ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በየጊዜው አስደንጋጭ ክስተቶችን በማስተናገድ ወደር የለውም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ቀጣናው በሚያስተናግዳቸው አስደንጋጭ ክስተቶች ምክንያት፣ በዓለም ላይ ከሚገኙ አስቸጋሪ ሥፍራዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ የግማሽ ክፍለ ዘመን ክስተቶችን በወፍ በረር ስንቃኝ፣ ኤርትራ በተራዘመ የትጥቅ ትግል ከኢትዮጵያ የተለያየችበት፣ ሶማሊያ በእርስ በእርስ ጦርነት ብትንትኗ ወጥታ ሦስት አገር የመሰለችበት ሁነት መቼም አይረሳም፡፡ ሶማሊያ እንደ አልሸባብና አይኤስ የመሳሰሉ አሸባሪ ድርጅቶች መፈንጫ የሆነችው አገረ መንግሥቷን በማጣቷ ነው፡፡ ደቡብ ሱዳንን ከዋናዋ ሱዳን ገንጥሎ አገር ለማድረግ የተካሄደው ከባድ ጦርነት፣ ከነፃነት በኋላ ደግ አልቆም ያለው የእርስ በርስ ውጊያና ዳፋው አሁንም ድረስ አለ፡፡ ወደ ዋናዋ ሱዳን መለስ ስንል ደግሞ ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮች ከፍተኛ ዋጋ ሲያስከፍሉ ቆይተው፣ የሰሞኑን አደገኛ ሁኔታ እንዴት እንደፈጠሩ እያየን ነው፡፡ ይህ ዘወትር ከመለስተኛ ግጭቶች እስከ የለየላቸው አውዳሚ ጦርነቶች የሚከናወኑበት የአፍሪካ ቀንድ፣ ካለፉት ጥፋቶች የመማር ዕድል እያለው የውክልና ጦርነት ማራመጃ ሆኖ መቀጠሉ የወትሮውን ሥጋት የበለጠ ያባብሰዋል፡፡
እንደሚታወሰው በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያ ሳትወድ በግድ ተገፍታ ወደ ምሥራቁ ዓለም ጎራ በመቀላቀል የሶቪዬት ኅብረት (ሩሲያ) ሸሪክ በመሆኗ ሳቢያ፣ አካባቢው የአሜሪካ መራሹ ምዕራብ ኃይልና የምሥራቁ የውክልና ጦርነት ዋነኛ ዕንብርት ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ከማንም በላይ ዋጋ ከፍላበታለች፡፡ ጂቡቲ የበርካታ ጉልበተኛ አገሮች የጦር ሠፈሮች አስተናጋጅ ሆና አካባቢውን ለከፍተኛ ጂኦ ፖለቲካዊ ትንቅንቅ ዳርጋለች፡፡ ሶማሊያ ጠንካራ መንግሥት መመሥረት አቅቷት አልሸባብን የመሰለ የአይኤስ ተባባሪ ይጫወትባታል፡፡ ሱዳን መረጋጋት ተስኗት ሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት ማሳካት ያልቻለችው፣ ግብፅን የመሰለች የረጅም ጊዜ አለቃዋ እጅና እግሯን ጠፍራ ስለያዘቻት ነው፡፡ የሱዳን ሁለቱ ጄኔራሎች የተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ በመሆናቸው ምክንያት፣ በመጨረሻም ዋና ከተማዋን ካርቱም የጦር ሜዳ አድርገው በቀጣናው ላይ አደጋ ደቅነዋል፡፡ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ኢትዮጵያም ውስጣዊ ችግሮቿን መልክ ለማስያዝ፣ ይህንን አደገኛ ትዕይንት መማሪያ ማድረግ አለባት፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን አካባቢያዊ ትርምስ እንዴት እያየነው ነው ሲባል ዕሳቤያችን ያስፈራል፡፡ ውስጣዊ ችኩቻውን ጋብ አድርጎ በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ባልተቻለባት ኢትዮጵያ፣ በአካባቢው ያንዣበበው አደጋ አገርን ለበለጠ ችግር እንዳይዳርግ ጥንቃቄ ለማድረግ የትብብር መንፈስ አይስተዋልም፡፡ በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ የአፍሪካ ቀንድ ቀውስ ሊስፋፋ የሚችልባቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ እየታወቀ፣ አሠላለፍን ከውጭ የተለያዩ ፍላጎቶች ጋር በማጣጣም ዕድል ሊመጣ ይችላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ወይም ሞኝነት ነው፡፡ በአካባቢው የጦር ሠፈሮችን ገንብተው አጋጣሚዎችን የሚፈልጉ ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጡት ለአገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ነው፡፡ ይህንን ጥቅም ለማሳካት ሲሉ ደግሞ የማይጨበጡ ተስፋዎችን በመስጠት ኢትዮጵያን የሚበታትን ድርጊት ሊያስፈጽሙ ይችላሉ፡፡ ከዘላቂ ጥቅም የሚበልጥ ወዳጅነትም ስለማይኖር የጥፋት ተባባሪያቸውን ሳይቀር ከምድረ ገጽ ያጠፋሉ፡፡ ከዚህ አኳያ እኛ ኢትዮጵያውያን ለማይጨበጥ ሥልጣን ወይም ጥቅም ብለን፣ አገራችንን የሚጎዱ ድርጊቶችን እንዳንፈጽም ምን ያህል ታማኝ ነን የሚለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አገርን መጉዳት ትልቅ ወንጀል ነውና፡፡
