በገነት ዓለሙ
ባለፉት አምስት ዓመታት ችግሮች ባጋጠሙን ቁጥር፣ ጣጣዎቻችን እየተዘረገፉ ባስቸገሩን ቁጥር፣ እኛም እየተዝረከረክን ችግሮቻችንን የሚከላከል ሳይሆን የሚጠቀምና የሚያባብስ ሥራ በሠራን መጠን፣ ደጋግመንና በየጊዜው የምናነሳው አንድ ዋና ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ዋና ጉዳይ ለውጡና የለውጡ ዓላማ ነው፡፡ ዛሬም ሆነ፣ ከዛሬ በፊት እጅግ በጣም ቀደም ብሎ የምን ለውጥ ነው? የምን ሽግግር ነው? ሽግግሩና ለውጡማ ተቀልብሷል የሚሉ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ይህ ግን የለውጡንና የሽግግሩን ዓላማ ምንነትና ይዘት አይለውጥም፣ አያናጋም፡፡ ለውጡ ሻል ያለ ዓለም ኢትዮጵያ ውስጥ ማቋቋም ነው፡፡ ሽግግሩ ወደ ዴሞክራሲ ማለፍ ነው፡፡ አገራችን ውስጥ ሻል ያለ ዓለም እንዲገነባ ለማድረግ መሠረታዊ መብታችንና ነፃነታችን መኗኗሪያችን መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን ዕውን መኗኗሪያ እንዲሆኑ ደግሞ የአገር ተቋማትና የመንግሥት ዓምዶች ነፃና ገለልተኛ፣ የየትኛውም ፓርቲ ወይም ቡድን ተቀጽላ ያልሆኑ ሆነው መታነፅ አለባቸው፡፡
ደጋግመን የምናነሳው፣ ወደፊትም፣ ነገ ከነገ ወዲያም አስፈላጊ በሆነ መጠን መልሰን መላልሰን የምንገልጸው ዋናው የጉዟችን ማዕቀፍ፣ ‹‹የእግር መንገዳችን››፣ ‹‹የዓይን ብርሃናችን›› ይኼው ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም፣ ዋና የፖሊሲ ጉዳይ ላይ ስንወስንም መረማመድ ያለብንም በዚህ አጠቃላይ ማዕቀፍና በዚህ ዋና ቅጥር ግቢ ውስጥ ሆነን ነው፡፡
እናም ያለንበትን ምዕራፍ የሽግግር ጊዜ የምንለው፣ ወይም እንዲያ ያለ የሽግግር ጊዜ ወይም ለውጥ ‹‹ተጀምሮ ነበር›› የምንለው፣ ሕገ መንግሥትን ካሰናካለ አፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ወደ ዴሞክራሲ የመሄድ፣ የማለፍ ጉዞ ውስጥ ስላለን ነው፡፡ ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ መግባትና ማለፍ ደግሞ ዝም ብሎ፣ ‹‹እስኪ ተነስቼ…›› ተብሎ የሚያያዙት መንገድ አይደለም፡፡ በአስተሳሰብ፣ በማኅበራዊ ግንኙነትና በመንበረ መንግሥቱ አውታራት ላይ የደረሱ ብልሽቶችን ማደስ፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታ ሥራ መሥራት ይፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም አገር ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በተግባር እንዲሠራ፣ ዴሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በአግባቡ ማቋቋም የግድ ነው፡፡ እዚህ አጠቃላይ አባባል ውስጥ የሥርዓተ መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ወይም ከቡድን ማጠንትና ሰንሰለት መለያየት አለበት፣ ፓርቲዎች ከባለጠመንጃነት መሰነባበትና መቆራረጥ ይገባቸዋል፣ በዚህ መሠረትም ፓርቲዎች ከአግላይነት መውጣትና ከዴሞክራሲ አሠራርና እሴቶች ጋር መግባት አለባቸው፣ ወዘተ ማለትን የመሳሰሉ ቅድመ ሁኔታዎች ይገኛሉ፡፡ ፓርቲዎች ሥልጣን ላይ የሚወጡት ብቸኛው ሕጋዊው መንገድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ፖሊሲዎቻቸውን በነፃነት አወዳድረው በተዓማኒ የምርጫ ሒደት በሚገኝ የድምፅ ብልጫ ውጤት መሆን አለበት፡፡
የአገሪቱ የበላይ ሕግ በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው የሚለው ነፃ ሐሳብ የሚንሸራሸርበት፣ ብዙ ፓርቲዎች የሚፍለቀለቁበት፣ ፓርቲዎች በነፃነት የሚወዳደሩበት፣ ሕዝብ በነፃ ተደራጅቶ በነፃነት የሚመርጥበት፣ ምርጫ ማሸነፍ ማለት (መንገዱ ያን ያህል ቀና ቢሆን) ሥልጣን መያዝ ማለት የሆነበት ሥርዓት አለኝ ብሎ ነው፡፡ የለውጡና የሽግግሩ ሥራ ይህ እንዳይሆን የከለከለውን ብልሽት ማስወገድ ነው፡፡ ገለልተኛ ተቋማት መፍጠር ነው፡፡
አገራችን ውስጥ ወደ እዚህ ሥርዓት ለመግባት ጉዞው የተጀመረው ከአምስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ ይህ ጉዞ ግን መጀመርያ በግርግሮች ደንበር ተገር ሲል ቆይቷል፡፡ በኋላም በጦርነት ተወግቷል፡፡ ጦርነቱን የቀሰቀሰው ምክንያት፣ አገር የሚያቃጥል እሳት መለኮስ የቻለው ፓርቲዎች ሰላማዊ ተፎካካሪዎች ባለመሆናቸው ነው፡፡ ይልቁንም መገለባበጥ የደረሰበት ገዥው ፓርቲ፣ ኢሕአዴግ ራሱ አገር ይገዛ የነበረው በሕወሓት ቁጥጥር ሥር የነበረ መንግሥታዊ አውታር ስለነበር ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትግራይ መቀሌ ላይ ‹‹የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራን በሚመለከት የተሰጠ መግለጫ›› ውስጥ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ (መጋቢት መጀመርያ አጋማሽ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት) ከብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ባለሥልጣናት ጋር ሲወያዩ ከሌሎች መካከል ስለ ‹‹DDR›› ትጥቅ የማስፈታት፣ ተዋጊነትን ስለማብቃት/ማቆም፣ ወደ ማኅበረሰብ መቀላቀል የኢትዮጵያን የከዚህ ቀደም ልምድና ተሞክሮ አንስተው የተናገሩትን እዚህ ላይ ጠቅሶ መንደርደሪያ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያ ውስጥ የ‹‹DDR›› ሥራዎች የተሠሩበት ሁለት አጋሚዎች እንደነበሩ፣ አንደኛው የ1983 ዓ.ም.፣ ሌላው ደግሞ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ የተደረጉ እንደሆኑ ገልጸው፣ ‹‹…ከአሁን በፊት ከዲሞብላይዜሽንና ከሪኢንተግሬሽን ጋር ተያይዞ ትግራይ ጥሩ ልምድ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ብዙ መልካም የሚባል ልምድ የሌለ ስለሆነ፣ አሁን የምናደርገው እንቅስቃሴ በተቻለ መጠን እነዚህን ስህተቶች እንዲያርም ሆኖ እንዲጠናቀቅ…›› የማድረጉን ተገቢነት ገልጸዋል፡፡
በዋነኛነት የምንነጋገረው ለውጥና ሽግግር ውስጥ፣ ወይም በዚህ ጎዳና ውስጥ ዴሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን ስለማደላደልና ስለማቋቋም ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ፓርቲዎችን ከባለጠመንጃነት ማቆራረጥና መለያየት ያስፈልጋል፡፡ የምናቋቁማቸው፣ የምንደራጅባቸው፣ የምንመርጣቸው ፓርቲዎች አመለካከታቸውና አሠራራቸው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንፈልጋለን፣ ሕግም ይህንን ይደነግጋል፡፡ ፓርቲዎች ራሳቸው በውስጣቸው የተሻለ ሐሳብንና የበለጠ የበቃ ሰውን የሚመርጡት በዴሞክራሲያዊ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ዋናው መነሻው የሥርዓተ መንግሥቱን ወታደራዊም ሆነ ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ሙሽትና ሰንሰለት መለያየት ነው፡፡ ፓርቲዎች ባለጠመንጃ አይደሉም፣ አይሆኑም ማለትማ የጥበብ መጀመርያው ነው፡፡ አሁን የምንገኘው የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ስድስተኛው ወር ውስጥ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አባላትን (የክልሎችን) ልዩ ኃይሎች ‹‹እንደገና የማደራጀት›› (ወይም የሪፎርም ሥራ) ብቻውንም ሆነ ከሌላ ችግራችን ጋር ተጎዳኝቶ የጫረው እሳት እንደተፈራውና እንዳስፈራራው ያህል የከፋ አደጋ ሳያደርስ ‹‹ድንገት›› አልፎን ሄዶ ባለበት ወቅት ነው፡፡ በአጠቃላይ የደረስንበት የዕድገት ደረጃም ሆነ የተያያዝነው የአፈጻጻም ጎዳና ወሳኝ ጥያቄዎችን አግተልትሎ የሚያነሳበት፣ ይህም ከመቼውም የበለጠ ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶን የሚጠይቅበት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ችግሮቻችንንና መፍትሔዎቻቸው ሁሉ በዋናው ዴሞክራሲን የማደላደል የሕግ የበላይነትን የማቋቋምና እሱኑ ሙጥኝ የማለት፣ የሚሉት ማዕቀፍ ውስጥ መወሰንና መታጠር ያለበት ወቅት ነው፡፡
