Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የታክስና ቀረጥ ክፍያዎችን በቴሌ ብር ለመሰብሰብ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ ድንበር የሚወጡና የሚገቡ ምርቶችን የሚቆጣጠር የቴክኖሎጂ ሥርዓት በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. እንደሚጀመር፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የታክስና የቀረጥ ክፍያዎችን በቴሌ ብር ለመሰብሰብ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና የጉምሩክ ኮሚሽን ስምምነት ካደረጉ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለውጭ ገበያ የሚወጡና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚገቡ ምርቶችን በመንገድ ላይ ቅሸባና ዘረፋ እንዳይደርስባቸው ክትትል ማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ ሥርዓት በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፡፡

ሥርዓቱ ከዚህ በፊት አስመጪና ላኪዎች በርካታ ሚሊዮን ብሮች ያወጡባቸው ምርቶች በቁጥጥር ሥርዓት ጉድለት የነበረባቸውና በቴክኖሎጂ የታገዙ ባለመሆናቸው፣ ሲቀሸቡና ሲጠፋባቸው እንደነበር ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. በተሽከርካሪዎች ላይ በሚገጠም ቴክኖሎጂ አማካይነት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ደበሌ ገለጻ፣ የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በማማከር እየተሳተፈበት ነው፡፡ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች መጋዘናቸው እስኪደርሱ ድረስ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆኑን፣ ቴክኖሎጂውም በቅሸባና በዝርፊያ ምክንያት ይታጣ የነበረው የውጭ ምንዛሪን ችግር ይታዳጋል ሲሉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በገቢና በወጪ ተሽከርካሪዎች ላይ ቁጥጥር የሚደረገው በኋላቀር አሠራር እንደነበር፣ ነገር ግን ከሰኔ በኋላ ተቆጣጣሪዎች በየትኛውም ቦታ ሆነው የሚከታተሉበት ሥርዓት እየተዘጋጀ በመሆኑ እንግልት እንደሚቀንስ ጠቁመዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮ ቴሌኮምና ጉምሩክ ኮሚሽን የታክስና የቀረጥ ክፍያዎችን በቴሌ ብር ለመሰብስብ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ በጉምሩክ ኮሚሽንና በኢትዮ ቴሌኮም መካከል የተደረገው ስምምነት፣ ለደንበኞች የታክስና የቀረጥ ክፍያዎች በቀላሉ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሆነው እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸው መሆኑን፣ በአያት ሬጀንሲ ሆቴል ስምምነት ሲያደርጉ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እንደተናገሩት፣ ከ183 ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር የሚከናወንበት አሠራር ዲጂታላይዝ ተደርጓል፡፡

ደንበኞች የታክስና የቀረጥ ክፍያዎችን በቴሌ ብር እንዲፈጽሙ ከመደረጉም ባሻገር፣ የሎጂስቲክስ አፈጻጸም እንዲሻሻል፣ ለመጋዘንና ለወደብ ኪራይ የሚከፈሉ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ፈጣን የጉምሩክ ክሊራንስ አገልግሎት ለማግኘት ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

የውጭ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ አምራቾችን ለማበረታታት፣ ምርቶች ወደ ተፈላጊው መዳረሻቸው በአጭር ጊዜ እንዲደርሱ ለማድረግ ተቋማት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ውጣ ውረዶችን ያቃልላል ተብሎ እንደሚጠበቅ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተነግሯል፡፡

ደንበኞች ካሉበት ሆነው በማንኛውም ጊዜ ክፍያቸውን
በቴሌብር ሱፐርአፕ ወይም በአጭር ቁጥር “*127#” መፈጸም የሚያስችላቸው በመሆኑ፣ አገልግሎት ለማግኘት የሚያወጡትን ወጪና የሚያባክኑትን ጊዜ ለመቆጠብ እንደሚያስችላቸው ተገልጿል።

ጉምሩክ ኮሚሽን ገቢውን በተሻለ ቅልጥፍና ለመሰብሰብ፣ የሥራ ማስኬጂያ ወጪንና ጊዜን በመቆጠብ፣ ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ እንዲሁም የሚጭበረበሩ የክፍያ ሲፒኦዎችን ለማስቀረት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

ቴሌ ብር ሁለት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ 31.2 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት የዲጂታል የኑሮ ዘይቤን ለማሳለጥ፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ‹‹በአንድ መተግበሪያ እልፍ ጉዳይ›› ወደ የሚያከናውኑበት ሱፐርአፕ ወደ ተሰኘ መተግበሪያ ማሳደጉ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች