Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹አብሪ›› የተባሉ የተደራጁ ወጣቶችን በአጃቢነት አካቶ የተንሰራፋው ኮንትሮባንድ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምባሆ ምርት፣ አዲስና አሮጌ አልባሳት፣ መድኃኒቶች፣ ምግብና መጠጦች፣ ኤልክትሮኒክስ ዕቃዎችና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶች በኮንትሮባንድ መንገድ በገፍ መግባታቸው ለአገሬው ሰው አዲስ አይደለም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የምርት ዓይነቶች ሰፍቶ፣ እንደ አደንዛዥ ዕፅ፣ ሕገወጥ መሣሪያ፣ የውጭ ገንዘብና ሌሎች ለየት ያሉ ምርቶች በኮንትሮባንድ ሲዘዋወሩ በሕግ አስከባሪዎች መያዛቸው መደመጥ ልማድ እየሆነ መጥቷል።

ተሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ከነፍስ ወከፍ እስከ ቡድን መሥሪያ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል በነበረው የውይይት መድረክ ስለኮንትሮባንድ ንግድ ገለጻ አድርገዋል፡፡

እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ ትክክለኛና ሐሰተኛ የውጭ ገንዘቦች ጭምር ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በሕጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገባ የውጭ ገንዘብ ጭምር በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡

ማዕድናት በኮንትሮባንድ መንገድ አገር በመውጣታቸው፣ ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እያሽቆለቆለ ይገኛል ብለዋል፡፡

ቡና፣ የደን ውጤቶች፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶና ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ያላትን የውጭ ምንዛሪ ለነዳጅ ብታወጣም ይህም በኮንትሮባንድ መንገድ ከአገር እንደሚወጣ አቶ ሙሉጌታ ያስረዳሉ፡፡

ከአንድ ወር በፊት ሪፖርተር በያቤሎ ከተማ ተገኝቶ ባደረገው ምልከታም፣ ነዳጅ በጠራራ ፀሐይ በኮንትሮባንድ መንገድ ሲወጣ ማየት የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን ታዝቧል፡፡

ጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ ከሚከውኑባቸው ሥልቶች አንዱ ምሽትን መጠቀም ሲሆን ለዚህም የተደራጁ ወጣቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ለሊትን የሚመርጡት የኮንትሮባንድ አንቀሳቃሾች ‹‹አብሪ›› የሚል ስያሜ በተሰጣቸው የተደራጁ ወጣቶች ታጅበው ምርቶችን ከአገር እንደሚያስወጡ የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣  ‹‹አብሪ›› የተባሉት አጃቢ ወጣቶች በኮንትሮባንድ የሚወጡ ምርቶች እንዳይያዙ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል።

እነዚህ የተደራጁ ወጣቾች አብዛኞቹ ለኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መንገድ ‹‹ጠራጊ›› ወይም አሳላፊ መሆናቸውን፣ አብዛኞቹ ወጣቶችም ዕፅ ወስደው የሚንቀሳቀሱ መሆኑን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሕገወጥ አሠራር እንደ አገር ኢኮኖሚያዊ ጫና ከመፍጠሩ በበለጠ፣ ወጣቱን የሰው ኃይል የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰብን በመቀስቀስ ረብሻ በመፍጠር መንገድ በመዝጋት ወጣቶችን ሴቶችን በማሳለፍ ጭምር በኮንትሮባንድ የሚወጡ ምርቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ የመንግሥት ተቋማት ተሽከርከሪዎችንና አምቡላንስ ጭምር በመጠቀም የሚያልፍ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዳሉ፣ ከዚህ ውስጥ የፌዴራል ፖሊስ አሽከርካሪዎች ይህን ተግባር ሲፈጽሙ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

ያለመፈተሽ መብት የተሰጣቸው አንዳንድ የአየርና የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ጭምር ዕቃዎችን በኮንትሮባንድ እንደሚያወጡና ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል፡፡

ኮንትሮባንድን በተመለከተ የሚዳኝበት ሕግ መኖሩን፣ የጉምሩክ አዋጅ ተብሎ 859/2006 እና ማሻሻያው ሕጉ አስተዳደራዊ ዕርምጃ ከመውሰድ፣ በኮንትሮባንድ ዕቃዎች ከመውረስ ጀምሮ እስከ 15 ዓመታት እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት ኮንትሮባንድን ለመግታትና በተለይም በኮንትሮባንድ የሚሠሩ ዜጎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንዲደርስበቸው ለማድረግ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ፣ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ክስረት ጭምር እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የተለዩ አካባቢዎች 

በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ከተለዩ አካባቢዎች መካከል ቀዳሚው መተላለፊያ ቀጣና ሶማሌ ክልል፣ ድሬዳዋ፣ ከተማና አካባቢው መሆናቸውን ጠቁመዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ ኮንትሮባንድ ዝውውር ከመስተዋሉ ባሻገር፣ የአካባቢው ማኅበረሰብንና የፀጥታ አካላትን ጭምር በማስተባበር ሥር የሰደደ ወንጀል የሚሠራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ቀጣና የጫት ምርት በኮንትሮባንድ መንገድ እንዲወጣ የሚደረግበትና በሕጋዊ መንገድ ከአገር በሚወጣው ላይ ጭምር ችግር የሚፈጠርበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛነት የተቀመጠው የደቡብ ክልልና ደቡብ ኦሮሚያ በተለይም ሞያሌ፣ ሻሸመኔ፣ አካባቢዎች የግብርና ምርቶች ከአገር የሚወጡበት የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበት ቀጣና መሆኑን ተናግረዋል፡፡    

