በዮሐንስ ወልደኪዳን
በሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 28 ቁጥር 2394 የእሑድ ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ዕትም ስለኤክስፖርት ሻይ ምርት ተግዳሮት በተመለከተ በወጣው ዘገባ ላይ ሙያዊ አስተያየቴን ስሰጥ ይህንን አጭር፣ ግላዊና ሙያዊ አስተያየት በሻይ ንዑስ ሴክተር ረዘም ላለ ጊዜ በተለያዩ የሙያና የአመራር ኃላፊነቶች ላይ እንደቆየና ዘርፉንም በአግባቡ እንደሚረዳ ግለሰብ፣ እንዲሁም በዜናው ላይ የወጣውን ዘገባ ብቻ መሠረት አድርጌ የሰጠሁት ነፃ አስተያየት መሆኑ እንዲታወቅና ጽሑፉም እንደ ድርጅቶቹ ይፋዊ ምላሽ ተደርጎ እንዳይወሰድ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
በኢትዮጵያ የሻይ ተክል በካቶሊክ ሚሲዮናዊያን እንደገባ ከሚታመንበት 1920 ዓ.ም. አካባቢ አንስቶ የልማት ዕድገቱ እጅግ አዝጋሚና ረጅም ጊዜ የወሰደ ነበር፡፡ ቢሆንም ከ40 ዓመታት ቆይታ በኋላ ይህ ትንሽ ጅማሬ እንደ እርሾ አገልግሎ፣ ለጉማሮና ውሽውሽ የሻይ ልማቶች መወለድ ምክንያት የሆኑ አነስተኛ እርሻዎችን በ1958 እና በ1966 ዓ.ም. በቅደም ተከተል እንዲቋቋሙ ምክንያት ሆኗል፡፡
የቀድሞው ወታደራዊው (ኢሕዲሪ) መንግሥትም በጉማሮና በውሽውሽ ለምተው ያሉትን አነስተኛ እርሻዎች መሠረት አድርጎ በመንግሥት በጀትና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የብድር ድጋፍ ዓይን ከፋች የሆኑ የሻይ ልማቶችን በተጠቀሱት ሥፍራዎች በማከናወን፣ የኢትዮጵያን የሻይ የልማት መጠንን ወደ 2‚200 ሔክታር በማሳደግ አገሪቱ የሻይ ፍጆታዋንና ፍላጎቷን በአገር ውስጥ ምርት እንድታሟላ መንገድ ጠረገ፡፡ ይህ ትልቅ ዕምርታን ያሳየ የልማት እንቅስቃሴ በያዘው መንገድ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ፣ አገሪቱ ለሻይ ልማት ተስማሚነት ካላት ዕምቅ ሀብት አንፃር ምናልባትም ኬንያን በመከተል የአፍሪካ ትልቋ የሻይ አምራች አገር የማትሆንበት ምክንያት አልነበረም፡፡
ከወታደራዊው መንግሥት ማክተም በኋላ የመንግሥትና የኢኮኖሚ ሥርዓት ለውጥን ተከትሎ ኢኮኖሚው ለግል ባለሀብቱ ክፍት በመደረጉ፣ በዜናው ላይ የተጠቀሱት ኢስት አፍሪካን አግሪ ቢዝነስና ቨርዳንታ ሃርቨስት መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ዘርፉን ተቀላቀሉት፡፡
ይህ ዘመን ጠገብ ዘርፍ የዕድሜውን ያህል ያለመስፋፋቱና ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ያለማበርከቱ፣ በእርግጥ ሴክተሩ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ተተብትቦ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ የሻይ ኢንቨስትመንት ተግዳሮትና ችግር የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፋችን ያለበት መዋቅራዊ ችግር ነፀብራቅ ቢሆንም በተለይ ሻይ ልማት ከሚፈልገው ከፍተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍላጎት፣ ቴክኖሎጂ፣ መሠረተ ልማት፣ ሙያና ዕውቀት፣ እንዲሁም ልማቱ ከአካባቢ ጥበቃና አያያዝ ጋር ካለው ተዛምዶና መስተጋብር አንፃር ፈትሾ ግልጽ አቅጣጫ ሊሰጠውና ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ ዘርፍ መሆኑ ደግሞ ከሌሎች አቻ ዘርፎች በበለጠ ትኩረት የሚሻ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡
በቅርቡ ተጀምረው ዛሬ በአንፃራዊነት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ አቻ የግብርና ሴክተሮች ለምሳሌ እንደ አበባ ልማት ያሉ ዘርፎች አሉ፡፡ የሥራ ዕድል ለዜጎች ከመፍጠራቸውም ባሻገር የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ስብጥር እንዲጨምርና በሌሎች አገሮች ተይዞ በነበረ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ በመሆን፣ ኢትዮጵያ ከዓለማችን ከፍተኛ የአበባ ምርት አምራቾች ውስጥ አንዷ እንድትሆን ካስቻሏት ዓበይት ምክንያቶች መካከል አንዱ መንግሥት ለዘርፉ ሲሰጥ የቆየውና አሁንም እየሰጠ ያለው ትልቅ ትኩረትና ክትትል ነው፡፡ እንዲሁም አመቺ የኢንቨስትመንት ምኅዳር ተጠቃሽ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ዛሬ ይህ የፍሎሪካልቸር ሴክተር ከራሱ ዕድገት ባሻገር ሌሎች የዘርፉ ደጋፊ ተቋማት እንደ ማሸጊያ፣ ግሪን ሀውስና የመስኖና ኬሚካል አምራችና አቅራቢ ኢንዱስትሪዎች እንዲያብቡና እንዲያድጉ ምክንያት የሆነውም የዚህ ትኩረት ውጤት ነው፡፡ ይህንን፣ ተከትሎ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ጠንካራ ተቋማዊ ማኅበር በማቋቋም የሴክተሩንና የአልሚዎችን ጥቅም የሚያስጠብቅ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ፣ ችግሮች ወቅታዊ ምላሽ ከመንግሥት እንዲያገኙ፣ የራሳቸውን የትምህርት ማዕከል (ኮሌጅ) በማቋቋም አልሚዎችና ሴክተሩ የሚገጥማቸውን የቴክኖሎጂና የዕውቀት ክፍተት በመሙላት፣ የዕውቀትና የመረጃ ፍሰት (የገበያ፣ ቴክኖሎጂ፣ ወዘተ) በአልሚዎች መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲነብር የሚያደርግ ማኅበር በመፍጠራቸው ከመንግሥት ለሴክተሩ የሚሰጠው ድጋፍ ትርጉም ያለውና መዋቅራዊ እንዲሆን ከማስቻላቸውም በላይ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ተፈላጊነትና ጉልህ ድርሻ በሚገባ አስቀጥለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ሴክተሩ በኤክስፖርት ምርት የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉና አቅም በፈቀደ መጠን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
በአንፃሩ ለሻይ ልማት እየተሰጠው ያለው ትኩረት እጅግ አናሳ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሻይ ኢንዱስትሪ ከሥሪቱ የአበባ ኢንቨስትመንት ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በላይ ሊያበረክት የሚችልበትን በርካታ ዕድሎችና ዕምቅ አቅም የያዘ ሴክተር ቢሆንም፣ የሌሎች አገሮች ተሞክሮም የሚነግረን ይህንኑና ተመሳሳዩን ነው፡፡ አዳጊ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች የመንግሥታቸው የፖሊሲ ድጋፍና አሠሪ ሥርዓትና ተቋማት መኖር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ መዋዕለ ንዋዩን ድጋፍ ባላቸው ሴክተሮች ላይ እንደሚያፈስ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ የአገራችንም የሻይ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ከተፈለገ የዘርፉ ባለሀብቶች ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለአበባው ሴክተርና መሰል ዘርፎች እንዳደረገው ድጋፍ ለሻይ ልማቱም በማድረግ ቅድሚያውንና ተነሳሽነቱን መውሰድን ዋነኛው ዕርምጃው ሊያደርግ ይገባል፡፡ ለውጤታማ ድጋፍና ዕገዛ ደግሞ መንግሥት ሴክተሩን በአግባቡ መገንዘብና ችግሮቹን ለይቶ ማውጣት ለነገ የማይባል የቤት ሥራው ይሆናል፡፡
- የሻይ ኤክስፖርት ጉዳይ
የሻይ ኤክስፖርት ምርትና ገበያ እንደ ሌሎቹ የአግሪ ቢዝነስ ምርቶች የመልከ ብዙ ሥልቶች፣ ድርጊቶችና ጥረቶች ድምር ውጤት ነው፡፡ በዓለማችን ከቀዳሚዎቹ የሻይ አምራችና ሻጭ ተርታ የምትሠለፈው ጎረቤታችን ኬንያ፣ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ በሴክተሩ ውስጥ ያለው የተደራጀና ተጣጥሞ የተዋቀረው ሥርዓቷ፣ ተለዋዋጭ መልክ ያለውን የዓለም ሻይ ገበያ ተግዳሮት በሚገባ እንድትቋቋመው አስችሏታል፡፡ዛሬ ኬንያ ጠንካራ የምርምርና የስርፀት ተቋምን በተለያዩ የሴክተሩ ባለድርሻ አካላትን (ሰፋፊ የእርሻ ባለቤቶች፣ አነስተኛ አርሶአደሮችና መንግሥት) በማካተት አቋቁማ፣ ችግር ፈቺና የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት የጠበቁ ምርምሮችን በማድረግ ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች፡፡ሻይ ከሰፋፊ የእርሻ ሰብልነት በተጨማሪ፣ በጓሮ ተክልነት በኬንያ አርሶ አደሮች መልማት ከጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ 65 በመቶ የኬንያ የሻይ ምርት የሚሰበሰበው ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ዛሬ ሻይ የኬንያ ቁጥር አንድ የኤክስፖርት ምርት የሆነውና የሚሊዮኖችን ሕይወት ቀያሪ ሴክተር እንዲሆን ያስቻለው በምኞት ብቻ ሳይሆን በጠንካራ የመንግሥት፣ የግሉ ሴክተርና የልማት አጋሮች የተቀናጀ የርብርብ ሥራና በመሠረተ ልማት አውታሮች፣ በእርሻና ማቀነባበሪያ ተቋማትን የማዘመን፣ ምርምርና ስርፀትን በአግባቡ ለመምራት ረጅም መንገድ ለመጓዝ በመድፈራቸውም ጭምር እንጂ፡፡ የሻይ ኢንቨስትመንት ተፈጥሮአዊው መገለጫውንና የእሴት ሰንሰለቱን ስንመለከት በውስጡ እርሻን (Farm)፣ ማቀነባበሪያ ፋብሪካን (Processing Plant)፣ ማሸጊያ ዩኒትን (Packing Unit) እና ገበያን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ኢንዱስትሪ በመሆኑ፣ በእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚኖር አለመጣጣምና ያለመናበብ የኢንዱስትሪውን የማምረትና የመሸጥ የሥራ ሒደት በእጅጉ ያውካል፡፡ለስኬታማ የኤክስፖርት ገበያ ሁለት አንኳርና መሠረታዊ ነገሮች ማሟላት የግድ ይላል፡፡ ገበያው በሚፈልገው የጥራት ደረጃ ማምረት መቻልና ያልዋዠቀና አስተማማኝ የምርት መጣኝ አቅርቦት በገበያው ውስጥ እንዲኖር ማስቻል ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት አስገዳጅ ሁኔታዎችን መወጣት ከቻልን የኢትዮጵያን የሻይ ኢንዱስትሪ ወደ ስኬት ጎዳና ማምጣት ጀምረናል ማለት ነው፡፡በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሻይ ኤክስፖርት ሥራ ዕድገትን የሚገድቡ በርካታ ፈተናዎች የተጋረጡበት ሲሆን፣ ተግዳሮቶቹን ለመፍታት በፖሊሲ፣ በመሠረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልማት የተደገፈ ከፍተኛ ሥራን በመሥራት የኢትዮጵያ የሻይ ኢንዱስትሪ ከሌሎች ሻይ አምራች አገሮች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን ማድረግ ግን ይቻላል። በኢንዱስትሪው ውስጥ ከተጋረጡ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል ጥቂቶቹ 1.1 ዝቅተኛ የመሠረተ ልማት አውታር በኢትዮጵያ የሻይ ምርት ዕድገትን ከሚያደናቅፉ ተግዳሮቶች አንዱና ዋነኛው ደካማ የመሠረተ ልማት አውታር ነው። ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ከሌሎቹ የአገራችን ክፍሎች አንፃር ዝቅተኛ የመንገድ አውታር፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ቴሌኮም አገልግሎት ያለው ክልል መሆኑ ነው፡፡ የአገራችንም ውስን የሻይ እርሻዎች ከአካባቢው ተስማሚነት አንፃር ከትመው ያሉት በዚሁ የአገራችን ክፍል ነው፡፡ በዜናው ከተጠቀሱት የሻይ አምራች ድርጅቶች መካከል አንዱ በትንሹ ለ12 ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በአካባቢው ባለመኖሩ፣ በራሱ ከፍተኛ ነዳጅና ኃይል አመንጪ የሆኑ የነዳጅ ጀነሬተሮችን በመጠቀም የሻይ ማቀነባበር ሥራውን ሲሠራ መቆየቱን አስታውሳለሁ፡፡ ዝቅተኛውን የመንገድና የኃይል አቅርቦት መሥፈርት ያለመሟላት ችግር በኤክስፖርት ገበያው ላይ የሚኖረው የተወዳዳሪነት እድምታን መገመት አያዳግትም፡፡ 1.2 ዝቅተኛ የጥራትና የምርታማነት ደረጃ በሰፋፊም ሆነ በአነስተኛ አርሶአደሮች የሚለማው የሻይ ምርታማነት ከአማካይ ሻይ አምራች አገሮች ምርታማነት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ በየእርሻ ልማቱ የሚገኙት አብዛኛው ምርት ሰጪ ዝርያዎች ላለፉት 40 ዓመታት በምርት ሥርዓት ውስጥ የነበሩና የቆዩ ዝርያዎችን መሆናቸው፣ እንዲሁም አገሪቱ በማምረትም ሆነ በማቀነባበር ሒደት ውስጥ የቆዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሟ ለአነስተኛ ምርትና ለሻይ ጥራት ችግር ዳርጓታል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ገበያ ከሌሎች ሻይ አምራች አገሮች ጋር መወዳደርን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡1.3 ውስን ዕውቀት የእርሻ ልማቶቹ የዕውቀት አያያዝና አስተዳደር ውስንነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሻይ አመራረት የቴክኒካል ዕውቀት ማነስ በሻይ ጥራትና ምርት ላይ ተፅዕኖ ያለው ሌላው ፈተና ነው። አገሪቱ የሻይ አምራቾችንና የአቀነባባሪዎችን ክህሎት ለማሻሻል በሥልጠና ፕሮግራሞችና ምርምር ላይ ኢንቨስት መደረግ አለበት። የአገሪቱን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የሻይ አመራረት ቴክኖሎጂ አለመዘጋጀቱና በአብዛኛው ጥቅም ላይ የዋሉት ቴክኖሎጂዎችና አሠራሮች በአብዛኛው ከኬንያ የተቀዱ መሆናቸው፣ ከምርምርና ስርፀት አንፃር ተክሉ ባለቤት አልባ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ፖሊሲ አውጪ፣ ድጋፍና ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶችም ሴክተሩን የሚረዱበት ውስንነት ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡1.4 ኤክስፖርት ገበያ በኢትዮጵያ የሚገኙ የሻይ አምራቾች በዓለም አቀፉ ሻይ ገበያ ላይ ወሳኝ የገበያው ተዋናዮች ባለመሆናቸው የዋጋ አወሳሰንና የገበያ መግቢያ ስትራቴጂዎች ላይ ተግዳሮቶች ይገጥማቸዋል፡፡ ቀጣይነትና መጠኑ ከፍ ያለ የኤክስፖርት ምርት ለማቅረብ በገዥዎችና በብሮከሮች ፊት እምነትና መተማመን ለማግኘት ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ካሏት እርሻዎች የምታመርተው የኤክስፖርት መጠን ውስንነት ይታወቃልና፡፡ ከሌሎች ከፍተኛ አምራች አገሮች የሚገጥማቸው ውድድርም ያለችውን አነስተኛ ምርት በዝቅተኛ የመሸጫ ኅዳግ ለመሸጥ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ፡፡ከ100 ዓመታት በፊት ሻይ ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ በተመሳሳይ ወቅት የገባ ቢሆንም፣ ዛሬ አገሮች በልማቱ የሰማይና ምድር ያህል ተራርቀው ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሻይ ረዘም ያለ ምርት ታሪክ ቢኖረውም ቅሉ፣ አገሪቱ የምታመርተውም ሆነ ወደ ውጭ የምትልከው የሻይ መጠን ከሌሎች ሻይ አምራች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው። የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ መጠን ለመጨመር መንግሥትና የሻይ ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት የሚከተሉትን ሥልቶች ማጤን ይገባቸዋል።2. የሻይ ጥራትን ማሻሻል የሻይ ኤክስፖርት መጠን ከሚጎዱ ቁልፍ ነገሮች አንዱ ጥራት ነው። ስለዚህ የዓለም አቀፍ ገዥዎችን ደረጃ ለማሟላት የኢትዮጵያን ሻይ ጥራት ደረጃን ማሻሻል አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንንም በተሻለ የሻይ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የምርት መሰብሰብንና የማቀነባበር አሠራሮችን በማዘመንና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን ከመስክ እስከ ፋብሪካ በመሥራት መተግበር ይቻላል።2.1 የማምረት አቅምን ማሳደግኢትዮጵያ ለሻይ ምርት ሰፊ እምቅ አቅም አላት፣ አሁን ያለው የማምረት አቅም ግን በአንፃራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ነው። በዓለማችን ያሉ ሻይ አምራች አገሮች ለሻይ ማስፋፊያ የሚሆን መሬታቸውን ከጨረሱ የሰነባበቱ ሲሆን፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለሻይ ልማት የሰፊ መሬትና ተስማሚ ምኅዳር ባለቤት ነች፡፡ ስለሆነም የሻይ እርሻን በማስፋፋት፣ ዘመናዊ የግብርና አሠራርን በማስተዋወቅ ተጨማሪ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲመጡ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተጀመሩ ሻይን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የማልማት ስትራቴጂ በተጠና መንገድ ተጠናክሮ በማስቀጠል፣ የተሻለ የፋይናንስ አቅርቦትና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የሻይ ሽፋንን በማሳደግ ሴክተሩ የሚሊዮኖች በረከት እንዲሆን ማስቻል ያስፈልጋል።2.2 ኤክስፖርትን ያማከለ የግብይት ስትራቴጂ ማዘጋጀት የኢትዮጵያ ሻይ ኢንዱስትሪ ውጤታማ የግብይት ሥልቶችን በመንደፍ የኢትዮጵያን ሻይ በዓለም አቀፍ ገበያ ማስተዋወቅ ይኖርበታል። ይህ ሊሳካ የሚችለው የተወሰኑ የገበያ ክፍሎችን በመለየትና በማነጣጠር፣ አሁን ከምንልከው ውስን ብትን ሻይ በተጨማሪ እሴትን የጨመሩ ምርቶችን እንደ ሃርባል ሻይ፣ ፍሌቨር ሻይ፣ ኢንስታንት ሻይ ምርቶችን በማከል የተሻለ ዋጋ የሚገኝበትን መንገድ መሻት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ሒደቶችን ሊያዘምኑ በሚችሉ ሰርተፊኬሽኖች አሠራርን በመደገፍ፣ ከአነስተኛ የኤክስፖርት የምርት መጠን ላይ የተሻለ ዋጋ ለማግኘት እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ አንዱ የብልሆች ዕርምጃ ነው፡፡ 2.3 ምርምርና ስርፀት በኢትዮጵያ የሻይ ጥራትና ምርታማነት ለማሻሻል ምርምር ተቋማት ድጋፍ በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የትኛውም የምርምር ተቋም የቴክኖሎጂና የምርምር ድጋፍ ሲያደርግ አይታይም፣ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ ስለሆነም መንግሥትና የሻይ ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት በምርምርና ልማት ላይ በሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ 2.4 የትብብርና የአጋርነት መድረክ መፍጠርአሁን ያለው ሻይ የምርት መጠንና የልማት ደረጃ፣ የዘርፉን ባለድርሻዎች ለውድድርና ለፉክክር የሚጋብዝ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከውድድር ይልቅ ትብብር ቢፈጥሩ ሴክተሩን ለማሳደግ፣ ችግሮቻቸውን ለመፍታትና በፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ተደማጭነት ለማግኘት ይረዳቸዋል፡፡ በመሆኑም በሻይ ምርት፣ ማቀነባበር፣ ማሸግና ሽያጭ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ከተመሳሳይ ዘርፎች ልምድና ትምህርት በመውሰድ ወደፊት የትብብር ማዕቀፋቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድጉ የሚችሉበት አንድ መደበኛ የትብብር መድረክ ቢፈጥሩ እጅግ ይጠቅማቸዋልና ጊዜ ሳያባክኑ ወደ ተግባር ቢገቡ መልካም ነው እያልኩ፣ ቁርጠኝነትን የሚጠይቁትን እነዚህንና መሰል ሥልቶችን በመተግበር ኢትዮጵያ የሻይ ምርት መጠኗን ማሳደግ፣ የሻይ ኢንዱስትሪዋን ማሻሻል፣ እንዲሁም የሻይ አምራች አርሶ አደሮችን ቁጥር በመጨመርና በገጠር የሥራ ዕድል መፍጠር በአስተማማኝ የምርት ጥራት ደረጃና አቅርቦትን በማረጋገጥ፣ ከሻይ የሚገኘውን የአገራችንን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ዕውን ማድረግ ይቻላል።ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