Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ተወላጆች በከተማዋ ካቢኔ ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ተጠየቀ

የአዲስ አበባ ተወላጆች በከተማዋ ካቢኔ ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምር ተጠየቀ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን በከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ውስጥ ተሳትፏቸው እንዲጨምርና እንዲጠናከር ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄው የቀረበው፣ ‹‹ምክንያታዊ ወጣት ለአዲስ አበባ ብልፅግና›› በሚል መሪ ቃል፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሁሉም ክፍላተ ከተሞች ከተውጣጡ 16 ሺሕ ይሆናሉ ከተባሉ ወጣቶች ጋር፣ ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ውይይት ባደረገበት መድረክ ነው፡፡

በመድረኩ ወጣቶቹ ካቀረቧቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል በአዲስ አበባ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ፣ እንዲሁም በከተማው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነው ሕዝብን በማገልገል ረገድ ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ነው የሚለው ይገኝበታል፡፡

ከልደታ ክፍለ ከተማ የወጣቶች ተወካይ የከተማው አስተዳደር የአዲስ አበባ ከተማ ተወላጅ ምሁራንን፣ በተለይም ወጣቱን በከተማው አስተዳደርና ካቢኔ ውስጥ በማስገባት፣ ‹‹የወጣቱ ተሳትፎ እንዲጠናከር ምን እየተሠራ ይገኛል?›› የሚል ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የአዲስ አበባ ነዋሪ ማለት ተወላጅም፣ አዲስ አበባ ውስጥ የኖረም ነው፤›› በማለት፣ ከተወላጅ አንፃር ከታየ ከአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው የከተማዋ ተወላጅ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹እስከ አዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነት ማዕረግ ድረስ ያሉ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ልጆች ናቸው፡፡ በነዋሪነትም ትናንት የመጡ የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ስንመረጥም ጀምሮ ለሕዝቡ በደንብ ገልጸናል፡፡ ከ20 ዓመታት በታች የኖረ በጣም ጥቂት ሰው ነው፤›› በማለት ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡

ከንቲባዋ አክለውም፣ ‹‹ተሳትፎው በቂ አይደለም ሊባል ይችላል፣ ነገር ግን አለ፡፡ እኛም እንደ አንድ ትኩረት እያየነው ነው፤››› ብለዋል፡፡ እንደ ከንቲባዋ ማብራሪያ ከአዲስ አበባ አመራር ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ሲሆኑ፣ የሴቶች ድርሻ ደግሞ 32 በመቶ ነው፡፡

ከመጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በ11 ክፍላተ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ 119 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 4,992 ብሎኮች ከ500 ሺሕ በላይ ወጣቶች ተወያይተው፣ የማጠቃለያ መድረክ ነው ተብሎ በተገለጸው የሚሊኒየም አዳራሽ ውይይት፣ በተወካይ ወጣቶች አማካይነት ሌሎች ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር፡፡

ከነዋሪነት መታወቂያ ጋር በተያያዘ በርካታ ዜጎች በአዲስ አበባ እየኖሩ ማግኘት እንዳልቻሉ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራንም በተመለከተ ውስብስብ የብድር አሰጣጥ ችግርና ወጣቱን ያላገናዘበ የዋስትናና ተያያዥ ጥያቄዎች እንዳሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

ከጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚነት አንፃር ወጣቶች የ30 በመቶ ተጠቃሚነት (ቅድሚያ ዕድል) እንዳላቸው ቢገለጽም፣ ወጣቶች ተጠቃሚ ባለመሆናቸው አስተዳደሩ ጉዳዩን ያጢነው የሚለው ጥያቄም ተሰምቷል፡፡

በሌላ በኩል ለረዥም ዓመታት በተደራጁ ወጣቶች ተይዘው የቆዩ ሼዶች፣ ለአዳዲስ ወጣቶች መተላለፍ እንደሚገባቸው፣ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በሚል በተጀመረው የእሑድ ገበያ የሸማች ማኅበራት ለማኅበረሰቡ የሚሸጥበት ዋጋና መደበኛ ነጋዴው የሚሸጥበት ዋጋ ተቀራራቢ በመሆኑ፣ ችግሩ ሊታይ ይገባል የሚሉት ሌሎች በወጣቶቹ የተነሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ፣ ከከተማዋ ነዋሪ ከ17 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጣት ሥራ ፈላጊ መሆኑን አስታውሰው፣ አስተዳደሩ በአሥር ዓመታት ዕቅዱ ይህንን መጠን ከአሥር በመቶ ለማውረድ እንዳለመና በዚህም የግሉ ዘርፍ አውራ እንዲሆን እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡  

በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ከአምስት ዓመታት በላይ ሼዶችን ይዘው የቆዩ፣ በኤክስፖርት ምርትና ቴክኖሎጂ ላይ ባልሠሩት ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ አቶ ጃንጥራር አስረድተዋል፡፡

የብድር ቢሮክራሲ በሁለት ዓይነት መንገድ መታየት እንደሚገባ፣ ብድር ተወስዶ መመለስ እንዳለበትና የመንግሥት ብድር እንዲመለስ ዋስትና መኖር እንደሚገባው ተጠቅሷል፡፡

የጠለፋ ዋስትና የሚባል፣ እንዲሁም በሌላ በኩል በማስያዣ የሚሰጥ የብድር ዓይነት እንደሚገኝ፣ በጠለፋ የሚሰጠው ብድር ምንም ዓይነት ማስያዣ ንብረት ሳይኖር ተደራጅተው ለመጡ ወጣቶች የሚሰጥ የብድር ሥርዓት መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህ ሒደት በአንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ በተለይም በክፍላተ ከተሞች እየተፈጠረ ያለ ቢሮክራሲ ካለ የብድርና ቁጠባ ተቋሙ ብቻ ሳይሆን፣ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጉዳዩን በክትትል ለመፍታት እንደሚሠራ አቶ ጃንጥራር ጠቁመዋል፡፡

ከቤት ግንባታ ጋር ተያይዞ የወጣቶች ተጠቃሚነት ጥያቄ በመረዳት በ70/30 አማራጭ አስተዳደሩ እስከ ሳይት ድረስ ያለውን መሠረተ ልማት በማሟላት፣ የግል ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው እንዲገነቡ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡

በዚህ የግንባታ ሒደት ለወጣቶች ሁለት ዓይነት ዕድል እንደተመቻቸ የገለጹት ከንቲባዋ፣ ከኮንስትራክሽን ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሠለጠኑ ከ210 ሺሕ በላይ ወጣቶችን ወደ ሥራ የሚያስገባ ምዝገባ በቅርቡ እንደሚጀመርም አስረድተዋል፡፡

‹‹መታወቂያ ማግኘት መብት ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ አዳነች፣ ነገር ግን አሰጣጡ በዋናነት ችግር ስለነበረበት ዕገዳው ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ መደረጉንና ከፍተኛ ሪፎርም ተደርጎበታል የተባለው የወሳኝ ኩነት ተቋም በቀጣይ በየክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች መታወቂያ የሚሰጥበትን አሠራር እንደሚዘረጋ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...