ለምን የእኛ አገር ፖለቲካ ውስጥ ብቻ መወያያ ሲሆን ‹‹እንግዳ›› ነገር እንደሚሆን አይገልጥልንም እንጂ ባለጠመንጃ ፓርቲዎች፣ የታጠቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ብሎ ዴሞክራሲ የለም፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት ወታደራዊም ሆነ ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ተፅዕኖና ሥውርም ሆነ ግልጽ ሰንሰለት ነፃ መውጣት አለበት፡፡ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ትግል ያጎደለው ይኼው ነው፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ የ1983 ዓ.ም. ‹‹አጋጣሚ›› ወዳነሱበት ጉዳይ እንጠጋ፡፡ ኢሕአዴግ ማለት በሕወሓት ብቸኛ ቁጥጥር ሥር በነበረ መንግሥታዊ አውታር ላይ ሆኖ ይገዛ የነበረ ፓርቲ ነው፡፡ ኢሕአዴግ መጀመርያ በኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት፣ በኋላም በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ስም ሥልጣን ሲይዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ያወጀው›› (በሽግግር ወቅት ቻርተሩ)፣
‹‹ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊ አምባገነን መንግሥት መገርሰስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበት ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት…›› ነው ብሎ ነው፡፡
ይህንን ዕድል ግን ሕወሓት ሠራዊቱን የኢሕአዴግ ሠራዊት ብሎ ሰይሞ ጭምር፣ የኢሕአዴግ ሠራዊት ለሽግግሩ ዘመን የማዕከላዊ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሆኖ እንዲያገለግል ሲወስን ተጨናገፈ፡፡ የሕወሓት ሠራዊት የኢትዮጵያ (የማዕከላዊ መንግሥት) የአገር መከላከያ ሠራዊት የማድረጉ ዕርምጃ የሕግ ሽፋን፣ የአሸሼ ገዳሜና የግርግር ሥርዓት/ሥነ ሥርዓት ነበረው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 8/1984፣ ‹‹የአገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት በዘለቄታ ማቋቋም ወደፊት በሕዝብ የሚመርጠው መንግሥት ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን፣ እስከዚያው ድረስ የአገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር ትልልቅ የፀጥታ መናጋቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ከሁኔታው ጋር የሚስማማ የመከላከያና የደኅንነት ፖሊሲ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ…›› ተባለና ነሐሴ 2 ቀን 1983 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት የመከላከያና የደኅንነት ፖሊሲ መርሆዎች›› ወጣ፡፡ በዚያው ዕለት የተሰባሰበው የተወካዮች ምክር ቤት (የሽግግር መንግሥት) በሰባተኛ መደበኛ ስብሰባው ያፀደቀው ነው፡፡
‹‹ስለማዕከላዊ የሽግግር መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሥምሪትና ስለፖሊስ ኃይል መቋቋም›› የወጣው አዋጅ ቁጥር 8/1984 ከሌሎች መካከል በመዘገበው ታሪክ መሠረት፣ የሽግግሩ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የመከላከያና የደኅንነት ፖሊሲ ሁለት በግልጽ የሚታዩ ጠንቆችን ትቶልን ሄዷል፡፡
አንደኛው የተጠቀሰው አዋጅ መግቢያ ላይ የተመለከተው፣ ‹‹በመከላከያና በደኅንነት ፖሊስ መርሆዎች መሠረት የመከላከያና ደኅንነት ኃላፊነት የማዕከላዊ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የብሔራዊና ክልላዊ መስተዳድሮችም ሚና እንዳላቸው የታመነ በመሆኑ›› የሚለው ነው፡፡
