የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ጉብኝት ለማድረግ አቅደው መከልከላቸውን ዋሽንግተን ፖስት ሾልኮ የወጣውን የአሜሪካ የስለላ መረጃ ጠቅሶ ዘገበ።
ሾልኮ የወጣው የፔንታጎን የአሜሪካ የመከላከያ ተቋም ሚስጥራዊ የስለላ መረጃዎችን የያዘው ሰነድ፣ የተመድ ኃላፊዎችን የመረጃ ልውውጦች የያዘ ሲሆን፣ በተለይም የዋና ጸሐፊው ጉተሬስ ውጥረት የበዛባቸው የቅርብ ጊዜ የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አጉልቶ እንደሚያሳይ ዘገባው ያመለክታል። በውጥረት ከተሞሉት የቅርብ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ልውውጦች መካከልም ኢትዮጵያንና ዩክሬንን የሚመለከቱ መረጃዎች ይገኙበታል።
ኢትዮጵያን በሚመለከተው መረጃ፣ ጉተሬስ በጦርነት የተመሰቃቀለውን የትግራይ ክልል እንዳይጎበኙ ፈቃድ መከለከላቸው እንዳስቆጣቸውና ቁጣቸውንም በተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ ለነበሩት ለታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) ለማሳወቅ ፈልገው እንደነበር፣ የስለላ መረጃውን ዋቢ አድርጎ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ጉተሬስ የኢትዮጵያን የሰላም ሒደትን ለመደገፍ በትግራይ ክልል ጉብኝት ለማድረግ አቅደው የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የጉተሬስን የጉብኝት ዕቅድ ውድቅ አድርገዋል።
በዚህም ምክንያት ዋና ጸሐፊ ጉተሬስ የተሰማቸውን ቁጣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ እንዲያደርሱላቸው፣ በተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ ለነበሩት ታዬ (አምባሳደር) ለመንገር ፈልገው እንደነበር ያስረዳል።
ጉተሬስ በታዬ (አምባሳደር) በኩል ለማድረስ ፈልገው የነበረው መልዕክት፣ በተመድ የሥልጣን ዘመናቸው ከየትኛውም መንግሥት እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ደርሷቸው እንደማያውቁና ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ፣ ከአቶ ደመቀ የደረሳቸው ደብዳቤ የመጨረሻው እንደሚሆንና አቶ ደመቀም ከዚህ በኋላ ‹እንደዚያ ዓይነት ደብዳቤ ለመጻፍ ዕድል እንደማይኖራቸው› አጽንኦት በመስጠት፣ የተሰማቸውን ቁጣ ማስተላለፍ እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት ሾልኮ የወጣውን የአሜሪካ የስለላ መረጃ ጠቅሶ ዘግቧል።
ነገር ግን ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዋና ጸሐፊው ጉተሬስን አግኝተው፣ በትግራይ ክልል ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት በመከልከላቸው ይቅርታ እንደጠየቋቸው እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 19 ቀን 2023 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት መናገራቸውን ዘገባው ያስረዳል።
በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ‹‹ጉተሬስ ለተወሰነ ጊዜ በፖለቲካ ውስጥ፣ ከዚያም በተመድ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ላለፉት ዓመታት የቆየ እንደ መሆኑ መጠን፣ ሰዎች እሱን መሰለላቸውና የግል ንግግሮቹን ማድመጣቸው አይገርምም ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ሾልከው የሚወጡ መረጃዎች የግል ንግግሮች ተዛብተው ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ከአሜሪካ መንግሥት ሾልኮ የወጣውን የስለላ መረጃ በተመለከተ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ተጠይቀው፣ ‹‹ይህ እኛ የምናረጋግጠው ነገር አይደለም፤›› ማለታቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። በተመሳሳይም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አለመስጠቱንም ዘገባው አክሏል።
ሪፖርተር የተመድ ዋና ጸሐፊ ጉተሬስ የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ከታደሙ በኋላ በትግራይ ክልል፣ እንዲሁም በጦርነት የተጎዱ የአማራና የአፋር ክልሎች አካባቢዎችን እንደሚጎበኙ በወቅቱ ዘግቦ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ሾልኮ የወጣውን መረጃ በተመለከተ ሪፖርተር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።