Saturday, July 13, 2024

ኢትዮጵያ የገባችበት የውጭ ዕዳ ጫና አጣብቂኝና የአበዳሪ አገሮች ፖለቲካዊ ፍልሚያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ከአገር ውስጥ ምንጮች የተበደረችውን ሳይጨምር፣ ከውጭ አበዳሪ ምንጮች ተበድራ ያልመለሰችው የዕዳ መጠን ዛሬ ላይ 28 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። 

ኢትዮጵያ ካለባት 28 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ውስጥ 54 በመቶ የተገኘው ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ በተለይም ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ እንደሆነ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱ የሚያወጣው የዕዳ ሁኔታ መግለጫ ያስረዳል። የተቀረው 25 በመቶ ደግሞ ከቻይና መንግሥትና ከቻይና አበዳሪ ተቋማት የተወሰደ ሲሆን፣ ቀሪው 21 በመቶ ደግሞ ከውጭ የግል አበዳሪዎች የተገኘ የንግድ ብድር ነው።

ከዓለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት ባንክ የሚገኙ ብድሮች ወለድ የሚከፈልባቸውና በአማካይ በ30 ዓመታት ውስጥ የሚከፈሉ በመሆናቸው፣ እንደ ዕዳ ጫና የሚቆጠሩ አይደሉም። 

ነገር ግን ከቻይና መንግሥትና ከግል አበዳሪዎች የተወሰዱት ብድሮች ግን፣ በከፍተኛ የወለድ ምጣኔ የተወሰዱና በመካከለኛ ጊዜ የሚከፈሉ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል።

ኢትዮጵያ ባለባት የውጭ ዕዳ መጠን ምክንያት በዓለም የገንዘብ ድርጅት ‹‹አይኤምኤፍ›› እና በዓለም ባንክ የዕዳ ሁኔታ ትንታኔና ምደባ ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸው አገሮች ምድብ ውስጥ ወድቃለች። ይህ ምደባ ኢትዮጵያ ተጨማሪ አዲስ የውጭ ብድር መውሰድ የማትችልበት የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሳለች እንደማለት ሲሆን፣ ተጨማሪ አዲስ የውጭ ብድር ለመውሰድ የምትገደድበት ሁኔታ ቢፈጠር፣ አሁን ከምትገኝበት ምድብ ወጥታ ብድር መክፈል የማይችሉ አገሮች ውስጥ የመውደቅ አደጋ ይገጥማታል።

ይህ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የሚጎዳ ከመሆኑም ባሻገር፣ ከዚህ ምድብ የመውጣት ሒደትንም አስቸጋሪ ያደርገዋል። በውጤቱም ኢትዮጵያ የምትፈልግውን የኢንቨስትመንት ካፒታል ከውጭ የምታገኝበት ዕድል ተከርችሞ፣ የማትወጣው የኢኮኖሚ ፈተና ውስጥ እንደሚከታት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ሰሞኑን ለመንግሥት ሚዲያዎች መረጃ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ጫናው የመጣው ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ለመሠረተ ልማት ግንባታ የተወሰደና ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው የኢኮኖሚ ውጤት ባለማምጣታቸው የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹የዕዳ መጠናችን ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጂዲፒ አንፃር ሲለካ ገና 24 በመቶ ላይ ነው። ስለዚህ ያለብን የዕዳ መጠን በጣም ዝቅተኛ ነው። ነገር ግን ዕዳውን ለመክፈል አሁን የአጭር ጊዜ የገንዘብ ችግር (የካሽ ፍሎ ችግር) ገጥሞናል፤›› ሲሉ አቶ ማሞ ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት የቡድን 20 አገሮች የዕዳ ጫናን ለማቅለል ባዘጋጁት የዕዳ መልሶ ማዋቀር ሥርዓት ለመጠቀም ከሁለት ዓመታት በፊት ጥያቄ ማቅረቧን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተመራና የብሔራዊ ባንክ ገዥን አቶ ማሞን ያካተተ ከፍተኛ ልዑክ በአይኤምኤፍ እና በዓለም ባንክ የ‹‹ስፕሪንግ›› ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ፣ በዚሁም የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ መልሶ በማዋቀር ዕፎይታ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በአሜሪካ ተገኝቶ ነበር።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ የዓለም ባንክ ባዘጋጀው የታዳጊ አገሮች የዕዳ ጫና ጉዳይን የተመለከተ ውይይት ላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ በወቅቱም ኢትዮጵያ በቡድን 20 አገሮች የተሰናዳውን የውጭ ዕዳ ጫና ማቅለያ ለመጠቀም ጥያቄ ካቀረበች ከሁለት ዓመታት በላይ እንደሆነው በመግለጽ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የዕዳ ማቅለያ በመጠየቋ ተቀጪ ሆናለች፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ይህንንም ሲያስረዱ፣ ኢትዮጵያ በዕዳ ማቅለያ ማዕቀፉ ለመጠቀም አስባ ጥያቄ ብታቀርብም ሒደቱ ከመዘግየቱ ባለፈ ጥያቄዋን ከማቅረቧ ጋር በተያያዘ ብቻ፣ የአገሮችን ዕዳ የመክፈል አቅም በሚለኩ ዓለም አቀፍ ደረጃ አውጪዎች (Credit Rating Agency) የመክፈል አቅም ደረጃዋ ዝቅ እንዲል መደረጉን አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት ለአውሮፓ አገሮች የሸጠችው ዩሮ ቦንድ ግብይት መቀዛቀዙንና የአበዳሪዎችን እምነት መሸርሸሩን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ያለባት የውጭ ዕዳ ግልጽ፣ ዝቅተኛና አበዳሪዎቿም የተወሰኑ መሆናቸውን የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፣ ‹‹ለመንግሥት አስጨናቂ የሆነው የዕዳ መጠኑ ሳይሆን፣ አብዛኛው የውጭ ዕዳ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የሚከፈል መሆኑ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይም ኢትዮጵያ በአውሮፓ ገበያ በሸጠችው ዩሮ ቦንድ ያገኘችው አንድ ቢሊዮን ዶላር የመክፈያ ጊዜ በመጪው ዲሴምበር ወር መሆኑ ተጠቅሷል። 