ሁለተኛው በአዋጁ አንቀጽ 3 (1) በሕግ የተወሰነውና ‹‹የኢሕአዴግ ሠራዊት ለሽግግሩ ዘመን የማዕከላዊ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሆኖ ያገለግላል›› ተብሎ የተደነገገው ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የሕወሓት ሠራዊት (በኢሕአዴግ ሠራዊት ስም) የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሆኖ ተመረቀ፡፡ የሌሎች ድርጅቶች ሠራዊቶች በዚህ የ1984 ዓ.ም. አዋጅ ክፍል አራት፣ በተለይም አንቀጽ 10 እና ተከታዮቹ እንደ ተደነገገው አዲስ ኃይል መመልመልን፣ ማሠልጠንና ማስታጠቅም ከመከልከል የጀመረ ዕርምጃ ቀስ እያለ በሕግ በተወሰነው ዘዴ ሽፋን (ስለድርጅቶች ሠራዊት አያያዝ ድንጋጌ) መበተን፣ ህልውና ማሳጣት፣ በመጨረሻም ሕወሓት/ኢሕአዴግ የተሸነፈውን የደርግን ሠራዊትም ሆነ ‹‹አብሮ››ት አጅቦ የገባውን የኦነግ ሠራዊት ባጠናቀቀበት መንገድ የ‹‹DDR›› ትርዒቱ ተከናወነ፡፡ ግፉም፣ ጠንቁም ዛሬም እንደ ተኩስ ግፍ ሲወሳና ሲተረክ ይኖራል፡፡ ያተረፈው ትምህርትም ቂም ሆኖ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ውስጥ ሲንቀሳቀስ/ሲላወስ ይታያል፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ ከዚህ የ1983 ዓ.ም. አጋጣሚ ‹‹ብዙ መልካም የሚባል ልምድ የሌለ ስለሆነ፣ እነዚህን ስህተቶች እንድናርም ተደርጎ እንዲጠናቀቅ…›› ማለታቸው ውስጥ፣ በ1983 እና በ1984 ዓ.ም. በዚህ ረገድ የተፈጸመው ግፍ ተዘርግፎ እስኪነገረን ሳንጠብቅ፣ የአገር ዴሞክራሲን በማደላደል ሰፊ አደራና ግዳጅ ውስጥ ፓርቲዎችን (ነባሮችንም ሆነ አዲሶቹን በማዕከላው መንግሥትም፣ በክልልም ሥልጣን ላይ የነበሩትንም ሆነ ተቃዋሚዎችን፣ የአገር ቤቶችንም ሆነ ከውጭ የመጡትን) ከባለጠመንጃነት፣ ከጠመንጃ ባለቤትነት መገላገልና ማቆራረጥ አለበት፣ ይህንን ማድረግ ማወቅ አለብን፡፡ ማወቅ ያለብን፣ ተግባራዊም ማድረግ ያለብን፣ ፓርቲን ‹‹ትጥቅ ማስፈታት›› ወደ ሰላማዊና ሕጋዊ ተፎካካሪነት መለወጥ ብቻ አይደለም፡፡ የሥርዓተ መንግሥቱ የትኛውም ቢሮክራሲ ከፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት መለያየቱን ጭምር ነው፡፡
በ1983 ዓ.ም. የጀመረው የሽግግር ወቅት ፖሊሲ ከቀበራቸው ጠንቆች መካከል አንዱ ‹‹የመከላከያና ደኅንነት ኃፊላነት የማዕከላዊ መንግሥት ብቻ ሳይሆን…›› መባሉ፣ በዚህም ብቻ ሳይወሰን ‹‹…የብሔራዊና ክልላዊ መስተዳድሮችም ሚና እንዳላቸው የታመነ…›› ነው መባሉ፣ ከሌሎች የክፍልፋይነትና የጎጠኝነት ዕይታዎች ጋር ተረባርቦ በየክልሉ ሁሉ/ወይም ከሞላ ጎደል በብዙ ክልሎች የታጠቀ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኛ የሆነ፣ ሕዝብን የእኔና የእኔ ያልሆነ፣ ባላገርና መጤ ብሎ የሚያንጓልልና ከሰው ሰው የሚለይ ፓርቲ፣ ክልልና ብሔር ፖለቲካ ውስጥ የተቀረቀረ ፖለቲከኛ የታጠቀ ኃይል አገሮች እንድንሆን አድርጎናል፡፡
እነዚህን ችግሮቻችንን፣ አዳዲስ የሚፈንዱትን፣ ድንገት ደርሰው የሚዘረግፉትንም ሆነ አስቀድመው የሚታወቁትን ጣጣዎቻችንና አደጋዎቻችን ስንጋፈጥ ሁልጊዜም የመገናኛና የመረባረቢያ አገር ግቢያችን ዴሞክራሲውን ማደላደል፣ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከየትኛውም ወገንተኛነት ነፃ የሆነ የመንግሥት አውታር መገንባት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ የክልል ልዩ ኃይሎችን ‹‹መልሶ ስለማደራጀት›› (እንደገና ስለማደራጀት፣ ‹‹ዳግም›› ስለማደራጀት፣ ወይም ‹በፌዴራል›› የፀጥታ ተቋማት ማደራጀት››) ስንናገር፣ ከዚህ ሁሉ በኋላም አደጋዎች ተቀልብሰው ሥራውም በተቻለ መጠን ተሠራ ብለን ‹‹…ከዛሬ ጀምሮ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል አደረጃጀት/መዋቅር