ሦስተኛው ቀጣና የሰሜን ኢትዮጵያ መሆኑን፣ ትግራይና አማራ ክልሎችን የሚያጠቃልል ሲሆን ከሌሎቹ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ በእነዚህ አካባቢዎች ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች የሚዘዋወርበት ነው ብለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መንስዔዎች

በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ መንስዔዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ናቸው በማለት አቶ ሙሉጌታ ያስቀምጣሉ፡፡ ኢኮኖሚያዊ መንስዔ የሚባለው ሀብት ለማግኘትና በአቋራጭ ለመበልፀግ በሚደረግ ትግል ነው፡፡ ማኅበራዊ ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ጋር በቋንቋ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት ተመሳሳይ በመሆናቸው ምክንያት የሚደረገው የሸቀጦች ዝውውር በመኖሩ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ ትልቁ ችግር ብለው ያስቀመጡት በኢትዮጵያ ኮንትሮባንድ በማኅበረሰቡ ውግዝ አለመሆኑ ሌላኛው አባባሽ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፖለቲካዊ መንስዔው ደግሞ መንግሥትን ለማዳከም የሚደረግ የሸቀጦችና ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር መኖሩን ገልጸዋል፡፡

መንስዔዎቹ በርካታ ቢሆንም በኮንትሮባንድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከግለሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ ሙሉጌታ ገለጻ፣ በኮንትሮባንድ መንገድ የሚገቡ ዕቃዎች በተለይ አምራች ዜጎች እየመከነ ይገኛል፡፡ መደበኛ ያልሆነ ጥናት ዋቢ አድርገው ምሳሌ የሰጡት አቶ ሙሉጌታ፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ በርካታ ሰዎች የዓይን ሕመምተኛ እየሆኑ ይገኛል ብለዋል፡፡ ይህም በኮንትሮባንድ የገቡ መድኃኒቶች ደኅንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ስለሚገቡ ወደ መርዛማነት የተቀየሩ መድኃኒቶች ፋርማሲ ገብቶ ስለሚሸጥ ማኅበረሰቡ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጡ ናቸው ብለዋል፡፡

በኮንትሮባንድ ለአገር የሚፈጥረው ትውልድን ከማምከን ጀምሮ መንግሥት አልባ አገር እስከ ማድረግ ጭምር ይደርሳል ሲሉ የችግሩን ግዝፈት ይናገራሉ፡፡ የችግሩን ግዝፈት የሚያስረዱት አቶ ሙሉጌታ፣ አገር የወከሉ ዲፕሎማቶች ያለመፈተሽ መብትን በመጠቀም፣ ከባድ የሆነና ለደኅንነት አደገኛ የሆኑ መሣሪያዎች ጭምር ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድን ያባባሰው ተብሎ የተቀመጠው ችግሩን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ አለመግባቱ ትልቅ ክፍተት ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ አባባሽ ምክንያቶች መካከል የጉምሩክ ታክስ ምጣኔ፣ የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ አለመቅረቡ፣ የተቋማት የአቅም ውስንነት ጭምር የኮንትሮባንድ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

በፍትሕ አካላት በኩል ደግሞ ከምርመራ እስከ ክስ ድረስ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ እስከ 1,000 ሰው በኮንትሮባንድ ንግድ መከሰሳቸውን አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ 1,000 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ፌዴራል ፖሊሲ ቢላኩም፣ ዝርዝርና ጥልቀት ያለው ምርመራ ተደርጎ ክስ አለመመሥረቱ ችግሩን አባብሶታል ይላሉ፡፡ የአደረጃጀት፣ የፖሊሲ ጉዳዮችን ማሻሻልና ከጎረቤት አገሮች ጋር በትብብር በመሥራት ችግሩን መቅረፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በተቋማት በክህሎትና፣ የቴክኖሎጂ ግብዓት ማደራጀት እንደሚገባ ገልጸው፣ ኮሚሽኑ በዚህ ዓመት ቦርደሮችን በዘመናዊ መንገድ የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን ለመቀጠም እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የኮንትሮባንድ ንግድ የፈጠረውን ችግር አንስተዋል፡፡ በተለይም በወርቅና በጫት ምርት ላይ የኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት የውጭ ገበያ የተላከው ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በምሳሌነት አሶሳን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት 20 ኩንታል ወርቅ መቅረቡን፣ በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ደግሞ ሦስት ኩንታል ብቻ ማቅረቡን ገልጸው ነበር፡፡

አብዛኛው ወርቅ በኮንትሮባንድ መንገድ ወደ ጎረቤት አገሮች እየተላከ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚላክ ዝቅተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ታንታለም ማዕድንን ጨምሮ በኮንትሮባንድ መንገድ ከአገር እንደወጣ የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ችግሩን ለመከላከል አካባቢዎቹን የፀጥታ ኃይሎች እንዲቆጣጠሩት መደረጉ ጠቁመዋል፡፡ 

የአገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊሲ ቀዳሚ ተግባርም ኮንትሮባንድን መከላከልና፣ መዋጋት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች