Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ17 ሺሕ በላይ ተቋማት የእሳትና የአደጋ ሥጋት የደኅንነት መሥፈርቶችን አላሟሉም ተባለ

ከ17 ሺሕ በላይ ተቋማት የእሳትና የአደጋ ሥጋት የደኅንነት መሥፈርቶችን አላሟሉም ተባለ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ17 ሺሕ በላይ ተቋማት የእሳትና የአደጋ ሥጋት የደኅንነት መሥፈርቶችን እንደማያሟሉ፣ የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የሙያና የቴክኖክ ድጋፍ ከተደረገላቸው በኋላ ምን ያህሎቹ የደኅንነት መሥፈርቶችን አሟልተዋል ተብሎ ፍተሻ ከተደረገባቸው 17 ሺሕ ተቋማት ውስጥ፣ 25 ብቻ ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት ደረጃን ያሟሉ መሆናቸውን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ይክፈለው ወልደ መስቀል አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

ለአብነት ፍተሻ ከተደረገባቸው 667 ፋብሪካዎች ውስጥ አምስቱ ብቻ የደኅንነት መቆጣጠሪያ አሟልተው የተገኙ መሆናቸው፣ በከተማዋ ከሚገኙ 180 ባለኮከብ ሆቴሎች ውስጥ 13 ብቻ የአደጋ ደኅንነት መሥፈርት አሟልተው የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ከዚህ በፊት በኮሚሽኑ በነበረ የአሠራር ሁኔታ በተለያዩ ጊዜያት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ የወሰዱ ቢኖሩም፣ ነገር ግን ደረጃውን የጠበቀ እንዳልነበረ ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ፍተሻ ከተደረገባቸው ተቋማት ብዙዎቹ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ያልገጠሙ፣ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር የሌላቸው፣ ዓለም አቀፍ የአደጋ ጊዜ ምልክቶችን ያላስቀመጡ፣ እንዲሁም በትልልቅ ግንባታዎች ላይ ለሚገኙ ሠራተኞች የተሟላ የደኅንነት መጠበቂያዎችን አለማሟላታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

እነዚህ ተቋማት የደኅንነት ደረጃቸውን ባለመጠበቃቸው ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም. ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ በሚሆን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በሌላ በኩል በእሳት አደጋ ሊወድም የነበረ 60 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ኮሚሽኑ ማትረፉን አስታውቀዋል፡፡

ለአደጋው መከሰት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ በዋናነት ግን የሰዎች የጥንቃቄ ጉድለት ትልቁና የመጀመርያው ነው ብለዋል፡፡

ከተቋማት ባሻገር የከተማዋ ነዋሪዎች ከሰል ከተጠቀሙ በኋላ ሳያጠፉ በመተኛት በጭስ ታፍነው የሚሞቱ መኖራቸውን፣ የተጠቀሙበትን ኤሌክትሪክ ሳያጠፉና የተለኮሰ ሻማን ሳያጠፉ በመተኛታቸው ብዙዎች በእሳት ተቃጥለው እንደሞቱ፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ይክፈለው ተናግረዋል፡፡

አደጋው ከግንዛቤ እጥረት አኳያ የሚከሰት ብቻ ሳይሆን በቸልተኝነት ጭምር የሚከሰት ነው ብለው፣ ‹‹አደጋን ለመከላከል እኛም ሚና አለን›› በሚል መሪ ቃል ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ኮሚሽኑ ባካሄደው ውይይት ላይ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ከሚከሰቱ ዋና ዋና አደጋዎች መካከል በእሳት አደጋ ምክንያት የሚጠፋው ሕይወትና የሚወድመው ንብረት የመጀመርያውን ድርሻ ይዞ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ፣ የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ፍሰሐ ጋረደው ናቸው፡፡

ደኅንነታቸውን ባላሟሉ ተቋማት ምክንያት፣ እንዲሁም በጎርፍ አደጋና በሕንፃዎች መደርመስ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የሞትና የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በመዲናዋ ዘጠኝ ቅርንጫፎችን በመክፈት ድንገተኛ የእሳት አደጋዎችን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሠራ ቢሆንም፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ቸልተኝነት ይስተዋላል ብለዋል፡፡

‹‹በተለይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋ ወደ ተከሰተበት ቦታ በሚሄዱበት ወቅት ሌሎች አሽከርካሪዎች መንገድ አለመልቀቅ፣ የተከሰተውን አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስበት ለማትረፍ እንዳንችል እያደረገን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ሔሊኮፕተርን ጨምሮ ዘመናዊ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያዎች ስለሌሉት፣ አደጋው ከተከሰተ በኋላ በቀላሉ ለመቆጣጠር አዳጋች ነው ሲሉ ኮሚሽነር ፍሰሐ አብራርተዋል፡፡

በተቋማት ላይ በሚከሰቱ አደጋዎች ሕጋዊ ዕርምጃ አለመውሰዱ ለአደጋው መስፋፋት ሌላኛም ምክንያት ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ይክፈለው ናቸው፡፡

አደጋ በተከሰተበት ተቋም ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ ሕግና ደንብ ባለመኖሩ፣ በአጥፊው አካል ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ ሳይወስድ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ታስቦ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ሕግ የፀደቀ መሆኑን አውስተው፣ ነገር ግን ለሕጉ ዝርዝር መመርያ ባለመዘጋጀቱ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ አልተጀመረም ብለዋል፡፡

በሕጉ ደረጃቸውን ሳይጠብቁ በሚሠሩ ተቋማት ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያና ከአሥር ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣትን ያካተተ መሆኑን፣ እንዲሁም በዚህ መስተካከል የማይቻል ከሆነ ፈቃድን እስከ መሰረዝ የሚያስችል መመርያ መካተቱን አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...