታቱ እንሰማና እንደገና ደግሞ አሁንም ፀጥታ ማስከበርን በመሰለ ሚና ላይ ተሰማርቶና ታጥቆ እንደሚገኝ እንሰማለን፡፡
የትግራይ መገናኛ ብዙኃን ዛሬም፣ አሁንም የሕወሓት ልሳን ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ለዚያውም ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ይገዛሉ፣ ይታመናሉ (ስምምነቱን አይቃወሙም) የሚባሉት የመገናኛ ብዙኃን መደበኛ ዜናና ፕሮግራም ስለ የ‹‹[ክልሉ] ግዛታዊ አንድነት››፣ የ‹‹[ክልል] ሕገ መንግሥታዊ ግዛት መመለስ›› ማለትን የመሰለ የስምምነቱን የቅን ልቦና አፈጻጸም ድንጋጌ ለአደጋ የሚያጋልጥ ደመኛና ጠንቀኛ የሆነ ርዕስ ሲያነሱና ሲጥሉ እንሰማለን፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች ስለ‹‹የጄኖሳይድ ኃይሎች›› ሲያወሩና ዜና ሲሠሩ የምንሰማውም በሰሜናዊ የአገራችን ክፍል ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ጦርነት ስላስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት የአምስት ወራት አፈጻጸም በምንነጋገርበት ወቅት ነው (በነገራችን ላይ ኅዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሰጠው የስምምነቱ አፈጻጸም ሞዳሊቲ መግለጫ በአንቀጽ 6 ሚዲያን በኃላፊነት ስለመጠቀም ይደነግጋል፡፡ የስምምነቱ አካል የሆነው ‹‹መግለጫ›› የስምምነቱ አንቀጽ 3 (2) እና አንቀጽ 12 የሚያቋቁሙትን ግዴታዎች መልሶ መላልሶ ያረጋግጣል፡፡ ግጭት በቋሚነት የማቆም ተግባር ደመኛ ፕሮፓጋንዳን፣ ተረክን፣ የጥላቻ ንግግርን ማቆምን እንደሚጨምር ስምምነቱ ‹‹የቅን ልቦና አፈጻጸም›› የሚባል ድንጋጌ እንዳለው አስረግጦ ይወስናል)፡፡ እንዲያም ቢሆን ግን፣ ከየትኛውም ፓርቲና ፖለቲካ ባለቤትነትና ተቀጽላነት የፀዳ ሚዲያ እናቋቁማን ማለት አምስት ዓመት የደፈነው የለውጡና የሽግግሩ ዋና መረባረቢያ በሆነበት፣ የፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣን በተዘረጋበት መላው ኢትዮጵያ ውስጥም ሚዲያና ፖለቲካ ዛሬም ገላጋይና ተቆጪ አላገኙም፡፡ የሌላውን ጎዶሎና ጥፋት የሚሞላ ‹‹ተረፍ›› ያለውና በአርዓያነት የሚጠቀስ በመንግሥት ባለቤነት ውስጥ ሆኖ ከመንግሥታዊ ፓርቲ ፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዘርፉና በሙያው ያስመዘገበውን ዓይነት አቻ ድልና ሪኮርድ ያሳየን የመንግሥት ሚዲያ የለም፡፡ እነዚህ ችግሮች ዋናው ሕመማችንን፣ ለዘላቂ ሰላም የተደረገው ስምምነት የሚጠይቀንን የግዳጅ አፈጻጸም ያወሳስቡበታል፡፡
‹‹የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን›› ሌላው ችግር ፈጣሪ ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ማለት ባለበጀት መሥሪያ ቤቱን ማለት አይደለም፡፡ የመንግሥት ሥራና አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ነው ወይ? መንግሥትን ራሱንና ሥራውንና አሠራሩን ፀሐይ ይሞቀዋል ወይ? ሕዝብ ያውቀዋል ወይ? ሁልጊዜም ለዘለቃው እንዲያ ሆኖ ተደራጅቷል ወይ? ተስፋ የሚሰጥ መልስ ያለው ጥያቄ አይደለም፡፡ ይህ ‹‹ልዩ ኃይል›› ማደራጀትን የሚመለከተውን ጉዳይ ይዘን ጥያቄውን ለመመለስ አንሞክር፡፡ መንግሥት የዚህን ጉዳይ አሠራሩን ግልጽ ለማድረግ መከራውን ማየት የጀመረው ዕርምጃው፣ ወይም ውሳኔው እሳት ከጫረ፣ የጫረው እሳት አገር እበላለሁ ማለት ከጀመረ በኋላ ነው፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መሥሪያ ቤት መግለጫ መጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ወጣ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩም የሚያዝያ 1 ቀን እሑድ ጠዋት መግለጫም ‹‹ተጨማሪ እሴት›› ይዞ አልመጣም፡፡ ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙም ማብራሪያ የሰጡት ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ከጮኸ›› በኋላ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ አሁንም መንግሥት የመንግሥታዊ ዕርምጃውን እጅና እግር፣ እዚህ ላይ የደረሰበትን ሒደትና አሠራር ግልጽ (ይጠብቃል) ግልጥልጥ አድርጎ አላስረዳም፡፡ ‹‹መንግሥት… አቅጣጫ አስቀምጧል…››፣ ‹‹…በዚህ መሠረት የየክልሉን ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችሏቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል…›› የሚለው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መግለጫ ራሱ ከመንግሥት ቋንቋ ይልቅ በፓርቲ አፍ መናገር የቀናው ነው፡፡ የገዥው የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአማራ ክልል የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ የሰጡት ማብራሪያም ዋናውን አንገብጋቢ ጉዳይ፣ እሳት ማጥፋትን የአደጋውን መስፋፋት መከላከልን በሚመለከት ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ መኖሩን ሳያስተባብሉ፣ እሳቸውም ያሳዩን ገዥው ፓርቲ ዛሬም መንግሥትንና ፓርቲን ‹‹በየፈርጃቸው ይለብሳሉ›› ማለትን ገና ገና ማወቅ ደረጃ ላይ አለመድረሳችንን ይመሰክራሉ፡፡
አሁን ያጋጠመንን አደጋ ተረባርበው ካወሳሰቡት ጉዳዮች መካከል ሌላው ልዩ ልዩ ልክና መልክ ይዞ ሲፈታተነን የኖው የውጭ ተፅዕኖ ነው፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ዋናው መሠረትና ‹‹መንፈላሰሻ›› ሕገ መንግሥቱ መሆኑ ትልቁ ድላችን ነው፡፡ አንቀጽ 6 የመነጨውና የተወለደውም ከዚህ ሕገ መንግሥታዊነት ውስጥ ነው፡፡ አንቀጽ 6 የትጥቅ ማስፈታት፣ የተዋጊነትን ሁኔታ ቀሪ ማድረግ፣ ወደ ሰላማዊ ኑሮ የመመለስ ተግባር ነው ‹‹DDR›› የሚባለው፡፡ በዚህ ስምምነት የተጠቀሰው ድንጋጌ እንደተወሰነው በኢዴፌሪ ሕገ መንግሥት መሠረትና ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር በተጣጣመና በገጠመ አሠራር ለሕወሓት ተዋጊዎች ደምላይ (ኮምፕሬንሲቭ) የ‹‹DDR›› ፕሮግራም ይቀረፃል፣ ሥራ ላይ ይውላል፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ይህ ግዴታና ፕሮግራም የሚፈጸምበትንም የጊዜ ማዕቀፍን ቢጋርም ያመለክታል፡፡ ይህንን የጊዜ ማዕቀፍ ይበልጥ ዝርዝር የሰጠው ኅደር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ናይሮቢ ላይ የተፈረመው የአፈጻጸም ሞዳሊቲ ስምምነት ነው፡፡ በተለይም በዚህ የናይሮቢ ስምምነት አንቀጽ 2 (1) (ዲ) መሠረት ከባድ መሣሪያዎችን የማስፋፋቱ ተግባር የውጭና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ካልሆኑ ኃይሎች ከክልሉ መውጣት ጋር አንድ ላይ ይከናወናል ተባለ፡፡ ከሌሎች መካከል በዚህ ምክንያት፣ በተለይም በዚህ የናይሮቢ ስምምነት አንቀጽ 2 (1) (ዲ) ድንጋጌ ምክንያት ናይሮቢ የፕሪቶሪያ ማስፈጸሚያ ነው ወይ? ናይሮቢ ፕሪቶሪያን ሊያሻሽል ይችላል ወይ? እውነትስ ይህ ማሻሻያ አይደለም ወይ? የሚሉ አቋሞች፣ ጥርጣሬዎችና ጥያቄዎች ተፈጠሩ፡፡
የሕወሓትን ትጥቅ መፍታት ከኤርትራ፣ ከሌሎች ኃይሎች ከክልሉ መውጣት ጋር ያቆራኘው የናይሮቢ ዲክላሬሽን፣ በተለይም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ያልሆነ ኃይል የሚለው ክፍሉ ሌላ ለጊዜው ተኝቶ የነበረ ጥያቄ/የተዳፈነ እሳት ጫረ፡፡ በዚህም ምክንያት የዋናው የፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 10 (4) ትርጉም፣ ትርጉም ብቻ ሳይሆን የጀርባ ‹‹ታሪክ›› ሁሉ መመርመርና መጠርጠር ተጀመረ፡ ‹‹ሁለቱም ወገኖች ውዝግብ ያስነሱ አካባቢዎችን በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ለመፍታት ተስማምተዋል›› ማለት ምን ማለት ነው? ምን ብለው ነው የተስማሙት? ይህ ውዝግብ የተነሳበት አካባቢ ራሱ ስሙ ማነው? ወልቃይት ፀገዴ ወይስ ምዕራባዊ ዞባ? ጥያቄው ራሱ ‹‹ፍርድ›› ወይም ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ ውዝግብ ያስነሳው አካባቢ በየትኛውም ስም ተጠራ፣ ውዝግቡ ራሱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታል ማለት (የስምምነቱ አንቀጽ 10 (4) ‹‹ውሳኔ››ም ከአንዱ ይልቅ ሌላውን ወገን ‹‹እኔን ይጠቅማል›› የሚያሰኝ ፍርኃትና ሥጋት የሚፈጥር ነው፡፡ በዘህም ምክንያት ነው የዚህ ክልል ወይም የዚያኛው ክልል ‹‹…ግዛታዊ አንድነት››፣ የእከሌ ክልል ‹‹…ሕገ መንግሥታዊ ግዛት መመለስ›› ብሎ ነገር ከስምምነቱ መንፈስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጋር ይጋጫል የሚባለው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሙያና ለኃላፊነት መታመንን የመሰለ ልዩ የጋዘጤኝነት ባህርይንና ጨዋነትን ይጠይቃል የሚባለው፡፡
የሕወሓትን ትጥቅ መፍታት፣ ሕወሓት በስምምነቱ አንቀጽ 6 መሠረት የተጣለበትን ግዴታ መወጣት (የአፈጻጸሙን ማረጋገጥ ጭምር)፣ የውል ባለዕዳ የሆነበትን ግዴታ ከመወጣት በላይ የአገር ሰላም፣ የአፍሪካም ሰላም ጉዳይ ነው፡፡ በአንቀጽ 6 የተወሰነውን የስምምነት ድንጋጌ ያወሳሰበው ግን በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ውስጥ ይህ ወይም ያኛው ቦታ (ለምሳሌ ድሬዳዋ) የማነው? የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ ጥያቄውን ለመመለስ ባለጉዳዩቹ ያለባቸው ግፊትና ተፅዕኖ ነው፡፡ ተፅዕኖና ጫናው የስምምነቱ ‹‹ታዛቢ››ዎች ብቻ ሳይሆን ‹‹ተሳታፊ›› ነን ከማለትም ትዕቢትና ጉልበተኝነት ይጀምራል፡፡ እነ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የመሳሰሉት ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆን ዋሶች ተብለው ሲጠሩ እንሰማለን፡፡ ከእነዚህ መካከል የአንዳንዶቹ ‹‹ኃይሎች›› ተግባር ከስማቸው በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የዩኤስ አሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ፣ በይዘቱም መግለጫው በተሰጠበት መድረክ ጭምር በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡
ሲጀመር መግለጫው የተሰጠው አሜሪካ የ2022 የዓለም አገሮችን (ከራሷ በተስተቀር) የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ይፋ ባደረገችበት መድረክ ነው፡፡ በዚህ መድረክ ከዚም በላይ ‹የአገሬ ሕግ ያጎናፅፈኛል›› ያሉትን ‹‹ሥልጣን›› ተጠቅመው ‹‹ፍርድ›› ሰጥተዋል፡፡
‹‹After careful review of the law and the facts, I have determined that members of the Ethiopian National Defense Forces (ENDF), Eritrean Defense Forces (EDF), Tigray People’s Liberation Front (TPLF) forces, and Amhara forces committed war crimes during the conflict in Northern Ethiopia.
‹‹Members of ENDF, EDF, and Amhara forces also commited Crimes Against Humanity, including murder, rape and other forms of sexcual violence, and persecution.
‹‹Members of the Amhara forces also committed and Crime Against Humanity of deportation of forcible transfer and commited ethnic cleansing in western Tigray.››
እንዲህ ያለ ‹‹ፍርድ›› በመደቡ የሚሰጠው በተለየ ሕግ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ ‹‹HR6600›› እና ‹‹S.3199›› ኢትዮጵያን ለማነቅና በማዕቀብ ለመቅጣት ብቻ ሳይሆን፣ የትኛውንም ዕርምጃ ለመውሰድ አፋቸውን ከፍተው አጋጣሚና ማመካኛ እየጠበቁ የቆዩ ሕጎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለምሳሌ ‹‹HR6600›› በአንቀጽ 10 ይህ ሕግ በፀደቀ ከ90 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ፣ በኢትዮጵያ ላይ እነዚህ ወንጀሎች ተፈጽመዋል የማለት ውሳኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲያሳልፍ ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር፡፡
በቅርቡ ደግሞ መጋቢት 26 ቀን የረሳናቸው የሚመስላቸው ካሉ አልረሳናቸውም ብለው ነው መሰለኝ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ‹‹እያየናችሁ›› ነው ብለውናል፡፡
‹‹The message to both the Government of Ethiopia and the Tigrayans is to make them understand that we are watching the settling of the conflict and will only normalize our relations in a gradual way, step-by-step, ›› Boreel said.
እና ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን እልም ያለ ችግር ተረባርበው ከሚያወሳስቡብን ጉዳዮች መካከል የውጭ ተፅዕኖ አንዱ ነው፡፡ የመንግሥት አመራር፣ የአሠራር ግልጽነት ደካማነትና በየጊዜም ዝርክርኩ እየወጣ መሄድም ይህንን ሁሉ አግዘውታል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