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ በአሜሪካ መካሄድ የጀመረውን የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ የጋራ ጉባዔ መጀመር አስመልክቶ፣ ባለፈው እሑድ ሚያዝያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ የአፍሪካ አገሮች ያለባቸውን ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ማቅለያና የመክፈያ ጊዜን በመልሶ ማዋቀር ለማራዘም ያቀረቡት የዕዳ መልሶ ማዋቀር ጥያቄ መዘግየት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ፣ ጋናና ዛምቢያ የገጠማቸው የዕዳ ጫና ቀውስ እየሰፋ በመሄዱ፣ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ዕዳቸውን ለማቅለልና የመክፈያ ጊዜው እንዲራዘም ያቀረቡት ጥያቄ ላይ በአስቸኳይ መወሰን ያስፈልጋል ብለዋል።

‹‹ሁሉም አበዳሪ ወገኖች ቃላትን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ጊዜው አሁን ነው፤›› ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ የአገሮቹን በተለይም የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ መልሶ በማዋቀር የዕፎይታ ጊዜ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆነው አገሮቹ (ኢትዮጵያን ጨምሮ) ከቻይና መንግሥት የወሰዱት ብድርና የብድር ስምምነቱ ሚስጥራዊ መሆን፣ ሌሎች አበዳሪ አገሮች የቀረበላቸውን የዕዳ መልሶ የማዋቀር ጥያቄ ለመመለስ ተቸግረዋል። 

ባለፉት ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ እንዳይሸጋሸግ ምክንያት የነበረው በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በምክንያትነት ይቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ግልጽ ያልሆነው የቻይና ብድር በምክንያትነት እየቀረበ ይገኛል።

አሜሪካ በዓለም የገንዘብ ድርጅት ላይ ያላትን ተፅዕኖ በመጠቀምና የቡድን 20 አገሮችን በማስተባበር፣ ታዳጊ አገሮቹ ከቻይና ያገኙት የውጭ ብድር ግልጽ ካልሆነ የዕዳ ጫናውን የማቃለል ተግባር እንዳይፈጸም ጫና እያደረገች ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት በተካሄደው የአሜሪካና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይም ይህ የአፍሪካ አገሮች ከቻይና ያገኙት ብድር ግልጽ አለመሆን፣ የአፍሪካ አገሮችን ለከፍተኛ የዕዳ ጫና እንደሚዳርጋቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በይፋ ገልጸው ነበር። 

አሜሪካ ይህንን የዕዳ ጫና ቀውስ ለመፍታት መሞከሯን የተናገሩት አንቶኒ ብሊንከን፣ ለአብነትም በቡድን 20 አገሮች ፓሪስ ክለብ በኩል፣ እንዲሁም በከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው ደሃ አገሮችን (HIPCI) በመጠቀም የዕዳ ቅነሳ ጥረቶችን መምራቷን ተናግረዋል። በዚህም እ.ኤ.አ. ከ1996 እስካሁን ድረስ በደርዘን ለሚቆጠሩ አገሮች 75 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የዕዳ ክፍያ ዕፎይታ ድጋፍ መስጠቷን፣ በድጋፉም ወደ 40 የሚጠጉ የዕዳ ጫና ያለባቸው አገሮች ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ30 በላይ የሚሆኑት የአፍሪካ አገሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት፣ በቡድን 20 አገሮች በተሰጠው ተመሳሳይ ድጋፍ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 2020 እስከ ዲሴምበር 2021 ድረስ 48 አገሮች ከ12.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የዕዳ ክፍያ ዕፎይታ እንዲያገኙ መደረጉን በመግለጽ፣ አሜሪካና የቡድን 20 አጋሮቿ የችግሩን መጠን ከመረዳት ያለፈ ትክክለኛውን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ዘላቂ ያልሆኑ የብድር ሸክሞች መጨመር በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ፈተና መሆኑ አጠራጣሪ እንዳልሆነ የገለጹት አንቶኒ ብሊንከን፣ የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን፣ ነገር ግን ከዚያ አስቀድሞ መፈታት ያለባቸው አሳሳቢ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል።