ኢትዮጵያ ምንም ነገር ያልጎደለባትና በፀጋዎች የተሞላች አገር እንደሆነች ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ይህችን የመሰለች በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች አገር አልምቶ ከሠለጠኑ አገሮች ተርታ ማሠለፍ ሲቻል፣ የድህነትና የተመፅዋችነት ምሳሌ በማድረግ ለመሳቂያና ለመሳለቂያነት የዳረጋት የቅንነት መጥፋት ነው፡፡ ከአንድ ዜጋ እስከ አገር መሪ ድረስ ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ ቅንነት ሲኖር ለሴረኝነት፣ ለክፋት፣ ለተንኮል፣ ለቂመኝነት፣ ለስንፍና፣ ለጥላቻ፣ ለከንቱ ዕሳቤዎችና ድርጊቶች ቦታ አይኖርም ነበር፡፡ ቅንነት በኢትዮጵያ ከላይ እስከ ታች ቢንሰራፋ ለኢትዮጵያውያን ምግብና መጠለያ የመጀመሪያ ጥያቄ አይሆኑም ነበር፡፡ ቅንነት ቢኖር በአንድ ለዘመናት ክፉና ደጉን በአንድነት እየተሳሰቡና እየተደጋገፉ እዚህ የደረሱ ኢትዮጵያውያን፣ በብሔርና በእምነት እየተከፋፈሉ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ሴራው አይደራም ነበር፡፡ ቅንነት የሁሉም ኢትዮጵያውን መገለጫ እንዲሆን ቢሠራ ኖሮ፣ ከራስ ጥቅምና ክብር በፊት አገር የምትባል የጋራ ጎጆ መኖሯ አይዘነጋም ነበር፡፡ ቅንነት በመጥፋቱ ግን የታሪካዊ ጠላቶች ሰለባ በመሆን እርስ በርስ መፋጀት ተለምዷል፡፡ እንደ እሳተ ገሞራ የሚንተከተክ ቀጣና ውስጥ ለአገር በጋራ ቀናዒ መሆን ካልተቻለ ውጤቱ መጥፋት ነው፡፡
የሱዳን ጦር መሪ አብዱልፈታህ አል ቡርሃንና የፈጥኖ ደራሽ ሠራዊቱ መሪ መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ አብሮ ሊዘልቅ እንደማይችል ሲነገርለት የነበረው ጥምረታቸው ፈርሶ፣ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያሏትን ካርቱም በከባድ መሣሪያዎችና በጦር አውሮፕላኖች እያስደበደቡ ንፁኃንን እያስገደሉ ነው፡፡ ሁለቱም ሥልጣኑን ከቀድሞው ወታደራዊ አምባገነን ኦማር ሐሰን አል በሽር በግልበጣ ሲረከቡ፣ ከሲቪሎች ጋር በተመሠረተ የሽግግር ምክር ቤት አማካይነት በምርጫ የሲቪል መንግሥት እንዲመሠረት ለማመቻቸት ቃል ገብተው ነበር፡፡ የሽግግሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ከሥልጣናቸው ሲፈነቅሉም፣ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶባቸው በርካታ ሱዳናውያን ተገድለዋል፡፡ በመጨረሻም ሁለቱ ጉልበተኞች የተለያዩ የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ አንግበው አገራቸውን ዶግ አመድ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ይህ አደገኛ ክስተት የግብፅን ሚስጥራዊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጭምር ያጋለጠ ነው፡፡ እኛስ አጋጣሚውን በመጠቀም ለውስጣዊ ችግራችን ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚረዳ ትምህርት መቅሰም እንፈልጋለን? ወይስ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› እያልን አገራችንን ከአደጋ ጋር እናፋጥጣለን?
ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን በተካሄደው የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ ስብሰባ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ በከፍተኛ የብድር ጫና፣ በምግብ ችግርና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ምክንያት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚያስፈልጋት መገለጹ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከፍተኛ የሆነ የብድር ጫና ያለባት አገር ስትሆን፣ ዜጎች ለመግለጽ የሚያስቸግረውን አደገኛ የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ተስኗቸዋል፡፡ የምግብና የሌሎች የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ንረት የብዙዎችን ሕይወት እያመሰቃቀለ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በየአካባቢው በሚፈጠሩ የፀጥታ ሥጋቶች ምክንያት ምርቶች ከቦታ ወደ ቦታ ሊንቀሳቀሱ ባለመቻላቸው፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረቱ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሮ የበለጠ አስመራሪ እያደረገው ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በየቦታው የፀጥታ ችግሮች ባሉባት ኢትዮጵያ፣ መሰንበቻውን ከልዩ ኃይል አደረጃጀት መለወጥ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ቀውስ በበዓል ገበያ ላይ ጭምር ያስከተለው የዋጋ ጭማሪ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ውስጣዊ ሰላም ጠፍቶ ኑሮ በከበደበት በዚህ ወቅት ከአደገኛው የሱዳን ቀውስ አለመማር ዋጋ እንደሚያስከፍል ይታወቅ!