የለም፣ አይኖርም›› ስንል፣ በተለይም መንግሥት ይህንን ሲናገር ሥራው ብቻ ሳይሆን ንግግሩ ራሱ በዋናው ጉዳያችን፣ በዋናው ዴሞክራሲን የማደላደልና ተቋማትን ነፃና ገለልተኛ አድርጎ በመገንባት የአገር ግዳጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ መዋል ማደሩን ማረጋገጥ አለብን፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ብዙ የሪፎርም ሥራ የተሠራበት አካል ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረው ተመሳሳይ ተቋም ምን ያህል የአንድ ፓርቲ ጥገኛና ‹‹የግል ንብረት›› እንደነበር ሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው አምሳያ የሌለው ጥቃትና ‹‹ዕርድ›› ባህርይ መነሻና ምክንያት አስረጂ ነው፡፡ በውጭ አገር የኢትዮጵያ ሠራዊት የሰላም ማስከበር ሥምሪት ላይ የተሰማራው ቡድን/አሃድ፣ ወዘተ. ከግዳጅ በኋላ ወደ አገር ሲመለስ ይዘገብና ይሰማ የነበረው የ‹‹ክዳት›› ልምድ ከፓርቲ ገለልተኛ የሆነ ተቋም ያለመገንባቱ ቋሚ ማስረጃ ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓት በተግባር ሲሠራ ለማየትና እንዲያ ዓይነት ሕይወት ውስጥም ለመኖር ዴሞክራሲን ማደላደል፣ የሕግ የበላይነትን በአግባቡ ማቋቋም የግድ ነው፡፡ ኢፌዴሪን በማዕከላዊ (ማለትም በፌዴራልና) በክልል መንግሥታት መካከል ያደላደለውና ያከፋፈለው ሕገ መንግሥት አገር የመከላከልን የመንግሥት ሥልጣን ለማን እንደሰጠና በየትኛው የመንግሥት የሥልጣን ደረጃ እንደ ከለለ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዥታ ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ምክንያት ‹‹የመከላከያና የደኅንነት ኃላፊነት የማዕከላዊ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የብሔራዊና የክልላዊ መስተዳድሮቹም ሚና እንዳላቸው የታመነ በመሆኑ›› የሚለው የሕወሓት/ኢሕአዴግ የነሐሴ 1983 ዓ.ም. የፖሊሲ መርህ ቅሪትና አባዜ ከሕወሓት ትጥቅ መፍታት ጋር፣ ሕወሓትን ከብረት ትግል ከማገላገል ጋር፣ ሕወሓትንና ሌሎች ፓርቲዎችን ጭምር ወደ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ከመመለስ፣ እንዲህ ያለ የሰከነና የሠለጠነ ዴሞክሲያዊ ትግልና ፉክክር የሚጠይቀውን ተግባርና ባህርይ ከማጎናፀፍ ጋር መሰናበትና ማስቀረት አለብን፡፡
ደግመን ደጋግመን ሕወሓት/ኢሕአዴግ የምንለው፣ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ሕወሓት፣ ሕወሓት ማለት የምመርጠው ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲገዛ የነበረው ኢሕአዴግ ይባል የነበረው ድርጅት ይዘት ሕወሓት ራሱ በመሆኑ ነው፡፡ ያራባቸው፣ በሥልጣን ላይ እያለ የሚያራባቸው የነበሩ ድርጅቶች ሁሉ የራሱ የሕወሓት፣ የዚያ አንድ ይዘት ልዩ ልዩ ቅርፅ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ስለነበር ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያንን ያህል ዘመን ሥልጣን ላይ የቆየው በየአምስት ዓመቱ ምርጫ መንግሥትነትን በሕዝብ እየተሾመ ሳይሆን ራሱን ኢሕአዴግን፣ በተለይም ሕወሓትን የኢትዮጵያ ዓምደ መንግሥት አደርጎ ያደራጀ ስለነበር ነው፡፡ የዚህ የመጀመርያው የማዕዘን ድንጋይ የተቀመጠው በጦርነት ሲያሸንፉና ቀደም ብለን እንደገለጽነውም የሕወሓት ተጋዳላዮችን የአገር የመከላከያ ሠራዊት ሲያደርግ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ ራሱ የመንግሥት ዓምድ ያልሆነበት፣ ፓርቲዎች ሁሉ በምርጫ ወጪና ወራጅ የመሆን እኩል ዕድል የሚያገኙበት ሥርዓት የመገንባት ቁምነገር መንግሥታዊ አውታራትን ከፓርቲ/ከፖለቲካ ታማኝነት ነፃ አድርጎ ማቋቋምን የመሰለ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ዕውቀት የጥበብ መጀመርያው አድርጎ ይነሳል፡፡ ሕወሓት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥትና አገር የመከላከያ ሠራዊት አንድ ብቻ ነው የሚል፣ የአዋጁን፣ የሕገ መንግሥቱን አዋጅ በጆሮ የሚነግር ስምምነት ከተፈረመ በኋላ፣ በዚህ ስምምነት አፈጻጸም ሒደት ውስጥ ሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በተሰማው መግለጫ ላይ የብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ድርቤ መኩሪያ የነገሩን፣ እሳቸው ‹‹ብዙ ጊዜ የማይገለጸው››፣ ‹‹ብዙ ጊዜ አልተገለጸም ነበር›› ብለው ደጋግመው አስረግጠው የነገሩን አዲስ ትኩስ ወሬ ሕወሓት የአየር ኃይል ትጥቅ መፍታቱንና ማስረከቡን ጭምር ነበር፡፡ ትጥቅ የማስፈታቱ፣ ፓርቲን ከመሣሪያ (ትግል) የማገላገሉ፣ በአጠቃላይ ፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት የማስፈጸሙና የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ መደላድል የመዘርጋቱ የዚህ ዘርፍ ሥራ በየፈርጁ ባለቤትና ተከታታይ ዕውቀትና ጥበብ የሚጠይቅ መሆኑ፣ ጉዳዩ በቀረበበትና አሁን በያዘው መልክ የሚያሳስብ፣ የሚቆረቁርና የሚያንገበግብ ሆኖ፣ የተሃድሶ ኮሚሽኑም/ኮሚሽነር በነገሩን ዜና ውስጥ ሰበር ዜና ሆኖ ያገኘሁት ሕወሓት የአየር ኃይል ትጥቅ መታጠቁ ያን ያህል ባለትጥቅ መሆን ድረስ የመንግሥት አውታራት ኢሕአዴጋዊነት፣ በተለይም ሕወሓታዊነት ፀንቶና ተጠናውቶን የቆየ ደዌ/በሽታችን መሆኑን ነው፡፡
መንግሥትና ፓርቲ መለያየት አለባቸው፣ የመንግሥት አውታራት ፓርቲያዊነት መከላከያም፣ ፀንቶ ዘብ መቆምን የመሰለ የዘወትር የጥበቃ ሥራ ይጠይቃል የምንለው በዚህ ሁሉ ምክንያት ነው፡፡ የመንግሥት አወታራት ወይም የተለያዩ ተቋሞቻቸው ፓርቲያዊነት እስካለና ችላ እስከተባለ ድረስ ዴሞክራሲ አይቋቋምም ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ እንደ ሰማነው ያለ አንድ ፓርቲ የምድር ጦር ብቻ ሳይሆን ‹‹የአየር ኃይል ትጥቅ›› ባለቤት ጭምር ሆኖ በሰበር ዜና ሲነገር እንሰማለን፡፡ እዚያ ‘ጋዜጣዊ መግለጫ’ ውስጥ፣ ሌሎችም የዚሁ ጉዳይ የተለያዩ ወገኖች የዜና ዘገባዎች ውስጥ የሚነገረንን ወሬ፣ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) የምንሰማው እንደ ወጉ፣ በወጉና በደንቡ መሠረተ ሊኖር ከሚገባው ከማስተንተን ጋር ብቻ ሳይሆን እየተሳቀቅንም ጭምር ነው፡፡ የስምምነቱ ተዋዋይ ወገኖች፣ ግራ ቀኙ፣ (ፌዴራል መንግሥቱና ሕወሓት) በየልሳናቸው ወይም በሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች አማካይነት እንደሚነግሩን ሕወሓት የከባድ መሣሪያ ትጥቅ አውርዷል፡፡ በዚህ መሣሪያ ምድብ ውስጥ የሚካተተውም ‹‹ብዙ ጊዜ የማይነገረው›› የተባለው የአየር ኃይል ትጥቅ ይገኝበታል፡፡ ሚያዝያ ወር የመጀመርያ ሳምንት ፍፃሜ አካባቢ እንደተነገረንና ‹‹የቡድን ትጥቅ› የማስፈታት ሥራ ከሚያዝያ 9 እስከ 16 ቀን ድረስ ይከናወናል በተባለው መሠረት ደግሞ፣ ሕወሓት ‹‹መካከለኛና ቀላል የቡድን መሣሪያዎች›› ትጥቅ የመፍታት ተግባር አከናወነ ወይም ‹‹የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ደንጎላት የተሰበሰቡ የመጀመርያ ዙር የቡድን መሣሪያዎችን በዛሬው ዕለት አስረክበ›› (ሚያዝያ 11 ቀን 2015 ዓ.ም.) ተብሎ ሲዘገብ ሰምተናል፡፡
ሱዳን ያለው ኃይል ስለሚባለው፣ ‹‹ጉዳችን››ም ሪፖርት ሲደረግ ሰምተናል፡፡ ‹‹ይነስም ይብዛ›› በሌሎች አካባቢዎችም ስላለ ኃይል በሪፖርት ሲነገር እንሰማለን፡፡ ይህ ሁሉ ግን ጥርት ባለ፣ ባለቤትና ዋቢ ባለው፣ እኔ አልፋለሁ፣ ኋላፊውና ተጠያቂው እኔ ነኝ ብሎ የሚያረጋግጥ የሥልጣን (የባለሥልጣን) የመረጃ ምንጭ ዋስትና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለመሆኑ የዚህ ጉዳይ፣ የአፈጻጸሙ ሒደት ባለቤት ማነው? የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሕገ መንግሥቱ እንደተደነገገውና በፕሪቶሪያው ስምምነትም ዋነኛው የውሉ ምሰሶ በሆነው መሠረት፣ ‹‹ከእኔ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በስተቀር ሌላ ኃይል፣ የታጠቀ ኃይል የለም›› ብሎ ቀናዒ ሆኖ ጉዳዩን ከእነ አፈጻጸሙ በዋና ባለቤትነት እየተከታተለ ነው? ስምምነቱንና አፈጻጸሙን ሸፍጥና ሸር፣ አሻጥርና ወለም ዘለም ባይነትም ሆነ ቸልተኝት እንዳይሸረሽረው የአገር መከላከል ሥራ እየሠራ ነው? የኢትዮጵያ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባርስ ከመከላከያ ኃይላችን ዋና የጉዳዩ ባለቤትነት ጋር እንዳይደበላለቅ እየተጠነቀቅን ነው? የስምምነቱ አፈጻጸም አካል ሆኖ ታኅሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈረመው የ‹‹MVCM›› (Monitoring, Verification, and Compliance Mechanism) ሥርዓት ያቋቋማቸው የሥልጣን አካላትስ? እየሠሩ ነው? ሥራቸውንስ ሕዝብና ሚዲያ እያወቀው ነው? መጠየቅ፣ ልንጠያየቅበትና ልንነጋገርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ትጥቅ በማስፈታት የስምምነቱ የአፈጻጸም ሒደት ውስጥ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የነፍስ ወከፍ ትጥቅ አንዱ ነው፡፡ መቀሌ በተሰጠው መግለጫ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ድርቤ መኩሪያ የሰጡትን ማብራሪያ/ማሳሰቢያ መነሻ አድርጎ ሊቀርብ የሚገባ ጥያቄ እንዳለ ማስታወስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ በገለጹት የዚህ ጉዳይ የአፈጻጸም ሒደት መሠረት የነፍስ ወከፍ ትጥቅ፣ ‹‹…ክልሉና የፌዴራል መንግሥት በመነጋገር የአካባቢው ሚሊሺያ፣ የአካባቢው መደበኛ ፖሊስ እንደ ማንኛውም ክልል የሚደራጀው መደበኛ ፖሊስና የአካባቢው ሚሊሺያ የሚታጠቀው ነው፡፡›› ይህንን ‹‹ማብራሪያ›› የሰጡት ይህንን ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ያደረገው በንግግራቸው ጠቆም እንዳደረጉት የነፍስ ወከፍ ትጥቅ ‹‹ተሰብስቦ ያው ወደ ማዕከል እንደሚከማች ዓይነት አስተሳሰብ ስላለ (በተለያየ አካባቢ) ይህ ግልጽ እንዲሆን ነው››፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል ድርቤ ግልጽ ካደረጉት ጉዳይ በላይ እጅግ በጣም ግልጽ መሆን ያለበት ሌላ ነገር አለ፡፡ በዚህ የ‹‹DDR›› ሒደት ውስጥ የተፈታውን፣ ተፈትቶም የተሰበሰበውንና የተመዘገበውን የነፍስ ወከፍ ትጥቅ ‹‹የአካባቢው መደበኛ ፖሊስ›› እና ‹‹የአካባቢው ሚሊሺያ›› ይታጠቁታል ለማለት መጀመርያ እነዚህ አካላት መኖር፣ በሕግ ህልውና ማግኘት አለባቸው፡፡ አሁን ትግራይን የሚያስተዳድረው ሚሊሺያም ሆነ መደበኛ ፖሊስ ማደራት የሚቻለው የክልሉ መደበኛ መንግሥት አይደለም፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው በስምምነቱ አንቀጽ 10 (1) መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ነው፡፡ በዚህ ጊዜያዊ አስተዳደርና በመደበኛው የክልሉ አስተዳደር መካከል ደግሞ የሰማይና የመሬት ያህል ልዩነት አለ፡፡
ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግሥቱ ‹‹ፍጡር›› ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የመጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ በትክክል እንዳለው፣ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 62 (9) እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 395/1995 አንቀጽ 14/2/ለ እንደተደነገገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የተቋቋመ ጊዜያዊ አስተዳደር ነው፡፡ ያኔ በ2013 ዓ.