ይህንን ሲገልጹ፣ ‹‹በተለየ ሁኔታ የሚያሳስበን ነገር ግልጽ ያልሆነ የውጭ ዕዳዎች ክምችት ጉዳይ ነው፡፡ ይፋ ባልሆኑ ስምምነቶች የተደበቁና ከሚዛን ውጪ የተከማቹ የውጭ ዕዳዎች አሉ፤›› ብለዋል።

‹‹አንዳንድ አበዳሪ አገሮች ለአንዳንድ የታዳጊ አገሮች ኩባንያዎች ወይም ለታዳጊ አገሮች ብድር ይሰጡና የስምምነት ውሉን በሚስጥር ይይዛሉ ወይም ግልጽ አያደርጉም፣ ይህ ማለት ደግሞ ሌሎች አገሮች አዲስ ብድር ለመስጠት ወይም የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ ሲደራደሩ፣ በሌሎች አበዳሪዎች የተሰጠ ብድር ሁኔታን ለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የዕዳ ሽግሽጉ ሳይሳካ አገሮች የማይችሉት የውጭ ዕዳ ተጭኗቸው ይወድቃሉ፤›› ብለዋል።

የዕዳ ግልጽነት ችግር የዕዳ ቀውስ አደጋን ብቻ ሳይሆን የዕዳ መክፈያ ጊዜን ለማራዘምና እነዚህን የዕዳ ጫናዎች በትክክል ለመፍታት እንቅፋት በመሆኑ፣ የአፍሪካ አገሮችን የውጭ ዕዳ ለማሸጋሸግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የዕዳ ግልጽነትን ወይም እነዚህ የውጭ ብድሮች የተሰጡበት መንገድ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ስለሆነም አበዳሪ አገሮችም ሆኑ የግል አበዳሪዎች እንዲሁም ተበዳሪዎች የዕዳና ብድር ግልጽነት እንዳይፈጠር የሚከለክሉትን መሰናክሎች ለማስወገድ፣ የበለጠ የፊስካልና የዕዳ ግልጽነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ መክረዋል።

‹‹ስለዚህ አበዳሪ አገሮችም ሆኑ የግል አበዳሪ ድርጅቶች ከእኛ ጋር በመሆን ተበዳሪ አገሮችን እንዲደግፉ እንፈልጋለን። ይህ ካልሆነ ግን ችግሩን አሜሪካ ብቻ ልትፈታው አትችልም፤›› ብለዋል።

በአሜሪካ እየተካሄደ ከሚገኘው የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የጋራ ጉባዔ ጎን ለጎን የዕዳ ጫና የገጠማቸው አገሮችና ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች የተገኙበት የቡድን 20 አገሮች ያሰናዱት የዕዳ መልሶ ማዋቀሪያ ማዕቀፍ ተግባራዊነትን ባዘገየው የዕዳ ግልጽነት ላይ፣ ዝግ ውይይት ረቡዕ ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዷል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ፣ ‹‹የዛምቢያና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጣም የሚያስፈልጋቸውን የዕዳ ዕፎይታ ጊዜ ሲጠብቁ በጣም ረዥም ጊዜ አሳልፈዋል፤›› ያሉት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹የተጀመረው የውጭ ዕዳን መልሶ የማዋቀር ሒደት እንዲፈጥን ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በድጋሚ አጽንኦት መስጠት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል። 

የዕዳ ጫናን ለማቃለልና የመክፈያ ጊዜን የማሸጋሸግ ሒደት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በወቅቱ መፈጸም እንዲቻል የዕዳ ግልጽነትና ሸክምን በእኩል የመጋራት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል። በመሆኑም አበዳሪ አገሮች፣ የግሉ ዘርፍ አበዳሪዎችና ተበዳሪዎች የብድር ውል ይዘቶችን ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ የዕዳ ግልጽነት እንዲፈጠር የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዕዳ ጫና ችግርን ትርጉም ባለው የብድር መልሶ ማዋቀር ለመፍታት እንዲችል፣ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የሚያስፈለገውን ቅድመ መረጃ እንደሚያጋሩም የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና መፈታት እንዳለበት በተደጋጋሚ እየገለጹ የሚገኙት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ የዕዳ መጠን አነስተኛ መሆኑንና አገሪቱም ከገጠማት የውስጥ ግጭት ቀውስ ወጥታ የኢኮኖሚ ሪፎርም መጀመሯን ያስረዳሉ። 

የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የጋራ ጉባዔ ከመጀመሩ ሁለት ቀናት አስቀድሞ ባወጡት ጽሑፍም፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓትን ማዋሀድና መዋቅራዊ ችግሮችን የሚፈታ ጥልቅ ሪፎርም እያደረጉ መሆናቸውን እንደ ማበረታቻ ተናግረዋል።

‹‹የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ማቅለያና ማራዘሚያ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ መስጠት ባለሥልጣናቱ ለጀመሩት የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል።

ከዚህም በመነሳት ኢትዮጵያ የዕዳ ማቅለያውን የምታገኝ ከሆነ አበዳሪ አገሮች የሚፈልጓቸውን የፖሊሲ ሪፎርሞች ተቀብላ መተግበር ልትገደድ ትችላለች። 

ከዚሁ የአሜሪካ የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የጋራ ጉባዔ ጎን ለጎን በተካሄደ የውጭ ዕዳ ጫና የተመለከተ ውይይት ላይ በተናጋሪነት የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ሪፎርምን የተመለከተ ጥያቄ መድረኩን ከመሩት የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ቀርቦላቸው ነበር። 

አቶ አህመድ በሰጡት ምላሽም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለመተግበር ባቀደው ሁለተኛው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፍርም ውስጥ ከተያዙት ውጥኖች አንዱ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ ላይ ጉልህ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገኝበት ጠቁመዋል። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ በቅድሚያ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የውጭ ዕዳ ማቅለያ ጥያቄ የሚያገኘው ምላሽ መታወቅ እንዳለበት ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማቱን ጨምሮ አበዳሪ አገሮች በኢትዮጵያ ማየት ከሚፈልጉት ሪፎርም አንዱ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ሪፎርም ላይ የሚያጠነጥነው፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሁለት የውጭ ምንዛሪ ትመና ሥርዓት (ሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ተመን) ማዋሀድ (Unification of the Foreign Exchange System) ነው። 

ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የጥቁር ገበያ ተዋናዮች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ ሳይሆን፣ ለጥቁር ገበያ ምንዛሪ ሥርዓት መፈጠር ምክንያት የሆነውን እውነተኛና የማያዳግም መፍትሔ በመውሰድ ነው። መፍትሔውም በአንድ ጊዜ አሊያም በሒደት የሚተገበር ‹‹Devaluation›› (የብር የመግዛት አቅምን ማዳከም) በማድረግ፣ ጥቁር ገበያው ከሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ ተመን በእጅጉ የሚልቅ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማወጅ እንደሆነ በዓለም ባንክ የተደረጉ ጥናቶች ይገልጻሉ። 

ኢትዮጵያ ይህንን የውጭ ምንዛሪ ሪፎርም ለማድረግ ዝግጅት እያደረገች ቢሆንም፣ የሪፎርሙ ትግበራ የሚወሰነው በውጭ የዕዳ ክምችቷ ላይ በምታገኘው የመክፈያ ጊዜ ሽግሽግና ሌሎች የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን ለመተግበር የምታገኘው ድጋፍ በሚፈጥረው የውጭ ምንዛሪ ቋት ዕድገት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይገልጻሉ።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የኢኮኖሚ ሁኔታ በተለይም ከሚስተዋለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አኳያ በውጭ ምንዛሪ ትመና ሥርዓት ላይ የሚወሰድ ማንኛውንም ማሻሻያ፣ ግሽበቱን በማናር ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ በእጅጉ እንደሚጎዳ እነዚሁ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በኢኮኖሚው ውስጥ ከሚፈጠረው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በተጨማሪ፣ በዚሁ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ምክንያት ያለባት የውጭ ዕዳ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሻብቅ በመግለጽ፣ መንግሥት ጥንቃቄ የተሞላበት መካከለኛ አማራጭ ላይ እንደማያማትር ያስረዳሉ፡፡

የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ብቻውን መፍትሔ ስለማያመጣ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተደርጎ ከዚህ ጋር በሚጣጣም ሁኔታ እንደሚተገበር የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ሰሞኑን ለመንግሥት ሚዲያዎች ተናግረው ነበር።

‹‹የውጭ ምንዛሪ ተመን ሪፎርም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አንቆ የያዘ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ የሚኖረው ሪፎርም ሁሉንም ሁኔታዎችን ባገናዘበና የተሟላ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ የሚፈጸም እንጂ፣ ሌላ ችግር ይዞ የሚመጣ ነጠላ መፍትሔ ውስጥ አንገባም፤›› ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -