በአበበ ፍቅር
ቁጥሩ እያደገ የመጣውን የወጣቶች ኃይል ማስተናገድና ከሚያመነጨው ትሩፋት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ምኅዳር ማመቻቸት ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡
ወጣቶች በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ዕድገት የበቁ፣ ለችግር የማይበገሩ፣ በማኅበረሰባቸው ልማት ንቁ ተሳታፊና ለአገራቸው ሰላምና ዕድገት መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ይሆኑ ዘንድ በወጣቶች ላይ ብዙ መሠራት አለበት፡፡
ለዚህም በአካባቢያዊ፣ ክልላዊና በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ጥምረትን ሊፈጥሩ፣ ለመብታቸው ጠበቃ ለመሆን የሚያስችል አቅም ሊገነቡ እንዲሁም የማኅበረሰባቸውን ችግር ለመፍታት የመሪነት ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ወጣቶችን አደረጃጀት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ያላቸው እምቅ ዕውቀት ጥቅም ላይ እንዲውል፣ ራሳቸው ለራሳቸው የሚወስኑበት አቅም እንዲጎለብትና የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲኖራቸው ማገዝ አስፈላጊ ነው፡፡
ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ለማስቸዋልም፣ ወጣቶችን በአዎንታዊ መልኩ ለማስተሳሰር፣ ለማንቃትና ዕውቅናን ለመስጠት ያለመ ‹‹ዛሬን በንቃት ነገን በስኬት›› በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 21 እና 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ የወጣቶች ፌስቲቫል ይካሄዳል፡፡
ፌስቲቫሉ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ከከፍታ የተቀናጀ የወጣቶች ፕሮግራም ጋር በመተባበር እንደሆነ የአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከፍታ የወጣቶች ፕሮግራም በመሪነት በሚተገብረው አምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ዋና አስተባባሪነት ለሁለት ቀናት የሚሰናዳ ፌስቲቫል እንደሆነ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቻላቸው ጥሩነህ ተናግረዋል፡፡
በፌስቲቫሉ በሙያና ጥረታቸው በስኬት ከበቁ ሰዎች ወጣት የሥራ ፈጠራ ባለሙያዎችና በንግዱ ዘርፍ ውጤታማ ከሆኑ ትልልቅ ሰዎች ጋር ተገናኝተው ልምድ ይቀስማሉ፣ ዕውቀትና ክህሎታቸውን ያዳብራሉ ተብሏል፡፡
ወጣቶች በቴክኖሎጂ፣ በንግድና በሥራ ፈጠራ ዙሪያ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት የሥልጠና ፕሮግራም እንደተዘጋጀ የገለጹት አቶ ቻላቸው፣ ሥራ ለመቀጠር ዝግጁ የሚያደርጓቸውን ለሥራ ቃለ መጠይቅ ማድረግና ሌሎች ለሥራ ቅጥር መሠረታዊ የሆኑ ችሎታዎችን እንዲያዳብሩ የሚረዱ አጭር የሥልጠና መድረኮች ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ፌስቲቫሉ የወጣቶችን ጤናና ደኅንነት እንዲሁም መልካም ሰብዕና የሚገነቡ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንና የሥነ ሥዕልና ፎቶ ጋለሪ ይታዩበታል ተብሏል፡፡
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ተሰጥኦቸውን የሚያሳዩበት መድረክ መዘርጋቱን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ 10,000 ወጣቶች የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የሚያዩበት፣ በትውልዶች መካከል ገንቢ ውይይቶችን የሚያደርጉበትና በልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበት ነውም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ፕሮግራሙ ከ18 የኢትዮጵያ ከተሞች የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን ትርጉም ባለው መልኩ ከኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹና አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራ እንደሆነ የከፍታ ማኔጅመንትና ሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ክብረ ወሰን ወርቁ ተናግረዋል፡፡
ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ወጣቶች እርስ በርስ እንዲገናኙ በማድረግ ትስስራቸውን በሚያጠናክር እንዲሁም የባህልና የልምድ ልውውጦች እንዲኖር መድረኩን ያመቻቻል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ወጣቶቹ አሁን ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ በሰላም ግንባታና በግጭት አፈታት ላይ ሐሳብ እንዲለዋወጡና ለየአካባቢያቸው የሚመጥን መፍትሔ እንዲያቀርቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በፌስቲቫሉ ሮፍናን፣ ቬሮኒካ አዳነ፣ ኒና ግርማ፣ ጃንቦ ጆቴ፣ አስጌ ደንዳሾና መስፍን ብርሃኑን ጨምሮ ሌሎች ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