ም. የፌዴሬሸን ምክር ቤት የሰጠው ውሳኔና ትዕዛዝ (የፌዴራል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚና አስተዳደራዊ የሥልጣን አካል በክልል ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ፣ የክልሉን ምክር ቤትና የክልሉን ከፍተኛ አስፈጻሚ አካል አግዶ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም የማድረግ) ጦርነት ውስጥ ስለነበርን እንደ ዛሬው ‹‹ዕውቅና›› አላገኘም ነበር፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ግጭቱንና ጦርነቱን በዘላቂነት በማቆም መንደርደሪያ ሲነሳ፣ ትግራይ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መልሶ ስለማቋቋምም ጥርጊያ መንገድ የሚያነጥፍ ሁኔታዎችን የሚወስኑ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ የስምምነቱ አንቀጽ 10 (1) የሚለው ‹‹በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የበላይ ተቆጣጣሪነት ሥር የክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ የሚያገለግል›› የጊዜያዊ አስተዳደር ነው፡፡ ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50 (3) መሠረት በምርጫ ከሚቋቋመው፣ ለወከለው የክልል ሕዝብ ተጠሪ የሆውን የክልሉ ምክር ቤት ከሚያቋቁመው አስተዳደር የተለየ ነው፡፡
ይህንን ሁሉና እዚህ ውስጥም የታቀፉ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን ከቁጥር በማስገባት ከፍተኛ የአፈጻጸም ጥንቃቄ ብቻ ሳይሆን፣ የውሳኔ ጥበብና ብልኃት እንደሚያስፈልግ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሕወሓት ትጥቅ ስለመፍታቱ እንሰማና እንደገና ደግሞ በተዘዋዋሪም ሆነ ቀጥታ ዓይን ባወጣ መንገድ በእሱ ስለሚታዘዝ ‹‹መደበኛ›› ፖሊስና ሚሊሺያ፣ ሕወሓት የሚመራው መንግሥት ስለሚያዘውና ስለሚያስተዳድረው የፀጥታ ማስከበር ሚናና ሙያ እየተነገረን ነው፡፡
ሌላው በጭራሽ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ‹‹ልዩ ኃይል እንደገና የማደራጀቱ›› ሥራ እስከ ዛሬ ብዙ የተለፋበትን፣ በተለይ በተለይ ደግሞ የአገር መከላከያ ሠራዊትን የሪፎርም ሥራ (ገለልተኛ አድርጎ የማቋቋሙ፣ ከፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት የማፅዳቱ ሥራ ሁልጊዜም የሚቀጥልና የማይቀለበስበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ የማይቦዘንበት፣ እንቅልፍ የማይተኛበት ራሱን የቻለ የአገር መከላከል ሥራ መሆኑን እያሳሰብን ጭምር) እንዳይበረዝ መሥጋትም ተገቢ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ገና ብዙ ሥራ የሚሠራበት፣ ከአገር መከላከያ ወይም ከወታደራዊ ሠራዊት የሚለይበትን ይዘትና ምልክት ሁሌም ለሕዝብ የሚያሳይ አድርጎ ሪፎርሙን ማጥለቅ፣ ምናልባትም መልሶ መመርመርና መቦርቦር ያስፈልጋል፡፡ ልዩ ኃይልን እንደገና ለማደራጀት ‹‹የተወሰደው ዕርምጃ አካል ሆኖ ግን መከላከያም ሆነ በተለይም ‹‹ሪፎርሙ›› ብዙም ያልጎበኘው የፌዴራል ፖሊስ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የክልል ፖሊሶች ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ጨዋታ ውስጥ እንዳይገቡ መጠንቀቅና መሥጋት የአባት ነው፡፡ የሥርዓተ መንግሥቱ ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ ከየትኛውም ፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት መለያየት አለባቸው ማለት፣ ፓርቲዎችን ከባለጠመንጃነት ከማገላገል ትጥቅ ከማስፈታት በላይ ብዙና እጅግ በጣም ተከታታይ የሪፎርም ሥራ ይጠይቃል የሚባለው በዚህ ሁሉ ምክንያት ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