Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ የሚያጠናቅቀውን አዲስ ተቋራጭ እየለየ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ የሚያጠናቅቀውን አዲስ ተቋራጭ እየለየ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

ቀን:

የአደይ አበባ ስታዲየምን ቀሪ የግንባታ ምዕራፍ የሚያጠናቅቀው ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ለመለየት የመጨረሻ ሒደት ላይ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ ስታዲም ግንባታን ተረክቦ ግንባታ ሲያከናውን የነበረውን የቻይናው ኮንስትራክሽን ዲዛይን ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን አስረክቦ እንዲወጣ መታዘዙን ተከትሎ፣ አዲስ ጨረታ ይፋ ያደረገው ሚኒስቴሩ  ተቋራጮችን እየለየ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አዝመራው ግዛው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ግንባታውን ለማጠናቀቅ በወጣው ጨረታ የተለያዩ የአውሮፓና የኤዢያ ተቋራጮች ፍላጎት እንዳለቸው ማሳየታቸውን ቢገለጽም ሚኒስቴሩ ግን የትኛውንም ተቋራጭ እንደለየ አልተገለጸም፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ አስተያየት ከሆነ የመጨረሻዎቹን የግንባታ ተቋራጭ ለይቶ በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ የጠቆመ ሲሆን፣ የተቋራጩን ስም ለመጥቀስ ትክክኛው ጊዜ እንዳልሆነና ጉዳዩን በሒደት ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡

በዚም መሠረት የጨረታው ሒደት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንደሆን በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝና ተቋራጩ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ሲደርስ ይፋ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡

የአደይ አበባ ስቴዲየምን ተረክቦ ግንባታ ሲያከናውን የነበረው የቻይናው ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱን አስረክቦ እንዲወጣ መታዘዙ ይታወሳል፡፡ የቻይናው ተቋራጭ በውሉ መሠረት ክፍያዎች ለመፈጸም ቀሪ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና በግንባታው ወቅት ተቋራጩ ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የግንባታ ማሽኖችን እንዲያወጣ መታዘዙ ተገልጾ ነበር፡፡

የቻይናው ተቋራጭ ጠቅልሎ መውጣቱን ተከትሎ አዲስ ይፋ በሆነው ጨረታ የአውሮፓ ኩባንያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ የቱርክና የጣሊያን ኩባንያዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ሚኒስቴሩ ከቻይናው ተቋራጭ ጋር የነበረው ውል በስምምነቱ መሠረት ውሉን ለማቋረጥ መስማማቱን ተከትሎ፣ ሙሉ በሙሉ ለቆ እየወጣ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም መሠረት ተቋራጩ፣ አስመጥቶ የነበረው የግንባታ ቁሳቁስ፣ ከዚህ ቀደም በተገዙበት የዋጋ ተመን አማካይነት ለተቋራጩ ክፍያ እንዲፈጽም ተደርጎ ለቀጣይ ገንባታ እንዲቀመጥ እንዲደረግ መወሰኑ አቶ አዝመራው ገልጸዋል፡፡

ቀጣይ ጨረታውን የሚያሸንፈው ተቋራጭ በቻይናው ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ኮርፖሬሽን ያልተጠናቀቁ ግንባታዎችን ያጠናቅቃል ተብሏል፡፡ በአንፃሩ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቋራጮች ሊሠሩ የሚችሏቸው ሥራዎች ለእነሱ እንደሚሰጡ፣ ነገር ግን ቴክኖሎጂ ነክ ሥራዎችን ጨረታውን የሚያሸንፈው የውጭ አገር ተቋራጭ ሙሉ በሙሉ እንደሚያከናውን ይጠበቃል፡፡

በቅርቡ የቻይና ተቋራጭ ባቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ ላይ መግባባት ባለመቻሉ፣ ከተቋራጩ ጋር የተገባው ውል እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡ የተገባው  ውል በቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ መሠረት የሥራ ወጪ ላይ 225 በመቶ የክፍያ ማስተካከያ በማድረግ 12.5 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተው ነበር፡፡

ተቋራጩ ግን የተከፈለውና በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን አንድ ላይ ለማከናወን ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲከፈለው ጥያቄ በማቅረቡ መስማማት ስላልተቻለ፣ በስምምነት ውሉን ለማቋረጥ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል ዕድሳት እየተደረገለት የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም ሊጠናቀቅ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ ብሔራዊ ቡድኑ ለሚኖረው ቀጣይ ዓለም አቀፍ የማጣሪያ ጨዋታ እንደሚደርስ ተገልጿል፡፡

የስታዲየሙ አብዛኛው የግንባታ ሒደት እንደተጋመሰ የተጠቆመ ሲሆን፣ የትራክ ግንባታው መጨረሻ ምዕራፍ እንደሚከናውን ታውቋል፡፡ የትራክ ግንባታውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ለመለየት ጨረታው ወጥቶ መለየቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...